ኢትዮጵያ በዘመቻ ችግኝ እየተከለች ትገኛለች። የችግኝ ተከላው የሰዎችን ጉልበት እና ብዙ ገንዘብ ሊወስድ እንደሚችል አያጠራጥርም። ሰሞኑን የተካሔደውን የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባካሔዱት ንግግር፤ በአማካኝ አንድ ችግኝ ለማዘጋጀት አንድ ዶላር ይፈጃል ብለዋል። እስከ አሁን የዘንድሮውን ጨምሮ ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ ከ40 ቢሊየን በላይ ችግኞች ተተክለዋል። ይህ ሁሉ ችግኝ ሲተከል ችግኝ ከማዘጋጀት ጀምሮ ጉድ ጓድ ቁፋሮን እና ተከላውን አካቶ ምን ያህል ትጋትን እንደሚጠይቅ መገመቱ ቀላል ነው።
ለችግኝ እና ለችግኝ ተከላ ይህ ሁሉ ጥረት ከተደረገ በኋላ፤ የሚገኘው ጠቀሜታ ምን ያህል ነው? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው። እኛም ችግኝ ተከላው በእርግጥ ምን ያህል ጠቃሚ ነው? ስንል የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አስተባባሪ የቴክኒክ ኮሚቴ አባላትን ጠይቀናል።
በኢትዮጵያ ደን ልማት ሚኒስቴር የችግኝ ተከላ ፕሮግራም አስተባባሪ ይተብቱ ሞገስ (ዶ/ር) እንደሚናገሩት፤ ደን ሊገለፁ የሚችሉ ብዙ ጥቅሞች አሉት። ደን የለበሰች አገር የተሻለ ብልፅግና ይኖራታል። ዝናብ እንዲዘንብ፤ ወንዞች በቂ ውሃ እንዲኖራቸው፤ የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል፤ የወንዞች ፍሰትን ለመቆጣጠር የሚረዳ ሲሆን፤ ለብዝሃ ሕይወት የሚያገለግል ነው።
ዋናው ነገር ግን ከኢትዮጵያ አንፃር ሲታይ፤ ከደን መጨፍጨፍ ታሪክ ወደ ደን አልሚነት ታሪክን መቀየር ትልቅ ቁም ነገር ነው። በዚህ በኩል ሕዝቡ ግንዛቤ እንዲይዝ ማድረግ ተችሏል። በእርግጥ ዛፎች በተተከሉ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ጥቅም አይሠጡም ማለት አይቻልም። አንዳንዶች ደግሞ በአምስት እና በአስር ዓመት ውስጥ ከፍተኛ ጥቅም ሊሰጡ ይችላሉ። አንዳንዶች ግን ትልቅ ጥቅም ለመስጠት ስልሳ ዓመት ሊፈጁ ይችላሉ።
እንደ ዶክተር ይተብቱ ገለፃ፤ ይህ አሁን ያለው መነሳሳት የኢትዮጵያ ሕዝብ ለደን ያለውን አመለካከት ከፍ አድርጎለታል። ሕዝቡ አመለካከቱ በማደጉ ወጥቶ እየተከለ ነው። አሁን ደግሞ የሚተክለውን ያህል ጥበቃው ላይም ትኩረት ከተደረገ ውጤት የማይገኝበት ምክንያት የለም። ነገር ግን ይሔ ነው የሚባል በአገር አቀፍ ደረጃ የተገኘው ጥቅም ተጠንቶ የተጠናቀረ መረጃ ሊኖር ይገባል።
የኢትዮጵያ አብዛኛው ተራራ በደን መሸፈን አለበት። ሆኖም ሽፋኑ ከ23 በመቶ አልፎ አያውቅም ነበር። የኢትዮጵያ ምድር 50 በመቶ በደን የተሸፈነ መሆን አለበት። ስለዚህ በሰፊው ችግኝ ተከላ መጀመሩ ጥሩ ነው። ይህ ለአሥር እና ለአሥራ አምስት ዓመት ቢቀጥል ምናልባትም የኢትዮጵያ የደን ሽፋን የሚፈለግበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ይቻላል። በዛ ምክንያት የሚመረተው ምርት ከፍ የሚልበት፤ የአካባቢ ጥበቃም የሚጠናከርበት ሁኔታ ይፈጠራል የሚል እምነት እንዳላቸው ይናገራሉ።
