ጥፍር መንቀል፣ በወንድ ብልት ላይ ሁለት ሊትር ውሃ የሞላው ላስቲክ ማንጠልጠል፣ የወንድን የዘር ፍሬ ማምከን፣ በሌሊት ጫካ ወስዶ እርቃን ማሳደርና አፍንጫ ውስጥ የእስክሪፕቶ ቀፎ መክተት፤ መሰል ኢሰብዓዊ ድርጊቶች በዜጎች ላይ ተፈጽመዋል፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ ከሰባት በማያንሱ ስውር የማሰቃያ ስፍራዎች ዜጎች ‘በአምቡላንስ እየተጓጓዙ ኢ- ሰብዓዊ ድርጊት ይፈጸምባቸው እንደነበር ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ለህዝብ ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡
በፖሊስ ጣቢያ፣ በማረሚያ ቤት እና በስውር እስር ቤቶች ውስጥ የነበሩ ተጠርጣሪዎችም በአሌክትሪክ ሾክ የማድረግ፣ ብልትን በፒንሳ የመሳብ፣ ዛፍ ላይ ሰቅሎ ለረጅም ጊዜ የማቆየትና የተለያዩ የስቃይ ተግባራት ይፈጸምባቸው እንደነበር ለመገናኛ ብዙሃን ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች ባለፉት ዓመታት ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና ዕንባ ጠባቂ ተቋም ገለልተኛ ባለመሆናቸው በኢትዮጵያ ዘግናኝ ሰብዓዊ መብት ጥሰት ቢፈጸምም እንኳ ጠንከር ያለ ሪፖርት አቅርበው አያውቁም በሚል ይተቻሉ፡፡
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያትም ሆነ በፀረ ሽብር አዋጁ የተከሰሱ ሰዎች ማሰቃየት እንደተፈጸመባቸውም ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ሳይቀር በሪፖርታቸው በተደጋጋሚ አመልክተዋል። ምንም እንኳን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በተለያየ መልኩ መፈጸማቸውን ተጎጂዎች አቤት ቢሉም እስከ ሚያዝያ ወር 2010 ዓ.ም ድረስ ተገቢ የሆነ ምርመራ ተካሂዶ የድርጊቱ ፈጻሚዎች በተጠያቂነት ወደ ሕግ እንዳልቀረቡ ነዉ የሚታወሰው፤
በአዲስ አበባ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁርና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ አመራር ዶክተር መረራ ጉዲና በኢትዮጵያ ውስጥ በዜጎች ላይ ይፈጸም የነበረውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከናዚ ጀርመን ጋር ያመሳስሉታል፡፡ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከአፄ ኃይለ ስላሴ ጀምሮ ይፈጸም እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በተለይ ከተማሪዎች እንቅስቃሴ ወዲህ ብዙ ተማሪዎች መብታቸውን ስለጠየቁ ብቻ ሰብዓዊ መብታቸው ተገፍፎ ለእስርና ለሞት ተዳርገዋል፡፡
የሰብዓዊ መብት ጥሰቱና አፈናው በደርግ ዘመንም ይበልጥ ተባብሶ መቀጠሉን አውስተዋል፡፡ በተለይ የተማሩና አገሪቱን ይቀይራሉ የተባሉ በርካታ ወጣቶች መጨፍጨፋቸውንና ለስቃይ መዳረጋቸውን ነው የሚወሱት።
በኢህአዴግ የስልጣን ዘመን መጀመሪያ ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ ለትንሽ ጊዜ ቢቀዛቀዝም ብዙም ሳይቆይ አፈናውና ጥሰቱ ተጠናክሮ መቀጠሉን ይናገራሉ፡፡ በተለይ ከምርጫ 1997 ዓ.ም ወዲህ አፈናና የመብት ጥሰቱ በዕቅድና ታስቦበት ይፈጸም ነበር ይላሉ፡፡
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የናዚ ጀርመን መንግሥት በአይሁዳውያን ላይ ግፍና ጭፍጨፋ የፈጸመባቸው ማጎሪያና ማሰቃያ ቤቶች ሙዚየም ሆነዋል፡፡ እነዚህን ሙዚየሞች ለመጎብኝት ዕድሉን ማግኝታቸውን ጠቅሰው፤ ኢህአዴግም ከናዚ ባልተናነሰ መልኩ ሰብዓዊ መብቶችን ይጥስና ሰዎችን ያሰቃይ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ማዕከላዊ በሚባለው የምርመራ ክፍልና ሌሎች በማይታወቁ እስር ቤቶች ውስጥ በዜጎቹ ላይ የሚዘገንን፣ ለማመን የሚከብድና ከኢትዮጵያዊያን ባህል ያፈነገጠ ድርጊት ይፈፅም እንደነበር በማሳያነት ያነሳሉ፡፡፡
