በህብረት ስንቆም ሰላምን ማስፈን ቀላሉ ፈተና ነው!!

ህብረት ለሰው ልጆች ማህበራዊ መስተጋብር ወሳኝ ሚና ያለው መርህ ነው። አብሮነት የተለየ ማንነትን፣ ባሕልን ወይም ሃሳብን የሚያከብርና የሚያስተናግድ በሰላም የመኖር መሠረት ነው። ዩኔስኮ የአብሮነት ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲከበር ያደረገው የዓለም ሕዝቦች የመልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ የቀለም፣ የኃይማኖት፣ የጎሳና የቋንቋ ልዩነቶች ሳያግዳቸው ማህበራዊ መስተጋብራቸውን እንዲያጠናክሩ በማሰብ ነው።

በመላው ዓለም በልዩነቶች ምክንያት የሚፈጠሩ ግጭቶችና አለመግባባቶች መጠነ ሰፊ ጉዳት የሚያስከትሉ መሆናቸውን ለማስገንዘብ፤ ህብረት ለሰው ልጆች ተሳስቦ ለመኖር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ለማሳየት ነው። አንዱ የሌላውን መብት አክብሮ ከሌሎች ጋር በመቻቻል መኖር መቻሉ ለዓለም ሰላም ወሳኝ መሆኑን ለማመላከት ጭምር ነው።

ኢትዮጵያውያን ከሌላው ዓለም የምንለይበትን የዛሬዋን የጳጉሜን አራት ቀን የምናከብረው “ኅብራችን ለሰላማችን” በሚል አብሮነታችንን በማጠናከር ሰላማችንን ለማጽናት በማሰብ ነው። ሰላማችን ከሁሉም በላይ ህብረትና አንድነታችንን የሚሻ መሆኑን ተገንዝበን ለሰላም ዘብ ለመቆም ቃል በመግባት ነው።

ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት ነው። ሰላም ከሌላ ሁሉም ነገር የለም። ስለ ነገ ማሰብም ሆነ ማቀድ የሚቻለው ሰላም ሲኖር ብቻ ነው። ለዚህም ነው ‹‹ሰላም የሁሉ ነገር ዋስትና መሠረት ነው›› የሚባለው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮች ሕዝብን ሰላም ነስተዋል። በሰላም ወጥቶ እንዳይገባ ሰርቶ እንዳይኖር እንቅፋት ሆነዋል።

የሕዝቦችን የሰላምና የአብሮነት ፍላጎት የማይመጥኑ፣ ትብብርና ወንድማማችነታቸውን ከማጠናከር ይልቅ የእርስ በእርስ ግንኙነት የሚያሻክሩ፤ በልዩነት ውስጥ ያለንን አንድነት ከማጉላት ይልቅ ልዩነት ላይ የሚያተኩሩ፤ አብሮነታችንን ወደ ገደል አፋፍ የሚገፈትሩ ክስተቶች አጋጥመውናል፣ ፈትነውናልም።

ይህንን ተከትሎ በተፈጠሩ ግጭቶቹ የሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመት ደርሷል፤ ዜጎች ለዓመታት ከኖሩባቸው ቀያቸው ተፈናቅለዋል። ከተወለዱበት፣ ካደጉበት እና ለዓመታት ከኖሩበት ስፍራ ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያዎች ኑሯቸውን የሚገፉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም።

ለበርካታ ዓመታት የኢትዮጵያውያንን የጋራ እሴቶች ከማጎልበት ይልቅ ልዩነቶች ላይ ተሰርቷል። በማንነት እና በሃይማኖቶች መካከል ጥርጣሬ እንዲነግስ በር በመክፈት አንደኛው ወገን ሌላኛውን እንዲጠራጠር ብሎም የበዳይና ተበዳይ ትርክት እንዲፈጠር አድርጓል።

የፖለቲካ ልሂቃን፣ የአክቲቪስቶች እና የአንዳንድ ምሁራን ትርክቶች ጥላቻ እንዲነግስ በር ከፍቷል። በአንዳንድ አካባቢዎች ሰላም እንዲጠፋ ከማድረግ ባሻገር በሰላም ወቅት የተገነባውን ህብረትና አንድነታችንን እየተፈታተነ ይገኛል።

