ዩናይትድ ኪንግደም አንዳንድ የጦር መሣሪያዎች ለእሥራኤል እንዳይሸጡ አገደች

ዩኬ ለእሥራኤል የምትሸጣቸው አንዳንድ የጦር መሣሪያዎች ዓለም አቀፍ ሕግ የሚጥስ ተግባር ሊፈፅማባቸው ስለሚችል በሚል ሽያጯን መግታቷን አስታውቃለች። የዩኬ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ ሀገራቸው ወደ እሥራኤል ከምትልካቸው 350 የጦር መሣሪያዎች መካከል 30 የሚሆኑትን አግዳለች ብለዋል።

ወደ እሥራኤል እንዳይላኩ ከታገዱት የጦር መሣሪያዎች መካከል የጦር አውሮፕላኖች፣ ሄሊኮፕተሮች እና ድሮኖች ይገኙበታል። አንድ የእሥራኤል ባለሥልጣን የዩኬ ውሳኔ “የተሳሳተ መልዕክት የሚያስተላልፍ እና የሚያበሳጭ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። ሚኒስትር ላሚ፤ እሥራኤል ራሷን የመከላከል መብቷን ዩኬ ትደግፋለች ብለው ይህ ውሳኔ የጦር መሣሪያ ማዕቀብ ተደርጎ መወሰድ እንደሌለበት አሳስበዋል።

የእሥራኤል የዲያስፖራ ጉዳዮች ኃላፊ የሆኑት አሚቻይ ቻክሊ ይህ ውሳኔ እሥራኤል በሐማስ ታግተው የተገደሉባት ስድስት ዜጓችን እየቀበረች ባለች ወቅት መሆኑ “ስሜታዊ” ያደርገዋል ብለዋል። “ከኢስላሚክ ስቴት ግሩፕ፣ ከአል-ቃዒዳ እና ሐማስ ጋር የሚደረገው ጦርነት ተመሳሳይ ነው። ይህ ጦርነት በምዕራባዊ ሥልጣኔ እና በአክራሪ ኢስላም መካከል የሚደረግ ነው” ብለዋል።

የእሥራኤል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ ውሳኔውን ተከትሎ በሰጡት አስተያየት ሀገራቸው ዓለም አቀፍ ሕግን ተከትላ እርምጃ እየወሰደች እንዳለች ተናግረዋል። ሌሎችም በዩናይትድ ኪንግደም ውሳኔ ደስተኛ ያልሆኑ ከፍተኛ የእሥራኤል ባለሥልጣናት በማኅበራዊ ሚዲያ ገፆቻቸው በውሳኔው የተሰማቸውን እያጋሩ ይገኛሉ።

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የዩኬ ኃላፊ የሆኑት ሳሻ ዴሽሙኽ በበኩላቸው ዕገዳው “በጣም ውሱን እና በተለያዩ ክፍተቶች የተሞላ ነው” ሲሉ አጣጥለውታል። ምዕራባውያን መንግሥታት ከእሥራኤል ጋር የሚያደርጉትን የጦር መሣሪያ ንግድ ተከትሎ ወቀሳ እየደረሰባቸው ሲሆን እስራኤል በሐማስ ላይ በከፈተችው ጦርነት ምክንያት በጋዛ ሰርጥ እየፈፀመችው ባለው ተግባር ትችት ይቀርብባታል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እንዳሉት በርካታ የሕዝብ እንደራሴዎች፣ የሕግ ሰዎች እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ብሪታኒያ ወደ እሥራኤል የምትልከውን የጦር መሣሪያ አስመልክቶ ያላቸውን ስጋት አጋርተዋል። አዲሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባለፈው ሐምሌ ወደ ሥልጣን እንደመጡ ብሪታኒያ ወደ እስራኤል የምትልከውን የጦር መሣሪያ መገምገማቸውን ተናግረዋል።

ላሚ፤ ግምገማው “እሥራኤል ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕግጋትን ጥሳለች ወይ?” የሚለውን አልተመለከተም ብለው “ይህ ነፃ የመሆን አሊያም የወንጀለኝነት ፍርድ አይደለም” ሲሉ የሀገራቸውን ውሳኔ ተከላክለዋል። የዩኬ መንግሥት ውሳኔውን ባሰፈረበት ወቅት እሥራኤል በጋዛ ያለውን እርዳታ እንዴት ታየዋለች እንዲሁም በቁጥጥር ሥር ያሉ ሰዎች እንዴት ትንከባከባለች የሚለውን ከግምት ማስገባቱን አስታውቋል።

ተንታኞች ውሳኔው ከወታደራዊ አንድምታው ይልቅ ፖለቲካዊው ያመዝናል ይላሉ። እሥራኤል አንድ በመቶ የጦር መሣሪያ ብቻ ነው ከዩኬ የምታስገባው። ዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛውን የጦር መሣሪያ ለእሥራኤል የምትልክ ሲሆን እሥራኤል ከምታስመጣቸው የጦር መሣሪያዎች መካከል 69 በመቶ ከአሜሪካ ነው የሚመጡት ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

 አዲስ ዘመን ነሐሴ 29/2016 ዓ.ም

Recommended For You