‹ህብር ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት› የጳጉሜን 3 አንቂ ሃሳብ ሆኖ ሲመጣ በብዙ ምክንያት ነው። ሉዓላዊነት የአንድ ሀገርና ሕዝብ የመኖር፣ የመሥራት፣ እንደሀገር የመቆጠር፣ የመበልጸግ እንዲሁም የደህንነት መሠረት ነው። ቤት በምሰሶ እንደሚጸና ሁሉ የሀገር የጽናቷ ማረጋገጫም ሉዓላዊነት ነው። ትውልድ ብለን ወደራቀ ነገ የምናሻቅበው፣ እድገት ብለን ወደሚመጣው የምናየው በሉዓላዊነት በኩል ነው።
ካለው ሀገራዊ ፋይዳ አንጻር የሉዓላዊነት ቀን ደግሞ ደጋግሞ ቢከበር መልካም ነው። ሉዓላዊነት የማንነት ትልቅ ስም ነው። ታሪክ፣ ባህልና ሥርዓት በዚህ እውነታ በኩል ሲንጸባረቁ ነው ዋጋ የሚያወጡት። ኪሳችን እንደያዝነው የዜግነት መታወቂያ ሉዓላዊነትም ብሄራዊ ክብራችን፣ ብሄራዊ መታበያችን ነው። ጳጉሜን 3 በዚህ ታላቅ ቀለም ተሰይሞ መምጣቱ እንዳለፈው ጊዜ መጪውንም በዚህ መንፈስ ለመቃኘት እድል የሚሰጥ ነው ።
አንድነትና አብሮነት በሚያስፈልገን ማግስት ላይ ሥለሉዓላዊነት መነጋገር እጅግ ጠቃሚ ነው። በእርግጥ እኛ ኢትዮጵያውያን ከማንም ቀድሞ ሥለሉዓላዊነት የተረዳን ሕዝቦች ነን። በዓድዋ፣ በካራማራ፣ በአንባላጌ፣ በኡጋዴን ሉዓላዊነታችንን አስጠብቀናል። ሀገር ማለት፣ ክብር ማለት ምን ማለት እንደሆነ ለዓለም ያሳየንበት በርካታ በጎ አጋጣሚዎች አሉን።
ሁለንተናዊነትን ያቀፈ የሉዓላዊነት እሳቤ ሀገርን ከኢኮኖሚ ጥገኝነት፣ ከተረጂነትና ከደህንነት ስጋት ነጻ የሚያወጣ እሳቤ ነው። ሁለንተናዊነት ብሄርብሄረሰባዊነትን ያቀፈ፣ ብዙሃነትን የዋጀ የኢትዮጵያዊነት ዘውግ ነው። ኢትዮጵያዊነትን የምናቀነቅንበት የትውልዱ አይን ገላጭ እውቀት ነው።
በርካታ ችግሮች አንቀው በያዙን ሰሞን ሉዓላዊነት ብለን መነሳታችን እጅግ በጎ ነገር ነው። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታዩ ላሉ ችግሮች መልስ የሚሰጥ በመሆኑ ሀገር ወዳድ ለሆኑ ሁሉ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ላይ የተበረከተ ስጦታ እንደሆነ የሚቆጠር ነው ።
ሉዓላዊነት ዋጋ የሚኖረው ሁለንተናዊነት ውስጥ ስለመሆኑ ታሪኮቻችን ምስክሮቻችን ናቸው። የተነሳንበት የማንነት ነቁጥ ከአብሮነት የጀመረ፣ በአብሮነት የቀጠለ ነው። በታሪክና በሀገር ፍቅር ዳብረን ወደዛሬ ስንመጣም በእንዲህ መሳዩ ድንበር የለሽ የሉዓላዊነት ቀለም ነው።
ነጻነትና ሚዛናዊነት የእትብታቸውን ሰፈር ከጥቋቁሮቹ ርስት ስር የተዉት ለምን ሆነና? ሠብዓዊነትና ጀግንነት በረዘመ እንዥርግ የሀበሻነት ወግ ስር ማድፈጣቸው በእንዲሁ አይደለም። በሀገሩ ቀልድ በማያውቀውና ብዙሃነትን በኢትዮጵያዊነት በመሰለ ሰውነት ነው።
‹ህብር ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት› መነሻው ሰውነት መድረሻው ኢትዮጵያ ናት። ህብር ውህድ ነው፣ ትስስር ድብልቅም ነው። ከብዙሀነት ውስጥ አንድነትን መውለድ፣ በአንድነት ብዙሀነትን መግለጥም ነው። ህብር ደማቅ ቀለም ነው..በአረንጓዴ ቢጫና ቀይ የደመቀ ማንነት። ህብር ብሄር ብሄረሰቦች ወደኢትዮጵያዊነት የሚያደርጉት የህብረት ዘመቻ ነው።