መንግሥት የሰላም ችግሩ በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች የሕዝቡን ሰላም ለመመለስ የሚያደርገው ጥረት ቢኖርም በሚፈለገው ደረጃ ውጤት ማምጣት አልተቻለም። የሰላም ጉዳይ ለአንድ አካል የሚተው አይደለም። ሰላም የሁሉም ጉዳይ ነው። ሰላምን ማስፈን የሚቻለውም እንደ ሀገርና ሕዝብ በህብረት መቆም ስንችል ነው። ለዚህ ደግሞ መተማመንና ለአንድ አላማ በጋራ መቆም ይጠይቃል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቁ ችግር ሆኖ የሚስተዋለው የመተማመን መጥፋት ነው። ርግጥ ነው በብዙ ሀገሮች በተለይም ሰልጥነዋል በሚባሉት ጭምር የመተማመን ስሜት እየተቀዛቀዘ ነው። ለችግሩ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ መፍትሔ አይሆንም። ለሀገር ሰላምም ሆነ ገጽታ ስለማይጠቅምም ቆም ብሎ ችግሮችን ለመቅረፍ መሥራት ያስፈልጋል።

ለኢትዮጵያውያን ትልቁ ነገር ሰላም ነው። ይህን አጥብቀን የምንሻውን ሰላም ግን ስለሰላም ስለዘመርን ብቻ ልናመጣው አንችልም። በህብረት ለሰላም መቆም ይገባናል። ሀገር ላይ ለተቃጡ አደጋዎች በህብረት ቆመን ስንመክት ኖረናል። አሁንም እየመከትን ነው። በልማቱም እንደዚያው። የቀረን ለሰላማችን በህብረት መቆም ነው። ይህንን የጋራ ፈተና ማለፍ የምንችለው በህብረት ስንቆም ነው።

በህብረት ስንቆም በብዙ ነገር ተዓምር እንፈጥራለን ተብሎ ተደጋግሞ የሚነገረው ከመሬት ተነስቶ አይደለም። በህብር ስንቆም ምድረ በዳ የነበሩ ቦታዎችን አረንጓዴ እናለብሳለን፣ እያለበስንም እንገኛለን። በሁሉም ዘርፍ ምርትና ምርታማነታችን እናሳድጋለን፣ በጠንካራ የሥራ ባሕል ድህነትና የተረጂነት አስተሳሰብን በመሠረታዊነት እስከ ወዲያኛው እናስወግዳለን። ይህን አስደማሚ ህብረታችንን በዓባይ ግድብና በአረንጓዴ ዐሻራ አሳይተናል።

በህብረት ስንቆም ከባድ የሚመስለውን ነገር ማሳካት እጅግ ቀላል ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን “የድር ቢያብር አንበሳ ያስር” ብሂል ባለቤቶች፤ በህብረት ከተነሳን ማሳካት እንደምንችል ሁነኛ ምሳሌ ነው።

በርግጥ ሰላም ማለት የግጭት አለመኖር ማለት አይደለም። ኢትዮጵያ ውስጥ ጦርነት ባልነበረባቸው ዘመናት ሁሉ፣ ለግጭት የሚዳርጉ ቅራኔዎች ስለመኖራችን ለመናገር የሚከብድ አይደለም፤ እንደ ሀገር ብዙ ፍላጎቶች ያሉባት ሀገር ከመሆኗ አኳያ ወደፊትም ይኖራል።

ቅራኔን በመነጋገርና በመወያየት ከመፍታት ይልቅ በኃይል መፍትሔ መፈለጉ ተለምዷል። በኢትዮጵያ ታሪክ ግጭቶች ሌላ ግጭት እየወለዱ የግጭት አዙሪት ውስጥ ተነክረን ሰላም አልባ ዘመናትን አሳልፈናል። ይህም በድህነታችን እንድንቀጥል ካደረጉን የልማት ወጥመዶች መካከል አንዱና ዋነኛው ነው።

የእርስ በርስ ግጭት አንድን ሀገር ከፍተኛ የኢኮኖሚ ውድመት ውስጥ እንደሚከትና በተለይ የእርስ በርስ ግጭቱ እየተራዘመ በመጣ ቁጥር ከግጭቱ የሚያተርፉ አካላት እየበረከቱ ስለሚመጡ ለቀጣዩ ግጭት መፈጠር በር እንደሚከፍት ታዝበናል።