ይተብቱ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ በዝርዝር ሲታይ ደግሞ የእንጨት ውጤቶችን ለማምረት እና የአገር ኢኮኖሚን ለመደገፍም የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ነው። የመኖ እና የፍራፍሬ ችግኞች ተተክለው በአጭር ጊዜ የሚታይ ጥቅም ይሠጣሉ። አቮካዶ እና ሌሎችም ማር ማነብን ጨምሮ ከወዲሁ እየተገኙ ያሉ ጥቅሞች አሉ። በተጨማሪ ከችግኝ ተከላው ጋር በተያያዘ እየተገኘ ባለ ውጤት ላይ በመመርኮዝ ወደ 25 የሚሆኑ የገጠር ልማት ፓኬጆች አሉ። አንድ ሰው ወደ ደቡብ ምዕራብ ሔዶ ቢያይ ተዓምር እየተሠራ መሆኑን ማረጋገጥ ይችላል። በከብት እርባታ፣ በንብ ማነብ ማለትም በማር፣ በቡና እና በቅመማ ቅመም በተለያየ መልኩ ከሕብረተሰቡ ጋር በመስራት የዜጎች ኑሮ እየተቀየረ ነው ይላሉ።
አሳታፊ የደን አስተዳደር ሥርዓትን በመተግበር ደን በፍቅር እንዲጠበቅ ማድረግ ተችሏል። በዚህም አካባቢው እየተለወጠ ነው የሚሉት ይተብቱ (ዶ/ር)፤ የችግኝ ተከላ ሲነሳ መኖ፣ ፍራፍሬ እና ዛፎች በውስን ጊዜ የተለያየ ጥቅም የሚያስገኙ ቢሆኑም፤ ከአካባቢ ጥበቃ አንፃር የሚታይ ውጤት እንዲመጣ ግን ከ10 እስከ 20 ዓመት መጠበቅ የግድ ነው ይላሉ። ነገር ግን ተከላው የሚያስገኘው ጥቅም ተስፋ ነው ብለን ብንል እንኳ አሁን የተተከለው ደን በውስጡ የያዘው ሃብት ከፍተኛ መሆኑን መካድ እንደማይቻል ይናገራሉ።
ይተብቱ (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ አሁንም ማግኘት ከሚቻለው አንፃር በቂ ጥቅም እየተገኘ ነው የሚል እምነት እንደሌላቸው በመጠቆም፤ መበርታት ቢቻል አሁንም ካለው ዛፍ ከግማሽ ትሪሊየን ያላነሰ ገቢ ማግኘት ይቻል እንደነበር ያብራራሉ። እስከ አሁን በግብርና የሚመረተው የሚሸመት እና የሚበላ ነው። ፍራፍሬ ይበላል፤ ከተረፈ ወደ ውጪ ይላካል። መኖውም የከብት ልማቱን ያሻሽለዋል። በሌላ በኩል በአብዛኛው አሁን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ እንጨት የሚውለው ለማገዶነት ወይም ለቤት ሥራ እንጂ ፋብሪካ ገብቶ ጣውላ እና ኤም ዲ ኤፍ ቦርድ፣ ቤኒየር ፕላይውድ እየተመረተ አለመሆኑን አስታውሰዋል። እንጨትን ኢንዱስትሪው ውስጥ በስፋት በማስገባት በስፋት መጠቀም ቢጀመር ግማሽ ትሪሊየን ማግኘት ይቻላል። የደን እንጨት የኢንደስትሪ ገበያ ላይ የሚንቀሳቀስ በመሆኑ ትራንስፎርም ማድረግ የሚያስችል አቅም ያለው ዘርፍ መሆኑን ማወቅ ይገባል ብለዋል።
‹‹ አሁን ላይ እያገኘን ያለነው ከ40 ቢሊየን የዘለለ አይደለም። ይህንን በ10 እጥፍ ማሳደግ ይቻላል። ›› ካሉ በኋላ፤ ለዚህ መፍትሔው ልክ እንደ አረንጓዴ ልማት የደን ሃብት የምርት እና የአጠቃቀም ንቅናቄ ተጀምሮ ወደ ሥራ ቢገባ ከደን የሚገኘው ጥቅም ቀላል አይሆንም ብለዋል። በተለይ ለውጪ ምንዛሪ የሚኖረው ጠቀሜታም ከፍተኛ እንደሚሆን አስረድተዋል። ይተብቱ (ዶ/ር) ሃሳባቸውን በዝርዝር ሲያስረዱ፤ ግማሽ ትሪሊየን ብር ማለት አስር ቢሊየን ዶላር ነው። ያንን ማግኘት ባይቻል እንኳ አምስት ቢሊየን ዶላር ማግኘት ይቻላል። ይህንን ማግኘት እየተቻለ አንድ እና ሁለት ቢሊየን ዶላር መለመን አይገባም ብለዋል።
