«የኢንዱስትሪ ምርት ፍላጎታችንን በራስ አቅም መሸፈን ከሉዓላዊነት ጋር የሚያያዝም ነው» አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ

አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ

የአንድ ሀገር እድገት የሚለካው ኢንዱስትሪው ባለበት የእድገት ደረጃና ለኢንዱስትሪ ባለው ምቹ ሁኔታ ነው። ዛሬ ላይ ያደጉ ሀገራት ተብለው የተለዩት በኢንዱስትሪው የበለጸጉት ናቸው። በተመሳሳይ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ተብለው የተቀመጡትም በኢንዱስትሪው መስክ እያስመዘገቡት ያለው ውጤት የሚያሰጣቸው መሆኑን እናያለን።

ኢትዮጵያ ለኢንዱስትሪ ምቹ ሁኔታዎች ካሉባት ነገር ግን በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ካልቻሉ ሀገራት መካከል አንዷ ሆና ቆይታለች። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ግን ዘርፉ በተለያዩ ተግዳሮቶች ውስጥም ሆኖ በየአመቱ አበረታች ውጤት እያስመዘገበ እንደሆነ ይነሳል። ለመሆኑ በኢትዮጵያ ያለው የኢንዱስትሪ ዘርፍ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል? ስንል በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ የሆኑትን አቶ ታረቀኝ ቡሉልታን አነጋግረን የሚከተለውን አጋርተውናል።

አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለው የኢንዱስትሪ ዘርፍ ውጤታማነት እንዴት ይታያል?

አቶ ታረቀኝ፡- የኢንዱስትሪው ዘርፍ ከሀገር እድገት ተለይቶ የሚታይ አይደለም። ወይንም የሀገርን እድገት ከኢንዱስትሪው ዘርፍ ለይቶ ማሰብ አይቻልም። ይህም በመሆኑ በኢትዮጵያ መንግሥት ሀገራዊ እድገትን ያፋጥናሉ ብሎ ቀዳሚ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራባቸው ካሉ አምስት ዘርፎች ማለትም ግብርና ፤ መአድን፤ ቱሪዝምና አይሲቲ ጋር ኢንዱስትሪውም ዋነኛ ትኩረት ሆኖ ይገኛል። በየትኛውም ሀገር የኢንዱስትሪውን እድገት ከሚወስኑት ነገሮች መካከል ደግሞ ለዘርፉ የተቀመጠው ፖሊሲ ውጤታማነት ትልቁን ስፍራ ይይዛል። ኢትዮጵያም በኢንዱስትሪው ዘርፍ ምን መሳካት እንዳለበት በግልጽ በፖሊሲ አስቀምጣ በመንቀሳቀስ ላይ ትገኛለች። ለዚህም ነው ብዙ ቀሪ ሥራዎች ቢኖሩም ላለፉት ተከታታይ ዓመታት ሊያሠራ የሚችል ፖለሲ በመቀመጡ በተግዳሮቶች ውስጥም እየታለፈ አበረታች ውጤት ለማስመዝገብ የተቻለው።

ከሀገሪቱ አጠቃላይ ኢኮኖሚዊ አስተዋጽኦ ትልቁን ድርሻ የያዘው የግብርናው ዘርፍ ሲሆን ኢንዱስትሪው ከአስራ አምስት በመቶ የዘለለ አይደለም። ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት አኳያም ሲለካ ያለው አበርክቶ ከሰባት በመቶ አይዘልም። በፖሊሲው የተቀመጠውም ዘርፉ ለአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ያለውን ድርሻ ማሳደግ ነው። ለዚህ ደግሞ የውጪ ኢንቨስትመንት መሳብ፤ በሀገር ውስጥ ያሉት የከፍተኛና መካከለኛና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎችን በቁጥር መጨመር አጠቃላይም የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታትና ከውጪ ያሉትን ለመሳብ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች በፖሊሲው ተቀምጧል።

በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ የምትጠቀምባቸው አብዛኛው የኢንዱስትሪ ምርት ከውጪ ሀገራት የሚገቡ ናቸው። አስተዳደራዊ ዳታዎች እንደሚያመለክቱት ዘንድሮ ብቻ ከኢንዱስትሪ ምርት ፍላጎት በሀገር ውስጥ አቅም መሸፈን የተቻለው አርባ በመቶ ብቻ ነው። ይህ አካሄድ ምንም እንኳን ገንዘቡ ኖሮን ከፍለን የምንገዛው ቢሆንም እንደ ሀገር ጥገኛ ማድረጉ አይቀርም። ይህም በረጅም ጊዜ በኢኮኖሚ ዘርፍ ዘላቂ ተወዳዳሪ እንዳንሆን ከማድረግ ባለፈ ዘላቂ ጥቅምን ለማስጠበቅ በሚሠሩ ሥራዎች ለይ የራሱ ተዕእኖ ይኖረዋል። በመሆኑም እንደ ሀገር ያለንን የኢንዱስትሪ ምርት ፍላጎት በራስ አቅም መሸፈን ከሉዓላዊነት ጋር የሚያያዝም ይሆናል። ይህንንም መሠረት በማድረግ በአስር አመቱ እቅድ የተቀመጠው ቢያንስ ሰማንያ በመቶ የኢንዱስትሪ ፍላጎትን በሀገር ውስጥ ምርት ለመሸፈን ሲሆን፤ ይህም ዘርፉ የሀገር ውስጥ ኢኮኖሚ የሚኖረውን ድርሻ ወደ ስልሳ በመቶ የሚያሳድግ ይሆናል።

አዲስ ዘመን፡- በኢንዱስትሪ ዘርፍ ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት የተጀመሩት ሥራዎች ምን ውጤት ተገኘባቸው ?

አቶ ታረቀኝ፡- በኢንዱስትሪው ዘርፍ እንደአጠቃላይ እስካሁን በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤት ተመዝግቧል ተብሎ የተለየው በተኪ ምርት ረገድ በተሠሩ ሥራዎች ነው። አዲሱ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ከዚህ በፊት ወጪ ምርቶች ለይ ብቻ ይደረግ የነበረውን የትኩረት አቅጣጫ በመቀየር ተኪ ምርቶችንም የሚያበረታታ ሆኖ የተዘጋጀ ነው። በዚህም በቀዳሚነት በተኪ ምርት ስትራቴጂ ዘጠና ስድስት የኢንዱስትሪ ምርቶች የተለዩ ሲሆን አስራ አንድ የምግብና መጠጥ፤ ሰላሳ ሶስት የጨርቅና አልባሳት፤ ስምንት ቆዳና የቆዳ ምርቶች፤ ሃያ ሶስት ኬሚካልና የኮንስትራክሽን ግብአት፤ ሃያ አንድ ብረትና ኢንጂነሪንግ ናቸው።

በስፋት ከውጪ ይገባ የነበረውን ብቅል መቶ በመቶ መተካት የተቻለ ሲሆን ለውጪ ገበያም ማቅረብ ተጀምሯል። የፓስታና የመኮሮኒ ስንዴ፤ የምግብ ዘይቶች፤ የፍራፍሬ ጭማቂዎችና የበለጸጉ ምግቦችንም በሀገር ውስጥ ምርት በከፍተኛ ደረጃ እንዲተኩ ለማድረግ ተችሏል። ከጨርቅና አልባሳት አኳያም ሱሪ፤ ቁምጣ፤ የውስጥ ሱሪ፤ ጅንስ ሱሪ የህጻናት አልባሳት፤ የሌሊት ልብሶች፤ ወዘተ በስፋት ተመርተዋል። ከቆዳ ምርቶች ጫማ የጫማ ሶል፤ ቦርሳ በከፍተኛ ሁኔታ እየተመረቱ ነው። በኬሚካል ምርት ረገድም መሠረታዊ ኬሚካል፤ የሳሙና ዲተርጀንት፤ ማሸጊያዎች የእንጨትና የወረቀት ምርቶች በስፋት እየተመረቱ ይገኛል። ከብረት ምርቶች ጋር በተያያዘም ማሽነሪዎች፤ ቧንቧዎች፤ አልሙኒየም ባር፤ የተሽከርካሪ አካላት፤ ከኤሌክትሪክ ጋር በተያያዘ ትራንስፎርመርና ኬብል ሌሎችንም ለማምረት እቅድ ተይዞ እየተሠራ ሲሆን በየአመቱም አበረታች ለውጥ ሊመዘገብበት ችሏል።

