እስራኤል በዌስትባንክ ባካሄደችው ዘመቻ የሀማስን መሪ ገደልኩ አለች

እስራኤል በዌስትባንክ ባካሄደችው ዘመቻ የሀማስን መሪ ገደልኩ አለች።

የእሥራኤል ጦር፣ እሥራኤል ወርራ በያዘቻት ሰሜናዊ ዌስትባንክ እያደረገ ባለው መጠነሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ የሀማስን መሪ እና ሌሎች ወታደሮችን ጄኒን ውስጥ መግደሉን አስታውቋል።

ጦሩ ባወጣው መግለጫ የእሥራኤል ኃይሎች ዊሳም ሀዜምን በመኪና ውስጥ መግደላቸውን እና “ለማምለጥ ሙከራ ሲያደርጉ በነበሩ ሁለት ሽብርተኞች” ላይ የአየር ጥቃት ማድረሳቸውን ገልጿል።

የፍልስጤም ጤና ሚኒስቴር በደቡብ ምስራቅ ጄኒን በምትገኘው የዛባዳህ ከተማ አቅራቢያ ሦሰት ወንዶች ተገድለዋል ብሏል። ቢቢሲ የፍልስጤም መገናኛ ብዙኃንን ጠቅሶ እንደዘገበው የእሥራኤል ኃይሎች በሕንጻዎች እና በከተማዋ መጠለያ ካምፖች የሚገኙ መሠረተ ልማቶችን ካወደሙ በኋላ ከቱልክአርም ወጥተዋል።

ባለፈው ሐሙስ በቱልክአርም ውስጥ መሪያቸውን ጨምሮ አምስት የታጣቂውን ቡድን አባላት መግደሉን የገለጸው የእሥራኤል ጦር ተጨማሪ ማብራሪያ አልሰጠም። የእሥራኤል ጦር “ሽብር ካከሸፈ፣ የሽብርተኞችን መሠረተ ልማቶች ካወደመ እና ታጣቂዎች ካጠፋ” በኋላ በቱባስ አቅራቢያ ከሚገኘው የአል ፋራ መጠለያ ካምፕ መውጣቱን አስታውቋል።

የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ግጭቱ በአካባቢው ያለውን አደገኛ ሁኔታ የሚባብስ ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ሀማስ ባለፈው ጥቅምት ወር በእሥራኤል ላይ ድንበር ጥሶ ያልተጠበቀ ጥቃት ከሰነዘረ ወዲህ በዌስትባንክ በርካታ ግጭቶች ተከስተዋል። የእሥራኤል-ሀማስ ጦርነት በድርድር መቋጨት ባለመቻሉ ምክንያት ጦርነቱ 10 ወራትን አስቆጥሯል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You