ሳይንስ መፍትሄን አመንጪ፣ አዳዲስ ነገር ፈጣሪ ነውና ዛሬም ከቱርፋቱ ውስጥ አንዱን መርጠን ለማሳየት መረጥን፡፡ ዛሬ ላይ አይጠቅም የሚባል ነገር የሌለን ያህል አንድን ነገር በመልሶ ማደስ ለሌላ ግልጋሎት ማዋሉ እየተለመደ መጥቷል፡፡ ተጠቅመው የሚጥሉት፣ አገልግሏል ብለው የሚቀብሩት ቁሳቁስ «አገልግሎታቸውን የጨረሱትን ወዲህ አምጡት የተሻለ አድርጌ እሰጣችኋለሁ» እያለን ነው ሳይንስ፡፡
ዕድሜ ለሳይንስ ምስጋና ለሀገሬ ተመራማሪዎች አገልግሎት ሰጥተው በየመንገዱ የሚጣሉ አካባቢን በማቆሸሽና ተፈጥሮን በማዛባት ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ ፌስታል እና መሰል የላስቲክ ውጤቶች መላ ተገኝቶላቸው ጥቅም ላይ መዋል፤ ለገቢ ምንጭ መሠረት መሆን ጀምረዋል፡፡
የሀገሬ ተመራማሪዎች ባላቸው ረቂቅ እውቀት በሚያደርጉት ያላሰለሰ ጥረት አስገራሚ እምርታዎችን እያገኙልን ነው፡ ፡ ዛሬ በሳይንስ አምዳችን ከወዳደቁ ላስቲኮችና ጥቅም ሰጥተው ከሚጣሉ ፌስታሎች የተለያየ ዓይነት ነዳጅ በምርምር መፍጠር የቻሉ ግለሰብና ሥራቸው የተመለከተ ጽሑፍ በዚህ መልክ አቅርበንላችኋል::
አቶ ሀበሻ አራጌ ይባላሉ። በአዲስ አበባ ኮተቤ አካባቢ ነዋሪ ናቸው። እኝህ ሰው ለሀገራቸው መልካም ማሰብን የሚያዘወትሩ ለለውጧ የሚታትሩ ታላቅ ህልም ያላቸው ተመራማሪ ናቸው፡፡ አንድ ሰሞን የሰሙት ዜና እጅግ አስከፋቸው፡፡
ስለ ሀገራቸው ኢትዮጵያ በአንድ የውጭ ሀገር እትም የሆነ መዝገበ ቃላት ማውጫ ላይ የተሰጠ ምሳሌ በጣም አስቆጫቸው፡፡ ይህች ሁሉም ነገር ያላት ምድር፤ በመልካም ነገር የምትታወቅ ሀገር በደህነቷ ብቻ በዚህ መልክ ትገለፃለች የሚል ውስጣዊ ቁጭት ፈጠረባቸው::
ያኔ ቃል ገቡ ለሀገራቸው ለውጥ ሊተጉ ባላቸው እውቀትና አቅም መልካም ነገርን ሊያበረክቱ ወሰኑ፡፡ እናም ያላቸውን የፈጠራ ሙያ ክህሎት ወደ ተግባር በመለወጥ ሀገሬ በዚህ መስክ ያለባትን ችግር ብቀንስ ብለው ውጥናቸውን ከግብ ለማድረስ ሌሊት ከቀን ያለ እረፍት መመራመር ጀመሩ፡፡
ጥረት ውጤት ያስገኛልና ከብዙ ልፋትና ጥረት በኋላ ምርምራቸው ትልቅ ውጤት አስገኘላቸው፡፡ የአካባቢን ገፅታ በማበላሸት የመሬትን ለምነት በመቀነስ ተፅእኖ ያሳድሩ የነበሩ ላስቲኮች በመሰብሰብ እና በምርምር በመቀየር ለመኪና፣ ለአውሮፕላን ለተለያዩ የኃይል ምንጭ ማሽኖች ሞተር የሚሆን ነዳጅ ማግኘት ቻሉ፡፡
ተመራማሪው አቶ ሀበሻ አራጌ ኮተቤ መምህራን ኮሌጅ አካባቢ በሚገኝ መኖሪያ ቤታቸው ቅጥር ግቢ ውስጥ አሁን ያገኙት ምርምርና ሌሎች የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን በመስራት ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ፡፡ የሀገራቸውን ለውጥና ዕድገት በመናፈቅ ሁሌም እንደሚተጉና የምርምር ሥራቸው ትጋትና መነሻ የሀገር ፍቅር መሆኑን ይገልፃሉ፡፡
ምን ፈጠሩ
