ዘጠኝ ወር በዝናብ የሚረሰርስ፣ ከዓመት ዓመት ምድሩ አረንጓዴ፣ ድንቅ የተፈጥሮ ፀጋ ያለው፣ ለሚሰሩ እጆች ምቹ የሆነ አካባቢ ነው ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል። የአየር ፀባዩ ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ምቹ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከክልሉ አልፎ ለሀገሪቱም ተስፋ የሚሆን ክልል ነው።
በክልሉ ምዕራብ ኦሞ ዞን ሜኤኒት፣ ዲዚ፣ ሱርማ፣ ዜልማሞ የሚባሉ ብሔረሰቦች ይገኛሉ። በነዚህ አካባቢዎች፤ ሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ከማድረግ ጎን ለጎን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በመከላከል ረገድም ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ነው በዞኑ በነበረኝ አጭር የሥራ ጊዜ ቆይታ የተገነዘብኩት። በአካባቢዎቹ ልማድና ወግ አንድ ወንድ ለሚያገባት ልጅ ቤተሰብ በጥሎሽ ብዙ ከብቶች(በሬዎች) መስጠት ይኖርበታል።
የሴት ቤተሰብ ይሄን እንደ ጥቅም ስለሚወስደው ሴት ልጅን ትምህርት ቤት ከመላክና የኢኮኖሚ አቅም እንድትፈጥር ከማድረግ ይልቅ መዳር (ለባል መስጠት) ይመረጣል። ስለ ነገ የልጁ ሕይወት ሳይሆን፣ ልጁን ሲድር በጥሎሽ ስለሚያገኘው የከብት ብዛት ነው የሚጨነቀው። እንዲህ ያለው ልማድ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣና ዛሬም ያልተቀረፈ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት እንደሆነ ነው ከአካባቢው ማህበረሰብ የሰማሁት።
አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች እንዳጫወቱኝ፤ ድርጊቱ ትልቅ ዋጋም እያስከፈለ ነው። በቂ የሆነ ከብት የሌላቸው የወንድ ቤተሰቦች የሚጠበቅባቸውን ጥሎሽ ለማሟላት ሲሉ ከአካባቢያቸው ራቅ ወዳለ ቦታ በመሄድ በድብቅ ከሰው በረት ውስጥ ከብት ነድተው እስከ መውሰድ ደርሰዋል። እንዲህ ያለው ድርጊትም በመደጋገሙ የሰው ከብት በሚወስዱና በሚወሰድባቸው መካከል የግጭት መንስኤ ሆኖ በአካባቢው ላይ ችግር እየተፈጠረ ነው።
የአካባቢውን ታዳጊዎች ከትምህርት ገበታና ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እያስቀረ ያለውን እንዲህ ያለ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ለመከላከል የግንዛቤ መፍጠሪያ ትምህርት በመስጠት የማህበረሰቡ ንቃተ ህሊና ከፍ እንዲል በማድረግ፣ እንዲሁም የአካባቢውን ሴቶች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት፣ የፖለቲካ ተሳትፎም እንዲኖራቸው እየተከናወኑ ስላሉ ተግባራት በዞኑ የተቋቋመውን የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ጠይቀን እንደሚከተለው ምላሽ ሰጥተውናል።
