‹‹የምግብና ስነ ምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤቶች ተገኝተዋል›› – ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ

ኢትዮጵያ በእንስሳት ሃብቷ በአፍሪካም ሆነ በዓለም ደረጃ የመሪነቱን ቦታ እንደያዘች ይታወቃል። ይሁንና ይህንን ሃብት ጥቅም ላይ በማዋል ለሕዝብና ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ ሚና በመጫወቱ ረገድ ወደኋላ የቀረች መሆንዋ በተደጋጋሚ ሲነሳ ይደመጣል። ይህንን ሃብት በማልማትና ሀገርን ከዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ እንዲሁም የሕዝቡን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ እንዲያስችል መንግስት ባለፉት ዓመታት የተለያዩ መርሃ ግብሮችን ቀርጾ ተግባራዊ አድርጓል።

ከእነዚህም መርሃ ግብሮች መካከል በዓለም ባንክ ድጋፍ በ58 ወረዳዎች ላይ ሲተገበር የቆየው የእንስሳትና ዓሳ ሃብት ፕሮጀክት እንዲሁም ባለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በመላ ሀገሪቱ እየተከናወነ ያለው የሌማት ትሩፋት ዋነኛው ነው። በእነዚህ መርሃግብሮች አማካኝነት በዘርፉ አበረታች ውጤቶች እየተገኙ ነው፤ ሆኖም ካለው እምቅ አቅም አኳያ ገና ብዙ ተግባራትን ማከናወን ይጠይቃል። በእነዚህና በሌሎችም የዘርፉ ተግዳሮቶች ዙሪያ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳን አነጋግረን እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በተለይ በቀንድ ከብት ሃብት ቀዳሚ ብትሆንም እስካሁን የሚገባውን ያህል ከዘርፉ ተጠቃሚ ያልሆንባቸውን አብይ ምክንያቶች ያስታውሱንና ውይይታችንን እንጀምር?

ዶክተር ፍቅሩ፡– ኢትዮጵያ በአጠቃላይ በእንስሳት ሃብት በአፍሪካም ሆነ በዓለም ቀዳሚ ሀገር ናት። ለዚህ ደግሞ ያላት አየር ንብረትና ስነም-ህዳር ምቹ መሆኑ በምክንያትነት የሚነሳነው። ያለውን ሃብት በሃብትነት ማስቀመጥ ሳይሆን ማልማት፣ ማሻሻል፣ ማዘመንና ወደ ተሻለ ጥቅም መቀየር ይጠይቃል። ይህ የሀገሪቱ ሕዝብና መንግስት ስራ ነው። የኢትዮጵያ ስታስቲክ ኤጀንሲ በ2021 ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው፤ ኢትዮጵያ 71 ሚሊዮን የዳልጋ ከብት፣ 52 ሚሊዮን ፍየል እና 42 ሚሊዮን በጎች አሏት። የጋማ ከብትና ግመል 20 ሚሊዮን ይጠጋሉ። በጥቅሉ ከ200 ሚሊዮን በላይ የሚጠጋ እንስሳ አላት። በዶሮ በኩል ደግሞ በየጊዜው የሚቀያየር ሲሆን፣ 75 ሚሊዮን ዶሮዎች እንዳሉ መረጃው ያሳያል። ይህንን በአጠቃላይ ስንደምር ሀገራችን የትልቅ ሃብት ባለቤት መሆንዋን ያመለካታል፡፡

ይህም ሆኖ ካለን የእንስሳት ቁጥር ልክ ጥቅም ላይ ማዋል አለመቻላችን የሁላችንም ቁጭት ነው። ሆኖም ጥቅም የምንለካበት መንገድ መስተካከል አለበት። ምክንያቱም ለእኛ እንስሳት ብዙ ነገራችን በመሆናቸውና የሚሰጡንም ጥቅም ከምግብና መጠጥ ያለፈ በመሆኑ ሃብቱ ሙሉ ለሙሉ ጥቅም ላይ አልዋለም ማለት አይቻልም። በተለይ በግብርናው ዘርፍ እንስሳት በርካታ ጠቀሜታ እንዳላቸው ይታወቃል፤ የበሬ ወይም የፈረስ ጉልበት ተጠቅመን እናርሳለን፤ እንወቃለን፤ ለትራንስፖርትና ሸክም እንገለገላለን። በአጠቃላይ ለእያንዳንዱ እንቅስቃሴያችን እንስሳ ትልቅ ሚና አለው። በእርግጥ ሌሎች ሀገራት ወደመከናይዜሽን ሙሉ ለሙሉ ስለተቀየሩ እንስሳቱን የሚጠቀሙባቸው ለስጋቸው ወይም ለወተታቸው ነው። እኛ ይህንን ጥቅምንም ጭምር ከግምት ውስጥ ማስገባት አለብን።

እንደተባለው ከስጋ፣ ወተትና እንቁላል አኳያ ከእንስሳቱ ብዛት ጋር የሚመጣጠን ምርታማነት የለንም። እነዚህን እንስሳት ወደ ውጭ ልከን እያገኘን ያለነው የውጭ ምንዛሬም አነስተኛ የእንስሳት መጠን ካላቸው አንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ የሚባል ነው። ይህ የሆነበት ምከንያት የስፔሻሊቲ ጉዳይ ነው። በዘርፉ ያደጉ ሀገራት ለወተት የሚይዟቸው ስፔሻሊቲ ዝርያዎች አሉ። ለስጋም እንዲሁ የሚመርጧቸው ዝርያዎች አሉ። እነዚህን ለይተን ማልማት ባለመቻላችን በዘርፉ የሚገባንን ጥቅም እንዳናገኝ አድርጎናል። ስለዚህ ከማልማት አንፃር ሊከናወኑ የሚገቡ ስራዎች አሉ፡፡

