የበርካታ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ አያሌ ባሕላዊ እሴቶች አሏት። ከእነዚህ እሴቶች መካከል ባሕላዊ የጋብቻ ስነስርዓቶች ይጠቀሳሉ። ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች መገለጫቸው የሆነ የራሳቸው ባሕላዊ የጋብቻ ስነስርዓት አላቸው። ባሕላዊ የጋብቻ ስነስርዓቶቹ የየብሔረሰቡ ብቻም ሳይሆኑ የሀገሪቱም ብቸኛ መገለጫዎች ናቸው።
የጋብቻ ስነስርዓቶቹ ከብሔር ብሔረሰብ ሊለያዩ ይችላሉ፤ በጋብቻ ስነስርዓቱ የሚስተዋሉ የማጨት፣ ሽምግልና የመላክ፣ መሰረግ፣ መልስና ቅልቅል ማድረግ፣ ወዘተ. በየራሳቸው ሰፊ ስነስርዓት ያላቸው የሀገር እሴቶች ናቸው።
ከእነዚህ አያሌ የብሔር ብሔረሰቦች የጋብቻ ስነስርዓቶች መካከል የከምባታ ብሔረሰብ ባሕላዊ የጋብቻ ስነስርዓት አንዱ ነው። የብሔረሰቡን ባሕላዊ የጋብቻ ስነስርዓት /ቦሎቻን/ በተመለከተ በርካታ የጽሁፍ መረጃዎች እንዳሉ የዞኑ ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ የባሕል ታሪክ ቅርስ ጥናትና ልማት ዋና የስራ ሂደት ቡድን መሪ አቶ ደስታ ዘለቀ ይገልጻሉ። ለዚህ ጽሁፍ ግን በአቶ ፈለቀ ብርሃኔ አዘጋጅነትና አሳታሚነት ‹ከምባታነት እሴቶቹ፣ ትምህርትና ልማት በሚል ርእስ ከተጻፈው መጽሀፍ ጋብቻን በሚመለከት የሰፈረውን መረጃ አቶ ደስታ አድርሰውናል። በብሔረሰቡ ዘንድ ሰርግ ‹‹ቦሎቻ›› ተብሎ እንደሚጠራ አቶ ደስታ አስታውቀዋል።
የአዲሱ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አንዱ ዞን በሆነው የከምባታ ዞን የሚኖረው የከምባታ ብሔረሰብ ጋብቻን የሚያስተሳስረው ከራሱ ጎሳ ጋር ሳይሆን ከሌላውም ጋር መሆኑን መረጃው አመልክቷል።
በመረጃው ላይ እንደሰፈረው፤ በከምባታ ብሔረሰብ ዘንድ ጋብቻን በተመለከተ የዘር ሀረግን እስከ ሰባት መቁጠር ተለምዷል። የዘር ሀረግ ከሰባት በላይ ሲሆን በጋብቻ መጣመርን አይቃወምም፤ ምንም ይሁን ምን ከጎሳው ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያለው ወይም ያላት ማግባት አይደገፍም።
በጥንተ ከንባታ ሕዝብ ዘንድ ጋብቻ የሚመሰረተው በአብዛኛው በወላጆች ምርጫ ነው። ቤተሰብ የራሱን ጎሳ ሀረግ ከፈተሸ በሁዋላ ይመጥነናል የሚለውን ጎሳ እና የኑሮ ደረጃን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለልጁ ትዳር ያፈላልጋል። በፍለጋው ሂደት ዘመድም ድርሻ አለው። የምትፈለገው ልጃገረድ ስትገኝ በአገናኝነት የሚወከለው የመሀል ዘመድ ነው፤ አንዳንዴ የሚያገባው ልጅ የተመረጠችውን ልጅ በድንገት ቤቷ ሄዶ እንዲያያት የሚደረግበት አጋጣሚ ቢኖርም፣ በአብዛኛው በጥንተ ከምባታ ሕዝብ ዘንድ ተጣማሪዎች የሚተያዩት በሰርጋቸው እለት ነው።
