የሊግ ካምፓኒው ሕግና መመሪያዎች ይከበሩ!

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማሕበር (ሊግ ካምፓኒ) በክለቦች ዝውውርና ከተጫዋቾች ደመወዝ ክፍያ አስተዳደር ጋር ተያይዞ የሚስተዋለውን የተጋነነ ወጪ ፈር የሚያስይዝ መመሪያን አውጥቶ ወደ ተግባር እንደገባ ይታወቃል። መመሪያው ከክለቦች አስተዳደር፣ አወቃቀርና ከፋይናንስ ሥርዓታቸው ጋር በተገናኘ በባለሙያ የተደገፈ ጥልቅና ሰፊ ጥናቶች ተካሂደው ወደ ማስፈጸሙ ሥራ ከገባ ሰንብቷል።

መመሪያው የክለቦችን የገንዘብ አወጣጥ በመቆጣጠር ጤናማ የፋይናንስ ሥርዓትን ለመፍጠር ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ተብሎ ታምኖበታል። እንደ ኢትዮጵያ ስፖርቱ ከመንግሥት ድጎማ ባልተላቀቀባቸው ሀገራትም ጥሩ መፍትሔ ተደርጎ ይወሰዳል።

የኢትዮጵያ ክለቦች ለዝውውርና ለተጫዋቾች ደመወዝ የሚያወጡት ገንዘብ ከገቢያቸው የማይገናኝ በመሆኑ ብዙ ትልልቅ ክለቦች እንደ ዋዛ ሲፈርሱና ሲንገዳገዱ መመልከት የተለመደ ነው። በዓለም እግር ኳስም የዚሁ ችግር ገፈት ቀማሽ የሆኑ ክለቦችን ማንሳት ይቻላል። ለዚህ ሁሉ መንስኤ የክለቦቻችን አወቃቀር፣ አስተዳደርና የፋይናንስ ሥርዓት ዘመኑን የዋጀ አለመሆንና ከትርፋቸው ይልቅ ኪሳራቸው ማመዘኑ ዋነኛው ምክንያት ነው።

የስፖርቱ ዘርፍ የፋይናንስ ሥርዓት በሕግና ደንብ የማይመራ ከሆነ የሚያስከትለውን ስብራት ለመጠገን አስቸጋሪና የማይቻል ያደርገዋል። ስፖርት ደግሞ የሚያንቀሳቅሰው ሀብት ትልቅና ብዙ ዓይነት ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች የሚያገናኝ በመሆኑ ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄን ይሻል።

ስፖርቱን በውጤታማነት ለመምራት ከሚያስችሉት የጥንቃቄ ተግባራት መካከል በሕግና ሥርዓት (መመሪያ) መምራት አማራጭ የሌለው መፍትሔ ይሆናል። በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን ከፍተኛ ገንዘብ በአግባቡ ለመምራትና ለመጠቀም የሚያስችል መመሪያ መውጣቱ የሚስተዋለውን ሌብነትና የሀብት ብክነትን ከመከላከሉም በተጨማሪ ስፖርቱንም የመታደጊያ መንገድ ነው።

እግር ኳስ ባደገባቸውና የሀገር ውስጥ ውድድራቸው ዓለም አቀፍ ተጽኖን መፍጠር በቻለባቸው ሀገራት እንኳን እንደፈለጉ ረብጣ ብሮችን መንዝሮ ተጫዋቾችን ማስፈረም አይቻልም። ለስፖርቱ ጤናማ ጉዞና በገቢ አቅማቸው አነስ ያሉ ክለቦችን ለመጠበቅ ሲባል በየደረጃው የፋይናንስ አስተዳደር ሕጎች ወጥተው ተግባራዊ ሲደረጉ እንመለከታለን።

በዚህም መሠረት ክለቦች ለተጫዋቾች ዝውውርና ደመወዝ ክፍያ ወጪ የሚያወጡት ባላቸው ሀብት ልክ ሳይሆን በሚያስገቡት ገቢ ልክ ነው። ይህም ማለት ከተጫዋቾች ዝውውርና እራሳቸው በፈጠሩት እግር ኳሳዊ የገቢ ምንጭ ምክንያት የሚያገኙትና ያወጡት ወጪ ተመጣጣኝ መሆን ይኖርበታል።

