አሜሪካ ለዩክሬን ተጨማሪ የ250 ሚሊዮን ዶላር የጦር መሳሪያ ድጋፍ አደረገች

አሜሪካ ለዩክሬን ተጨማሪ የ250 ሚሊዮን የጦር መሳሪያ ድጋፍ ማጽደቋን አስታወቀች

በትናንትናው እለት የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮላድሚር ዘለንስኪ ከአውሮፓ አጋሮቻቸው እና ከአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ጋር በጀርመን ተገናኝተዋል።

በውይይቱ ጦርነቱን ለማስቆም በሩሲያ ላይ ተጨማሪ ጫናዎች እንዲደረጉ ፕሬዚዳንቱ ጠይቀዋል።

በተጨማሪም በሩስያ ውስጥ ጥቃት ለመፈጸም እንዳይውሉ የተከለከሉትን የረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎችን ለመጠቀም ጥያቄ አቅርበው ውድቅ ተደርጎባቸዋል።

ፕሬዚዳንቱ በሩስያ ዋና የአየር ማዘዣ ላይ ጥቃት ለመፈጸም ነው በረጅም ርቅት ሚሳኤሎች ላይ የተጣለው ክልከላ እንዲነሳ የጠየቁት።

የአሜሪካው የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስተን ለዚህ በሰጡት ምላሽ የረጅም ርቀት ሚሳኤሎችን በሩስያ ውስጥ ጥቃት ለመፈጸም ጥቅም ላይ ማዋል የጦርነቱን ውጤት አይቀይረውም ብለዋል።

በሩስያ ውስጥ የሚገኙ ግዙፍ ኢላማዎችን ለማጥቃት ካስፈለገም ዩክሬን የራሷን ድሮኖች መጠቀም ትችላለች ነው ያሉት። ሚኒስትሩ በዚህ ውግያ በራሱ ወሳኝ የሚሆን የተለየ አቅም የለም የሩስያን ጥቃት ለመመከት የሚያስፈልገው የተቀናጀ ጥቃት እና ስትራቴጂ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ኬቭ በሩስያ ውስጥ ጥቃት ከመሰንዘር ይልቅ በድንበሯ ውስጥ እየገፋ የሚገኘውን የሞስኮ እግረኛ ጦር አቅምን ማሽመድመድ ላይ ብታተኩር መልካም ይሆናል ያሉት የመከላከያ ሚኒስትሩ፤ አሜሪካ ለዚህ ዘመቻ የሚያግዝ ተጨማሪ የ250 ሚሊዮን የጦር መሳሪያ ድጋፍ ማድረጓን አስታውቀዋል።

ከአሜሪካ በተጨማሪ ጀርመን 12 ከባድ መድፎችን የሰጠች ሲሆን፤ ካናዳ 80 ሺህ ከአየር ላይ የሚተኮሱ ሮኬቶችን በመጪዎቹ ወራት ለመስጠት ቃል ገብታለች።

ዩክሬን በምዕራባዊ ሩስያ ከርሰክ ግዛት ድንገተኛ ጥቃት ከፈጸመች በኋላ ወደ ፊት ለመጓዝ ጥረት እያደረገች ሲሆን፤ ሩስያ በበኩሏ በጦርነቱ የዩክሬን ዋነኛ የሎጂስቲክ መተላለፊያ የሆነችውን ፖክሮቨስክ ከተማን መቆጣጠር ላይ ትኩረት አድርጋለች።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ጳጉሜን 3 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You