እሥራኤል በሊባኖስ የሚገኙ የሄዝቦላ ዒላማዎችን በአየር መደብደብ ጀመረች

የእሥራኤል መንግሥት የሀገሪቱ አየር ኃይል ተዋጊ ጄቶች በሊባኖስ በሚገኙ የሄዝቦላ ዒላማዎችን እየደበደቡ መሆኑን አስታወቀ። በሌላ በኩል ሄዝቦላ የእሥራኤል ወታደራዊ ጣቢያዎችን ዒላማ ያደረጉ በመቶች የሚቆጠሩ ሮኬቶችን ወደ ሰሜናዊ እሥራኤል ማስወንጨፉን ጠቅሷል።

የእሥራኤል መከላከያ ሚኒስትር ትናንት ባወጣው መግለጫ ወደ እሥራኤል ሚሳኤሎችን እና ሮኬቶችን ለመተኮስ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መታየታቸውን ተከትሎ እራስን የመከላከል እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል ብሏል። “ይህን ስጋት ለመቀልበስ በተደረገ እራስን የመከላከል ተግባር አይዲኤፍ (የእሥራኤል መከላከያ ኃይል) አሸባሪዎችን ዒላማ ያደረገ ጥቃት እየፈጸመ ይገኛል” ሲሉ የእሥራኤል ጦር ቃል አቀባይ ዳንኤል ሃጋሪ ተናግረዋል።

የእሥራኤል መንግሥት ጥቃቱን መውሰድ ከመጀመሩ በፊት ሠላማዊ ሰዎች ሄዝቦላ ከሚገኝባቸው አካባቢዎች እንዲርቁ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል ብሏል። በኢራን የሚደገፈው የሺዓ ሙስሊም ቡድን የሆነው ሄዝቦላ በበኩሉ መጠነ ሰፊ የሆነ የድሮን ጥቃት እሥራኤል ላይ መክፈቱን አስታውቋል። እሥራኤል ከሳምንታት በፊት የቡድኑን ከፍተኛ የጦር መኮንን መግደሏን ተከትሎ ሄዝቦላ የበቀል እርምጃ እንደሚወስድ ሲዝት መቆየቱ ይታወሳል።

ከዚህ በተጨማሪ እሥራኤል የሐማስ የፖለቲካ ቢሮ ኃላፊ የሆኑትን እስማኤል ሃኒዬን በኢራን መዲና ቴህራን መግደሏን ተከትሎ በመካከለኛው ምሥራቅ ሰፊ የሆነ ጦርነት መቀስቀሱ አይቀሬ ነው ሲባል ቆይቷል። የሄዝቦላን የድሮን ጥቃቶችን ተከትሎ እሁድ ንጋት ላይ በሰሜናዊ እሥራኤል በሚገኙ አካባቢዎች የማስጠንቀቂያ ደውሎች ሲሰሙ ነበር።

የእሥራኤል መከላከያ ኃይል ወደ 100 የሚጠጉ የጦር ጀቶቹ እየተሳፉ በሚገኙበት የአየር ድብደባ በ40 ቦታዎች የነበሩ በሺዎቹ የሚቆጠሩ የሄዝቦላ የሮኬት ማስወንጨፊያዎችን ማውደሙን አስታውቋል። የእሥራኤል የጦር ጀቶች የሄዝቦላን ሰው አልባ አውሮፕላን አየር ላይ ሲያወድሙ የሚያሳዩ ምስሎች ጭምር እየወጡ ነው። ሁለቱ ኃይሎች የወሰዷቸውን ወታደራዊ እርምጃዎች ተከትሎ በሰው እና በንብረት ላይ የደረሰው የጉዳት መጠን እስካሁን ድረስ አልታወቀም።

እንደ የእሥራኤል መከላከያ ኃይል ከሆነ ሄዝቦላ ከ150 በላይ ተተኳሾችን ከሊባኖስ ድንበር ሆኖ ወደ እሥራኤል ተኩሷል። የጦሩ ቃል አቀባይ ሃጋሪ እንዳሉት በምላሹ የእሥራኤል አየር ኃይል በደቡባዊ ሊባኖስ በሚገኙ ዒላማዎች ላይ ድበደባዎችን እየፈጸመ ይገኛል። ሄዝቦላ እስካሁን ድረስ 11 የእሥራኤል ወታደራዊ ጣቢያዎችን ዒላማ ያደረጉ 320 ሮኬቶችን ማስወንጨፉን አስታውቋል።

የእሥራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ የደኅንነት ካቢኔያቸውን አስቸኳይ ስብሰባ መጥራታቸውን አስታውቀዋል የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ኔታኒያሁ እና የመከላከያ ሚኒስትሩ ዮአቭ ጋላንት “ሁኔታዎችን በቴል አቪቭ ሆነው እየመሩ ነው” ብሏል። ከእሥራኤል እና ሐማስ ጦርነት በኋላ በመካከለኛው ምስራቅ ከፍተኛ ውጥረት መከሰቱን ተከትሎ እሥራኤል እና ሊባኖስ የተኩስ ልውውጥ ሲያደርጉ ቆይተዋል። ምዕራባውያን እና በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ ሀገራት ቀጣናውን ወደለየት ጦርነት ሊያስገባ ከሚችል እንቅስቃሴ እሥራኤል እና ሄዝቦላ እንዲታቀቡ ሲጠይቁ ቆይተዋል። የእሥራኤል እና የሄዝቦላ ጦርነት አይቀሬ ነው መባሉን ተከትሎ እንደ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ካናዳ፣ ጀርመን እና ፈረንሳይ ያሉ ምዕራባውያን ሀገራት ዜጎቻቸውን ከሊባኖስ ሲያስወጡ ቆይተዋል።

አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You