ታላቅ ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ

የምሁር ዕውቀት የሰዎችን ኑሮና አኗኗር ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሻሻል የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለበት ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ በእያንዳንዱ የዕውቀት ዘርፍ የሚደረግ ጥናትና ምርምር የሰዎችን ሕይወት በማሻሻል ላይ ማዕከል ያደረገ መሆን እንዳለበትም እንዲሁ፤ ስለዚህ፣ አንድ ሰው በትክክል “ምሁር” ለመባል ብቁ የሚሆነው ዕውቀቱን ከራሱ አልፎ በሌሎች ሕይወት ላይ ለውጥና መሻሻል ለማምጣት የሚጠቀምበት ከሆነ ነው። ምሁርነትም ከዚህ አንፃር ታይቶና ተመዝኖ የሚሰጥ ክብር እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ።

ስለዚህ ምሁር ማለት በልምድ፣ በትምህርትና በልዩ ልዩ መንገድ ያገኛቸውን ማስተዋሎችና ዕውቀት በሃሳብ መልክ ለኅብረተሰቡ የሚያቀርብ ሰው ነው። ለዚህ ቃል ብቁ ሆነው የተገኙ ጥቂት የሚባል ቁጥር የሌላቸው በዓለም መድረክ ላይ የሀገራቸውን ስም ያስጠሩ ዕንቁ ኢትዮጵያን አሉ፤ ከእነዚህ መካከል ፕሮፌሰር አንድሪያስ እሸቴ አንዱ ናቸው።

አብዛኞች እንደዋዛ ጥለዋት በሚለይዋት ዓለም በተቃራኒው ጥቂቶች ከራሳቸው ለሌሎች የሚተርፍ አስተዋጽኦ አበርክተው ማለፉ ይሳካላቸዋል። በሚያልፍ ዕድሜ የማያልፍ ሥራ ሠርተው ስማቸው ሲወሳ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ከቀናት በፊት ከዚህ ዓለም ድካም ያረፉት ፕሮፌሰር እንድሪያስ፣ ባለዕውቀት፣ ብስለት ከጥበብ ጋር ከሰመረላቸው ለኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ከሰሩ ኢትዮጵያውያን መካከል እንደሆኑ ብዙዎች ይመሰክሩላቸዋል።

ፕሮፌሰር አንድሪያስ እሸቴ፣ ከወላጅ እናታቸው መንበረ ገብረማርያም እና ከወላጅ አባታቸው ከእሸቴ ተሰማ ተወልደው በመሀል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ልጅነታቸውን አሳልፈዋል፡፡

ከእናት እና አባታቸው በመቀጠል ያሳደጓቸው አጎታቸው ጀማነው አላብሰው ወጣትነታቸውን ደግሞ በፓንክረስት ቤተሰቦች ውስጥ እንደ ልጅ በመሆን ትምህርታቸውን እየተከታተሉ በእንክብካቤና በንባብ ራሳቸውን በእውቀትና በልምድ ማጎልበት ችለዋል፡፡

በሀገራችን ኢትዮጵያ የዘመናዊ ትምህርት ቤት ፋና ወጊ በመሆን በሚጠቀሰው ዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የትምህርት ሕይወታቸውን ‘ሀ’ ብለው የጀመሩት የያኔው አንድሪያስ እሸቴ፣ በዊልያምስ ኮሌጅ ትምህርታቸውን ተከታትለው ከየል ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን እስካገኙበት ጊዜ ድረስ ሰፊ የንባብ ልምድና የፍልስፍና ሕይወት ውስጥ ያለፉ ናቸው፤ ከሀገር ውጭ በተለያዩ ቦታዎች ከሰሩና በበርካታ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ካስተማሩ በኋላ ወደ ሀገር ውስጥ በመመለስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት በመሆን አገልግለዋል።

ከዚህ በመቀጠል በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ለቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ አማካሪ በመሆን አገልግለዋል፡፡ በ1987 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ሲረቀቅም በአባልነት የራሳቸውን ሚና አበርክተዋል፡፡

ፕሮፌሰሩ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት በነበሩበት ወቅት በርካታ ለትውልድ የሚሻገሩ ሥራዎችን የሰሩ ሲሆን፣ በፕሬዚዳንትነት ጊዜያቸው ካበረከቷቸው አስተዋፅኦዎች መካከል በፖሊሲ ደረጃ ውሳኔን በማሳለፍ ዓይነስውራን በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ገብተው ትምህርታቸውን መከታተል እንዲችሉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ምሁር እንደሆኑ ይጠቀሳል፡፡ በጋይዳንስ እና ካውንሲሊንግ ስር የነበረውን ለብቻው በማውጣትና ቦታ ሰጥቶ ሕንፃ በማሰራት የመጀመሪያውን የአካል ጉዳተኞች ተማሪዎች ማዕከል ወይም (የልዩ ፍላጎት ድጋፍ ማዕከል) ያቋቋሙት ፕሮፌሰሩ ናቸው፡፡