በጋራ ባህልና ታሪክ፣ በህብር ወግና ሥርዓት ኢትዮጵያ የሚለውን ትልቁን ስም ማጽናትም ነው። ይሄ ህብረ ቀለም ሉዓላዊነትና ሁለንተናዊነት ሲታከሉበት ሀገር የሚለውን ሙሉ ስም ይይዛል። ለዚህም ነው ጳጉሜን በሉዓላዊነት የምንዘክረው።
ሉዓላዊነት ሀገር ተኮር በጎ አስተሳሰቦች የሚንጸ ባረቁበት ቢሆንም ከዛ ትይዩ በተለያየ መንገድም ሊገለጽ የሚገባው ነው። የኢኮኖሚ ፣ የፖለቲካ …ወዘተ ሉአላዊነት በአንድ ሀገር ላይ እጅግ ወሳኝ ነገሮች ናቸው። አሁን ባለው ወቅታዊ የሀገራችን ሁኔታ ከዋናው እና ከማዕከሉ ሀገራዊ ሉዓላዊነት ጎን ለጎን የነዚህም ፋይዳ አስፈላጊ ነው።
ድሃ ሀገርና ሕዝብ የሚለውን የቆየ ስም ራሱን በምግብ በቻለ እና መካከለኛ ገቢ ያለው በሚል ስም መቀየር በኢኮኖሚ ሉዓላዊነት የሚገለጽ በጎ ገጽታ ነው። በበቃና በበለጸገ ተፈጥሮ መሃል ጸድቀን ድህነትን ታግሎ መጣል ሳንችል ድሃ በሚለው አስጸያፊ ስም ስር በዙ ዘመናትን ከርመናል። የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ደግሞ ለዚህ መሳዩ ሀገራዊ ውጥንቅጥ ምላሽ የሚሰጥ ነው።
ፖለቲካዊ ሉዓላዊነትም ከዚህ ጋር አብሮ የሚጠራ ጉዳይ ነው። ባልዘመነና ሃሳብ ተኮር ባልሆነ የፖለቲካ ምህዳር በርካታ ዋጋዎችን ከፍለናል በመክፈል ላይም እንገኛለን። ወደ አንድ ወገን ባጋደለ፣ የጥላቻና የዘረኝነት ትርክትን ለመፍጠር በተመቸ ሥርዓት ሰላም አጥተን፣ አንድነት ርቆን በብዙ ችግር ውስጥ ሰንብተናል።
ከሰላም ፈጣሪነት ወደሰላም ናፋቂነት፣ ወደጦርነትና የእርስ በርስ ግጭት ከገባን ሰነባብተናል። የፖለቲካ ሉዓላዊነት ሀገራዊ ጥያቄ ሆኖ የሚነሳው እዚህ ጋ ነው። ለዚህ አይነቱ ሀገራዊ ችግር በፖለቲካ መሠልጠንና የነቃ የውይይት መድረኮችን መፍጠር የፖለቲካ ሥልጣኔውን ከማዘመን ጎን ለጎን ወደ አዲስ የፖለቲካ ሉዓላዊነት የሚያሸጋግረን ነው።
ልክ እንደዚሁ ሁሉ የዲፕሎማሲ ሉዓላዊነትም ስለሰላምና ደህንነት፣ ስለበጎ ግንኙነት የሚተጋ እሳቤ ነው። ለይተን አየናቸው እንጂ ሁሉም የሀገር ክብር ሉዓላዊነት ቅርንጫፎች በመሆን ሲጠሩ የከረሙ ናቸው። በየትኛውም ዘርፍ ላይ ሀገርና ሕዝብን የሚጠቅም ሥራን ከሠራን ይሄ በራሱ የሉዓላዊነት መገለጫ ምልክት ነው።
አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ትግላችን ከድህነት ጋር፣ ከኋላቀርነት ጋር ነው። ስለሰላም፣ ስለልማት፣ ስለአብሮነት እየታገልን እንገኛለን። እነዚህ ሁሉ መልስ የሚያገኙት በሁለንተናዊ ሉዓላዊነት አብረን ስንቆም ነው። አዲሱን ዓመት በሀገር ፍቅር የሉዓላዊነት ስሜት መቀበላችን ያለፈውን በይቅርታ መጪውን በእርቅና በፍቅር እንድንቀበለው የሚያደርግም ነው። ከውስጥም ከውጪም የተቃጡብንን ችግሮች በድል እንድንወጣ ከማድረጉም ባለፈ ስለብሄራዊ ጥቅምም ዋጋ ያለው ነገር ነው።
ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 3 ቀን 2016 ዓ.ም