አገልግሎት ሰጥተው ከሚጣሉ ፌስታልና ላስቲኮችን ወደ ነዳጅ መለወጥ:: ከዚያም ቤንዚል፣የአውሮፕላን ነዳጅ፣ኪሮሲን፣ ናፍጣ፣ የሞተር ዘይት እና መሰል የኃይል ምንጮችን በምርምር አግኝተዋል፡፡ የፈጠራ ሥራው በመኪኖች እና በሌላ በነዳጅ በሚሰሩ ማሽኖች ተሞክሮ ውጤታማነቱ የተረጋገጠ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም በተመራማሪው በመመረት የሙከራ አገልግሎት ላይ ይገኛል፡፡
የተነሳሽነቱ ምክንያት፡–
የፈጠራ ሥራውን ለመስራት ዋነኛ መነሻቸው ሀገርን የመለወጥ ፍላጎት ነውና የግል ጥረት ማድረግን እንደ ስንቅ ይዘው፤ በየአካባቢው የሚያዩት የወዳደቀ ፌስታልና ቆሻሻ ለምን ጥቅም ላይ አይውልም? አካባቢን ከመጠበቅ ባለፈስ ለምን ጥቅም እንዲሰጥ አይደረግም የሚሉ ጥያቄዎች በውስጣቸው መፈጠሩ ለምርምራቸው ምክንያት ሆነ፡፡
የሰው ልጅ የሚገጥመው አካባቢያዊና ማህበራዊ ችግሩን የመፍቻ መንገድ መመራመር ስለሆነ አቶ ሀበሻ አካባቢያቸውን የበከለ ገፅታን ያበላሸ የተጣለ ፌስታልና ላስቲክ ወደ ጥቅም ማዋል አሰቡና ተገበሩት፡፡ አቶ ሀበሻ የሀበሻውን አካባቢያዊ ችግር የሚቀርፍ በደንብ ከተሰራበት ደግሞ የውጭ ምንዛሬ እጥረትን በመቀነስ ለሀገር ኢኮኖሚ ትልቅ አስተዋፅዖ ማበርከት የሚችል የፈጠራ ሥራ አበረከቱ፡፡
ሥራው አሁን ያለበት ደረጃ
የአቶ ሀበሻ የምርምር ሥራ በአሁኑ ሰዓት ለአገልግሎት በመዋል ላይ ይገኛል፡፡ ለተለያዩ ተሽከርካሪዎች በመሸጥ ለገቢ ምንጭ ሆኖቸዋል። በስፋት ለማምረት እና ራሳቸውንም ሆነ ሀገርን ለመጥቀም እንዳይችሉ ደግሞ የቦታ ችግር ፈተና እንደሆነባቸው ይናገራሉ፡፡
ለፈጠራው እውቅና
ከኢትዮጵያ አዕምሯዊ መብት ጽሕፈት ቤት የምርምር ሥራ የባለቤትነት መብት የምስክር ወረቀት (ሰርተፍኬት)፣ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እውቅናና የ2011 የወርቅ ሜዳሊያ እና የገንዘብ ሽልማት አግኝተዋል፣ከተለያዩ ተቋማት ድጋፍና የትብብር ድጋፍ ተችረዋል፡፡
ከባዱ ፈተና
አቶ ሀበሻ የምርምር ሥራቸውን ለማከናወን ሲነሱን በምርምር ሥራቸው ሂደት ነገሮች ሁሉ አልጋ በአልጋ ሆኖላቸው አልነበረም፡ ፡ ይልቁንም የምርምር ሥራ ትዕግስትና ተደጋጋሚ ሙከራ ማድረግ የሚጠይቅ ስለነበር ሳይሰለቹ መትጋትና የሚገጥሙ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ማለፍ ግድ ብሏቸዋል፡፡ የመስሪያ ቦታ ችግር የገንዘብ እጥረትና ለምርምር ሥራ የሚያገለግሉ በቂ ቁሳቁሶች አለማግኘትም ለአቶ ሀበሻ በምርምር ወቅት የገጠማቸው ፈተና መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ለምርምሩ ድጋፍ
የምርምር ባለሙያው አቶ ሀበሻ በሀገር ደረጃ አሁን አሁን ለምርምር ሥራ የሚሠጠው ትኩረት ጥሩ ቢሆንም አሁንም ለመስኩ ትኩረት መስጠትና ተገቢውን ድጋፍ ሊደረግ እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡ ተመራማሪዎች ያለባቸውን የገንዘብ እና የምርምር ቦታና ቁሳቁስ እጥረት ለመቅረፍ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ክትትልና ድጋፍ ሊያደርግላቸው ይገባል፡፡ የማህበረሰቡን ችግር ለመቅረፍና ሀገራዊ የሳይንስ ግኝትና ፈጠራን ለማበረታታት በሚደረግ ጥረት ሁሉም ተሳታፊ ሊሆን እንደሚገባም ተመራማሪው ሀሳባቸውን ያቀርባሉ፡፡