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ የገቢ መመጣጠን የሚባለው ነገር የማይታወቅና ለመተግበርም አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል። ምክንያቱ ደግሞ ክለቦች የሚንቀሳቀሱት በመንግሥት በጀት በመሆኑና ከማውጣት ውጪ መልሶ የሚያስገቡት ገቢ ባለመኖሩ ነው። በተጨማሪም ክለቦቻችን ውድድሩን ለምን እንደሚያካሂዱ እና ጥቅሙ ምን እንደሆነ ግልፅ ዓላማን ባለመያዛቸው ነው ማለትም ይቻላል። በየዓመቱ እያንዳንዱ የፕሪሚየር ሊግ ክለብ ከአስር እስከ መቶ ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ቢሆንም የሚያስገባው ገቢ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።

ይህ ገንዘብ የሚወጣው ከደሃው ማኅበረሰብ መቀነት ተፈቶ ነው። በሕግና ሥርዓት ባለመመራቱም ለብክነት ሲዳረግ ቆይቷል። የሀገሪቱ እግር ኳስ ግን ከነበረበት ደረጃ ፈቀቅ አላለም። ፈር ያጣው የገንዘብ አወጣጥ ወጣቶች የመጫወት እድል እንዲነፈጋቸውና እግር ኳሱም ከወደቀበት እንዳይነሳ የራሱን ሚና ተጫውቷል።

በዚህም የተነሳ ብዙ ክለቦች ለተጫዋቾቻቸው ደመወዝ መክፈል ሲያቅታቸውና በየጊዜው የሆቴል ወጪን እንኳን መሸፈን አቅቷቸው መነጋገሪያ እስከ መሆን የደረሱበትን አጋጣሚ ጥቂት አይደለም። ይሄንን የክለቦች መፍረስ ስጋት የሆነውን የፋይናንስ ችግር ለመቅረፍ የክለቦች ዝውውርና ደመወዝ ክፍያ አስተዳደር መመሪያ በህግና መመሪያ ለመምራት የፕሪሚየር ሊጉ አክሲዮን ማህበር በቅርቡ አንድ መላ ዘይዷል።

በዚህም መሠረት አንድ ክለብ በዓመት ማውጣት የሚችለው 57 ሚሊዮን 750 ሺ ብር እንዲሆንና ዝቅተኛው 18 ሺህ ብር እንዲሆን ራሳቸው ክለቦች ይሁን ብለው መመሪያውን አፅድቀዋል። በብዙ ሂደቶች ውስጥ አልፎ የመጣውና እግር ኳሱን ከመጥፋት እንደሚታደግ ተስፋ የተጣለበት ይህ የዝውውርና የደመወዝ ክፍያ አስተዳደር መመሪያ ለተግባራዊነቱ አሁንም ትኩረትን ይሻል።

መመሪያውን ያፀደቁት ራሳቸው ክለቦች እየጣሱት ይገኛሉ። በደላሎች ሰንሰለት የተጠለፈው የዝውውር ጉዳይ አሁንም እንደተለመደው ቀጥሏል። ክለቦችና የሥራ ሃላፊዎቻቸውም የዚህ ተባባሪ ናቸው። መመሪያው እንዳይተገበር ብዙ ስልቶችን በመንደፍ ላይ እንደሆኑ አክሲዮን ማህበሩም ያመነው ጉዳይ ነው። መመሪያውን ከመጀመሪያውም ጀምሮ ለማስፈጸም አጨብጭበው የተቀበሉ አንዳንድ ክለቦችና ኃላፊዎች ማንገራገርና የማጭበርበሪያ መንገዶችን ሲፈልጉም በግልፅ እየታየ ነው።

ክለቦች ተጫዋቾችን በመመሪያውና በተቀመጠው በጀት መሠረት ከማስፈረም ይልቅ፣ አንዳንድ የማይመስሉ የመደለያና የማማለያ ነገሮችንም ወደ ማድረግ እየሄዱ ነው። ለምሳሌ ከተቀመጠው የበጀት እርከን በላይ ከባለሀብቱና ከነጋዴው ሰብስበን እንከፍላለን፣ መሬት እንሰጣለን የሚሉና በፍጹም ለማጭበርበር በር የሚከፍቱ መንገዶችን ለመከተል እየተሞከረ ነው። በተጨማሪም በማጭበርበሩ መንገድ ተጫዋቾችን የመነጣጠቅና ደንቡን ለመተግበር የሚሞክሩ ክለቦችን ለአደጋ የሚያጋልጥ ሂደቶችንም እየተመለከትን እንገኛለን።