እናም አሉ ዶክተሩ፤ ዳግም ይህን ዓይነት ኢሰብዓዊ ድርጊት እንዳይፈጸም በመንግሥት ብዙ ሥራዎች መሠራት አለባቸው፡፡ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት በዘላቂነት እንዲከበር መሠራት ከሚገባቸው ጉዳዮች መካከል የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንንና የምርጫ ቦርድን እንደገና ማደራጀት፣ የፍርድ ቤቶችን ነፃነት ማክበር፣ የጸጥታ ተቋማትን ገለልተኛ ማድረግ የሚሏቸው ይገኙበታል፡፡
በምርጫ ስልጣን የሚይዝና ለኢትዮጵያ ህዝብ ተጠያቂ የሆነ መንግሥት መፍጠር አስፋላጊ ነው የሚሉት ዶክተር መረራ፤ ይህን ለማሳካትም መንግሥት የምርጫ ህጎችን የማሻሻልና የምርጫ ቦርድን አመራር የመቀየር ሥራ ጀምሯል፡፡ ሌላው የፀረ ሽብር ህጉም ቢሆን እኔን ጨምሮ ብዙ ሰዎች የተከሰሱበትና በዚህ ሰበብ ግፍ የተፈጸመበት ነው፡፡ ይህን ህግ ለማሻሻል ሥራው ተጀምሯል፡፡ ይህ ጥሩ ጅምር ቢሆንም ከዳር ማድረስ ተገቢ ነው ባይ ናቸው፡፡
የፀረ ሽብር ህጉ ብቻ ሳይሆን በተለይ ከምርጫ 97 ወዲህ ለአፈና ተብለው የጸደቁ ብዙ ህጎች አሉ፡፡ መንግሥት እነዚህ ህጎች ሙሉ በሙሉ የሚሻሻሉበትን መንገድ መፍጠር አለበት፡፡
እንዲሁም የዴሞክራሲ ተቋማት የሚባሉትን፤ ለምሳሌ ዕንባ ጠባቂ ተቋምና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መንግሥት ቢያፈርሳቸው ይሻላል ይላሉ፡፡
ምክንያቱም ተቋማቱ የተፈጠሩት የኢህአዴግን ወንጀሎች ለመደበቅ እንጂ፤ የዜጎችን መብቶች ለማስከበር አይደለም፤ ከምርጫ ቦርድ ቀጥሎ የኢትዮጵያ ህዝብ በጣም የሚጠላቸውና ኢህአዴግን ለማገልገል፣ ለአፈና ስርዓቱ ሽፋን ለመስጠት የተፈጠሩ ናቸው፡፡ እናም መንግሥት እነዚህን ተቋማት እንደገና ማዋቀር ይኖርበታል፡፡
የምርጫ ቦርዱን ከላይ እስከ ታች ድረስ እንደገና የማዋቀር፣ የፍትህ ስርዓቱን ችሎታ ባላቸውና ህግን መሰረት አድርገው በሚሠሩ ባለሙያዎች ማወቀሩ፣ አፋኝ ህጎችን እንዲሻሻሉ ማድረግ፤ በአጠቃላይ መንግሥት ደግሞ ዜጎችን ለማገልግል እንጂ ለማፈን እንዳልተፈጠረ ማሳየት የሚያስችል የሲቨል ሰርቪስ ሪፎርም ማካሄድ አለበት፡፡
ሌላው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የነበረው የጸጥታ አካል ገለልተኛ ሆኖ ህዝቡን ማገልገል ያልቻለ፣ እንዲያውም የአንድ ገዥ ፓርቲ ጉዳይ አስፈጻሚ ሆኖ ሲሠራ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ትሄድ፤ አትሄድ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ይቋቋም አይቋቋም የሚለው ወሳኙ እሱ ነው፡፡ የደህንነት ተቋሙም ቢሆን እስከአሁን በነበረው ሂደት ራሱ ያሠራል፣ ይመረምራል እናም ፍርድ ቤት ያቀርባል፡፡ እንዲሁም ለፖሊሶች ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡
ስለዚህ የመካላከያ ሠራዊቱንና የደህንነት አካሉን ገለልተኛ ሆኖ ሁሉንም ህዝብ በሚያገለግል መልኩ እንደገና ማዋቀሩ አስፋላጊ ነው፡፡ የብሄር ብሄረሰቦች ስብጥሩም መስተካከል ይኖርበታል፡፡ በተለይ የደህንነት አካሉ ከማሰርና ከምርመራ ሥራ ማውጣት አለበት፡፡ እርግጥ ነው የደህንነት ኃላፊው የለውጥ ሥራ እንደጀመሩ ሲናገሩ ሰምቻለሁ፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያምንበት የደህንነት ተቋም መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ሲሉ ዶክተር መረራ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህገ – መንግሥት አንድ ሦስተኛው ክፍል ስለ ሰባዓዊ መብቶችና