ከዚያ እንፃር ዝርያን ማሻሻልን ይጠይቃል። ለምሳሌ እንደሀገር ያሉት የወተት ከብቶች ቁጥር በጣም አነስተኛ ነው። ስጋም ስፔሻላይዝድ ያደረጉ በዓለም ላይ የሚታወቁ ዝርያዎች በሚፈለገው ልክ የለንም። ከዚያ አልፎ ተርፎ ደግሞ አያያዙ ደካማ የሚባል ነው። ገጠር አካባቢ እንስሳቱ በበረት ውስጥ የሚኖሩ በመሆናቸው ለብዙ ችግር የተጋለጡ ናቸው። ዝናብ የሚዘንብባቸው በመሆኑ የሚተኙት ጭቃ ውስጥ ነው። ይህ ብቻውን እንኳን ምርታማነት ላይ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ አለው። አሁን አሁን እየተሻሻለ ይምጣ እንጂ አመጋገባቸውማ ባህላዊ ሲሆን፣ ጠዋት ጠዋት ለግጦሽ ከማሰማራት በዘለለ በተገቢው መጠን የተመጣጠነ መኖ አይሰጣቸውም፤ ይልቁኑም ግጦሽ ፍለጋ ረጅም ርቀት እንዲጓዝ ስለምናደርጋቸው በተለይ ላሞቹ የሚሰጡን የወተት መጠን ዝቅተኛ እንዲሆን ምክንያት እንደሆነ ግልፅ ነው። በዚህ ሂደትም የበሽታ መከላከል ስራ በቅጡ የማይሰራ በመሆኑ በርካታ ከብቶችን ሳንጠቀምባቸው ይቀራሉ።

ስለዚህ በጥቅሉ ዝርያ ማሻሻል ላይ ባለመስራታችን፤ የመኖ አያያዛችንም ደካማ በመሆኑና የበሽታ ቁጥጥሩም ጠንካራ ባለመሆኑ ባሉን እንስሳት ልክ ተጠቃሚ እንዳንሆን አድርጎናል። እነዚህ ስራዎች ባለመሰራታቸው ምክንያት ምርታማነት ላይ ያለውን ተፅዕኖ ለአብነት ለማሳየት አንዲት የሀገረሰብ ዶሮ በዓመት 40 እንቁላል ብቻ ስትጥል፤ የፈረንጇ ደግሞ እስከ 320 እንቁላል በዓመት መስጠት ትችላለች። ሁለቱ ሲነፃፀሩ ስምንት እጥፍ ልዩነት አለው፡፡

ወደ ላሞችም ብንሄድ የእኛ ላም በቀን የምትሰጠው ወተት አንድ ነጥብ አምስት ሊትር ሲሆን፣ የተሻሻሉ ዝርያ ያላቸው የወተት ላሞች የሚሰጡት ግን በአማካኝ 15 ሊትር ወተት ነው። ያ ማለት አንዷ የፈረንጅ ላም የእኛን አስር ላም ትተካለች ማለት ነው።

በነገራችን ላይ ሀገራችን በንብ መንጋ ብዛትም ከአፍሪካ አንደኛ ነች። በጥቅሉ 10 ሚሊዮን የሚጠጋ የንብ መንጋ እንዳላት መረጃዎች ያሳያሉ። ከሰሜን ጫፍ እስከ ትግራይ እስከ ቦረና ድረስ፤ ከሱማሌ ኦጋዴን እስከ አሶሳ ድረስ ተስማሚ የአየር ንብረትና ስነምህዳር አላት። ግን አሰራራችን ኋላቀር በመሆኑ ለቤተሰብ ፍጆታ የሚውል ማር ለማግኘት እንኳን የሚቸግርበት ሁኔታ አለ። እስካሁን ባለው ሁኔታ የንብ ማነብ ስራው እየተመራ ያለው በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል በባህላዊ ቀፎና ዘዴ ነው። ባህላዊ ቀፎ ምርታማነቱ በዓመት በአንድ ጊዜ ቆረጣ 10 ኪሎ ግራም ብቻ የሚገኝ ሲሆን፣ በዘመናዊ ቀፎ ደግሞ 30 ኪሎ ማግኘት ይቻላል። ዘመናዊ ቀፎዎችን በብዛት በማሥቀመጥና የተለያዩ ተክሎችን በመትከል በአንድ ዓመት ሶስት ጊዜ ማር መቁረጥ ያስችለናል።

አዲስ ዘመን፡- እነዚህን ችግሮች በመፍታት የዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ በሚኒስቴሩ የተሰሩ ስራዎችን ቢጠቅሱልን?