ሆኖም ተጋቢዎቹ ፈቃደኝነታቸው እንደሚጠየቅ መረጃው ጠቁሞ፣ ካልተስማሙ የሚፈርስበት ሁኔታ እንዳለም አመልከቷል። መረጃው እንደጠቆመው፤ ቤተሰብ ከውሳኔ ላይ ሲደርስ ሽማግሌዎች ተልከው በትዳር ለመዛመድና ልጃቸውን እንዲድሩ የመጠየቅ ባሕል በጥንት ከምባታዎች ዘንድ የተመለደ ነው። ሽማግሌዎቹ ወደ ሴቲቱ ቤተሰብ ሲሄዱ ስለመጡበት ጉዳይ በተዘዋዋሪ ያስረዳሉ። ቤተሰቡም በነገሩ ላይ ለማሰብ ጊዜ ይጠይቃል፤ መግደርደርም ተለ ምዷል።
የልጅቷ ቤተሰቦች ሽማግሌ ሲላክባቸው ወዲያውኑ ምላሽ አይሰጡም፤ ለሌላ ጊዜ ይቀጥራሉ። ይህም የሚደረገው ለትዳር የጠየቀው ቤተሰብ ምን አይነት ጎሳ እንደሆነ፤ የትዳር ጠያቂው ባህርይ፣ ስለ ቤተሰቡ ሀብት፣ ስለዝናቸውና ስለመሳሰሉት መረጃ ለማሰባሰብ እና ለማጣራት ሲባል ነው። በተሰጠው ቀነ ቀጠሮ መሰረት ሽማግሌዎች ለትዳር ከምትፈለገው ልጅ ቤተሰብ ቤት ገብተው ሲቀመጡ ጋያ እንዲያጤሱ የልጅቷ ቤተሰቦች ከሰጧቸው የመስማማታቸው አንዱ ምልክት መሆኑን ገለጹላቸው ማለት ነው፤ ሽማግሌዎቹም በባሕሉ መሰረት ይዘው የመጡትን ለምለም ሳር በእናት እጅ በማድረግ የወላጆችን ጉልበት እና ትከሻ ስመው ይቀመጣሉ።
መረጃው እንደጠቆመው፤ ቀጣዩ ሂደት ጥሎሽ የሚሰጥበት ነው፤ ይህም የቃል ማሰሪያ ቀን/ አንገተ ሱንቂ በሪ (የእጅ መሳሚያ ቀን) / መቁረጥና የጋብቻ ስነ ስርዓት የሚፈጸምበት ቀን የሚወሰንበት ነው። ጥሎሽ በከምባትኛ ቋንቋ ‹‹ቆታ›› በሚል ይጠራል፤ ጥሎሽ በእጮኛው ቤተሰብ አና በእጮኛዋ ቤተሰብ መካከል በሽማግሌዎች አማካይነት የሚቀርብ ነው።
ለምትታጨዋ ቤተሰብ ወደፊት ለሚደረገው የሰርግ ድግስ እገዛ የሚደረግ ሲሆን፣ የልጅቷ ቤተሰብ ሙሽሪት አግብታ ወደ ትዳሯ ሰትሄድ ከወላጆቿ ስጦታዎች ይበረከትላታል። ጥሎሹ ከአቅም አንጻር ይወሰናል።
በጥንተ ከምባታ ባሕል መሰረት አባት ‹‹ቆላ››፣ እናት ‹‹ቂጣና ላንዳ›› ለብሰው ጊደርና ወይፈን በስጦታ ሲያበረክቱ ‹‹ዌቴቾ›› /የማጥንት እንጨት/ የማበርከት ስነ ስርዓትም ይካሄድ ነበር። ‹‹ዌቴቾ ›› የሚሰጠው ጥሩ መዓዛ ያለው እጽ በመሆኑ፣ ትርጉሙም ሙሽሮች የትዳር ሕይወታቸው ሁልጊዜ በደስታ የታጀበ እንዲሆን መመኘትን የሚያመለክት ነው።
የከብት ስጦታ/ ጌጌያ/ ም ይደረጋል። ይህ የሚደረገው መተዳደሪያቸውን ለመደጎም ሲሆን፣ ጥሎሽ ሲሰጥ መደራደርም ያለ ነው። ጥሎሹን ላመጡት ሽማግሌዎች መጠነኛ ድግስ ተዘጋጅቶ ግብዣ ይደረግላቸዋል። በወላጆች አማካይነት የሚደረገው ይህን አይነት የማጣመር ሂደት በከምባትኛ ቋንቋ ‹‹ቆርሲሻ›› በመባል ይታወቃል ሲል መረጃው ያመለክታል።