ለዘመናት ሲዘሩ የቆዩ የጥላቻና የመከፋፈል ዘሮች ፍሬ አፍርተው ሕብረተሰባችንን ያስተሳሰሩት ክሮች እየላሉ የመጡበት አንድም ቆም ብለን መነጋገር ባለመቻላችን ሌላም ለሚገጥሙን ችግሮች በህብረት የመመከት ባሕላችን እየላላ በመሄዱ ነው።

ዛሬ ላይ በህብረት ቆመን ለሰላም ትኩረት መስጠት አልረፈደም። ለሰላም በጋራ መቆምና የሰላምን መንገድ ማገዝ አማራጭ የሌለው መንገዳችን ነው። መንግሥት ፍትሃዊነትን በማስፈን፣ ዲሞክራሲን በማስረፅ፣ የፍትሕ ተቋማትንም ገለልተኛ እንዲሆኑ በማድረግ ለዜጎች ለሰላም ትኩረት መስጠቱ እንደተጠበቀ ሆኖ በሰላም ዙሪያ የሚሰሩ አካላት የሃይማኖት ተቋማት፣ የሀገር ሽማግሌዎች በርግጥ አሁን ባለንበት ሁኔታ ሰላምን ለማስፈን ከእኛ ምን ይጠበቃል? ብለው ራሳቸውን መጠየቅና ተግተው መሥራት ይኖርባቸዋል።

ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ሁሌም ሰላም ወዳድ እንደሆኑ አያሌ የታሪክ ክስተቶች ምስክር ናቸው። ይህንንም ባለንበት ዘመን እንኳን ደጋግመው አሳይተዋል። ያልሻረ ቁስል ይዘው እንኳ እጃቸውን ለሰላም ከመዘርጋት ተቆጥበው አያቁም፤ የሰላምን ዋጋ ጠንቅቀው ያውቁታልና።

ለችግሮች ነፍጥ በማንገብና ጦር በመስበቅ መፍትሔ የማፈላለጉ እውነታ፤ የሀገር ተስፋ የሆነውን ወጣት እንደ ቅጠል ከማርገፍና የሀገር ኢኮኖሚ ከማድቀቅ የዘለለ ፋይዳ አላመጣልንም።

ሰላምን በግለሰብ፣ በቤተሰብ፣ በማኅበረሰብና በተቋም ደረጃ በማስረጽ፣ የዜጎችን፣ ወጣቶችን በጎ ፈቃደኝነትንና የመስጠት ዜግነታዊ ኃላፊነትን ባሕል ለማድረግ በህብረት መነሳት ግድ ይለናል። ሰላምን ለማምጣት ከታሪካዊ ቅራኔዎቻችን ይልቅ ለታሪካዊ መግባባታችን ቅድሚያ መስጠት ይጠይቃል።

ኢትዮጵያን ከማናቸውም ዓይነት ፍላጎትና ዓላማ በላይ ሀገራዊ ትስስራቸውን ማጥበቅ ከቻሉ፤ ከችግሮቻቸው በላይ መሆን የሚያቅታቸው አይደሉም ፣ ክንዳቸውን አስተባብረው ለጋራ አላማ መንቀሳቀስ ከቻሉ ሁሌም አሸናፊዎች ናቸው፤ ለዚህም ብዙ የታሪክ ማስረጃዎችን መጥቀስ ይቻላል።

ከዚህ ውጭ በተናጠል ሆነ አንዱ በሌላው ላይ የበላይ በመሆን ሀገር መለወጥ ሆነ ማሳደግ እንደማይቻል በተደጋጋሚ አይተዋል። ኢትዮጵያ ማደግም ሆነ መለወጥ የምትችለው የሕዝቦቿ ሰላም ሲረጋገጥ ነው። አሁን ላይ ኢትዮጵያን በአንዳንድ አካባቢ እየፈተናት የሚገኘው የሰላም ጥያቄም መመለስ የሚችለው ልጆቿ እንደ ታላቁ የዓድዋ ድል ስለሰላም በአንድነትና በህብረት ሲነሱ ብቻ ነው። ዛሬም ይሁን ትናንት ኢትዮጵያውያን በህብረት ቆመን የዘመመ አቅንተናል፣ የማይቻል የሚመስለውን ችለን አሳይተናል። አሁንም አያቅተንም።

