እ.አ.አ. ከ1956 ጀምሮ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው “ቲዩ-95” ሳያርፍ ከ13 ሺህ በላይ ኪሎ ሜትሮችን መጓዝ ይችላል፡፡ “ገዳዩ የኒዩክሌር ቦምብ ጣይ አውሮፕላን” የሚለው የሩሲያውን “ቲዩ-95” ቦምብ ጣይ አውሮፕላን በአጭሩ ይገልጸዋል።
ዩክሬንም ሰሞኑን አውሮፕላኑ ከደቡብ ምዕራብ ሩሲያ ኤግልስ የአየር ማዘዣ ተነስቶ ወደ ግዛቴ ጉዞ ጀምሯል ብላለች። የአየር መቃወሚያ ሥርዓቷ በተጠንቀቅ እንዲጠባበቅ ያዘዘችው ኬቭ፤ ከቦምብ ጣይ አውሮፕላኑ የተወነጨፉ ሚሳኤሎች በሰዓታት ውስጥ ወደ አየር ክልሏ እንደሚደርሱ ጠቁማለች።
አውሮፕላኑ አራት ሞተሮች ያሉት ሲሆን፤ ክሩዝ ሚሳኤሎችና አውዳሚ ቦምቦችን መሸከምና ማስወንጨፍ ይችላል። የአቪየሽን ባለሙያዎች እንደሚሉት “ቲዩ-95” ሶቪየብ ህብረት ከሠራቻቸው ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች ሁሉ ስኬታማው ነው። በተርባይን ሞተር ከሚንቀሳቀሱ ዘመናዊ አውሮፕላኖች ውስጥም ፈር ቀዳጅ ነው።
የሩሲያው “ቲዩ-95” ቦምብ ጣይ አውሮፕላን ዲዛይን የተሠራው በኦስትሪያው የአቪየሽን ተመራማሪ ፈርዲናንድ ብራንድኔር በተመራ ጀርመናውያን መሃንዲሶች ቡድን ነው። 12 ሺህ የፈረስ ጉልበት ያላቸውን የአውሮፕላኑን ተርባይን ሞተሮች የሠሩት ባለሙያዎች በሩሲያ በእስር ላይ ይገኙ የነበሩ ጀርመናውያን ናቸው።
ግዙፉ ቦምብ ጣይ አውሮፕላን የሚሸከመው የጦር መሣሪያ ብቻ ሳይሆን ድምጹም የሚያሸብር ነው፤ በሰማይ ላይ እየበረረ በባህር ሰርጓጅ መርከቦች ውስጥ የሚገኙ ባለሙያዎች ጭምር ይሰሙታል።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ይህን የሰማይ ላይ አሸባሪ እስከ 2040 ድረስ አገልግሎት እየሰጠ እንዲቆይ ማቀዱም ተዘግቧል።
ዘ ናሽናል ኢንተረስት ጋዜጣ እንዳስነበበው ይህ አውሮፕላን ከአሜሪካው “ቢ-52” ቦምብ ጣይ አውሮፕላን ጋር የሚፎካከር ነው። በቀዝቃዛው ጦርነት የተሰጣቸው ተልዕኮ፣ የመጫን አቅምና ለረጅም ዓመታት አገልግሎት መስጠት የሁለቱ ሃያላን ሀገራት ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖችን ያመሳስላቸዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 22 ቀን 2016 ዓ.ም