ለብቻው ሞደርን አርት ሙዚየም በመባል የገብረ ክርስቶስ ሥራዎች አሁን ባሉበት መልኩ ተለይተው እንዲቀመጡና እንዲጎበኙ፤ ተያይዞም ጥናትና ምርምር እንዲሰራባቸው አስደርገዋል፡፡ እንዲሁም ከሰባ ዓመታት በላይ ባስቆጠረው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያዋ ሴት ምክትል ፕሬዚዳንት የዛሬዋ ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም የተሾመችው በዚሁ ጊዜ ነው፡፡ በርካታ በፒ.ኤች.ዲ ደረጃ አዳዲስ የትምህርት ዘርፎች እንዲከፈቱ ያደረጉት አበርክቶ ይጠቀሳል፡፡

ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋን የሴት ፕሮፌሰር፣ ፕሮፌሰር የዓለምፀሐይ መኮንን ማዕረጉን ያገኙት በዚሁ በፕሮፌሰሩ የፕሬዚዳንትነት ጊዜ ነበር። በዕለቱም በሽልማት ሁሉ በማበረታታት በደስታ ብዛት ዕንባ ተናንቋቸው እንደነበር በዕለቱ በመድረኩ የታደሙ ታዳሚዎች ይመሰክራሉ፡፡

ፕሮፌሰሩ ሴቶችን ከማብቃት ጋር ስማቸው በተደጋጋሚ ተያይዞ ይነሳል፡፡ በተጨማሪም በፕሬዚ ዳንትነት ዘመናቸው ከሰሯቸው ሥራዎች ሌላው ከትምህርት ክፍሉ ወጥተው ሙዚቃ፣ ቴአትርና ስዕል አንድ ላይ በመሆን ራሳቸውን ችለው እንደ ኮሌጅ ቢቋቋሙ በማለት የተለያዩ ምሁራንን በመጋበዝ ኮሌጁን በእግሩ እንዲቆም አድርገዋል፤ በተጨማሪም ለቴአትር ትምህርት ቤት ታላቁን አዘጋጅ አባተ መኩሪያን ወደ ዩኒቨርሲቲው በማምጣት አዲሱ ትውልድ ልምዱን እና እውቀቱን እንዲቀስም ያደረጉት እኚሁ ፕሮፌሰር አንድሪያስ እሸቴ ናቸው ይላል ታሪካቸው፡፡

ፕሮፌሰር አንድሪያስን፣ ሌሎች የሀገራችን ምሁራን ሲገልጿቸው፤ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በዋነኝነት በሕግ ፍልስፍና ዙሪያ ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማድረግ በርካታ የሕትመት ውጤቶችን ከማሳተም ባለፈ ሕግና አዋጅ በማርቀቅና የፖሊሲ ማሻሻያ በማድረግ ለሀገርም ሆነ ለአፍሪካ የራሳቸውን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረግ የቻሉ ፈላስፋ ናቸው ይሏቸዋል፡፡

አንድሪያስ፣ ገና በወጣትነታቸው በመጀመሪያ ባሳተሙትና ሪቻርድ ፓንክረስት በሚያሳትሙት “Ethiopia observer” የተሰኘው መፅሔት ላይ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ብዙም ያልተወራለት የኢትዮጵያ የመረዳጃ ሀብቶች ስለሆኑት ስለ እድር፤ እቁብ እና ማህበራት ዙሪያ ከሪቻርድ ፓንክረስት ጋር በመሆን “self-help in Ethiopia” በሚል ርዕሰ አርቲክል በመፃፍ ባሕላችን ከሌላው ዓለም ጋርም ምን ዓይነት መስተጋብር እንዳለው በመዳሰስ እና በመዘርዘር በተጨማሪም ሀገር በቀል እውቀትና ባሕልን አጉልቶ በማሳየት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነበራቸው፡፡

ፕሮፌሰር አንድሪያስ በሥራ ዘመናቸው በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ የሥራ ተሞክሯቸው በዩኔስኮ የሰብዓዊ መብት፣ የሰላም እና የዴሞክራሲ ሊቀ-መንበር በመሆን አገልግለዋል፡፡