ዶክተር ፍቅሩ፡– ግብርና ሚኒስቴር ዋነኛ ስራው ችግሮችን እየፈተሸ መፍትሔ ማበጀት ነው። ለዚህም ነው ባለፉት ዓመታት ዝርያ በማሻሻል፣ የመኖ ፋብሪካ በመትከል፤ ዘመናዊ መሳሪዎችን ለአርሶአደሩ በማከፋፈል ላይ ትኩረት አድርገን የቆየነው። በተለይም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ችግሮችን ለመፍታትና የአሰራር ስርዓታችንን ለማዘመን ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተን ስንሰራ ቆይተናል። ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትራችን ኢኒሼቲቭ በሆነው የሌማት ቱሩፋት መርሃግብ በዘርፉ ከፍተኛ እምርታ ተመዝግቧል፤ የሕዝቡ ፍላጎትና ግንዛቤም ጨምሯል።

ለዘርፉ ምርታማነት መጎልበት መንግስትም የፖለቲካ ቁርጠኝነቱን በማሳየቱ በተጨባጭ በሚታይ መልኩ በቤተሰብ ደረጃም ሆነ እንደ ሃገር ምርታማነት በከፍተኛ መጠን አድጓል። ከዚህ በፊት ምንም አይነት በጀት በበቂ ሁኔታ የማይያዝለት ዘርፍ አሁን ላይ በክልሎች ደረጃ ራሱ ትልልቅ በጀት መያዝ ተጀምሯል። ለምሳሌ አምና ለንብ ቀፎ ብቻ ተብሎ ኦሮሚያ የመደበው 135 ሚሊዮን ብር ነው። ከዚህ በፊት ግን የአርሶ አደሩን ስራ አይቶ እንኳ ለመመለስ የሚያስቸግር የስራ ማስኬጂያ ገንዘብ የሚያጥርበት ሁኔታ ነበር። ግብዓቶችንና አቅርቦትን በማሻሻል፤ ስልጠና በመስጠት ብዙ ለውጦችን ማምጣት ተችሏል።

ለዚህም ለአብነት እንኳን ብንጠቅስ የሌማት ቱሩፋቱ ከመጀመሩና ከተጀመረ በኋላ የመጡትን ለውጦች ማየት እንችላለን። ዝርያ ማሻሻል ስራ አንፃር ሁለት የውጭ ዝርያዎችን አባላዘር ተጠቅመን ከሌማት ቱሩፋት በፊት (2014 ዓ.ም) ላይ በጣም ትልቅ ስራ ሰራን ብለን በኢትዮጵያ ደረጃ የሰራነው 500 ሺ ሲሆን፣ በአንድ ዓመት ልዩነት ግን ሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን ከብቶችን ዝርያ ማሻሻል ችለናል። ይህም ከበፊቱ ጋር ሲነፃፀር ከአምስት እጥፍ በላይ ነው። የሚጎትቱንና አቅማችንን የሚፈትኑን ነገሮች ባይኖሩ ከዚያም በላይ መስራት ይቻላል።

ወተትንም ያየን እንደሆነ ከሌማት ቱሩፋት በፊት በአጠቃላይ ከግመል፣ ከፍየልና ላሞች ሰባት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ሌትር የተመረተ ሲሆን፣ ዘንድሮ ዘጠኝ ነጥብ 997 ቢሊዮን ሊትር ወተት ማግኘት ችለናል። በተጨማሪም በ2014 ዓ.ም 26 ሚሊዮን የዶሮ ጫጩት ያሰራጨን ሲሆን፣ ዘንድሮ 72 ሚሊዮን ጫጩት ለአርቢዎች ማድረስ ችለናል። ይህንን ስናይ በሶስት እጥፍ አድጓል ማለት ነው። በዚያው ልክ የእንቁላልና የዶሮ ስጋን በጣም በከፍተኛ ሁኔታ ልዩነቶችን አሳይቷል። ከሁለት ዓመት በፊት ሶስት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን እንቁላል የተመረተ ሲሆን፣ በ2016 ዓ.ም ደግሞ አምስት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን እንቁላል አምርተናል። በእርግጥ እቅዳችን ስድስት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ነበር፤ መሃል ላይ ችግር ስለነበረ የእቅዳችንን 94 በመቶ አሳካተናል። ይህም ትልቅ ስኬት ነው።

ወደ ዘመናዊ ቀፎ ስንሄድ በአጠቃላይ ዘመናዊና የሽግግር ቀፎ ብለን የወሰድነው 2014 ዓ.ም ላይ 905 ሺ ነበር፤ ዘንድሮ ግን የሰራነው ወደ ሁለት ሚሊዮን አካባቢ ነው። ምርቱም ያደገ ሲሆን፣ ከሁለት ዓመት በፊት እንደሃገር 147 ሺ ቶን ይመረት የነበረውን የማር ምርት ዘንድሮ ወደ 272 ሺ ቶን መድረስ ችሏል። ከጫጩት ዓሳ ስርጭት አንፃር ደግሞ ከአንድ ሚሊዮን ተነስተን ላይ ስድስት ነጥብ አራት ሚሊዮን የዓሳ ጫጩት አሰራጭተናል፤ ይህ እንደሃገር በጣም ትልቅ እድገት የሚባል ነው። ምርቱንም በዚያ ልክ ለማሳደግ የሰራን ሲሆን፣ በዚህ ረገድም ከ78 ሺ ቶን ወደ 132 ሺ ቶን የዓሳ ምርት ከፍ አድርገናል። በጥቅሉ እነኚህ ውጤቶች ዋና ዋናዎቹ እንጂ በርካታ አበረታች እምርታዎችም ተመዝግበዋል፤ ይህም ሲባል ግብዓት በቀጥታ የሚሆኑትን ነው ያቀረብኩት እንጂ ለእነዚያ ደግሞ አስቻይ የሚሆኑ ብዙ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከዝርያ ማሻሻል ጋር ተያይዞ የተሰራው አበረታች ቢሆንም የሊኩዊድ ናይትሮጂን እጥረት እንዳለ በእርባታ ተግባር ላይ በተሰማሩ አካላት ይነሳል፤ በተለይ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ላይ ያለው ማሽን በተደጋጋሚ ብልሽት የሚያጋጥመው በመሆኑ መቸገራቸውን አይተናል፤ ይህንን ችግር ለመፍታት ምን ያህል ጥረት ተደርጓል?

