መለወጥ (ሪፎርም) ማለት ምን ማለት ነው?

በምሁራን ይተንተን ከተባለ ሰፊ ማብራሪያ እና ጥልቅ ትርጓሜዎች ሊኖሩት ይችላል። ለማንም ሰው ግልጽ በሆነ መንገድ በአጭሩ ይገለጽ ከተባለ ግን መለወጥ ማለት መሻሻል ማለት ነው። ከዘመኑ ጋር መሄድ ማለት ነው። ከኋላቀር አመለካከትና አሠራር ወደ ዘመናዊ አመለካከትና አሠራር መለወጥ ማለት ነው።

ዛሬ የ‹‹ሪፎርም›› ቀን ነው ተብሏል። ቃሉ የእንግሊዝኛ ሲሆን የተዋወቀው ከኢህአዴግ ጊዜ ጀምሮ ነው። በእንግሊዝኛ ሲሆን ምናልባት የተለየ ውበት እና ክብደት ያለው ሊመስለን ይችላል። በራሳችን ቋንቋ መለወጥ፣ መሻሻል፣ መዘመን… ማለት ነው። ስለዚህ በዚህ ጽሑፍ የመለወጥ ቀን እያልን እንቀጥላለን።

ይህ ቀን ለእኛ ለኢትዮጵያውያን በጣም ያስፈልገናል። እንዲያውም በዓመት ቢያንስ ስድስት ጊዜ ቢከበር እና ቢታወስ ጥሩ ነበር። ምክንያቱም የሁሉም ችግሮቻችን መነሻው አለመለወጣችን ስለሆነ! ‹‹Re-form›› የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል እንደገና መሠራት፣ እንደገና መታደስ፣ እንደገና መመሥረት…. የሚል ትርጉም ይሰጠናል። በዚህ መሠረት ከሄድን በዋናነት የሚያገለግለው ለተቋማት ነው። ለመንግሥታዊ አደረጃጀት ነው። በተደጋጋሚ ከመንግሥት አፍ የምንሰማውም ለዚህ ነው። ያም ሆኖ ግን እንደ ኢትዮጵያ ደግሞ መለወጥ (reform) የሚያስፈልገን እንደ ግለሰብ ጭምር ነው። እንደ ግለሰብ ሲባል በዋናነት ታዋቂ ፖለቲከኞችንና ምሁራንን የያዘ ማለት ነው። እንደ መንግሥትም ሆነ እንደ ሕዝብ ለውጥ (ሪፎርም) ካላደረግን ወደ አደገኛ ችግሮች እየገባን ነው። ለውጥ ያላደረግንባቸውን ችግሮቻችንን እንታዘብ!

ዓለም ከሰው ልጅ መብት አልፎ የእንስሳትና ጥቃቅን ነፍሳት መብት ጥበቃ ላይ ደርሷል። የአውሮፓ ሀገራት በመካከላቸው ያለው ድንበር በአራዳ ክፍለ ከተማ እና በጉለሌ ክፍለ ከተማ እንዳለው ልዩነት ማለት ነው። አንድ ሰው ከአዲሱ ገበያ ወደ ፒያሳ ሲወርድ የጉለሌ ክፍለ ከተማን የት ጋ እንደጨረሰ እና አራዳ ክፍለ ከተማ ከየት ጋ እንደሚጀምር አያውቅም። የአውሮፓ ሀገራት ድንበር ልክ እንደዚያ እንደሆነ ብዙ የቆዩበት ሰዎች የጻፉትን አንብበናል፤ የተናገሩትን ሰምተናል። የታዛቢዎች አገላለጽ ተጋነነ ቢባል እንኳን በ21ኛው ክፍለ ዘመን የአውሮፓ ሀገራት የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ እንዳልሆኑ ሁላችንም የምናውቀው ነው። ለምን? ስለተለወጡ!