በመምሪያው የህፃናት ዘርፍ መብት ደህንነት ሥርፀትና ማስፋፊያ ባለሙያ ወይዘሮ ተስፋዬ ወረታ እንደነገሩን፤ አካባቢው ላይ ሴት ልጅ የሀብት ምንጭ ተደርጋ ነው የምትታየው። በራስዋ የመወሰን መብት የላትም። ሴት ብዙ ሀብት ታመጣለች የሚለው አስተሳሰብ በማህበረሰቡ ውስጥ በስፋት በመኖሩ ምክንያት ሴት ልጅን ወደ ትምህርት ቤት አለመላክ በስፋት የሚስተዋል ችግር ነው። ሴት ልጅ የሚድር ቤተሰብ ከወንዱ ቤተሰብ በጥሎሽ 30 ከብቶችና አንድ ክላሽ ያገኛል ወይንም ይሰጠዋል።
ድርጊቱ ከባሕል ተጽዕኖ ጋር የሚያያዝና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት እንደሆነ፣ ማህበረሰቡም ይህን ልማድ በቀላሉ የሚተወው ዓይነት እንዳልሆነ ነው ወይዘሮ ተስፋዬ የሚናገሩት። እንደ ወይዘሮ ተስፋዬ ገለጻ፤ ግንዛቤው ቢፈጠርም ተፈጻሚ እንዲሆን የሕግ ማዕቀፍ አብሮ መተግበር ይኖርበታል። ተባባሪ ለመሆን ፈቃደኛ ያልሆነን አካል በሕግ እንዲጠየቅ ካልተደረገ ችግሩን ለመቅረፍ ያስቸግራል ሲሉም አክለዋል።
በሕግም ተፈጻሚ እንዲሆን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ላይ ልየታ መደረጉንና ለጥሎሽ የሚሰጠው የከብት መጠን እንዲቀንስ በክልሉ ምክር ቤት ፀድቆ ሥራ ላይ መዋሉን አስታውሰዋል። ወደ ተግባራዊ አፈፃፀም በመግባት ቀደም ሲል በጥሎሽ ይሰጥ የነበረውን የከብት መጠን ከ30 ወደ አምስት ከብቶች ማውረድ መቻሉን ነው የገለጹልን።
ወይዘሮ ተስፋዬ፤ አምስት ከብቶችና አንድ ክላሽ እንዲሰጥ በሕግ የተወሰነው ተፈጻሚ እንዲሆን፣ ለሕግ ያልተገዛም ተጠያቂ እንዲሆን ቢደረግም ተግባራዊነቱ ላይ ጥርጣሬ አላቸው። ለሕጉ ተገዥ የሆነና ያልሆነ ተብሎ የተለየ አካል ስለመኖሩ እስካሁን በመምሪያው በኩል መረጃ አለመኖሩንም ነግረውናል። መምሪያው አሁንም ችግሩ እንዳልተፈታ ማረጋገጫ አድርጎ የሚወስደው ሴት ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ የሚፈለገውን ያህል አለመኖራቸውን በማየት እንደሆነ ነው ያስረዱት።
‹‹በመምሪያው በኩል እየተደረገ ባለው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት፣ ከዚህ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ወጥታ የተማረች አንድ ሴት ማግኘት ከተቻለ ለራስዋና ለሌሎችም መብት የምትከራከር ሴት ለመፍጠር ነው። በዚህም ብዙዎችን ተደራሽ በማድረግ ችግሩን በጊዜ ሂደት መከላከልና ማስቀረት ይቻላል›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡
ሌላው ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ብለው ወይዘሮ ተስፋዬ የገለጹልን፤ አንድ ወንድ ሁለትና ከዚያ በላይ ሚስት ማግባት ጉዳይ (ድርብ ጋብቻ)ነው። ድርብ ጋብቻ ማህበራዊም ኢኮኖሚያዊም ቀውስ የሚያስከትል መሆኑ በተግባር እየታየ ነው። በማህበራዊ ጉዳይ እያስከተለ ያለው ችግር በሚስቶች መካከል አለመግባባት መፈጠሩ ነው። አንዳንዶቹ በአንድ ጣሪያ ሥር የሚኖሩ በመሆናቸው በየእለቱ ስለሚገናኙ በመካከላቸው የሚፈጠረው ግጭት የበዛ ነው።