የጥንተ የከምባታ የሰርግ ስነ ስርዓት ብዙ ታዳሚ የሚገኝበት ሳይሆን፣ ከሁለቱ ቤሰቦች ውስን ቁጥር የሚሳተፍበት ነበር። ከሰርጉ አስራ አምስት ቀናት በፊት ጀምሮ በሙሽራው ቤት እየዘፈኑ ስራ ማገዝ የስነ ስርዓቱ አካል ተደርጎ ይታያል፤ በዚህም ወንዶች ጌሾና የመሳሰሉትን ይወቅጣሉ፤፣ ልጃገረዶች ደግሞ በባሕላዊ ወፍጮ እህል ይፈጫሉ። ይሄኔም ‹‹ መለሌ አኩምቦዳ፤ ወዘነ ዘርቱምቦዳ፣ ወልሴ ዶሬኖ›› / ልዩ ባለሙያ ወይም ልባም ካልሆነች፣ በሌላይቱ ትቀየራለች/ እያሉ ሙሽሪት የተስተካከለ ቁመና፣ ቁንጅናና ክህሎት እንዲኖራት በዘፈን አማካይነት ይጠቁማሉ።
ለሙሽሪት አባት የተሰጠውን የእጅ መንሻና ጥሎሽ ቁጥር በመናገር የሙሽሪትን ቤተሰብ በአሽሙር መልክ በዘፈን የመወረፍ ልምድም እንደነበር መጽሀፉ አስፍሯል። ከስንኞቹ መካከል ‹‹ መጠር ቱምቤእጋ መጨተ ሀራሩ፤ መገሬ ጎቲገ መንጋጋሙ / ኤበሉ/ ፣ መጭአች አጉር ፣ መሀ በርግ ሶሀኖ›› እያሉ ያሾፋሉ። የሙሽሪት ቤተሰቦች በበኩላቸው ሙሽሪትን ለመውሰድ የመጡትን አጃቢዎች ‹‹ ፌሶ ፌሶ ሚነኖ፣ ፊሴሬካ መጠኖ፣ ገስሙንኩስ ሀዋንቹ /ኤበሉ/፣ ጋሎ ቲሚ የራንቹ፣ ዜማ ኦሱተ ሶሀኖ›› እያሉ ክፉኛ እንደሚያብጠለጥሏቸውም ተብራርቷል።
በመረጃው እንደተመለከተው፤ ጥንተ ከምባታ ለሰርግ ድግስ በዋናነት የሚያዘጋጀው ምግብ ቆጮ፣ የጎመን ጮባሮ እና ከቡእላ የሚዘጋጀውን ሙቾና አይብ ናቸው። መጠጡ ደግሞ ሱሱጎና ጩሙቶ/ ቦርዴ/ ናቸው። በስጦታ መልክ ‹‹ ጌጌያ›› የሚሰጠው ጊደር፣ ወይፈን፣ ጅባ፣ ቅቤ፣ ወዳሬ፣ ቄጣ፣ ኢትሌ፣ ላንዳ፣ ልዩ ልዩ ስፌት እቃዎች፣ አንደ ወንሾሾ ደጉዴ፣ ሜሜ፣ ሁፎ፣ ሙታ፣ መሬት እና ፈረስ እንደ ገጸበረከት ሊሰጡ ከሚችሉት መካከል ናቸው። ተጨማሪ ስጦታ እንዲሰጥ ሰርገኛው እና ዘፋኞች ሲገፋፉ ቤተሰብ መልስ ሊሰጥ ‹‹ቡላ ኮሪን፣ ባዮ ሱሉሙታ ቆንቴም›› በቅሎን ከነኮርቻው፣ ቦቃ ጊደርን ሸልመናል/ ብሎ መልስ ይሰጣል። በመጨረሻም ወላጆች ምርቃታቸውን ይሰጣሉ።
ሙሹሪት በምትሸኝበት ወቅት የመፎጋገር እና በሽሙጥ መነካካት የነበረ ሲሆን፣ ዘፈን ግን እስከዚህም የጎላ አልነበረም። በጥንተ ከምባታ ባሕል ልጃገረድ ተድራ ስትወጣ አግቢው ወዳሬ /የቆዳ ውጤት/ ለብሶ ነው። ስልጣኔ እያሰፋ ሲሄድ ‹‹ባልቶ›› ይዞ መጥቶ ማልበስ የባህሉ አንዱ ክፍል ነው። ሙሽሪትን ለመውሰድ የመጡ ሰርገኞችም ወደ ቤት እንዲገቡ ከተፈቀደ በኋላ ቤተሰብ ሙሽሪትን ከመስጠቱ በፊት በወደፊት ሕይወቷ ኃላፊነት የሚወስድ ሽማግሌ ተለይቶ እንዲታወቅ ጥያቄ ያቀርባል።