እኛ ግን እያሰብን ያለነው ስለአሁኑ እና ስለወደፊቱ ሳይሆን መቶ ምናምን ዓመታትን ወደኋላ ተመልሰን ነው። ከ200 ዓመት በፊት በነበረ ጉዳይ ዛሬ ላይ እየተጣላን ነው። ከዚህ በፊት እንዳልኩት፤ ከዛሬ 200 ዓመት በፊት ከነበረ አንድ የእኛ ሰፈር ሰውየ ዛሬ ላይ በሕይወት ያለ አንድ የሩቅ ምሥራቅ ሀገር ዜጋ ይቀርበኛል። ለምን? የጋራ ዘመን ላይ ነው ያለነው። መሐል ሀገር ለምኖረው ለእኔ ከ100 ምናምን ዓመታት በፊት ከነበረ አንድ የሰፈራችን ሰው የኢትዮጵያ ጫፍ ላይ ያለ የአሁኑ ሰው ይቀርበኛል። ምክንያቴም ብዙ የጋራ ጉዳይ አለን። እያደረግን ያለነው ግን ወደኋላ በመመለስ የዛሬውን ብቻ ሳይሆን የወደፊቱን ትውልድ ጭምር ሕይወት ማበላሸት ነው። ይህን አመለካከታችንን እስካልቀየርን ድረስ እንደ ሀገር ለውጥ (ሪፎርም) አይኖረንም።

ወደ ተቋማት አሠራር ስንሄድ ደግሞ በተደጋጋሚ እንደታዘብነው ዛሬም አሰልቺ እና አታካች አሠራር ላይ ነን። ምንም እንኳን የቢሮ ንጽህና እና ሌሎች ለዓይን ማራኪ የሆኑ አካላዊ ገጽታዎች ላይ ለውጥ ቢኖርም አሠራር ላይ ግን አሁንም ብዙ ነገር ይቀራል። ይህ ችግር ግን የተቋማቱ ብቻ ሳይሆን እንደ ማህበረሰብ ያልቀረፍነው የአመለካከት ችግር ስላለ ነው። ከዚህ በፊት በሌላ አጋጣሚ የጠቀስኩት አንድ ማሳያ ልጥቀስ።

ከዓመት በፊት ከፓስፖርት ጋር ለተያያዘ ጉዳይ ስመዘገብ ያጋጠመኝ ነው። ክፍያው በሞባይል ባንኪንግ ብቻ ነው። የሞባይል ባንኪንግ ክፍያ አገልግሎት ከተጀመረ ቆይቷል። እናም የምዝገባ ቦታው ላይ ክፍያው በዚህ አማራጭ ብቻ መሆኑ ሲነገር በጣም ሲቆጡ እና ሲደነፉ የነበሩ የተማሩ የሚባሉ ሰዎች ነበሩ። ለመብታቸው ተቆርቋሪ እና መብታቸውን አስጠባቂ መስለው ሲደነፉ ዓለም የደረሰበትን ደረጃ ግን አያውቁም ነበር ማለት ነው። የያዙት ስልክ ግን ከመቶ ምናምን ሺህ በላይ የሚገዛ ነው። ይህ እንደ ሕዝብ ያለብን የአመለካከት ችግር ነው።

በተቋማት በኩል ደግሞ፤ አንድ ነገር ‹‹እንደዚህ አድርጉ›› ተብለው ትዕዛዝ ከተሰጣቸው ‹‹ለምን? እንዴት?›› ብሎ መጠየቅ የሚባል ነገር የለም። ዝም ብለው ተቀብለው ‹‹ከላይ መጣ ትዕዛዝ ነው›› በማለት ተገልጋዩን ሕዝብ ማጉላላት ነው። ‹‹ኧረ ይሄ ነገር እንዴት ይሆናል? ምን ነክቷችሁ ነው? ይህ እኮ የለም?›› ሲባሉ ‹‹እኛ ምንም ማድረግ አንችልም ከላይ የመጣ ትዕዛዝ ነው›› በማለት ያደፋፍኑታል።