ግጭቱ የቀነሰ ቢሆንም በተለያየ ቦታ በሚኖሩት መካከልም ቢሆን አለመግባባት አይጠፋም። በተለይ ደግሞ ባል ወደ አንዷ ሴት የማድላት ሁኔታ ከተፈጠረ ተጎጂ ነኝ ብላ የምታስበው ባሏን እስከ መግደል እርምጃ ትወስዳለች። እንዲህ ያለው ወንጀል ደግሞ ልጆችንም ተጎጂ ያደርጋል። ልጆች ተንከባካቢ በማጣት፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ግንኙነታቸውም ጭምር ይጎዳሉ።
እንዲህ ያሉ ችግሮች እንዳይከሰቱ ለመከላከል፤ መምሪያው የክልሉ ምክር ቤት ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ጋር ተያይዞ ያስቀመጠውን የሕግ ማዕቀፍ አቅጣጫ መሠረት በማድረግ ትምህርታዊ ግንዛቤ በመስጠት ድርብ ጋብቻ እንዲቀር ጥረቱን አጠናክሯል። ወይዘሮ ተስፋዬ፤ በተለይ ግድያ የፈፀመች ሴት በሕግም ጭምር ስለምትጠየቅ አንዲት ሴት ከግድያ ድርጊት እንድትቆጠብ አስተማሪ ይሆናል የሚል እምነት አላቸው።
የሰዎችን የጤና ሁኔታ ካለመረዳት ጋር ተያይዞም በተለምዶ የሚጥል (ኢፕሊብሲ) የሚባለውን በሽታ ማህበረሰቡ ተላላፊ ነው በሚልና በተሳሳተ መንገድ በመረዳት ታማሚዎችን ማግለልና ከቤት አውጥቶ ጎዳና ላይ መጣል እየተበራከተ የመጣ ችግር መሆኑንና በማህበረሰቡ እየተፈፀመ ያለው ነገር ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊት የተለየ አለመሆኑን አስረድተዋል። ስለበሽታው በቂ ግንዛቤ በማስጨበጥ ማህበረሰቡ ከድርጊቱ እንዲቆጠብ ከጤና ባለሙያዎች ጋር በመሆን የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እየተሰጠ መሆኑንም አመልክተዋል።
ሌላው ወይዘሮ ተስፋዬ በተጽዕኖ ያነሱት፤ የገጠሯ ሴት ከባሏ ጋር ባላቸው የጋራ ሀብት ላይ የማዘዝና የመወሰን መብቷ የተገደበ መሆኑን ነው። እንዲህ ያለውን አስተሳሰብ በመቅረፍ የሴቷን መብት ማስከበር የሚቻለው አንዱ ተከታታይነት ያለው ግንዛቤ መፍጠር፣ በሌላ በኩል ደግሞ ጠንካራ የልማት ሥራ ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ በሚፈጥሩት የኢኮኖሚ አቅም ችግሩን እንዲሻገሩት ማስቻል ነው።
በሌሎች አካባቢ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ተደርጎ የሚወሰደው የሴት ልጅ ግርዛት ግን በአካባቢው ላይ ባለመፈፀሙ እንደ ችግር የሚነሳ እንዳልሆነ ነው ወይዘሮ ተስፋዬ የነገሩን።
በወሊድ ምክንያት የሚሞቱ እናቶች እንዳይኖሩ በወረዳዎች በሚገኙ የጤና አገልግሎት መስጫዎች (ጤና ጣቢያዎች) የእናቶች ማቆያዎች መዘጋጀታቸውንና እናቶች የመውለጃ ጊዜያቸው ሲደርስ ቀድመው በማቆያ ውስጥ ገብተው የወሊድ አገልግሎት የሚያገኙበት ሁኔታ መመቻቸቱንም ገልፀውልናል።
እናቶች የመውለጃ ቀናቸው እስኪደርስ በማዕከሉ በሚኖራቸው ቆይታ በሚያገኙት የምግብና የተለያዩ አገልግሎቶች በተጨማሪ ማህበራዊ ጉዳዮቻቸውንም ለመወያየት እድል የሚሰጣቸው እንደሆነና እናቶች በጤና ተቋም ውስጥ ለመውለድ ፍላጎት እንዲኖራቸው ያነሳሳ መሆኑን ገልጸዋል። ይህም በመልካም ጎን ይወሰዳል ብለዋል።
