ሩሲያ በ92 አሜሪካውያን ላይ ማዕቀብ ጣለች።
የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው በ92 አሜሪካውያን ላይ ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል።
ማዕቀብ የተጣለባቸው አሜሪካውያን ወደ ሩሲያ እንዳይገቡ፣ እንዳይሠሩ እና በሩሲያ ያላቸው ገንዘብ እንዳይንቀሳቀስ ታግደዋል።
ማዕቀብ ከተጣለባቸው አሜሪካውያን መካከል የዎልስትሪት ጆርናል፣ ኒዮርክ ታይምስ፣ ዋሽንግተን ፖስት እና ሌሎችም ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሚዲያዎች ውስጥ የሚሠሩ ጋዜጠኞች አሉበት።
ከጋዜጠኞች በተጨማሪም የሕግ ባለሙያዎች፣ ተመራማሪዎች፣ ታዋቂ የንግድ ሰዎች እና የሙያ ማኅበራት አመራሮች ማዕቀቡ ተጥሎባቸዋል።
በአጠቃላይ ሩሲያ ወደ ግዛቷ እንዳይገቡ ማዕቀብ የጣለችባቸው አሜሪካውያን ቁጥር ከ2 ሺህ እንዳለፈ ቪኦኤ ዘግቧል።
ባሳለፍነው ሳምንት አሜሪካ ከዩክሬን ጦርነት ጋር በተያያዘ በ400 ሩሲያ እና ቻይናውያን ላይ ያነጣጠረ ማዕቀብ መጣሏ ይታወሳል።
ሩሲያም በአሜሪካ ለተጣለባት ማዕቀብ የአጸፋ እርምጃ የወሰደች ሲሆን ቻይና የዋሽንግተንን ማዕቀብ
ከማውገዝ ባለፈ እስካሁን ተመሳሳይ ማዕቀብ ስለመጣሏ አልታወቀም።
ለአንድ ሳምንት በሚል የተጀመረው የዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት ሦስተኛ ዓመቱ ላይ ይገኛል። ጦርነቱ በድርድር እንዲያልቅ በተለያዩ አካላት ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም ጦርነት እንደቀጠለ ይገኛል።
የዩክሬን ፕሬዚዳንት ሩሲያን ወደ ድርድር ለማምጣት በሚል በምዕራብ ሩሲያ በኩል በምትገኘው ኩርስክ ግዛት የተለያዩ ቦታዎችን ተቆጣጥራለች።
ሩሲያ የዩክሬንን ጥቃት በምዕራባውያን ሀገራት ድጋፍ የተደረገብኝ ነው በሚል ጉዳዩ ወደ ሦስተኛው የዓለም ጦርነት ሊያመራ ይችላል ስትል አስጠንቅቃለች።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ነሐሴ 24/ 2016 ዓ.ም