በአደራ መልክ ኃላፊነቱን የሚወስደው ሽማግሌ ተግባር ተጣማሪያን በኑሯቸው የሀሳብ ግጭት እና ነገሮች ሲወሳሰቡ ችግሮችን መፍታት ነው። ሽማግሌው ተለይቶ ከታወቀ በሁዋላ ሙሽሪት ወደ ውጭ ከመውጣቷ በፊት ቅቤ ተቀብታ ወደ ደጃፍ ወጥታ በወላጆቿ በእህቶቿ በወንድሞቿ በቅርብ ዘመዶቿ እና በሽማግሌዎች ከተመረቀች በሁዋላ የሁሉንም እጆች መዳፍ ትሰማለች። ከምባታ ሴት ልጁን ለትዳር አውጥቶ ሲሰጥ ክፉ ነገር ሲደርስባት ከባል ሌላ በጉዳዩ ዙሪያ ኃላፊነት የሚወስድ ግለሰብ ተለይቶ እንዲሰጥ ያደረገበት ባሕላዊ አርቆ አሳቢነት እጅግ የሚደነቅ ነው።
ዱሮ አጃቢዎች ሙሽሪትን ለመውሰድ የሚመጡት በእግር ነበር፤ ሚዜዎቹ እና አጃቢዎቹ ሙሽሪትን በትከሻቸው ተራ በተራ በመሸከም ይወስዷት ነበር። ይህ ግን በሂደት በጋማ ከብት ተተካ። ሙሽሪት ከሚዜዎቿ ጋር ወደ ሙሽራው ቤት የምትወሰደው በጭፈራ ታጅባም ነበር። በጋማ ከብት ጀርባ ላይ ተቀምጣ ስትሄድ በተለይ በበቅሎ ላይ ከሆነ ሙሽራው ቤት ስትደርስ የእንሰት ቅጠል በባዝራ ጀርባ ላይ ተደርጎ ለአፍታ ተቀምጣ እንድትወርድ ይደረጋል። የዚህ ስነ ስርዓት ዋና መልእክት ሙሽሪት ፍሬያማ እንድትሆን ማሰብን ያመለክታል ሲል መረጃው ጠቁሟል።
በመረጃው እንደተመለከተው፤ ከጋማ ከብት ጀርባ ስትወርድ ከደጃፍ ላይ ጅባ ተነጥፎላት በተዘጋጀው ቦታ ትቀመጣለች። ሁለት ሕጻናት ወንድና ሴት በሁለቱ ጭኖቿ ላይ እንዲቀመጡ ይደረጋል። የዚህ ስነ ስርዓት ዋና ትርጉምም ሙሽሪት ከአብራኳ በሚገኘው ፍሬ እንድትንበሸበሽ መልካም ምኞት ለመግለጽ ነው።
አማቷ አዲስ ስም ታወጣላታለች። ከሙሽሪት ወላጆች ቤት የተሰጣት ንብረት አንድ በአንድ ርክክብ ይደረጋል። ይህ ስነ ስርዓት ተከናውኖ እንዳበቃ ሙሽሪት በሚዜ ታዝላ፣ በአጃቢዎች ተከባ ወደ ተዘጋጀላት እልፍኝ ትወሰዳለች። ይሄ ደግሞ የሙሽራው እህቶች በር ዘግተው በመያዝ ስጦታ አንዲሰጣቸው መጠየቃቸውን ይያያዙታል። ስጦታ ለመስጠት ቃል ይገባናም ሙሽሪት ወደ እልፍኝ እንድትገባ ይደረግና በተዘጋጀው ቦታ የጫጉላ ጊዜዋን ታሳልፋለች።
ለአማቾቿ ክብር ስትልም የጫጉላ ጊዜዋን ብትጨርስም፣ እስከምትወልድ ድረስ በይፋ ፊቷን አታሳይም። ወልዳ ከተመረቀችና የባል ቤተሰብም ስጦታ ሰጥቷቸው የራሳቸውን ጎጆ ቀልሰው መኖር ሲጀምሩ ባህሉ መሰረት ተጥሎባት የነበረው የመሸፋፈኑና በይፋ ያለመታየት ገደብ ያበቃና ማኅበራዊ ሕይወት ትጀምራለች።
መልስ ‹‹ ምንአግሽ›› የመጥራት ባሕል ያለ ሲሆን፣ ይህ ልምድ የቤተሰብ ዝምድናን ለማጎልበት፣ ትውውቁን ለማጠናከር፣ እርስ በርስ መዛመድን በጥልቅ ለማሳየት እና አቅምን ለማሳየት የሚደረግ ስነ ስርዓት ነው። በዘመኑ በዋናነት የሚቀርበው ግብዣ ቆጮ ከአይብ ጋር ሲሆን፣ መጠጡ ሱሱጎና ጩሙቶ ነው። በሂደት በሬና በግ እየታረደ የመስተንግዶው እንድ አካል ሆነ።