ከላይ ትዕዛዝ ሲመጣ፤ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ አገናዝቦ ‹‹ይህ በዚህ ይስተካከል›› ብሎ አስተያየት መስጠት ያስፈልጋል። ለሕዝቡ ከላይኛው አካል ይልቅ የታችኛው አካል ይቀርባልና የሚፈጸሙ እና የማይፈጸሙ ሁኔታዎችን መለየት አለበት። ቢቻል ቢቻል የላይኛው አካል የሚባለው ራሱ በጥናት የተደገፈ እና ሀገራዊና አካባቢያዊ ሁኔታዎችን ያገናዘበ ቢሆን። ከታች ያለውን አካልም ሃሳብ እንዲሰጥ ዕድል ቢሰጥ፤ አለበለዚያ ብዙ ጊዜና ገንዘብ ባክኖ የተጀመረ አዲስ አሠራር ተግባራዊ ሳይሆን ከንቱ ሆኖ ይቀራል ማለት ነው።

የአመለካከት ለውጥ በሰፊው ያስፈልገናል። ለሁሉም ነገር መሠረት የሚሆነው የአመለካከት ለውጥ ነው። ቅንነት ሲኖር ነው። አለበለዚያ ስምን ማደስ፣ ስምን መለወጥ፣ ስምን ማሻሻል አይቻልም። አሁንም የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን አሠራር ምሳሌ አድርገን እንታዘብ።

የሀገራችንን ነባራዊ ሁኔታ እናውቃለን፤ ተቋማት ሁሉ ነገር የተሟላላቸው ላይሆን ይችላል። ቢያንስ ግን በራሳቸው የሚያዝዙበትን የአዕምሯቸውን ቅንነት ቢጠቀሙ ምን ችግር ነበረው? አንድ አገልግሎት ለማግኘት አስፈላጊ የሚባሉ ሰነዶችን ይዘን እንሄዳለን። የሚያስፈልጉ ሰነዶችን ሲጠይቁን ግን በትህትና ሳይሆን በቁጣ ድምጸት ‹‹ምንድንትስ ያስፈልጋል!›› ልያዝ አልያዝ ሳያውቅ/ሳታውቅ ልክ እንዳልያዝኩ በሚመስል ድምጸት መናገር ለምን አስፈለገ? ይሄ ማለት አገልግሎት ሰጪው ‹‹አይቻልም!›› የሚባልበት ሰበብ ይፈልጋል ማለት ነው። ይሄ ስንፍና ብቻ ሳይሆን ተንኮል ጭምር ነው።

ለጉዳዩ የሚያስፈልገውን ነገር ሳላሟላ አገልግሎቱን ካላገኘሁ አልልም፤ ቢያንስ ግን አለማሟላቴን ካረጋገጡ በኋላ እንደማይቻል በትህትና መናገር ምን ይከብዳል? ግዴለም! ትህትናውንም ቢሆን ‹‹አንተን አልለማመጥም!›› ብሎ መተው ይቻላል፤ ቢያንስ ግን መቆጣት ያለበት/ያለባት አለመሟላቴን ካረጋገጡ በኋላ ነው። ለዚያውም እኮ ደግሞ ምን እንደሚያስፈልግ እንኳን በትክክል ሳይናገሩ ነው። በየጊዜው በሚቀያይሩት አሠራር ደንበኛውስ ቢሆን የሚያስፈልጉትን በሙሉ በምን ያውቃል?

በአጠቃላይ ሀገራዊ ለውጥ (ሪፎርም) የሚኖረን እንደ መንግሥትም ሆነ እንደ ሕዝብ ዘመኑ የደረሰበት ደረጃ ላይ ለመድረስ የሚያስችል አሠራር ሲኖረን ነው፤ ለዚህ ደግሞ ዘመናዊ አመለካከት ይኑረን!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጳጉሜን 2 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You