ነፃነቶች የሚዘረዝር ነው። ይኸው ህገ መንግሥትም ሁሉንም ዓይነት የሰብዓዊ መብት ዘርፎች ማለትም የሲቪልና የፖለቲካ፥ የኢኮኖሚ፥ የማህበራዊና የባህል መብቶች እንዲሁም፤ የአካባቢ ደህንነትና የልማት መብቶችን አጠቃልሎ የያዘ ነው። በተጨማሪም በአንቀፅ 9(4) መሰረት ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶችም የሀገሪቱ ህግ አካል እንደሆኑ የመሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ትርጉምም ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቻው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ህግጋት፥ ስምምነቶችና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሰነዶችና መርሆዎች ጋር በተጣጣመ መልኩ የሚተረጎሙ መሆኑን ህገ መንግሥቱ በግልጽ አስቀምጧል።
በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 18 ኢሰብዓዊ አያያዝ ስለመከልከሉ ሲገልጽ ማንኛውም ሰው ጭካኔ ከተሞላበት፣ ኢሰብዓዊ ከሆነ ወይም ክብሩን ከሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት የመጠበቅ መብት አለው፤ ቢልም በተለያዩ ማረሚያ ቤቶችና የምርምራ ክፍሎች ዜጎች ኢ ሰብዓዊ ድርጊት ሲፈጸምባቸው ቆይቷል፡፡
በዚሁ ህገ መንግሥት አንቀጽ 19 የተያዙ ሰዎችን መብት በተመለከተም፤ የተያዙ ሰዎች በአርባ ስምንት ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት የመቅረብ መብት አላቸው፤ ቢልም ለረጅም ዓመታት ፍርድ ቤት የማይቀርቡበት ሁኔታ ይታያል፡፡ እስከአሁን ድረስም የት እንዳሉ የማይታወቁ በርካቶች ናቸው፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ ከትናንት በስቲያ የዓለም የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ የፀደቀበት 70ኛ ዓመት በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ሲከበር እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለሰብዓዊ መብት መከበር ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች ነው፡፡ መንግሥት በፍትህ ሥርዓቱ ላይ ከፍተኛ ሊባል የሚችል ለውጥ እያደረገ ነው፡፡ የፀረ ሽብርና የመገናኛ ብዙሃን አዋጆችን ጨምሮ የተለያዩ ሕጎች እንዲሻሻሉ ሥራዎች ተጀምረዋል፡፡
በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን መንግሥት መፍታቱንም አፈ ጉባኤው አውስተው፦
ስልጣናቸውን ከለላ በማድረግ በእስረኞች ላይ የመብት ጥሰት ፈፅመዋል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦች ደግሞ ለህግ እየቀረቡ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ዕርምጃዎች መንግሥት ለዜጎች ሰብዓዊ መብት መከበር ያለውን ቁርጠኝነት ያረጋግጣሉ ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በሱማሌ ክልል ዜጎች በክልሉ መንግሥት በተፈጸመባቸው አሰቃቂ ድርጊት በጠራራ ፀሐይ ይሰቃዩና ይገደሉ እንደነበር ደግሞ የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሙስጠፋ ማህሙድ በተለያዩ ቦታዎች ብዙ ሰዎች ተገድለው በጅምላ የተቀበሩባቸው ጉድጓዶች መገኘታቸውን አዲስ ዘመን ጋዝጣ ቃለ መጠይቅ ባደረገላቸው ወቅት በአብነት ጠቅሰዋል፡፡ ይህ ጉዳይ ተጣርቶም ድርጊቱን የፈጸሙ ባለስልጣናት ለህግ የሚቀርቡ መሆኑን ነግረውናል፡፡
