በሱዳን የውሃ ግድብ ተደርምሶ ከመቶ በላይ ሰዎች ሕይወታቸው አለፈ

በምስራቃዊ ሱዳን የሚገኝ የውሃ ግድብ ተደርምሶ ከአንድ መቶ በላይ ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉ ተገለጸ፡፡ 20 መንደሮችን ባጥለቀለቀው ጎርፍ 200 ሰዎች የደረሰቡት አልታወቀም፡፡

ከፖርት ሱዳን 40 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኝው 25 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ የመያዝ አቅም ባለው አራባት ግድብ አካባቢ የጣለ ከፍተኛ ዝናብ ግድቡ እንዲደረመስ ምክንያት መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

ሰሞኑን በደረሰው አደጋ ሮይተርስ የሟቾች ቁጥር 30 መሆኑን ሲዘግብ ቢቢሲ 60 መሻገሩን አስነብቧል፤ በተጨማሪም 50 ሺህ ሰዎች ይኖሩባቸው የነበሩ መኖሪያቤቶች በጎርፉ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በአካባቢው ይኖሩ የነበሩ ዜጎች አካባቢውን ለቀው በከፍታ ቦታዎች ላይ ሰፍረው ይገኛሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት በ20 መንደሮች ላይ ጉዳት አድርሷል በተባለው አደጋ ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪ ከ150 እስከ 200 የሚደርሱ ሰዎች የደረሱበት አልታወቀም ተብሏል፡፡

በአካባቢው የነፍስ አድን ሥራዎች በመከናወን ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአካባቢውን ባለሥልጣናት ጠቅሶ ባወጣው መረጃ የአደጋው የጉዳት መጠን የታወቀው በግድቡ ምእራብ በኩል በሚገኙ አካባቢዎች ብቻ መሆኑን ገልጾ የግድቡ የምስራቅ አካባቢ በከፍተኛ ውሃ በመሸፈኑ ያደረሰውን ጉዳት ማወቅ አለመቻሉ ተመላክቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት የሱዳን መንግሥት አስተዳደር የመንግሥት ሃላፊዎች እና ዲፕሎማቶች መገኛ ከሆነችው ፖርት ሱዳን በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘው አራባት ግድብ የፖርት ሱዳን ዋነኛ የውሃ ምንጭ ሲሆን የሀገሪቱ ዋነኛ የቀይ ባህር ወደብ የሚገኝበትና በርካታ የርዳታ ቁሳቁሶች የሚተላለፉበት አካባቢ እንደነበር ታውቋል፡፡

በዚህ የተነሳም ፖርት ሱዳንን ጨምሮ በአካባቢው የሚገኙ ከተሞች በመጪዎቹ ቀናት ከፍተኛ የመጠጥ ውሃ እጥረት እንደሚያጋጥማቸው ተመላክቷል።

ሱዳን ባወጣችው መረጃ በዘንድሮው የዝናብ ወቅት በመላ ሀገሪቱ 132 ሰዎች መሞታቸውንና 118 ሺህ ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You