ለዘለቄታው ለሠላም እራሱን ያስገዛ እና ዘብ የሚቆም ትውልድ ለመፍጠር

የሠላም ጉዳይ ለኛ ለኢትዮጵያውያን ዋነኛ ወቅታዊ አጀንዳችን ነው፤ ለምናስበው፤ በብዙ አስበን ወደ ሥራ ለገባንባቸው ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎቻችን ስኬት ሠላም ወሳኝ ነው። ብዙ ዋጋ ያስከፈሉንን ትናንቶችን ተሻግረን ዛሬን የተሻለ፤ ነገን ደግሞ ብሩህ አድርገን ለመቀበል ሀገራዊ ሠላማችንን ተጨባጭ ማድረግ የግድ ነው ይህን ማድረግ ካልቻልን ልፋታችን “ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ” መሆኑ የማይቀር ነው።

ከሠላም እጣት ጋር በተያያዘ በየዘመኑ ብዙ ዋጋ ከፍለናል፤ በየዘመኑ የነበሩ ትውልዶች በልማት የመለወጥ፤ ከትናንት ችግሮች የመሻገር፤ ተለውጦ የመለወጥ መሠረት ለመጣል ያደረጉት ጥረት በሠላም እጦት ሳይሳካላቸው ቀርቷል። የተገላቢጦሽ አብዛኛው ታሪካችን የግጭት ታሪክ ሆኗል። በግጭት አዙሪት ውስጥ ገብተን መውጣት እቅቶን ያልተገባ ዋጋ እየከፈልን ዘመናት ተቆጥረዋል።

በዚህም ለብዙዎች የሚተርፍ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤቶች ሆነን፤ ከፍ ያለ ልማትን መሸከም የሚችል የሰው ሀብት እያለን ፤ የዓለምን ቀልብ የሳበ ተስማሚ የአየር ንብረት ባለቤቶች ሆነን ሳለ፤ የከፋ ድህነት እና ኋላ ቀርነት መገለጫዎች ሆነናል። የእለት ተእለት ሕይወታችንን ማሸነፍ ተስኖን ተመፅዋች ለመሆን ተገድደናል። ዜጎች በሀገራቸው ተስፋ እያጡ ከሚሰደዱባቸው ሀገራት መካከል ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነን።

በርግጥ ገና ከጅምሩ ስለ ልማት ለማሰብ ሠላም ያስፈልጋል፤ የልማት ሀሳቦችን ወደ ተግባር ለመለወጥ ሠላም ያስፈልጋል ፤ ልማትን ዘላቂ ለማድረግ እና ለትውልዶች ለማሸጋገር ሠላም ያስፈልጋል። ይህ ሠላም የሚመጣው ግን ስለሠላም በብዙ በማዜም፤ የሠላምን አስፈላጊነት የሚተነትኑ ጥናቶች በማካሄድ፤ ስለ ሠላም ብዙ የአደባባይ ዲስኩሮችን በመደስኮር ወይም የሠላምን አስፈላጊነት የሚያሳስቡ የፓናል ውይይቶችን በማድረግ አይደለም ።

ሠላም በራሱ ከሰው ልጅ መንፈሳዊ እና አዕምሯዊ እድገት ጋር አብሮ የሚያድግ፤ ለሰው ልጅ የእለት ተእለት ሕይወት ከመሠረታዊ ፍላጎቶቹ እኩል የሚያስፈልግ ሰብዓዊ እሴት ነው። ተሻጋሪ ለሆኑ ግለሰባዊ ሆነ ማኅበረሰባዊ ስብዕናዎች በመሠረታዊነት የሚጠቀስ፤ በተለይም አንድ ማኅበረሰብ እንደ ማኅበረሰብ ወደ አደገ/የተሻለ መንፈሳዊ ሆነ አዕምሯዊ እድገት እንዲሻገር የሚ ኖረው አስተዋፅዖ የማይተካ ነው።