በአሜሪካን ሀገር በነበሩበት ወቅት በሰብዓዊ መብቶች ንቅናቄ ላይ ንቁ ተሳታፊ ነበሩና በብላክ ፓንተር ፓርቲ ውስጥም ተሳትፎ የነበራቸው ምሁር ነበሩ፡፡ በሞራል እና ፖለቲካዊ ፍልስፍናዎች እንዲሁም ሥነ-ምግባር ላይ ያተኮሩ የድርሰት ውጤቶችን በበርካታ መንገዶች ለሕትመት አብቅተዋል፡፡ ከፍልስፍና ባሻገር ስለ ኢትዮጵያ አጫጭርም ሆነ ረጃጅም አርቲክሎችን በተለያየ ወቅት አስነብበዋል።

ፕሮፌሰሩ፣ በሙሉ ጊዜያቸው ተምረዋል፤ አስተምረዋል፤ ተፈላስፈዋል፡፡ በአስተማሪነት ከአገለገሉበቸው ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በአሜሪካን ሀገር በሚገኘው ብራውን ዩኒቨርሲቲ፣ ዩሲኤልኤ፣ በርክሊን፣ ፔንሲልቬንያ ዩኒቨርሲቲ ከሀገር ውጭ ያስተማሩባቸው ቦታዎች ሲሆኑ፣ በርካታ ተማሪዎችም ማፍራት ችለዋል።

የተለያዩ ቦታዎች ማስተማር ብቻ ሳይሆን የተለያዩ የትምህርት ዓይነቶችንም በማስተማር ይታወቁ ነበር። ከፍልስፍና እስከ ሥነ-ምግባር፣ ከሃይማኖት እስከ ሥነ-ውበት፣ ከወንድማማችነት እስከ ነፃነት በርካታ ፍልስፍናዎችን ማጋራት ችለዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅናን ካተረፉ ዝነኞች ውስጥ በአሜሪካ ከዋነኞቹ የፖለቲካ ፈላስፋ መሀል ጆሴፍ ኮን እንዲሁም የሂውማን ራይትስ ዎች ፕሬዚዳንት ኬኔት ሮፍ ከፕሮፌሰሩ ተማሪዎች ውስጥ ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ፕሮፌሰሩ፣ ገና በወጣትነታቸው በኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ወቅት ታዋቂ ምሁር ከነበሩት ውስጥ አንዱ ነበሩ። በብዕር ተጋድሎአቸው፣ ከጥቁሮች መብት ጋር ባላቸው አቋም፣ በአንባቢነታቻው፣ በምሁርነታቸው ብቻ አልነበረም የሚታወቁት፤ ይልቁንም በመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን) ፓርቲ ውስጥ በመታቀፍ አባል ሆነው ለሀገራቸው ያበረከቱት ፖለቲካዊ አስተዋፅኦ አብሮ ይነሳል፡፡

ፕሮፌሰር አንድሪያስ፣ ከታላላቆቹ ፈላስፎች ውስጥ የፕሌቶ፣ የማርክስ እና ሄግልስ አድናቂ ሲሆኑ፣ ከሀገር ውስጥ ምሁራን እነ ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ እና መንግሥቱ ለማ ሥራዎችን ማንበባቸውን እና መውደዳቸውን ሳይሸሽጉ ለሥነ-ጽሑፍም ከፍተኛ ፍቅርና ክብር እንዳላቸው ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡

ከማስተማር እና ከዩኒቨርሲቲ ሕይወት ባሻገር በተለያዩ ዘመናት በጦርነት ሰበብ በርካታ የሀገር ቅርሶች፣ የቤተክርስትያን እና የሀገር መዛግብት፣ መስቀል እንዲሁም የብራና መጻሕፍቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ለመመለስ ታስቦ በተቋቋመው የተወሰዱ እና የተዘረፉ የኢትዮጵያ ቅርሶችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስመለስ በነበረው ኮሚቴ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር ከፍተኛ ሙግት በመግጠም እና በማሳመን የተወሰኑትን ሀብቶች በጊዜው ማስመለስ ከቻሉ የኮሚቴ አባላት ውስጥ አንዱ ፕሮፌሰር አንድሪያስ እሸቴ ናቸው፡፡

ፕሮፌሰር እንድሪያስ፣ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በ1995 ሕገ-መንግሥት በሚሻሻልበትና በሚረቀቅበት ወቅት የሕገ-መንግሥት እና አስተዳደር ጉዳዮች አስተባባሪ አባል በመሆን አገልግለዋል፡፡ በቦርዱም ውስጥ ከፍተኛ የሆነ አስተዋፅኦ እንደነበራቸው ይነገርላቸዋል፡፡