እንደ ወይዘሮ ተስፋዬ ገለጻ፤ በሴቶች ሁለተናዊ ተጠቃሚነት ዙሪያም መምሪያው የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል። የሥራ ዕድል የመፍጠሩ ተግባር አካባቢው ላይ ያለውን የግብርና ሥራ ዕድሎች ለመጠቀም ነው ጥረት እየተደረገ ያለው። በግብርናው ዘርፍ ለመሰማራት ከሚያስችሉ ብዙ እድሎች መካከልም፣ ከብት ማድለብ፣ ዶሮ ማርባት፣ ንብ ማነብ ሴቶች በቀላሉ ሊሰማሩባቸው የሚችሉ የሥራ ዘርፎች ናቸው። ቡና እና ቅመማቅመም አካባቢው ላይ የሚለሙ ሀብቶች እንደሆኑና በዚህ ረገድም እድሉ ሰፊ ነው።
ሴቶችን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ አካባቢው ላይ እየተንቀሳቀሱ ያሉ መንግሥታዊ ያልሆኑ የተለያዩ ድርጅቶች እያገዙ ይገኛሉ። ድርጅቶቹ ሴቶች በግብርናው ዘርፍ ከብት በማድለብ ላይ ተሰማርተው ገቢ በማግኘት የኢኮኖሚ አቅም እንዲፈጥሩ እያገዟቸው ይገኛሉ። ጎን ለጎንም የቁጠባ ባህል እንዲያዳብሩ ከሚያገኙት ገቢ እንዲቆጥቡ የግንዛቤ ትምህርት ይሰጧቸዋል፡፡
ሌላው በግብርና ዘርፍ ሴቶች ተሰማርተው ውጤታማ የሆኑበት ደግሞ የሽንኩርት ልማት ሥራ ነው። በተለይም በዞኑ ማጂ ተብሎ በሚጠራው ወረዳ ላይ ሴት የልማት ቡድኖች ሽንኩርት በማልማት ውጤታማና ሞዴልም ተደርገው የሚጠቀሱ እንደሆኑ ነው ወይዘሮ ተስፋዬ ለአብነት የጠቀሱት።
ያለሙትን ሽንኩርት ጅማ ከተማ ድረስ ወስደው እንዲያቀርቡ የገበያ ትስስር በመፍጠር የገበያ ችግርን ለመፍታት ጥረት መደረጉንም አንስተዋል። በሽንኩርት ልማት ሥራ ላይ የተሰማሩት የልማት ቡድኖች የኢኮኖሚ አቅም በመፍጠር ኑሮአቸውን ማሻሻል እንደቻሉና ለሌሎችም በአርአያነት እንደሚጠቀሱ ገልጸዋል።
እንደ ወይዘሮ ተስፋዬ ማብራሪያ፤ መምሪያው ዋና ዓላማ አድርጎ የተቋቋመውና እየሰራ ያለውም ህፃናት፣ ሴቶችና ወጣቶች መብቶቻቸው እንዲጠበቁላቸውና እንዲከበሩላቸው እንዲሁም በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ተጠቃሚ እንዲሆኑና በፖለቲካውም ተሳትፎአቸው እንዲጎለብት ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ሁለተናዊ ተጠቃሚነታቸው እንዲያድግ ማድረግ ነው፡፡
መምሪያው አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያንና ለተለያየ ችግር ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን የተመለከቱ ጉዳዮችንም እንዲሰራ በመደረጉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህንንም አካቶ እየሰራ ይገኛል።
የማህበራዊ አገልግሎቱ ዋና ትኩረትም ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው የማህበረሰብ ክፍሎችን በራስ አቅም የሚቻለውንና ከአጋር አካላት ጋር የሚሰራውን ለይቶ እገዛ የሚያገኙበትን መንገድ በማመቻቸት ለችግራቸው በመድረስ ያሉባቸውን ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ማቃለል ነው፡፡