ክለቦቹ እንዲያወጡ በተመደበላቸውና በመመሪያው መሰረት እንዲንቀሳቀሱ ጠንከር ያለና አስተማሪ ቅጣት ከወዲሁ መተላለፍ ይኖርበታል። ክለቦችም እውነት ለእግር ኳሱ መቀጠልና ማደግ የሚያስቡ ከሆነ ከእንደዚህ አይነት ድርጊት ተቆጥበው እና የገበያ እቅድ ይዞ መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል። የስፖርት መሠረተ ልማት ባልተሟላበትና እግር ኳሱ ባላደገበት ሀገር ከአፍሪካ ሶስተኛ ከፍተኛ ደመወዝ ከፋይ ነገር ግን በውጤት ደግሞ አርባኛ ደረጃ ይዞ መቀጠል ያስወቅሳል።

ከዚህ ቀደም ከፍተኛ የደመወዝ ክፍያ 50 ሺ ብር እንዲሆን ስምምነት ተፈርሞ ሳይተገበር እንደቀረው ሁሉ አሁንም ይታሰብበት። እግር ኳስ ክለብ ከተባለ ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታና ዓለም አቀፍ አሠራርን ተከትሎ መቀጠል አለዚያ፣ የሕዝብ ገንዘብ መበዝበዣ ሆኖ መቀጠል መቆም አለበት። የራሱ ቢሮ እንኳን የሌለውና ከአንድ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ መውጣት ያልቻለ ክለብ በገፍ የሚከሰክሰውን ገንዘብ ቀንሶ መሠረተ ልማት ማሟላትና ታዳጊዎች ላይ ማዋል ይኖርበታል።

ከሚመለከተው ተቋም እና ባለሙያ ይልቅ እግር ኳሱን እና ሲስተሙን እንደ ግል እርስታቸው ገብተው የሚዘውሩትን አካላት በቶሎ ለይቶ የማውጣት ሥራ በፍጥነት ሊከወን ይገባል። በተጫዋቾች ዝውውር ውስጥ ሕጋዊ ፍቃድ ሳይኖራቸው የሚሠሩ አካላትን በአፋጣኝ መላ ሊባል ይገባል።

በኢትዮጵያ አራት ሕጋዊ ፍቃድ ያላቸው የፊፋ የተጫዋቾች ወኪል (ኤጀንት) ብቻ እንደሆኑ ፌዴሬሽኑ ያስታወቀ ሲሆን ወደ ሕጋዊነት የመምጣት ፍላጎት ያላቸውን ለይቶ ሌሎቹ ላይ በወንጀል ሕግ መሠረት ርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል። በዚህ ሰንሰለት ውስጥ የሚገኙ ሁሉም አካላት እግር ኳሱ ሲኖር ነው የሚኖሩት እና ፈጥኖ ወደ ሕጋዊ መስመር በመግባት ለእግር ኳሱ እድገት የድርሻቸውን ይወጡ።

የጉዳዩ ባለቤቶች የሆኑት ተጫዋቾች፣ አሠልጣኞችና ክለቦች ቤታቸውን ለማፍረሱ አይሯሯጡ። እግር ኳሱ የሚኖሩበት ቤታቸው በመሆኑ የሚደርስበትን ጉዳት በባለቤትነት ፊት ለፊት ሆኖ መፋለም እንደሚኖርባቸው ሌላ ሰው የሚነግራቸው መሆን የለበትም። የነሱን ነጭ ላብ ማንም ደላላ እንዳሻውና እንደፈለገው ማድረግ አይኖርበትም። እስከ መቼ ነው የነሱን ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ማንም የሚፈነጭበት? መብታቸውን በማስከበር በሠሩት ልክና በትክክለኛ መንድ የላባቸውን ለማግኘት መሥራት ላይ ማሰብ ይኖርባቸዋል።

ሁሉም በተሰጣቸው ግንዛቤና ኃላፊነት መሠረት ለመመሪያው ተግባራዊነት ከምንጊዜውም በላይ አበክረው መሥራት አስፈላጊ ነው። የመገናኛ ብዙሃንም ጉዳይን በአንክሮ በመከታተል ጉዳቱን እና ጥቅሙን ለብዙሃኑ ሕዝብ በማቅረብና የሙስና ወንጀሎችን በማጋለጥ ለተግባራዊነቱ መሥራት ይኖርባቸዋል። የተቋቋመው ኮሚቴም ሳይውል ሳያድር ጉዳዩን በእንጭጩ በመቅጣት የተጣለበትን ኃላፊነት መወጣት ከተወቃሽነት መዳኛው መንገድ ነው። መንግሥትም ይሄንን በትኩረት ተመልክቶ የመጨረሻ እልባት እንዲያገኝ በሚመለከተው ጉዳይ ተሳትፎን በማድረግ ስፖርቱን ሊታደግ ይገባል።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ነሐሴ 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You