ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሠላም እና መረጋጋት ስጋት የሚሆኑ እንቅስቃሴዎችን በትኩረት ትከታተላለች

የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ካለው ስትራቴጂክ ጠቀሜታ አኳያ የብዙዎችን ትኩረት የሚስብ፤ ሰፊ ጣልቃ ገብነት የሚስተዋልበት፤ በዚህም ምክንያት ከስድስት አስርት ዓመታት በላይ ባለመረጋጋት እና በግጭት ውስጥ የቆየ አካባቢ ነው። የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦችም የሚፈልጉትን ሠላም እና ልማት እውን ማድረግ ሳይችሉ ዓመታትን በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ለማለፍ የተገደዱ ናቸው።

በተለይም በሶማሊያ የተፈጠረው መንግሥት አልባነት እንደ አልሸባብ እና አይ ኤስ ኤስ የመሳሰሉ ጽንፈኝ እና አሸባሪ ኃይሎች በአካባቢው በስፋት እንዲንቀሳቀሱ፤ ከአካባቢው አልፈው ለዓለም ስጋት እንዲሆኑ አድርጓል። ችግሩ በቀጣናው ዘላቂ ሠላም ለማምጣት የሚደረገውን አሕጉራዊ ሆነ ዓለም አቀፍ ጥረት ፈትኗል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት ለሶማሊያ ሕዝብ ካለው ቅርበት /ወንድምነት/ የተነሳም ዓለም አቀፍ፤ አሕጉራዊ እና አካባቢያዊ የሠላም ማስከበር ተልዕኮዎችን ወስዶ ሕዝቡ ከጽንፈኛ እና ሽብርተኛ ቡድኖች የሚደርስበት ፈተና ለማቅለል፤ የተሻለ የሠላም አየር እንዲተነፍስ ለማስቻል ብዙ መስዋዕትነት የጠየቁ ወታደራዊ ተልዕኮዎችን ወስዶ በስኬት ተወጥቷል።

በዚህም የሶማሊያ ሕዝብ ከጽንፈኛ እና ከአክራሪ ቡድኖች የሚደርስበትን አስቸጋሪ ፈተናዎች ተሻግሮ አንጻራዊ የሆነ የሠላም አየር እንዲተነፍስ አድርጓል። ከዚህም ባለፈ ቡድኖቹ ከሶማሊያ ውጪ ባሉ የአካባቢው ሀገራት ሠላም እና መረጋጋት ላይ ጫና እንዳይፈጥሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት ያበረከቱት አስተዋፅዖም የማይተካ ነው ።

ይህ ብዙ የሕይወት መስዋዕትነት የጠየቀ የኢትዮጵያ አስተዋፅዖ አካባቢውን በማረጋጋት ሆነ በአካባቢው የተሻለ ሠላም ለማስፈን ስለነበረው ድርሻ ከማንም ይልቅ ለሶማሊያ ሕዝብ የተሰወረ አይደለም። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከሁለት አስርት ባላነሰ ጊዜ በሶማሊያ ያደረገው ቆይታም የዚሁ እውነታ ተጨባጭ ማሳያ ነው።

ይህንን ዓለም አቀፍ እውቅና ያተረፈ በሕይወት መስዋዕትነት ላይ የተመሠረተ የኢትዮጵያን የክፉ ቀን አጋርነት፤ ለማጠልሸት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሶማሊያ መንግሥት በኩል የሚስተዋሉ ያልተገቡ አካሄዶች ለሶማሌ ሕዝብ እና ለታሪክ የሚተዉ ናቸው። የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ የሞራል እና የታሪክ ተጠያቂነት ማስከተላቸው የማይቀር ነው።

የሶማሌ መንግሥት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ያሉትን አንዳንድ ልዩነቶች በድርድር ከመፍታት ይልቅ፤ በአካባቢው ሠላም እና መረጋጋት መስፈኑ ብሔራዊ ጥቅማችንን ይጎዳዋል የሚሉ ኃይሎችን ጣልቃ በማስገባት፤ በአካባቢው ውጥረትን ለማንገሥ እየሄደበት ያለው፤ የተሳሳተ የዜሮ ብዜት መንገድ የሶማሊያ ሕዝብ ፍላጎት ነው ተብሎም አይታመንም።

የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት የአካባቢው ሠላም ከሁሉም በላይ ለራሳቸው ሆነ ለአካባቢው ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት ስትራቴጂክ አቅም እንደሆነ ያምናሉ። በየትኛውም ሁኔታ በአካባቢው የሠላም ስጋት የሚፈጥር እንቅስቃሴ በአንድም ይሁን በሌላ ስለሚመለከታቸው ሁኔታውን አቅልለው የሚመለከቱት አይሆኑም።

በተለይም አካባቢውን ወደ አለመረጋጋት ሊወስዱ የሚችሉ የተለያዩ ፍላጎቶችን ያላቸው ኃይሎች ወደ አካባቢው የሚያደርጉትን የትኛውንም በዓይነት ያልተገባ እንቅስቃሴ በልዩ ትኩረት ይከታተላሉ። የነዚህ ኃይሎች ዋንኛ ተልዕኮ በአካባቢው አለመረጋጋት ለመፍጠር በመሆኑም ጉዳዩን በብሔራዊ ጥቅም እና ሠላም ላይ የሚደረግ ትንኮሳ አድርገው ይመለከቱታል ።

የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው በአካባቢው ሊኖር በሚችለው ሠላም እና መረጋጋት፤ ከዚህ በሚመነጭ ልማት እንደሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝብ በከፍተኛ ሁኔታ ያምናሉ። ለዚህም ሲሉ በሠላም ሆነ በልማት ዙሪያ ከአካባቢው ሀገራት ጋር ፍትሐዊ የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ባደረገ መልኩ አብሮ መንቀሳቀስ የሚያስችሉ ስትራቴጂ ነድፈው እየተንቀሳቀሱ ነው።

ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሕዝብ ዘላቂ ሠላም ለማምጣት የከፈለችው የሕይወት መስዋዕትነትም ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ፤ አሁን ላይ አካባቢውን በኢኮኖሚ ለማስተሳሰር የምታደርገውም ጥረት ከዚሁ የመነጨ ነው። በቀጣይም በአካባቢው ዘላቂ ሠላምን በማስፈን ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለማስከበር የምትሄድበት ኃላፊነት የተሞላበት አካሄድ የዚሁ እውነታ ተጨባጭ ማሳያ ሊሆን የሚችል ነው ።

ከዚህ ውጪ በየትኛውም መንገድ ለሀገሪቱ ሆነ አጠቃላይ ለሆነው ለቀጣናው ሠላም እና መረጋጋት ስጋት ሊሆኑ የሚችሉ ጣልቃ ገብነቶችን፤ ለቀጣናው ሀገራት ሕዝቦች እውነተኛ ሠላም እና ልማት ስትል በትኩረት ትከታተላለች፤ አስፈላጊም ሆኖ ሲገኝ ሠላሟን እና ብሔራዊ ጥቅሞቿን ስጋት ውስጥ የሚጨምሩ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ኃላፊነት በሚሰማው መንገድ አስፈላጊውን እርምጃ ትወስዳለች።

አዲስ ዘመን ነሐሴ 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You