በዚህ ረገድ በ2016 ዓ.ም ለማሳካት በእቅድ ተይዞ የነበረው 2 ነጥብ 31 ቢሊዮን ዶላር ማዳን ነበር። አፈጻጸሙም ሁለት ነጥብ ስምንት አራት አራት ቢሊዮን ሊደርስ ችሏል። ከዚህ ውስጥ እንደ ዘርፍ ትልቁን ድርሻ ማለትም አንድ ነጥብ አራት ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር የያዙት ከምግብና መጠጥ ጋር የተያያዙት ምርቶች ናቸው። ከዚህ በመቀጠል ኬሚካል 832 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዶላር፤ ማኑፋክቸሪንግና ቴክኖሎጂ 96 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ዶላር ፤ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች ሶስት መቶ ሃያ ሚሊዮን ዶላር፤ ጨርቅና አልባሳት መቶ አራት ሚሊዮን ዶላር፤ በየደረጃቸው ለመታደግ ተችሏል። ለቱሪዝም አገልግሎት የሳፋሪ ኮም መኪና በሀገር ወስጥ እንዲመረት መደረጉ፤ ለኮሊዶር ልማት እየዋሉ ያሉት የስማርት የመብራት ፖሎች በአምስት ኢንዱስትሪዎች ለማምረት መቻሉ ከቅርብ ጊዜ ውጤታማ ሥራዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።

በተኪ ምርት ረገድ በቅድሚያ ወደ ሥራ ከተገባባቸው ዘርፎች መካከል አልባሳትና ጨርቃ ጨርቅ አንዱ ነው። በዚህም የተማሪዎችና የሚሊተሪ ዩኒፎርም ለመተካት በተሠራው ሥራ መቶ በመቶ በሀገር ውስጥ መሸፈን ተችሏል። እነዚህን ምርቶች ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ ግብአት ለማሟላትና ዘላቂነትን ለማረጋገጥም ከውጪ የሚገባውን ጨርቅ ለመተካት ከክር ጀምሮ ወደ ማምረት እየተገባ ነው። በተጨማሪ ቀደም ብለው ተጀምረው ውጤት ከተመዘገበባቸው መካከል የቀለም፤ የወረቀት የእንጨት ምርቶች፤ ለህክምና አገልግሎት የሚውል ፋሻ፤ የጅንስ ልብስ፤ የጫማ ሶል እና ልዩ ልዩ የቆዳ ውጤቶችም ይጠቀሳሉ።

ከቆዳ ምርት ጋር በተያያዘ ለጸጥታ አካላት የጫማ አቅርቦትንም መቶ በመቶ መሸፈን የተቻለ ቢሆንም ካለው የቆዳ ምርት አቅም አኳያ ሲታይ አሁንም ብዙ ሥራ የሚጠበቅ ይሆናል። ኢትዮጵያ ከአፍሪካ በቀንድ ከብት አንደኛ ነች። የስጋ ምርትን በብዛት ተጠቃሚ ስላለም በየአመቱ የሚታረዱትም እንስሳት ቁጥር ከፍተኛ ነው። ነገር ግን አሁንም ድረስ ለስጋው እንጂ ለቆዳው ትኩረት አይሰጥም። እንደ ሀብት የሚታየውም ስጋው እንጂ ቆዳው አይደለም። በሌሎች ዓለማት ከጅምሩ ወደ ከብት ርባታ ሲገቡ ከፍተኛ ተጠቃሚነትን ከቆዳው እናገኛለን በሚል አሳቤ ነው። በኢትዮጵያ ግን የእንስሳት ርባታ ሲካሄድም ቆዳን ከግምት ያስገባ ምንም የሚሠራ ነገር የለም። ይልቁንም ከብቶቹ በርባታ ወቅት በሚደርስባቸው ድብደባና በተለያዩ ነፍሳት መበላት ቆዳቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ይደርሳል።

በእርድ ወቅትም አብዛኛው አራጅ ዋጋው አነስተኛ በመሆኑ ለቆዳው ብሎ የሚያደርገው ጥንቃቄ የለም። በዚህም የመቀደድ የመፋፋቅ ጉዳት ስለሚደርስብት ወደ ገበያው ሳይቀርብ ይቀራል። ቆዳ የሚሰበስቡ ማህበራትም ተጠቃሚነቱ የተቀዛቀዘ በመሆኑ የንግድ ዘርፍን እስከ መቀየር የሚደርሱት በርካቶች ናቸው። በዚህም አሁንም ድረስ በክልሎች በዞንና ወረዳዎች ደረጃ በቂ የመሰብሰቢያ ማእከላት የሉም። በተጨማሪ አንደ ቆዳ ለማቆየት የራሱን ክብደት አንድ ሶስተኛ ጨው ይፈልጋል። ለቆዳ ምርት ማቆያ የሚቀርበው የጨው መጠን በቂ አለመሆንም አንዱ ችግር ነው። ይህንንም ለመቅረፍ በአንድ ወገን ብቻ የሚቻል ባለመሆኑ ከሚመለከታቸው አካላት ማለትም ከግብርና ሚኒስቴር፤ ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርና ከኢንዱስትሪ ባለቤቶች ጋር በመሆን የጋራ እቅድ አዘጋጅተን ወደ ሥራ እየገባን እንገኛለን።

