“ሀገርን በድል ማስቀጠል የተቻለበት ሂደት ለቀጣይ የእድገት ጉዟችን እንደወረት የሚወሰድ ነው” – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፡- ሀገርን በድል ማስቀጠል የተቻለበት ሂደት ጠቃሚ ተሞክሮዎች የተገኙበትና ለቀጣይ የእድገት ጉዞ እንደወረት የሚወሰድ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለፁ።

የመሻገር ቀን “የመሻገር ጥሪቶች፤ የአዲስ ብርሃን ወረቶች” በሚል መሪ ሃሳብ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ትናንት በሳይንስ ሙዚየም ተከብሯል።ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በመርሃግብሩ ላይ፤ “ባለፉት ስድስት ዓመታት እንደ ሀገር በርካታ ውስብስብ ፈተናዎች ቢያጋጥሙንም ፈተናዎቹን በመቋቋም አንፀባራቂ ድል ማስመዝገብ ችለናል። ሪፎርም ሲጀመር አታካች ቢመስልም በሂደት እየፈካ እንደሚሄድ በለውጥ ጉዟችን አረጋግጠናል” ብለዋል።

በተለያዩ የልማት መስኮች የተጀመሩ ሰፋፊ ሥራዎችና የተገኙ ድሎች የመንግሥትን የፖሊሲ አቅጣጫዎች ትክክለኛነት እና የሀገራዊ ብልፅግና ፍኖቱ የኢትዮጵያን ራዕይ እንደሚያሳካ የሚያመላክቱ መሆናቸውንም ጠቁመዋል። በግብርናው ዘርፍ በስንዴ ልማት የታየው ለውጥ የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ፣ የአርሶ አደሩን ሕይወት በማሻሻል፣ የግብርና ኢኮኖሚውን በማጎልበትና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት ረገድ ጉልህ ድርሻን አበርክቷል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በውጤቱም ኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት ከምትታወቅበት የስንዴ ልመና ወጥታ የውስጥ ፍላጎትን በማሟላት ስንዴ ለውጭ ገበያ መላክ ወደቻለችበት ታሪካዊ ምዕራፍ መሸጋገሯን አንስተዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት የቱሪዝም ዘርፉ የመንግሥት ቀዳሚ የትኩረት መስክ ሆኖ በገበታ ለሸገር፣ በገበታ ለሀገርና በገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ፀጋ የሚመጥኑ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ማልማት መቻሉንም አመላክተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ዘርፉ ተወዳዳሪነት እንዲጠናከር፣ የኤክስፖርት ንግድ እንዲስፋፋ እና ከውጭ የሚገቡ የኢንዱስትሪ ምርቶች በሀገር ውስጥ ምርቶች እንዲተኩ በማድረግ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል እንደፈጠረ የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በተለያዩ ምክንያቶች ማምረት ያቆሙ ኢንዱስትሪዎችን ወደተሟላ የማምረት እንቅስቃሴ በማስገባትና አቅማቸውን በማሳደግ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች በመተካት ረገድ የታየው እመርታዊ ሽግግር ትምህርት የሚወሰድበትና ላስቀመጥነው ሀገራዊ ራዕይ ስንቅ ሆኖ የሚያለግል ነው ብለዋል፡፡

የሁሉም ኢትዮጵያውያን ዐሻራ ያረፈበትና የትውልዱ የቃልኪዳን ሃውልት የሆነው ዓባይ ግድብ በአሠራርና በአመራር ውስንነት ምክንያት ተንገራግጮ ከቆመበት፣ ብልሃት በተመላ ቆራጥ ውሳኔ እና አመራር ሃይል ወደሚያመነጭበት ደረጃ እንዲሸጋገር በማድረግ የሉዓላዊነት መገለጫ እንዲሆን መደረጉንም አመላክተዋል።

ካለፉት ፈታኝ ጉዞዎች ትምህርቶችንና ተሞክሮዎችን በመውሰድ ለቀጣይ ድሎች መታጠቅና ተስፋን መሰነቅ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፣ አዲስ ዓመት አዲስ ተስፋ የሚሰነቅበት፣ በጎ ጅማሮ የሚበሰርበትና አዲስ ምዕራፍ የሚታወጅበት እንደመሆኑ መጠን መንግሥትና ሕዝብ በታደሰ ቁርጠኝነትና በጠነከረ የትብብር መንፈስ ለላቀ ስኬትና ድል መዘጋጀት ይኖርባቸዋል ነው ያሉት፡፡

በተገኙ ድሎች ሳንኩራራና በሚገጥሙን ፈታናዎች ሳንደናቀፍ በጀመርነው የእድገትና ብልፅግና ሂደት በፍጥነት በመጓዝ ድህነትንና ኋላ ቀርነትን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ ይገባናል። ለዚህም ሁሉም ዜጋ ሀገርንና ሕዝብን በቅንነት፣ በታታሪነትና በፍፁም ቁርጠኝነት ማገልገልና ለላቀ ሀገራዊ ድል መዘጋጀት አለበት ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት በፈታኝ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች ውስጥ ብታልፍም በአማካይ ሰባት ነጥብ ስድስት በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ፣ ከሰሃራ በታች ሦስተኛ ከምስራቅ አፍሪካ ደግሞ አንደኛ የሆነ ግዙፍ ኢኮኖሚ ያላት ሀገር ሆናለች ብለዋል።

በመድረኩ በተለያዩ ዘርፎች በተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች የተገኙ ውጤቶች፣ ተግዳሮቶችና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን የሚዳስስ ዘጋቢ ፊልም ቀርቧል። ኢትዮጵያ ባለፋት ስድስት ዓመታት ያጋጠሟትን ፈተናዎች ተሻግራ ዛሬ ላይ እንድትደርስ ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል ለተባሉ በኢነርጂ፣ በግብርና እና በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፎች አስተዋፅኦ ላበረከቱ የተለያዩ አካላትም እውቅና ተሠጥቷል።

ተስፋ ፈሩ

አዲስ ዘመን ጳጉሜን 2 /2016 ዓ.ም

Recommended For You