ዶክተር ፍቅሩ፡- ከዚያ በፊት ግን የማዳቀል አቅማችን ጨምሯል ሲባል የሊኩዊድ ናይትሮጂን ማምረት አቅምም እንዲሁ ማሳደግ መቻላችንን መግለፅ እወዳለሁ። በተደጋጋሚ የሚነሳው ከዝርያ ማሻሻል ጋር ተያይዞ የሊኩዊድ ናይትሮጂን እጥረት ነው። እርግጥ ወደ 20 የሚጠጉ የሊኩዊድ ናይትሮጂን ማሽኖች በኢትዮጵያ አሉ። ከመቀሌ ጀምሮ ባህርዳር፣ ደብረብርሃን፣ ቃሊቲ፣ ሻሸመኔ፣ ሃዋሳ፣ ሶዶ፣ ወልቂጤ፣ ነቀምት፣ ጅማ፣ ሚዛን፣ ሐረርና ሌሎችም አካባቢዎች ላይ ማሽኑ አለ። ሆኖም አብዛኞቹ ከጊዜ ብዛት በተደጋጋሚ ብልሽት ያጋጥማቸዋል። ይህንን ጉዳይ እግር ለእግር ተከታትለን ለማስጠገን ጥረት አድርገናል።

ሆኖም አሮጌ ማሽኖች አፈፃፀማቸው በጣም አነስተኛ በመሆኑ በእነሱ ላይ ተንተርሰን መቀጠል የለብንም። ስርጭቱም ደግሞ አንዳንድ ቦታ ላይ ፍትሐዊ አይደለም፤ ይህንንም ለመቀየር ብዙ ስራ ሰርተናል። በአጠቃላይ ወደ አስር የሚጠጉ የሊኩዊድ ናይትሮጂን ማሽን ግዢ እቅድ ተይዞ በአሁኑ ወቅት የገቡ አሉ፤ አንዱ ቃሊቲ ላይ ተተክሏል፤ የሚቀረን ማስመረቅ ነው። አሶሳ ላይ የግዢ ሂደቱ አልቆ በመጓጓዝ ላይ ነው። ሶስት ደግሞ በዓለም ባንክ ድጋፍ እየተከናወነ ባለው ፕሮጀክታችን አማካኝነት ግዢ ተፈፅሞ መስከረም ላይ የሚገባ ይሆናል። ተጨማሪ አምስት ደግሞ በግዢ ሂደት ላይ ነው። በመሆኑም ከዚህ ቀደም ባልነበረባቸውም ሆነ አሮጌም በሆኑባቸው ቦታዎች ላይ ለመተካትና ከዚህ የበለጠ ለመስራት አቅደን እየተንቀሳቀስን ነው።

እንደተባለው በተለይ ወልቂጤ ላይ ያለው ማሽን ተደጋጋሚ ብልሽት ያጋጥመዋል። ዘንድሮ ይህንን ችግር ለመፍታት ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፤ ሆኖም ከግዢ ሂደቱ መራዘም ጋር ተያይዞ ወዲያው ሊደርስልን ስላልቻለ በጣም በትኩረት የሰራነው ሲበላሽ ፈጣን የሆነ የጥገና አገልግሎት እንዲያገኙና ወደ ስራ እንዲገቡ ተደርጓል። ያም ቢሆን ካለው ሰፊ የሕዝብ ፍላጎት አንፃር በነባሩ አሮጌ ማሽን ነው ስንሰራ የነበረው፤ በዚያ ሁኔታ መቀጠል ደግሞ ከመሰረቱ ችግሩን እንደማይፈታ አውቀን ነው ወደ ግዢ ሂደት የገባነው። በኢትዮጵያ በዚህ ደረጃ በአንድ ጊዜ ተገዝቶ አያውቅም። ጥረት እየተደረገ ያለው ማሽኖቹ በሁሉም ክልል እንዲኖርና እዚህ ድረስ መመላለሱን ለማስቀረት ነው። ይህ ከመሰረቱ ችግሩን ይቀርፍልናል ብለን እናምናለን። በቀጣይ ዓመት የሊኩዊድ ናይትሮጂን ጉዳይ በእርግጠኝነት ችግር ሆኖ የሚቀጥል አይሆንም።

ዝርያ ማሻሻል ላይ በአርቴፊሻልና በሊኪዊድ ናይትሮጂን ብቻ ሳይሆን ኮርማ በማሰራጨትም እንዲዳቀሉ እናደርጋለን። በተለይ ራቅ ባሉ አካባቢዎች ላይ የኮርማ ስርጭት በስፋት ይካሄዳል። በተጨማሪም ይህንን እንደስራ ፈጠራ ተጠቅመው አገልግሎት በሰጡ ቁጥር ገቢ የሚያገኙ አሉ። እዚህ ላይ የተመረቱ ዝርያዎች ጤነኛና ምርታማ መሆናቸውን የማረጋገጥ ስራ ይሰራል። አሁን ላይ የኮርማ አባላዘር የማምረቻ ቴክኖሎጂ ኢትዮጵያ ውስጥ የለም፤ እየተገዛ የሚመጣው ከውጭ ነው። ማምረቻው ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲተከል ከውጭ ኩባንያ ጋር መነጋገር ጀምረናል። ይህ መሆኑ ኢትዮጵያ ትልቅ የእንሳስት ሃብት ያላት፣ ዝርያ ማሻሻል ላይ በስፋት እየተሰራ በመሆኑና ለአውሮፓም ሆነ ለመካከለኛው ምስራቅ ቅርብ መሆንዋ የተሻለች በመሆኗ ኩባንያው ፋብሪካውን ቢከፍት አዋጭ ይሆናል። በመሆኑም ችግሩን ከመሰረቱ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው።

