ቤት ሊዘርፍ የገባው ጣሊያናዊ ሌባ ቁጭ ብሎ መጽሐፍ ሲያነብ ተያዘ

ቤት ሊዘርፍ የገባው ጣሊያናዊ ዘራፊ ስለ ግሪክ ሚቶሎጂ [አፈ-ታሪክ] የሚተርክ መፅሐፍ ቁጭ ብሎ ሲያነብ መያዙ ተሰምቷል። የጣሊያን መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት የ38 ዓመቱ ዘራፊ በጣሊያኗ መዲና ወደሚገኝ አንድ አፓርትማ በበረንዳ ተንጠልጥሎ ነበር የገባው። ግለሰቡ ሊዘርፍ ወዳሰብው ቤት ከገባ በኋላ ከአልጋው አጠገብ ስለ ሆሜር ኢሊያድ የሚተርክ መፅሐፍ ሲያገኝ ቁጭ ብሎ ማንበብ ይጀምራል። የ71 ዓመቱ የቤቱ ባለቤት ከእንቅልፋቸው ነቅተው ሲመለከቱ ሌባው በመፅሐፉ ተመስጦ ሲያነብ ያገኙታል። የሌባው በቁጥጥር ሥር መዋል በመገናኛ ብዙኃን ከተነገረ በኋላ የመጽሐፉ ጸሐፊ ሌባው “አንብቦ እንዲጨርስ” አንድ ዕትም እንደሚልክለት ለመገናኛ ብዙኃን ተናግሯል።

መጽሐፍ ሲያነብ በቤቱ ባለቤት ዕይታ ውስጥ የገባው ሌባ ደንግጦ በገባበት በረንዳ በኩል ለማምለጥ ሲሞክር ነበር በቁጥጥር ሥር የዋለው። በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ በበረንዳ ተንጥልጥሎ የገባው የሚያውቀውን ሰው ለማግኘት እንደሆነ ለፖሊስ ተናግሯል።

“እኔ የማውቀው የእንግዳ ማረፊያ ቤት [ቤድ ኤንድ ብሬክፋስት] ውስጥ የገባሁ መስሎኝ ነው። መጽሐፉን ሳገኘው ጊዜ ማንበብ ጀመርኩ” ሲል ለፖሊስ ቃሉን ሰጥቷል ‘ዘ ጋድስ አት ሲክስ ኦክሎክ’ የተባለው መጽሐፍ ፀሐፊ የሆነው ጂዮቫኒ ኑቺ፤ ኢል ሜሳጌሮ ለተሰኘው ጣቢያ “የሚገርም ነው” ሲል ተናግሯል። “እጅ ከፍንጅ የተያዘውን ሰው አግኝቼ አንድ ዕትም ልሰጠው እፈልጋለሁ። ምክንያቱም በቁጥጥር ስር የዋለው እያነበበ ስለሆነ ንባቡን እንዲያጠናቅቅ እፈልጋለሁ” ብሏል።

“በጣም የሚገርም ነው። ሰብዓዊነትንም የሚያሳይ ነው” ብሏል ጸሐፊው። ሌባው በቁጥጥር ሥር ከመዋሉ በፊት ከሌላ ቤት የዘረፈው ነው የተባለ በጣም ውድ የሚባሉ ልብሶችን የያዘ ቦርሳ አዝሎ ነበር። ጸሐፊው ኑቺ በሰጠው ቃለ-ምልልስ ከግሪክ አማልክት መካከል በጣም የሚያደንቀው ሄርሜስ የተባለው የሌቦች አምላክን እንደሆነ ተናግሯል። ሄርሜስ ከግሪክ 12 የኦሊምፒያን አማላክት አንዱ ሲሆን የንግድ፣ ሀብት፣ ዕድል፣ እንቅልፍ፣ ቋንቋ እና ሌብነት አምላክ ነው ይባልለታል።

አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You