ደቡብ አፍሪካዊው ቢሊየነር ዳንጎቴን በመብለጥ የአፍሪካ ቁጥር አንድ ሀብታም ሆነ

ደቡብ አፍሪካዊው ቢሊየነር ዳንጎቴን በመብለጥ የአፍሪካ ቁጥር አንድ ሀብታም ሆነ።

ደቡብ አፍሪካዊው ቢሊየነር ጆናታን ሩፔርት ናይጄሪያውን ባለሀብት አሊኮ ዳንጎቴን በመብለጥ የአፍሪካ ቁጥር አንድ ሀብታም መሆኑን የብሉምበርግ ቢሊየነርስ ኢንዴክ መረጃ ያመለክታል።

ሩፔርት ካርቴር እና ሞንትብላንክ የመሳሰሉ ብራንዶች ያሉትን እና በዓለም ግዙፍ ከሚባሉት የቅንጦት እቃ አምራች ኩባንያዎች ውስጥ አንዱ የሆነው የሪችሞንት ባለቤት ነው። የሩፔርት ጠቅላላ የሀብት መጠን ከ1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር ወደ 14 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ሲያድግ ከዓለም 147 ደረጃ እና ከዳንጎቴ ደግሞ 12 ደረጃዎችን ከፍ እንዲል አድርጎታል።

ብሉምበርግ እንደዘገበው ከሆነ፤ የናይጄሪያዊው ሀብት በ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ቀንሶ አጠቃላይ ሀብቱ 13 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ሆኗል። የዳንጎቴ ሀብት መጠን መቀነስ አብዛኞቹ ኩባንያዎቹ ያሉባትን የናይጀሪያን የኢኮኖሚ ፈተና የሚያሳይ ነው።

ዳንጎቴ ግሩፕ የተባለው የንግድ ድርጅታቸው በነዳጅ ማጣሪያ ኩባንያው በፈጠረው የምርት መዘግየት እና በአቅርቦት መዛባት ምክንያት በርካታ ችግሮች አጋጥሞታል። ሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ችግር ውስጥ ብትሆንም፣ ዳንጎቴ ባለፈው ጥር ወር በፎርብስ መጽሄት ለተከታታይ 13ኛ ጊዜ የአፍሪካ ቁጥር አንድ ሀብታም ተብለው ነበር።

ነገርግን ብሉምበርግ በቅርቡ ያወጣው መረጃ ዳንጎቴ በአፍሪካ ሁለተኛ በዓለም ደግሞ 159ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ሩፔርት አጠቃላይ ሀብት የጨመረው የቅንጦት እቃዎች ዘርፍ ከፍተኛ አፈጻጸም በማሳየቱ ነው።

ሌላኛው ደቡብ አፍሪካዊ ቢሊየነር ኒኪ ኦፐንሂመር በ13.3 ቢሊዮን ዶላር አጠቃላይ ሀብት በአፍሪካ ሦስተኛ ሲሆን ግብጻዊው ባለሀብት ናሴፍ ሳዊሪስ ደግሞ በ9.48 ቢሊዮን ዶላር አራተኛ ሆኗል።

ብሉምበርግ እንደፎርብስ ሁሉ የዓለም ሀብታም ሰዎች ባላቸው አጠቃላይ ሀብት ላይ ሊኖር የሚችለውን እለታዊ ለውጥ ይከታተላል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ነሐሴ 23/2016 ዓ.ም

Recommended For You