ከዚህ ጋር ተያይዞ አዲስ አበባና ቢሾፍቱ ላይ ተወስነው የነበሩ የመኖ ማቀነባበሪያዎች ለማስፋት ከፍተኛ ስራ ሲሰራ ነበር። የመኖ ማቀነባበሪያ ክልሎች ቢያንስ አንዳንድ እንዲኖራቸው የሚል አቅጣጫ ተሰጥቶ አዳዲስ እየተከፈቱ ነው። በቅርቡ አሶሳ ላይ ተተክሏል። ከዚህ በፊት ከቦንጋ ቢሾፍቱ ድረስ እየመጡ ነበር የሚወስዱት። አሁን እዛው ቦንጋ በመተከሉ ወጭና እንግልት ቀርቶላቸዋል። ጅግጅጋ ላይም አዲስ ማቀነባበሪያ የተተከለ ሲሆን፣ ሃዋሳ ላይ ሁለትና ሶስት በግልም ሆነ በኢንተርፕራይዞች ተከፍተው እየተሰራ ነው። ባህርዳር ላይ ትልቅ ኤክስፖርት ደረጃ የሚያደርግ ፋብሪካ ተክቷል። አዲስ አበባና ቢሾፍቱ ላይ ተጨማሪ ብዙ አሉ፣ እነሱም በሙሉ አቅማቸው እንዲሰሩ እየተደረገ ነው። ሆኖም አሁን ላይ በሚሊዮኖች እጥፍ እየጨመርን በመሆኑ በዚያው ልክ መኖ መጨመር አለብን።

አዲስ ዘመን፡- በሌማት ትሩፋት መርሃግብሩ የተያዘው ውጤታማነት ቆላማ አካባቢዎች ላይ ለምን መድገም አልተቻለም? በተለይ በእነዚህ አርብቶአደር አካባቢዎች የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ እንደሃገር ፈተና የሆነበት ምክንያት ምንድን ነው?

ዶክተር ፍቅሩ፡– እንደሀገር ባለፉት ዓመታት የግብርና ምርታማነት ለማሳደግ በተሰሩ ስራዎች የምግብና ስነ ምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚችሉ ውጤቶች ተገኝተዋል። ሆኖም በተለይ ትልቁ የእንስሳት ቁጥር ያለው ቆላማና አርብቶአደር አካባቢዎች ላይ እንደመሆኑ በሚፈለገው ደረጃ ተሰርቷል ማለት አይቻልም። እነዚህ አካባቢዎች ደግሞ እንደሚታወቀው ለብዙ ችግሮች ተጋላጭ ናቸው። በተለይም የአየር ንብረት አሳሳቢ የሆነባቸው በመሆናቸው የሚፈለገው ለውጥ አልመጣም፤ አብዛኛው የሌማት ትሩፋት የሚሰራባቸው አካባቢዎች ለጥምር ግብርና ምቹ በሆኑ ደጋና ወይናደጋ አካባቢዎች ነው። አስቀድመን ያነሳቸው እንደሊኪዊድ ናይትሮጂን ማምረቻ ያሉ መሰረተ ልማቶች በእነዚህ አካባቢዎች ባለመኖራቸው ማዳቀልና ማባዛትም አስቸጋሪ ነው። የዶሮ ማባዣ ማዕከላት በአብዛኛው ያሉት ደጋና ወይናደጋው ክፍል ነው። እነዚህ አካባቢዎች ደግሞ የተረጋጋ ሕይወት የሚኖሩ ማኅበረሰቦች ያሉባቸው ናቸው። በመሆኑም ከመጀመሪያውም ለዝርያ ማሻሻል የሚያስፈልጉ መሰረተ ልማቶች አልተዘረጉም።

ከዚያ በተጨማሪ በየጊዜው በዓለም ላይ የሚከሰተው የአየር ንብረት ለውጥ ብዙ ጉዳቶችን ሲያደርስ ነበር። አንድ ጊዜ ጎርፍ፤ ሌላ ጊዜ ድርቅ ይከሰታል። ይህ በሚሆንበት ጊዜ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እንስሳት ይሞታሉ። እንስሳ ሞተ ማለት ደግሞ እዚያ አካባቢ የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሕይወታቸው የተመሰረተው በእንስሳቱ ላይ በመሆኑ መፈናቀል፤ የኑሮ መሰረቱ መናጋት፣ ለበሽታና ለሞት መጋለጥ ይመጣል። በዚህ አካባቢ ያለውን ችግር ለመፍታት ሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን በዋናነት የሚሰራው የውሃ አቅርቦቱን ማሻሻል ነው። ይህንን በሁሉም ክልል በሚባል ደረጃ የውሃ ስራ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ነው። ለእንስሳቱ ውሃ ለማጠጣት ብቻ ሳይሆን ለመኖ ልማት የሚሆንም ነው። በእነዚህ አካባቢዎች የሚሰሩት የልማት ስራዎች በግብርና ሚኒስቴር ብቻ አይደሉም፤ ቆላማና አርብቶአደሮች አካባቢ ሚኒስቴር፣ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርና የተለያዩ ድርጅቶች ጭምር ነው።