የወደፊት እቅድ
ተመራማሪው አሁን ካገኙት የምርምር ሥራ በተጨማሪ ልዩ ልዩ ምርምሮችን በማድረግ ላይ ሲሆኑ ከተለያዩ ተረፈ ምርቶች ለአገልግሎት ሊውል የሚችል ኬሚካል ለማምረት የሚያስችል ምርምር በማድረግ ጥሩ ውጤት በማግኘት ላይ መሆናቸውን ይዘረዝራሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ችግር ፈቺ የሆኑ ምርምሮችን በማድረግ ወደፊት በመስኩ የላቀ አስተዋፅኦ ማበርከት ህልማቸው ነው፡፡
ሀገራዊ ችግርን ማህበረሰባዊ መሰናክሎችን የሚቀርፉ የምርምር ሥራዎች በሀገር ደረጃ ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተሰራባቸው መሆኑንና አሁን ያለውም የምርምር ሥራቸው በተለያዩ ተቋማት ኮሚቴ ተዋቅሮ በስፋት ሊሰራበት ታቅዷል። ለዚህም መንግሥታዊ የሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እያደረጉ መሆኑንና ወደፊት መልካም ነገር እንደሚጠብቁ በተስፋ ይናገራሉ::
የተመራማሪው መልዕክት
የምርምር ሥራ ተደጋጋሚ ጥረትና ትጋት እንደሚያስፈልገው እሙን ነው፡፡ አቶ ሀበሻ ከሕይወት ልምዳቸውና የምርምር ተሞክሯቸው ለጀማሪ ተመራማሪዎችና በመስኩ ለተሰማሩ ባለሙያዎች ተስፋ ሳይቆርጡ መትጋትና መልካም ውጤት በማግኘት ተደጋጋሚ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡ በተለይ ለጀማሪ ተመራማሪዎች ታላቋን ሀገራቸውን እንዲያስቡና በምርምር ሥራቸው ማህበራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው ምክረ ሀሳባቸውን ያቀርባሉ፡፡
አቶ ሀበሻ የምርምር ሥራዎች በተፈለገው መልክ ተግባር ላይ ውለው ጥቅም እንዲሰጡ ለምርምር ሥራዎቹ እውቅና ከመስጠት በተጨማሪ የምርምር ሥራ ምቹ የሚያደርጉ ሁኔታዎች በመንግሥት ሊመቻቹ እንደሚገባና አሁን በሳይንስ ዘርፍ እየታዩ ያሉ ለውጦች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አፅንዖት ሰጥተው የሚያነሱት ነጥብ ነው፡፡
የእርሳቸውን የምርምር ውጤት ከውጤት ለማድረስና ማህበራዊ ጠቀሜታውን የላቀ ለማድረግ የገጠማቸውን ችግር በማሳያነት በማንሳት ተመራማሪዎች በሞራልና በተሻለ መንፈስ ሥራቸውን መስራት የሚያስችላቸው ምቹ ሁኔታ ወሳኝ መሆኑን ተመራማሪው ይገልፃሉ፡፡ እኛም የምርምር ሥራ ሀገራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ያለው ሚና ከፍተኛ ነውና ትኩረት ለመስኩ እንላለን፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 28/2011
ተገኝ ብሩ