ሶማሊላንድ ግብፅ በሶማሊያ እያደረገች የምትገኘውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ አጥብቃ እንደምትቃወም አስታወቀች።
የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባወጣው መግለጫ የውጭ ኃይሎች በጎረቤት ሶማሊያ መስፈር ሽብርተኝነትን ለመዋጋት እና ሠላምን ለማስፈን ሲደረግ የነበረውን ጥረት የሚጎዳ ነው ሲል ገልጿል።
ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ የግብፅን አደገኛ እንቅስቃሴ እንዲያወግዝ የጠየቀው መግለጫው “የእኛንም ሆነ የጎረቤቶቻችንን ሠላም አደጋ ላይ የሚጥል የማንኛውንም የውጭ ኃይል ጣልቃገብነት አንታገሰም” ብሏል።
የቀጣናው ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሀገራት ቀጣናውን ወደ ከፋ አለመረጋጋት ውስጥ ከሚከቱ አካሄዶች በመታቀብ ልዩነቶችን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት እንዲያደርጉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ጠይቋል።
መግለጫው አክሎም በአካባቢው ያለው ያልጸና ሠላም መሰል ድርጊቶች ውጥረቶችን በማባበስ አስከፊ ቀውስ ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ስጋቱን ገልጾ ሶማሊላንድ መሰል ድርጊቶችን ከዳር ቆሟ እንደማትመለከት አቋሟን አንጸባርቃለች።
ግብጽ እና ሶማሊያ በቅርቡ የወታደራዊ ስምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ ከቀናት በፊት የግብጽ እቃ ጫኝ የጦር አውሮፕላኖች በሶማሊያ መታየታቸው መዘገቡ አይዘነጋም።
ካይሮ ሠራዊቷን ለሠላም ማስከበር ተልዕኮ ወደ ሶማሊያ ለመላክ ጥያቄዋን በይፋ ማቅረቧ የሚታወስ ነው።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 25 ቀን 2016 ዓ.ም