አፋር፤ ሱማሌ፣ ኦሮሚያ ደግሞ ቦረና አካበቢ ላይ በእኛ ሚኒስቴር የተቆፈሩ የውሃ ጉድጓዶች አሉ። ከዚሁ ጎን ለጎን መኖ ልማት ላይ በስፋት እየተሰራ ነው። ሰሞኑን ቦረና ላይ ታይቶ የማይታወቅ መኖ ለምቷል። ስለዚህ ግብርና ሚኒስቴር ከመኖ ዘር አቅርቦት ጀምሮ ለሁሉም ክልል በየዓመቱ የተሻሻለ መኖ አቅርበን በእነኚህ የግጦሽ ቦታዎች ላይ እንዲተከሉ ይደረጋል። ከዚህ ቀደም የነበረው ያልተሻሻለ ዝርያ በመሆኑ ምርታማነቱ አነስተኛ ነው፤ ይህም እንዲሻሻል ሚኒስቴሩ እየሰራ ነው። እኔ የምመራው ቡድንም በየዓመቱ ይሰማራል፤ በየዓመቱ ድጋፍ ያደርጋል።

መኖ ልማት ላይ በተፈጥሮም በስፋት የሚመረትባቸው ወቅቶች አሉ፡፤ ይሁንና ከብቶቹ የሚችሉትን ግጠው ሌላው የሚበሰብስበትና የሚባክንበት ሁኔታ ነበር። በዚህ ሁኔታ ደግሞ ያለውን ችግር በዘላቂነት መፍታት አያስችልም። በመሆኑም መኖ ስናመርት በአግባቡ መሰብሰብ፤ ማከማቸትና በጥንቃቄ መያዝ አለበት በሚል በርካታ የመኖ ማከማቻ በየክልሉ እንዲሰራ ተደርጓል። ይህም ትርፍ ሲመረት በጊዜያዊነት የሚጠቀሙትን ተጠቅመው ሌላውን አስቀምጠው በድንገተኛ ጊዜ ከመሃል ሀገር ጭነን የምንወስደውን ያስቀራል። እንደአጠቃላይ በድርቅና በጎርፍ ምክንያት የሚመጡትን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት እየሰራን ነው። አልፎ አልፎ የሚከሰቱት ውስን ችግሮች በስተቀር አሁን ላይ እየተካሔደ ባለው አሰራር የምግብና ስነ ምግብ ዋስትና ማረጋገጥ የግብርና ሚኒስቴርም ቁልፍ ተግባር ነው፤ በዚያው ልክ እየሰራን ነው፤ በዚህ መልኩ ከተረጂነት ለመላቀቅ እየተኬደበት ነው።

ይህም ብቻ ሳይሆን ከቀንድና ጋማ ከብት ልማት ባሻገር አርብቶአደሮቻችን ዶሮ ልማት ላይ እንዲገቡ፤ የውሃ አካላት ያሉባቸው አካባቢዎች ላይ ዓሳ በማምረትና በተወሰኑት የእንስሳት ውጤቶች ላይ የተመሰረተውን ኑሯቸውን የተለያየ አማራጭ እንዲኖራቸው ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው። የማር ምርትንም በተመሳሳይ በተሻለ ሁኔታ እንዲሰሩ በሌማት ትሩፋቱ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው። እንደተነሳው አብዛኛው የእንስሳት ሃብታችን ያለው እዚያ አካባቢ ቢሆንም በወተት በኩል የተሻሻለ ዝርያ ያለው በከተማና በከተማ ዙሪያ ነው። በዚያ ልክ እዚያ ቆላማ አካባቢዎች ላይ መስራት ያስፈልጋል።

ከሁሉ በላይ የግብርና ሚኒስቴር ዋና ተልዕኮም የምግብና የስነ-ምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ነው፤ ከዚያ አልፎ ከውጭ የሚገቡትን መተካትና ወደ ውጭ የሚላኩትን የግብርና ምርቶች መጠን ማሳደግና የስራ እድል መፍጠር ነው። እንደ አጠቃላይ ከሰራነውና ካስመዘገብነው አንፃር ጥሩ መሻሻሎች አሳይተናል። ከሚጠበቅብን አንፃር ግን ብዙ መሄድ አለብን። የጠቀስኳቸውን የሚኒስቴሩን ዓላማ ከማሳካት አንፃር ብዙ ስራዎች መስራት አለብን።

አዲስ ዘመን፡- በሌማት ትሩፋቱ ምርታማነትን ቢጎለብትም የገበያ ትስስሩ ላይ በአምራቾቹ የሚነሱ ቅሬታዎች አሉ፤ በተለይ እንቁላልና ወተት ምርት በስፋት ቢመረቱም የገበያ ጉዳይ አሳሳቢ እንደነሆነባቸው ይጠቀሳል፤ በአንፃሩ ደግሞ በተለይ ከተሞች አካባቢ እነዚህ ምርቶች የቅንጦት ምግብ ሆነው ኅብረተሰቡ እንደልቡ እያገኘ አይደለም። እነዚህን ሁኔታዎች ለማጣጣም ምን እየተሰራ ነው?