የህገ መንግሥት አባት የሚባሉት ዶክተር ፋሲል ናሆም በኢትዮጵያ በዜጎች ላይ ሲፈጸም የነበረው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ኢ-ህገ መንግሥታዊና ኢ- ሰብዓዊ ነው፡፡ ከኢትዮጵያዊነት ባህልና አስተሳሰብ ያፈነገጠም ጭምር ነው፡፡ ይህ ድርጊት ወንጀል ብቻ ሳይሆን እንሰሳነትም ነው፡፡ ሰብዓዊነት የጎደለው ተግባር በማንኛውም መንግሥት ሲፈጸም ፈጽሞ ተቀባይነት ሊያገኝ አይችልም ሲሉ ይገልጹታል፡፡
እናም፤ በአገራችን ሲፈጸም የነበረው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከሃይማኖትም ሆነ ከህገ መንግሥት አንጻር መወገዝ ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ምን ይምሰል ለሚለው እንደገና አይቶ በዚህ መልክ ቢሻሻል ቢባል ችግር የለውም፡፡ ፍትሕ አስጣጥን በተመለከተ ብዙ ይቀረናል፡፡ ወደፊት ደግሞ ይህ ዓይነቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይፈጸም የሚያስፈልገው ሥራ ሁሉ መሠራት አለበት የሚል ሃሳብ አላቸው፡፡
የህገ መንግሥቱ መሰረታዊ ትምህርት ሰብዓዊ መብት ማክበር ነው፤ የሚሉት ዶክተሩ ህገ መንግሥቱን የሚያከብረው ደግሞ ህዝብም መንግሥትም ነው፡፡ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ጭምር፤ ከዚህ በመነሳት ህገ መንግሥቱን ተከትለው የሚወጡ የተለያዩ ህጎችን፣ ደንቦችንና መመሪያዎችን ሥራ ላይ ማዋል ተገቢ ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሚደረገው የግለሰብና የህዝብ ነፃነትና ሰብዓዊ መብት ለማክበር፣ ለማስከበርም ጭምር ነው፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስልጣን እንደተጠበቀ ሆኖ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ማቋቋሙ ከሰብዓዊ መብት ማስከበር አንፃር ዛሬ በደረስንበት ደረጃ ላይ ሆኖ መፈተሹ ጠቃሚ ነው የሚል እምነት አላቸው፡፡
ሌላው አሉ ዶክተር ፋሲል፤ ቀዳሚ ትኩረት ተሰጥቶት መሠራት ያለበት ትምህርት ላይ ነው፡፡ መንግሥት ከሕፃናት መዋያ ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ በስነ ምግባር የበለጸገና የሰዎችን መብት የሚያከብር ዜጋ በማነጽ ረገድ ትልቅ የቤት ሥራ ይጠብቀዋል፡፡ በሰዎች ላይ ኢሰብዓዊ ድርጊት መፈጸም ወንጀል ቢሆንም ይህን እያወቀ የሚፈጽም ካለ መቀጣት አለበት፡፡ ዋናው ግን ማስተማሩ ይቀድማል፡፡
‹‹ሰብዓዊ መብት ጥሷልና እንቅጣው የሚለው ጉዳይ የመጨረሻው ዕርምጃ ነው›› የሚሉት ዶክተር ፋሲል፤ ከሕፃናት አስተዳደግ ጀምሮ ስነ ምግባር ያለው፣ የሰዎችን ሰብዓዊ መብት የሚያከብር፣ ለህግ የሚገዛና ለእውነት እንጂ ለገንዘብ የማይገዛ ዜጋ ለማፍራት ቤተሰብ፣ ህብረተሰቡ፣ የሃይማኖት አባቶችና መንግሥትም አስተሳብ የመቀየር ሥራ ሊሠሩ ይገባል ነው የሚሉት፤
እንደ ዶክተር ፋሲል ገለጻ፤ የሃይማኖት አባቶችም ወንድምህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደደው የሚለውን በተግባር ጭምር ማስተማር አለባቸው፡፡ ህብረተሰቡም ቢሆን ለልጆች መገፋፋትን ሳይሆን ፍቅርን ሰጥቶ ማሳደግ ይኖርበታል፡፡ መንግሥትም ዜጎች በመልካም ስነ ምግባር ታንጸውና ሰብዓዊ መብት ማከበርን እንደ ባህል ቆጥረው እንዲራመዱ የሚያደርግ ስርዓተ ትምህርት ቀርጾ መተግበር ይጠበቅበታል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከወጡበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች ከእስር ተፈትተዋል። እንዲሁም በእርሳቸው የስልጣን ዘመን መጀመሪያ ላይም በሱዳን፣ በኬንያ እንዲሁም በሳውዲ አረብያ በእስር ሆነው ሲሰቃዩ የነበሩ በርካታ ኢትዮጵያዊያን እንዲለቀቁ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።
አዲስ ዘመን ታህሣሥ 3/2011
ጌትነት ምህረቴ