ከደን የሚገኘውን ጥቅም የበለጠ ለማሳደግ ዘርፉን ከኢንደስትሪ ጋር ማስተሳሰር እና የተጠናከረ ድጋፍ ማድረግ፤ ገብቶ መስራት እንዲሁም ሠው ማሰልጠን ይፈልጋል ያሉት አደፍርስ (ዶ/ር)፤ ግብርና 200 እና 300 ሚሊየን ኩንታል ቢያመርትም የሚያስገኘው ገቢ ከሁለት ትሪሊየን አያልፍም። እዛ ላይ የግብርናን አንድ አራተኛ ያልታሰበ ገቢ ወደ ኢኮኖሚው ቢገባ አገርን የሚደግፍበት ሁኔታ ብቻ ሳይሆን የሚፈጠረው የሥራ ዕድልም ከፍተኛ እንደሚሆንም ተናግረዋል። ስለዚህ ችግኝ ከመትከል ጎን ለጎን የደን አጠቃቀም በአግባቡ እየተመራ መሔድ ይኖርበታል። ይህ ከሆነ በሶስት እና በአራት ዓመት ውስጥ ግማሽ ትሪሊየን ብር ማግኘት እንደቀላል የሚታይ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ አረንጓዴ አሻራን በመተግበር የኢትዮጵያን መሬት በማዳን አገሪቷን ዛፍ ያለባት፤ ዝናብ በበቂ መጠን የምታገኝ፤ በርሃማነት የሌለባት፤ ገበሬው ዘርቶ የሚያጭድባት እንድትሆን እንሥራ በማለት እየተሠራ ነው። ስለዚህ ችግኝ ተከላው ድርቅ ቢመጣ ሕዝቡ ድርቅን የሚቋቋምበት እና የማይሰደድበት እንዲሁም ሕዝቡ በመሬቱ የሚጠቀምበት ሁኔታ ይፈጠራል።
ሌላኛው ፋይዳ አሁን የተተከሉት ችግኞች ከተተከሉበት ቀን ጀምሮ በካይ ጋዝን እያመቁ ነው። በሂደት አምስት እና አስር ዓመት ሲሞላቸው እና ትልልቅ ሲሆኑ፤ መሬቱ በአረንጓዴ ሲሸፈን ብዙ ካርበን ማለትም ዓለም ላይ ሙቀት ያመጣውን ካርበን ወይም በካይ ጋዝ ያምቃሉ። ይህ ትልቅ አስተዋፅኦ ነው።
እንደ አደፍርስ (ዶ/ር) ገለፃ፤ በአረንጓዴ አሻራ ብዝአሕይወት ይጠበቃል። የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ከፍ ይላል። የደን ሽፋን ከፍ ሲል ብዙ ዝናብ ይዘንባል። ብዙ ዝናብ ኢትዮጵያ ውስጥ ከዘነበ የውሃ እጥረት ያለባቸው በኢትዮጵያ ዙሪያ ያሉ የታችኛው አገሮች በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አማካኝነት ውሃ ያገኛሉ። ስለዚህ ለጎረቤቶች ውሃ የሚላክበትን፤ ለዓለም ደግሞ ብክለት እና ሙቀት የሚቀንስበትን፤ የተበላሹ የስነምህዳር ግልጋሎቶች የሚሻሻሉበት እንዲሁም ምርትና ምርታማነትን የሚጨምርበት ሁኔታ ይፈጠራል።
ኢትዮጵያ ስታመርት የምታመርተው ለጎረቤቶቿም ጭምር ነው። ብዝአ ሕይወት ለኢትዮጵያውያን ብቻ አይደለም፤ ለግብፅም ለኬኒያም ለሁሉም ያገለግላል። እነዚህ የሚተከሉት ችግኞች ውስጥ መድሃኒት ይኖራል። ለአንድ አደገኛ በሽታ መድሃኒት የሚሆን ዕፅዋት መገኘት ይችላል በማለት የተናገሩት፤ አደፍርስ (ዶ/ር) ሌላው አውሮፓዎች በተደጋጋሚ የሚያነሱት ስጋት በስደተኞች ጉዳይ ላይ ያተኮረ መሆኑን በማስታወስ፤ ደንን ማልማት የሚሰደዱ ወጣቶች ከመሄድ ይልቅ በአገራቸው እንዲሠሩ እና ውጤታማ እንዲሆኑ ያስችላል ብለዋል።
የአረንጓዴ ልማት ሥራ ወጣቶች ለስደት የሚገፋቸው ነገር እንዲቀንስ ያግዛል። ያሉት አደፍርስ (ዶ/ር)፤ የችግኝ ጣቢያ ሲቋቋም ወጣቶች ሥራ ያገኛሉ። ምርትና ምርታማነትን እየተሻሻለ ሲመጣ የተወሰነው ወጣት ራሱን ይቀይራል። ረሃብን ችግርን ለመቀነስ፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል፤ የበረሃማነት መስፋፋትን ለመቀነስ ያግዛል። ኢትዮጵያ የሔደችበትን መንገድ ተከትላ ኬኒያም እንደ ኢትዮጵያ በስፋት ባይሆንም መትከል ጀምራለች። ይህ በራሱ ለዓለም እየተበረከተ ያለ ጥቅም ነው። በአጠቃላይ የችግኝ ተከላው በተለያየ መልኩ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 21/2016 ዓ.ም