በጥንተ ከምባታ ዘንድ በሽማግሌ ከሚጠየቅ እና በቤተሰብ አማካይነት ከሚቀነባበር መተጫጨት በተጨማሪ ‹‹ሜዱ›› /ጠለፋ/ እና ‹‹ሄራሙ›› በልጃገረድ ስምምነት የሚደረግ የትዳር ጥምረት እንደነበር መረጃው ያስታውሳል። ጠለፋ እና በልጃገረዷ ስምምነት የመጣመር አካሄድ በቤተሰብ ደረጃ ብዙ የማይደገፍ ቢሆንም፣ በባሕሉ ውስጥ ነበር። በተለይ ልጃገረድ በራሷ ፈቃድና ስምምነት በውዴታ የምታደርገው ትዳር ከገዛ ቤተሰቧም ጋር የሚያጋጭ አንዳንዴም እስከ መረገም ሊያደርስ የሚችል ነው።
ጠለፋ በተለይ በጠላፊው እና በተጠላፊዋ ቤተሰብ መካከል ወደ ጠላትነት ተቀይሮ በጉዳዩ ላይ ከቤተሰብ በተጨማሪ በጎሳዎች መካከል ወደለየለት መቃቃር እና ደም እስከመቃባት ሊያደርስ ይችላል። አንዳንድ ጽንፈኛ ቤተሰብ ተጠላፊዋ ብትወልድ አንኳ እስከማለያየት የሚያደርደስበት አጋጣሚም ሲከሰት ተስተውሏል። ጠለፋ /ሚዱ/ ሆነ በማባበልና በማግባባት /ሄራንቻ/ የተደረገ ጋብቻ የቤተሰብ ሚና የሌለው ቢሆንም፣ በአገሬው ሽማግሌ የማግባባትና የማብረድ ጥረት እርቅና ሰላም በቤተሰቦች መካከል እንዲወርድ የሚደረግበት ሁኔታም አለ። ይህም ባሕላዊ የእርቅ ሂደት ከምባቶች ነገሮችን በጥሞና የመፍታት ብቃታቸውን በይበልጥ ያሳያል።
በከምባታ ባሕል ብዙ ሚስት ማግባት በጣም የተስፋፋ አልነበረም። ሆኖም ግን ባል ሲሞት፣ የሟቹን ሚስት ወንድም አልያም የቅርብ ቤተሰብ ‹‹ ረጊታ ›› / ውርስ/ ማግባት በተወሰነ ደረጃ ይፈጸም ነበር። ከምባታ የዚህን አይነት ባሕል ያዳበረው ለሟች ልጆችና ሚስት ከማሰብ በመነጨ መሆኑን መረጃው ይገልጻል። ከዚህ በተጨማሪም ሟች ያፈራው ንብረት ወደ ባዳ እጅ እንዳይገባ ለመከላከልም ጭምር መሆኑን ያመለክታል። ሁለት ሚስት የማግባት ሁኔታ በአንዳንድ አጋጣሚዎች፣ ከእምነት፣ ከሀብትና ከማኅበራዊ ሕይወት ጋር ተያይዞ የሚደረግበት ሁኔታ እንዳለም ተጠቁሟል።
ዛሬ ትዳር የመመስረቱ ሁኔታ በሁለቱ ተጠማሪያን መካከል እየተደረገ ወደ ዘመናዊነት እየተሸጋገረ እንደሆነ የጊዜው ነባራዊ ሁኔታ ያሳያል። ወደ ዘመናዊነት መቀየሩ የሚያስከፋ አይሆንም። ዋና ነገሩ አዲሱ ዘመናዊ የመተጫጨት እና የመጋባት ሁኔታ ምን ያህል የአባቶችን ወግ እና ባሕል ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው የሚለው ነጥብ ከጥቅሙ እና ከጉዳቱ አኳያ ተያይዞ ቢታይ መልካም ይሆናል። አንድ ነገር ዘመነ ማለት ፍጹም ሆነ ሳይሆን ተግዳሮትም አብሮት እንደሚመጣ መዘንጋት የለበትም። ጥሩ እና መልካም ባሕል ከዘመኑ ጋር እንዲሄድ ቢደረግ የከምባታ የትዳር ባሕልና እሴት ተጠብቆ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ይረዳል የሚል እምነት እንዳለም በመረጃው ተጠቁሟል።
ኃይሉ ሣህለድንግል
አዲስ ዘመን ነሐሴ 24 ቀን 2016 ዓ.ም