ምዕራባውያን ከፍተኛ ድጋፍ አላቸው ተብለው የሚጠረጠሩት የቬንዙዌላ ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ወደ ስፔን ኮበለሉ።
የተቃዋሚ ፕሬዚዳንታዊ እጩ የሆኑት ኢድሙንዶ ጎንዛሌዝ ወደ ስፔን መኮብለላቸውን የቬንዙዌላ መንግሥት አስታውቋል።
መንግሥት የሚቆጣጠረው ብሔራዊ የምርጫ ኮሚሽን ባለፈው ሐምሌ ወር የተካሄደውን ምርጫ ኒኮላስ ማዱሮ ማሸነፋቸውን ካወጀ በኋላ ጎንዛሌዝ ተደብቀው መቆየታቸውን እና የእስር መያዣም ወጥቶባቸው እንደነበር ቢቢሲ ዘግቧል።
የቬንዙዌላ ምክትል ፕሬዚዳንት ዴሊሲ ሮድሪጉዝ በማህበራዊ ገጻቸው ጎንዛሌዝ በካራካስ የሚገኘው የስፔን ኤምባሲ እንዲያስጠልላቸው መጠየቃቸውን እና ከስፔን መንግሥት ጥገኝነት መጠየቃቸውን ገልጸዋል።
ምክትል ፕሬዚዳንቷ አክለው እንደገለጹት፤ ካራካስ በሰላም እንዲሄዱ ፈቅዳ ጎንዛሌዝ ከሀገር ወጥተዋል። የስፔን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆሴ ማኑኤል አልባሬዝ ጎንዛሌዝ በራሳቸው ፍቃድ በስፔን የአየር ኃይል አውሮፕላን ከሀገር ወጥተዋል ብለዋል።
የስፔን መንግሥት የሁሉንም የቬንዙዌላ ዜጎች የፖለቲካ መብት ለመጠበቅ ቁርጠኛ ነው ብለዋል ምክትል ፕሬዚዳንቷ። የስፔን ሚዲያዎች እንደዘገቡት ከሆነ፤ ጎንዛሌዝ በስፔን የፖለቲካ ጥገኝነት አግኝተዋል።
ጎንዛሌዝ ከሀገር እየወጡ ባሉበት ወቅት የጸጥታ ኃይሎች በካራካስ የሚገኘውን የአርጀንቲናን ኤምባሲ ከበው ነበር። ስድስት የፕሬዚዳንት ማዱሮ ተቃዋሚዎች በዚህ ኤምባሲ ውስጥ ይገኛሉ።
ፕሬዚዳንት ማዱሮ እ.አ.አ. ሐምሌ 28 የተካሄደው ምርጫ አሸናፊ መሆናቸው ከታወጀ በኋላ ሀገሪቱ ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ገብታለች።
አሜሪካን፣ የአውሮፓ ህብረትን እና በርካታ የላቲን አሜሪካ ሀገራትን ጨምሮ ብዙ ሀገራት ካራካስ የምርጫውን መረጃ ይፋ ካላደረገች የፕሬዚዳንት ማዱሮን ማሸነፍ አንቀበልም ሲሉ መቃወማቸው ይታወሳል። የማዱሮ መንግሥት ከምርጫ ወዲህ ተመድ “የፍርሀት ድባብ መፍጠር” ባለው ርምጃ ሁለት ሺህ 400 ሰዎች ታስረዋል።
ተቃዋሚዎች ማዱሮ 52 በመቶ ድምጽ አሸንፈዋል ያለውን የምርጫ ካውንስል ውጤት አልተቀበሉትም። ጎንዛሌዝም በቁጥጥር ስር ውለው ስለሰጉ ከምርጫው ወዲህ ተደብቀው ቆይተዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሰኞ ጳጉሜን 4 ቀን 2016 ዓ.ም