የሶማሊያና ግብፅን ወታደራዊ ስምምነት የተቃወሙት የፓርላማ አባል ከኃላፊነታቸው ተነሱ

ከአጋሮቻቸው ጋር በመሆን የግብፅ ሠራዊት ወደ ሶማሊያ መግባቱን የሚቃወም መግለጫ የሰጡት የሳውዝ ዌስት ግዛት የፓርላማ ቤት አባል አብዲረሺድ ሞሃመድ ኑር ጂሌይ፤ በሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ተሹመውበት ከነበረው “የጤና እና ሥነ ምግብ ልዩ ልዑክ” ኃላፊነታቸው ተነስተዋል።

የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ፤ የልዩ ልዑክ ከኃላፊነት መነሳት ባስታወቁበት መግለጫቸው የሀገሪቱ ዜጎች የሀገራቸውን ሉዓላዊነት “ለመጠበቅ እንዲነሱ” ጠይቀዋል።

ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ፤ ነሐሴ 26 ቀን 2016 ዓ.ም የጤና እና ሥነ ምግብ ልዩ ልዑኩን ከኃላፊነት ማንሳታቸውን ያስታወቁት ከሳውዝ ዌስት ግዛት የተወከሉ የፓርላማ አባላት መግለጫ መስጠታቸውን ተከትሎ ነው።

የሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት አባል ከሆኑ ግዛቶች አንዱ የሆነው ሳውዝ ዌስት፤ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያዋስን ድንበር አለው።

የፓርላማ አባላቱ ውይይት ካደረጉ በኋላ የሰጡት መግለጫ በዋነኛነት ሶማሊያ እና ግብፅ በገቡት ወታደራዊ ስምምነት ላይ ትኩረት ያደረገ ነው። ሁለቱ ሀገራት ፕሬዚዳንቶቻቸው በተገኙበት በካይሮ ወታደራዊ ስምምነቱን የተፈራረሙት ከሁለት ሳምንት በፊት ነበር።

ይህንን ስምምነት ተከትሎም ባለፈው ሳምንት ሁለት የግብፅ የጦር አውሮፕላኖች ጦር መሣሪያዎችን ጭነው ሞቃዲሾ ደርሰዋል። መግለጫ የሰጡት የሳውዝ ዌስት ግዛት የተወከሉ የፌዴራል ፓርላማ አባላት፤ ይህ ስምምነት ለፓርላማ አለመቅረቡን በመጥቀስ ተቃውመዋል። የሶማሊያው ፕሬዚዳንት “እርስ በእርሳቸው ከሚቃረኑ ሀገራት ጋር የተለያዩ ስምምነቶች ገብተዋል” ሲሉ ወቅሰዋል።

የፓርላማ አባላቱ፤ ስምምነቱ “ወደ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ የሚያስገባ ነው” ብለው እንደሚያምኑም ገልጸዋል።

ስምምነቱ “የናይል ጉዳይ” ወደ ሶማሊያ የሚያመጣ እና “በአፍሪካ ቀንድ ላይ ጦርነትን ሊያመጣ የሚችል” እንደሆነ ያስታወቁት የፓርላማ አባላቱ፤ ይህ አይነቱ ግጭት በተለይም በሳውዝ ዌስት ግዛት ሕዝብ ላይ ችግር የሚያስከትል መሆኑን ጠቁመዋል።

የሶማሊያ መንግሥት ከግብፅ ጋር የገባው ስምምነት ተቃውሞ የገጠመው ከሳውዝ ዌስት ግዛት ከተወከሉት የፓርላማ አባላት ብቻ አይደለም። ቅዳሜ ዕለት የሳዌዝ ዌስት ግዛት ውስጥ የምትገኘው ሁዱር ከተማ ነዋሪዎች በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) ውስጥ እያገለገሉ ላሉት የኢትዮጵያ ወታደሮች ድጋፋቸውን በመግለጽ ሰልፍ ማድረጋቸውን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ነሐሴ 28 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You