ህቫልድሚር በሚል ስያሜ የሚጠራውና የሩሲያ “ሰላይ” ነው ተብሎ የሚጠረጠረው ዓሳ ነባሪ በሩሲያ እና ኖርዌይ ድንበር ላይ ሞቶ ተገኘ፡፡ ኖርዌይ የሞተውን ዓሳ ነባሪ አካል በሙውሰድ ምርምር እንደምታደርግበት አስታውቃለች፡፡
ምዕራባውያን ሀገራት ሩሲያ ዓሳ ነባሪን በማሠልጠን የአርክቲክ ሀገራትን እየሰለለች ነው ሲሉ ይደመጣል። ሀገራቱ ይህንን እንዲሉ ያስቻላቸው ደግሞ ነጩ ዓሣነባሪ ሩሲያ ከኖርዌይ እና ስዊድን ጋር በምትዋሰንባቸው አካባቢዎች በመታየቱ ነበር።
ይህ ዓሳ ነባሪ ወገቡ ላይ ሰው ሠራሽ ቁስ መታየቱ፣ ዓሳ ነባሪው በተለየ መንገድ ለሰዎች ፍቅር ያለው መሆኑ የሩሲያ ሰላይ ነው እንዲባል ምክንያት ሆኗል። ሩሲያ በበኩሏ ዓሳ ነባሪው ለስለላ ሥራ ሥልጠና በመስጠት አሰማርተዋለች መባሏን አስተባብላለች።
በአርክቲክ ውሃማ አካባቢዎች በተደጋጋሚ የሚታየው ይህ ዓሳ ነባሪ ምን አልባት ከእንስሳት መንከባከቢያ ስፍራ ያመለጠ ሊሆን እንደሚችል ግምቷን ተናግራለች።
ይሁንና ይህ ብዙ የተባለለት ነጩ ዓሳ ነባሪ በሩሲያ እና ኖርዌይ ባሕር ላይ ዓሣ እያጠመዱ የነበሩ አባት እና ልጅ አግኝተውታል ሲል ዘ ጋርዲያን ዘግቧል።
ይህ ዓሳ ነባሪ ለሩሲያ ይሰልላል መባሉን ተከትሎ ህቫል የሚለውን የኖርዌይ ቋንቋ እንዲሁም የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ስምን በመውሰድ “ህቫልዲሚር” የሚል ስያሜ ተሰጥቶት ነበር።
የእንስሳት አፍቃሪ ሰዎች በዚህ ዓሣ ነባሪ ሞት ምክንያት ማዘናቸውን ገልጸው፤ እንስሳቱ እስከ ባለፈው ዓርብ ድረስ ጤናማ እንደነበር ተናግረዋል።
ሩሲያ በበኩሏ ስለ ዓሣ ነባሪው አሟሟት የምታውቀው ነገር እንደሌለ ገልጻ እንስሳትን ለውትድርና ተግባራት መጠቀም እንደማይገባ አስታውቃለች።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ነሐሴ 28 ቀን 2016 ዓ.ም