ዶክተር ፍቅሩ፡- ይህ ችግር የለም አልልም፤ ይህ የሆነባቸው በርካታ ምክንያቶች ግን አሉ። በተለይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ስርነቀል የሆነ ለውጥ ሲመጣ ክፍተት መፈጠሩ አይቀርም። በተለይ ደግሞ የእንስሳት ምርት የሚበላሹ ነገሮች በመሆናቸው ወዲያውኑ ለተጠቃሚዎች መድረስ መቻል አለባቸው። ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው የሌማት ትሩፋት መርሃግሩ ማሳያ ያልነው የዘንድሮ የእንቁላል ምርት ነው። ከሶስት ሚሊዮን ወደ አምስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሲደርስ ገበያውን ማስተሳሳር ካልተቻለ የሚፈጥረው ነገር ይታወቃል። ያም ቢሆን መመገብ ካለብን አንፃር ይህ ምርት በጣም ትንሽ ነው። አንዳንድ ቦታ ላይ ደግሞ እንቁላሉ ተመርቶ ቤት ውስጥ ረጅም ጊዜ በመቀመጡ ችግር ይደርስበታል። ወተትም ከጥሬ ባለፈ እሴት ተጨምሮበት የሚያመርትና ወደ ገበያ የሚያደርሱ አግሮ ኢንደስትሪዎች በዚያው ልክ ሊኖሩን ይገባል።

ከዚህ አንፃር በእንቁላል በኩል እስከአሁን የእሴት መጨመር ስራ ኢትዮጵያ ውስጥ አልተሰራም። ሌላ ሃገር ወደ ዱቄት ተቀይሮ እንቁላሉን ብቻ ሳይሆን ዱቄቱም በብዙ መልኩ ጥቅም ላይ ይውላል። ሌላው ይቅርና የቀዝቃዛ ማስቀመጫ ስርዓት መፍጠር ያስፈልጋል። በዝቅተኛ ሙቀት ከተቀመጠ እስከ ስድስት ወር ሊያገለግል የሚችልበት እድል አለ። እነዚህን መሰረተ ልማቶች መዘርጋት ያስፈልጋል። በወተት በኩልም በተለያዩ መንገዶች እሴት ተጨምሮበት ታሽጎ ረጅም ጊዜ እንዲያገለግል በተለይ ከእኛ ባህል አንፃር በፆም ወቅት እሴት ተጨምሮበት ፆም ሲፈታ ሰው በእርጎ፤ በቂቤና በአይብ መልኩ እንዲመገብ ለማድረግ መሰራት አለበት። በርካታ የወተት ማቀነባበሪያዎች አሉ፤ ግን እየተመረተ ካለው ምርት አንፃር ብዙ መስራት ያስፈልጋል። ከዚህ ቀደም የነበሩት ፋብሪካዎች ወተት አጣን ብለው ቅሬታ ያቀርቡ ነበር፤ አሁን ደግሞ በእነሱና በአምራቹ መካከል የዋጋ አለመግባባት አለ። እነኚህ ነገሮች ሙሉ ለሙሉ መፈታት አለባቸው።

ለምሳሌ ከምባታ ከፍተኛ የወተት ምርት ያለበት ቦታ ነው። እስከ 97 በመቶ ዝርያው የተሻሻለ ከብት ያለበት ቦታ ነው። የዚያ አካባቢ ማኅበረሰብ ዋነኛ ጥያቄ የገበያ ትስስርና ማቀነባባሪያ ጉዳይ ነው። እዚህ ላይ አንደኛ ወተትን ወደገበያ እንዲያቀርቡ የሚያስችላቸውን ማቀዝቃዣ ተሽከርካሪ ገዝተን ሁለት ለኦሮሚያ ሁለት ለአማራ፤ አንድ ለሲዳማ፤ አንድ ለደቡብ፤ አንድ ለማዕከላዊ ኢትዮጵያ ሰጥተናል። ስለዚህ ከንባታ አካባቢ ያለው ጥያቄ መኪና ከመስጠት በተጨማሪ የወተት ማቀነባበሪያ ዘንድሮ ተገንብቷል። ሲዳማ ላይ በጣም በስፋት የወተት ምርት አድጓል፤ በነገራችን ላይ በሌማት ቱሩፋት ምርጥ አፈፃፀም ያለው ሲዳማ ነው። ዛሬ ከሐዋሳ በዚያ ቦቴ መኪና አስር ሺ ሊትር ወተት ወደ አዲስ አበባ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ይመጣል። በተመሳሳይ ከአማራ ክልል ሰሜን ሜጫ ከተባለ ስፍራ በየቀኑ ወተት ይመጣ ነበር።

ስለዚህ ምርትና አግሮ ኢንዱስትሪውን ለማገናኘት ድጋፎች እያደረግን ነው። ግን እኛ እያለምን ያለነው በአጭር ጊዜ በጣም ከፍተኛ ምርት ይመጣል ብለን ነው። በዚያ ልክ ደግሞ እነዚህ እሴት መጨመር የሚያደርጉ ኢንዱስትሪዎች መጨመር አለባቸው። ማኅበራትን አደራጅተን ማምረቱ ብቻ ሳይሆን ወደ አግሮ ኢንዱስትሪ እንዲገቡ ጥረት ማድረግ ይገባል። እሴት መጨመርና የገበያ ትስስር ትልቁ የቤት ስራችን ነው። በፊት ስለምርት ነበር የምናነሳው፤ አምርተን ደግሞ ለገበያ ካልቀረበ እየተመረተ ያለውን ወደኋላ የሚመልስ ስለሆነ እሱን እንደትልቅ ኃላፊነት ወስደን በቀጥታ ስራው ከሚመለከታቸው ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርና ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር ተቀናጅተን አሁን እንደ ችግር የሚነሱትን ነገሮች መፍትሔ መስጠት የግድ ይላል።

አዲስ ዘመን፡- የእንስሳት ሃብቱን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በዓለም ባንክ ድጋፍ በ58 ወረዳዎች ላይ ላለፉት ስድስት ዓመታት ሲተገበር የቆየው ፕሮጀክት የመጀመሪያው ምዕራፍ ተጠናቋል። ለመሆኑ አፈፃፀሙ ምን ይመስላል? የሁለተኛው ምዕራፍ ዝግጅትስ በምን ደረጃ ላይ ነው?