ሁሉም ሃይማኖቶች እና ሃይማኖታዊ አስተምህሮዎች፤ ከሁሉም በላይ ለሠላም ትኩረት ሰጥተው የሚንቀሳቀሱት፤ የሠላምን አስፈላጊነት ከቁሳዊው ዓለም ባለፈ ለሰብዓዊ መሻት ስኬት መሠረታዊ አቅም አድርገው የሚሰብኩት። እያንዳንዱ ምዕመን /የየትኛውም ሃይማኖት ተከታይ/ ለሠላም ከፍ ያለ ዋጋ ሰጥቶ፤ ስለሠላም ከቋንቋ ባለፈ አዕምሮውን፣ ልቡን እና መንፈሱን ሰጥቶ እንዲንቀሳቀስ የሚያበረታቱት የሠላምን ውድ ዋጋ ከግምት በማስገባት ነው።

እኛ ኢትዮጵያውያን በተለይም የክርስትናን ሆነ የእስልምናን ሃይማኖት በመቀበል የረጅም ዘመን ታሪክ ያለን፤ በሃይማኖቶቹ አስተምህሮ ውስጥ ስለ ሠላም ሲነገረን ያንኑ ያህል ዘመናት ያስቆጠርን ሕዝቦች ነን። ይህ ብቻ አይደለም ከሕዝባችን ከ90 ከመቶ የሚበልጠው ሃይማኖተኛ እንደሆነም ይታመናል። በዚህ ሁሉ ውስጥ ሆነን ግን ሠላማችንን አጽንተን መቀጠል ሳይቻለን ተመሳሳይ ዘመናት ተቆጥረዋል።

ዘመናት መቆጠራቸው ብቻ ሳይሆን፤ እንደ ሀገር ከትልቅ የሥልጣኔ ማማ ላይ ወርደን፤ ኋላቀርነት እና ተመፅዋችነት መለያችን ሆኗል። በቀደሙት ዘመናት እንደሀገር የነበረንን ሞገስ አጥተን አንገት በሚያስደፋ የታሪክ ትርክት ውስጥ ለማለፍ ተገድደናል። አሁን አሁን ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ መለያችን የሆኑ ማኅበረሰባዊ እሴቶቻችንን እያጣን ለራሳችን እንግዳ በሆነ ግራ አጋቢ መንገድ ላይ ቆመን ተገኝተናል ።

ከግለሰቦች የሠላም እጦት የሚነሳው፤ አጠቃላይ የሆነው ሀገራዊ የሠላም እጦት ትርክታችን፤ አሁን ላይ በአግባቡ ካልተገራ ምን ያህል ዋጋ ሊያስከፍለን እንደሚችል ያለፉት አራት የፈተና ዓመታት ተጨባጭ ማሳያ ናቸው። በአንድም ይሁን በሌላ የችግሩ ሰለባ ያልሆነ ዜጋ ካለመኖሩ ጋር በተያያዘ፤ የችግሩ አሳሳቢነት ለየትኛውም ጤነኛ ዜጋ በግልጽ የሚታይ፤ አደገኛነቱም አሳሳቢ መሆን የሚካድ አይሆንም።

ችግሩን በአዲስ የፖለቲካ ባሕል በውይይት እና በድርድር ለመፍታት የሚደረገው ጥረት አሁናዊ ለሆነው የሠላም መሻት የሚኖረው አስተዋፅዖ የማይተካ ቢሆንም፤ ለዘለቄታው ለሠላም እራሱን ያስገዛ እና ዘብ የሚቆም ትውልድ መፍጠር ያስፈልገናል። ለዚህ ደግሞ ወላጆች፤ የሃይማኖት ተቋማት እና ሀገራዊ የትምህርት ሥርዓቱ ስለ ሠላም ሐዋሪያ ሆነው መቆም፤ ለዚህ የሚሆን ዝግጁነት እና ተቋማዊ ስብዕና መፍጠር ይጠበቅባቸዋል።

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ነሐሴ 28 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You