የአፍሪካ ህብረት የሰብዓዊ መብቶች መታሰቢያ ፕሮጀክት ጊዜያዊ ቦርድ ሊቀ-መንበር እና አባል በመሆን ፓን አፍሪካነትን በፅኑ ከሚያቀነቅኑ ምሁር ውስጥ በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡ እንዲሁም የጣና ፎረም ከፍተኛ ደረጃ መድረክ ሊቀ-መንበር በመሆን እና የፌዴሬሽን መድረክ ቦርድ አባል በመሆን አገልግለዋል።

ፕሮፌሰሩ፣ ከጽሑፎቻቸው መካከል ስለ “ወንድማማችነት” የጻፉት ጽሑፍ በኢትዮጵያ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ ትልቅ ሚና ተጫውቷል ይባልላቸዋል። ከሦስቱ አስተሳሰቦች፣ “ነፃነት፣ እኩልነት እና ወንድማማችነት” ውስጥ የምዕራቡ ዓለም የፖለቲካ ፈላስፋዎች “ነፃነት እና እኩልነት” ላይ ያተኮሩ እና “ወንድማማችነትን” ችላ ብለዋል የሚሉት ፕሮፌሰር አንድሪያስ፤ በኢትዮጵያ የብሔር ፌዴራሊዝም አውድ ውስጥ “ወንድማማችነት” የሚለውን ሃሳብ የጋራ ቋንቋ እና ባሕል ላላቸው ብሔረሰቦች መተግበር አስተማማኝ ስለመሆኑ ይናገሩ ነበር።

ፕሮፌሰሩን ከሥራ ሕይወታቸው ባሻገር የቅርብ ወዳጆቻቸው ሲገልጧቸው ‘አንባቢና ሙሉ ፈላስፋ ነው’ ይሏቸዋል፡፡ ‘የምትተማመኑበት ጓደኛ፣ አዋቂ እና ተጫዋች ነው፡፡ ስስ የሆነ ነፍስ አለው፤ የተጎዳ ሰው ካየ በዕንባ ሀዘኑን ይገልፃል፡፡ ደግና ለሴቶች መብት አብዝቶ የሚጨነቅ ሰው ነው፡፡’ ብለው ይገልጿቸዋል። በኢትዮጵያ ቁልፍ የታሪክ ሁነቶች ውስጥ ታዛቢ ብቻ ሳይሆኑ ቁልፍ ተሳታፊም ነበሩ፡፡

ፕሮፌሰር አንድሪያስ እሸቴ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨር ሲቲ ፕሬዚዳንት በነበሩበት ወቅት በዩኒቨርሲቲው ውስጥ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች እውቅና እንዲያገኙና ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠርላቸው ለሚደረገው ጥረት ድጋፍ በማድረግ በሀገራችን የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ የአካል ጉዳተኞች ማዕከል ተቋቁሟል፤ በርካታ አገልግሎቶችን በመስጠት ላይም ይገኛል።

በዚህ ሳይቆም የኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማኅበር መሠረታዊ የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ ስልጠና በዩኒቨርሲቲው ሥነ ልሳን ክፍል በኩል ጥያቄ አቅርቦ ለጥያቄው መልካምና ቀና ምላሽ በመሰጠቱ መስማት የተሳናቸው የብሔራዊ ማኅበር አባላት በየሳምንቱ መጨረሻ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ መሠረታዊ የምልክት ቋንቋ ስልጠና ለረጅም ጊዚያት ሲሰጥ ቆይቷል።

በዚህም ለኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ እና መስማት የተሳናቸው ባሕል ትምህርት በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ደረጃ እንዲሰጥ ተደርጓል። ፕሮፌሰር አንድሪያስ እሸቴ፣ መስማት የተሳናቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ቋንቋና ባሕል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እዚህ ደረጃ መድረስና የበርካታ መስማት የተሳናቸው የከፍተኛ ትምህርት እድል መከፈት መሠረት የጣሉ ባለውለታ ነበሩ::

ፕሮፌሰር አንድሪያስ፣ ከወለዱት ልጃቸው አሉላ አንድሪያስ በተጨማሪ የአባት ፍቅር እየሰጡ ያሳደጓቸው የቀድሞ ባለቤታቸው የእሙዬ አስፋው ሁለት ልጆችን ታጠቅ እና አደይን ጨምሮ የሶስት ልጆች አባት ነበሩ። እኛም እኚህን ጉምቱ የሀገር ባለውለታ ምሁር በዚህ መልኩ ያስታወስናቸው ሲሆን፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መፅናናትን እየተመኘን ነው፡፡

ክብረአብ በላቸው

 አዲስ ዘመን ነሐሴ 29/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You