ዶክተር ፍቅሩ፡– ስለሁለተኛ የፕሮጀክቱ ምዕራፍ በመንግስት ደረጃ በይፋ ስልተገለፀ ብዙም መናገር አልችልም፤ በሂደት ላይ ነው። ይህ ፕሮጀክት አንቺም እንዳነሳሽው ላለፉት ስድስት ዓመታት ደጋና ወይና ደጋ ላይ ባሉ 58 ወረዳዎች ላይ ሲተገበር ቆይቷል። በግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በምንሰራው ስራ በርካታ አስተዋፅዎችን አበርክቷል። ለምሳሌ አስቀድሜ ያነሳሁልሽን የወተት መኪና የገዛነው በዚህ ፕሮጀክት አማካኝነት ነው። በ27 ወረዳዎች ላይ ሞዴል የዶሮ መንደር ብለን የዶሮ ማሳደጊያ ተቋማትን አሳድገናል። በዚሁ ፕሮጀክት ወጣቶች እዚያ ላይ ተደራጅተው የአንድ ቀን ጫጩት ይወስዱና እስከ 65 ቀን አሳድገው ቄብ ሲሆኑ ይሸጣሉ። የዓሳ ጫጩት የምናሰራጨው በዚሁ ፕሮጀክት አማካኝነት ሲሆን፣ የዓሳ ማስፈልፈያ ማዕከላትን አርባምንጭ፣ ባቱ፣ ባህርዳር፣ ሰበታና ሃዋሳ ላይ ተገንብተዋል። ዓሳን ለማጥመድ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች እስከ ጀልባ ድረስ ገዝተን አሰራጭተናል፡፡

ዝርያ ማሻሻል ላይ እንዲሁ አስቀድመን ያነሳነው የሊዊኪድ ናይትሮጂን በመንግስት በጀት የሚቻል አይደለም፤ የገዛነው በዚህ ፕሮጀክት ነው። ፆታው የተለየ ኮርማ አባላዘር ስናሰራጭ የነበረውም በዚሁ ፕሮጀክት በተመደበ በጀት ነው። እንደአጠቃላይ አስተዋፅኦው በሃገርም ሆነ በፕሮጀከት ደረጃም ጥሩ የሚባል ነው። ከዚያ ባለፈ ያለፕሮጀክት ወረዳ በወጥነት መሰራት ያለባቸው ስራዎች አሉ። ለምሳሌ በሽታ መቆጣጠር ላይ ደስታ መሰል በጎችና ፍየሎች ላይ የሚከሰት በሽታን ለመከላከል በሃገር ደረጃ ስትራቴጂ ቀርፀን በ2027 ከኢትዮጵያ እናስወግዳለን ብለን ክትባት እየሰጠን ነው፤ ይህንን ስራ የሚደግፈው ፕሮጀክቱ ነው፡፡

ከቴክሎጂ ሽግግርም አንፃር ሆለታ ላይ የዴሪ ማዕከል ብለን እየሰራን ነው። ብዙ ቴክሎጂዎችን ወደ ኢትዮጵያ ሊያስገባ የሚችል ስራ እየተሰራ ነው። እንደ አጠቃላይ በዚህ ፕሮጀክት እየተሰራ ያለው ስራ ከፕሮጀክት ከጊዜያቸው በላይ ዘመን የሚሻገሩ ለሃገር ሃብት ሆነው የሚቀጥሉ ስራዎችን ነው። ለወጣቶች፤ ለሴቶች፤ ለአቅመ ደካሞች ትልቅ አቅምና የስራ እድል የፈጠረ ፕሮጀክት ነው። የጋራ ፍላጎት ኖሯቸው ተደራጅተው የጀመሩ ማኅበራት አሁን ላይ ብዙዎቹ አቅማቸው አድጎ ወደ ሕብረት ስራ ማኅበራት እየደረሱ ነው።

ሁለተኛው ምዕራፍ ሊቀጥል የቻለውና ድጋፍ ያገኘነው በመጀመሪያው ምዕራፍ ባስመዘገብነው ውጤታማ ስራ ነው። ስለዚህ ሁለተኛው ምዕራፍ የነበሩትን መልካም ተሞክሮች ይዘን የምንቀጥልበት፤ ካለፈው ወረዳ ቁጥር የበለጠ ወረዳዎችን ጨምረን የምንሰራበት፤ በጀቱ በእጥፍ የሚሆንበት፤ አሁን ላይ ፈቃድ አግኝተናል፤ ያለነው ሰነድ የማጥራት ስራ ላይ ነው። አብዛኛው ግን ትኩረት የሚያደርገው ቅድም እንደክፍተት ያየናቸውና መስራት አለብን ባልንባቸው ስራዎች ላይ ነው። በተለይም እሴት መጨመርና በከፍተኛ ካፒታልና አቅም የሚሰሩ ስራዎች ላይ ያተኩራል። ጥናቱ ሲጠናቀቅ በይፋ የምናሳውቀው ይሆናል።

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።

ዶክተር ፍቅሩ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ነሐሴ 23 /2016 ዓ.ም

 

Recommended For You