ኢትዮጵያን ከግላዊና ከቡድናዊ ፍላጎት በላይ ማድረግ በሚያስችል የአስተሳሰብ መሠረት ላይ መቆም ከቻልን አሁናዊ ችግሮቻችንን መሻገር አያቅተንም ፤ ልዩነትን ይዞ ለኢትዮጵያ ዘለቄታዊ ሰላምና ጥቅምም መተባበር አይቸግረንም፤ ኢትዮጵያ የሁላችንም እንደሆነችው ሁሉ፣ ችግሩም የጋራችን ከችግሩ መውጫ መንገድም የሁሉም የተባበረ ትግል ነው።

ሰዎች ከራሳቸውና ከአካባቢያቸው ጋር ሰላም ኖሯቸው ለጋራ እድገትና አብሮ መኖር አስተዋጽኦ ካደረጉ ህብረት አለ። ህብረት ካለ ሰላም አለ። ሰላም ከፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ኑሮ ባሻገር ሰዎች ከሰዎች፣ ከተፈጥሮና ከአካባቢ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ስለሚመለከት ሰላም ሁሉን አቀፍ ነው።

በሀገር ደረጃ ባለፉት ዓመታት ሰላምን ለማስፈን የሰላም ሚኒስቴር ከማቋቋም ጀምሮ በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል። ማኅበረሰቡን ያሳተፈ የዳበረ ዴሞክራሲን የማጽናት፣ የላቀ ብሔራዊ መግባባትን የመፍጠር፣ የሰላም ግንዛቤና ሁለንተናዊ ተሳትፎን የማሳደግ የውይይት መድረኮች ተካሂደዋል፣ እየተካሄዱም ይገኛሉ።

ማህበራዊ ሀብቶቻችንንና ባሕላዊ እሴቶቻችንን በመገንባት ሂደት በተለይም የሰላም እናቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት ተቋማት በባለቤትነት እንዲሳተፉና እንዲያግዙ በማድረግ ለዘላቂ ሰላም ምቹ ምህዳር ተፈጥሯል። ከሲቪክ ማኅበረሰቡ ጋር በመሆን ሰላምን በማስፋፋት፣ ግጭትን በመከላከልና ዴሞክራሲን በማስፈን ላይ በቅንጅት ለመሥራትም ተሞክሯል። ግን በቂ አይደለም፣ የሁሉንም ኢትዮጵያዊ በህብረት መቆም ቢታከልበት ውጤቱ ፈጣንና የጎላ ይሆናል።

በተለይም በአሁኑ ጊዜ፣ የዓባይን ግድብ ለማጠናቀቅ ጥረት በሚደረግበትና ሀገር ወዳዱ ሕዝብ በሚረባረብበት፤ ግብጽንና ግብረአበሮቿ ከልማት ጉዟችን ለማሰናከል በተጠናከረ ዘመቻ ውስጥ በሚገኙበት ታሪካዊ ወቅት ለሰላማችን አብዝተን መሥራት ይጠበቅብናል።

ሀገራችን ከየትኛውም የውጭ ጥቃት ልንከላከል የምንችለው በአንድነት ስንቆም ብቻ ነው። በህብረት ስንቆም አንድነት መተሳሰብና ወንድማማችነት ይዳብራሉ። እንዲህ ሲሆን ደግሞ ሰላማችንን ለመመለስ የምናደርገው ጉዞ ይሰምራል። የሚገጥሙን ፈተናዎች ቢኖሩም በህብረት ከሰራን ፈተናዎችን ወደ እድል እየቀየርን ወደ ስኬት እንተማለን።

አንድነት ኃይል ነው፣ መተባበር ደግሞ የችግሮች ሁሉ ቁልፍ ነው። ኢትዮጵያን ሰላምና ፍቅር የሰፈነባት ለማድረግ ፤ እንደ እህትና እንደ ወንድም በአንድነት ለመነጋገር፣ ለመሥራት እና በጋራ ለመጠቀም በንጹህ ልቦና ማበር ግዴታችን ነው። የጋራ አሸናፊነት መሳሪያ የሆነውን ሰላም ማንገብ ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ በህብር ቀን ላይ ቆመን የሰላም ዘብ ለመሆን ቃል ልንገባ ይገባል።

ልዑል አበበ

አዲስ ዘመን ሰኞ ጳጉሜን 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You