ሴቶችም ሆኑ ወጣቶች በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚና በፖለቲካ ብቁ ሆነው መውጣት የሚችሉት፣ በሕፃናት በኩልም ስለመብቱና ደህንነቱ ተሟጋች የሆነ ዜጋን መፍጠር የሚቻለው፤ በማህበር ተደራጅተው ሲንቀሳቀሱ ነው። በመሆኑም በተለያዩ አደረጃጀቶች ሴቶችና ወጣቶች የኢኮኖሚ አቅማቸውን በማሳደግ ከጥገኝነት እንዲላቀቁ፣ ሕፃናትም ደህንነታቸው እንዲጠበቅና መብታቸውም እንዲከበርላቸው፣ ያሉባቸውን የተለያዩ ችግሮች ለመፍታት መምሪያው ኃላፊነቱን ሲወጣ ቆይቷል። አሁንም እየሰራ ይገኛል።
በሕፃናት ላይ የሚፈፀም የመብት ጥሰትን ለመከላከልና ደህንነት ለማስጠበቅ የፖሊስ ኃይል ትብብር ወሳኝ በመሆኑ በጋራ ሆኖ መሥራቱ አስፈላጊ እንደሆነ የተገለጹት ወይዘሮ ተስፋዬ፤ በባልና ሚስት መካከል በሚፈጠር አለመግባባት ፍች ሲፈፀም ተጎጂ የሚሆኑት ሕፃናት መሆናቸውን በመጥቀስ፣ ሕፃናቱ ችግር ላይ እንዳይወድቁ ቀለብ መቁረጥና መሰል ጉዳዮችን ለማመቻቸት የፍትህ አካል እገዛ አስፈላጊ እንደሆነም አስረድተዋል።
እንደ ወይዘሮ ተስፋዬ ማብራሪያ፤ በሥነ ምግባር የታነፀ በሥራ ውጤታማ የሆነ ትውልድ ለማፍራትም የደባል ሱስ ተጋላጭነትን ለማስቀረት ወጣቶች ላይ እየተሰራ ነው። መምሪያው የንቅናቄ መድረኮችን በማዘጋጀት አካባቢው ላይ መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ አድርጓል። ወጣቱ የኢኮኖሚ አቅም እንዲፈጥርም ለሥራ የሚሆን ብድር እንዲመቻች በመምሪያው ከተከናወኑት ተግባራት መካከል ይጠቀሳል።
ወጣቶች ለተሻለ ሥራ እንዲነሳሱ መዝናኛዎች ሊኖራቸው እንደሚገባ በማሰብም የወጣት ማዕከላትን በማቋቋም እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል። በዚህ ረገድም በደቡብ ኦሞ ዞን ሐመርና በና ፀማይ ወረዳዎች በተለያየ መንገድ የአካባቢውን ማህበረሰብ ለማገዝ በቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝና ባለቤታቸው ሮማን ተስፋዬ ስም በተቋቋመው ‹‹ኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን›› እገዛ ማዕከሉ ውስጥ መሟላት ያለባቸው ነገሮች ተሟልተው ወጣቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል።
የወጣቶች መዝናኛ ማዕከሎች በሻይና ቡና አቅርቦትና በተለያየ አገልግሎት መልሶ ለወጣቶች የሥራ እድል በመፍጠር፣ ወጣቶች አልባሌ ቦታ እንዳይውሉ በማስቻል፣ ሲጋራ ከማጨስና ጫት ከመቃም እንዲቆጠብ ማዕከላቱ የሚሰጡት እገዛ ከፍተኛ በመሆኑ ጥቅሙ ዘርፈ ብዙ እንዲሆን አስችሏል።
መምሪያው እነዚህን ሁሉ ተግባራት እያከናወነ ያለው በዞኑ በሚገኙ ሰባት ወረዳዎችና ሶስት ከተማ አስተዳደሮች ውስጥ አስር መዋቅሮችን ዘርግቶ በመንቀሳቀስ መሆኑን ወይዘሮ ተስፋዬ በቆይታችን ነግረውናል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ነሐሴ 28 ቀን 2016 ዓ.ም