በአጠቃላይ በተኪ ምርቶች እንቅስቃሴ ውጤት እንዲመዘገብ በመንግሥት በኩል የተወሰዱት ርምጃዎች ቀዳሚውን ድርሻ ይይዛሉ። ይህም ሆኖ የሀገር ውስጥ ምርትን ከመጠቀም አኳያ ክፍተት በመኖሩ የመንግሥት ተቋማት ቅድሚያ የሀገር ውስጥ ምርትን እንዲጠቀሙ አቅጣጫ ተቀምጧል። በቀጣይ በአመለካከት ረገድ በግለሰብ ደረጃ የሚስተዋለውን ክፍተት ለመሸፈን የሚሠሩ ሥራዎች ይኖራሉ።

 አዲስ ዘመን፡- የኢንዱስትሪው ዘርፍ የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ከመሸፈን ባለፈ የውጪ ምንዛሬ ምንጭ ለማድረግ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ምን ውጤት አስመዝግበዋል?

አቶ ታረቀኝ፡- የሀገር ውስጥ ምርትን ለውጪ ገበያ ማቅረብ አንዱ ትኩረት ተሰጥቶበት አቅድ ተይዞለት አየተሠራ ያለ ሥራ ነው። የአስር አመቱ እቅድ ከወጪ ንግድ ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት እንደሚሠራ ተመላክቷል። በዘንድሮው አመት ብቻ ሶስት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር የሚያወጣ ምርት ወደ ውጪ የተላከ ቢሆንም የኢንዱስትሪ ምርት ድርሻ ከዘጠኝ በመቶ በታች ነው። አብዛኛው የግብርና ምርት ነው። ይህ መሻሻል ይኖርበታል፡፡ አብዛኛው ገቢ ከኢንዱስትሪ ምርት መገኘት ይኖርበታል። ለዚህ ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸውን ጥራታቸውን የጠበቁ ምርቶችን ማውጣት የግድ ይላል። ይህንንም መነሻ በማድረግ በአንድ በኩል ኢንዱስትሪዎች ጥራት ላይ ትኩረት አድርገው እንዲያመርቱ እየተሠራ ሲሆን በሌላ በኩል የውጪ ገበያ መዳረሻዎችን ለማስፋትም የተያዙ አቅዶች አሉ።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ያበረከተው አስተዋጽኦ እንዴት ይታያል?

አቶ ታረቀኝ ፡- በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ዘርፉ ከፌዴራል እስከ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ትኩረት እንዲያገኝና በንቅናቀቄ የተለያዩ ተግባራት እንዲከናወኑ አስችሏል። በተጨማሪ ወደ አምራች ዘርፍ የሚገባውን ኢንቨስትመንት እያሳደገ ሲሆን ዘንድሮ ብቻ አንድ ሺ 119 ባለሀበቶች ገብተዋል። ከዚህ ውስጥ 220 የውጪ ባለሀብቶች ሲሆኑ ሌላው የሀገር ውስጥ ዜጋ ነው። ይህም በካፒታል ደረጃ አንድ መቶ አስራ ሰባት ቢሊዮን ብር ኢንቨስት ተደርጎበታል። በዚህ ረገድ እስከ ቅርብ ጊዜ እንደ ትልቅ ተግዳሮት ይነሳ የነበረው የፋይናንስ አቅርቦትም እየተሻሻለ መጥቷል።

ከዚህ ቀደም የነበረው የፕሮጀክት፤ የሥራ ማስኬጃ፤ የሊዝ፤ የውጪ ምን ዛሬ አቅርቦት አነስተኛ ነበር። ይህንን ለማስተካከል የካፒታል ፍሰት እንዲጨምር አቅጣጫ ተቀምጦ እየተተገበረ ይገኛል። ዘንድሮ ብቻ ለአነስተኛና መካከለኛ ስድስት ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ለትልልቅ ኢንዱስትሪዎች ደግሞ 54 ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ብር ማቅረብ ተችሏል። በሙሉ አቅም የማምረት አቅም አጠቃቀምን በተመለከተም ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሲጀመር አርባ ሰባት በመቶ ነበር። ዘንድሮ በዘርፍ ቢለያይም በአማካይ ከሃምሳ ዘጠኝ በመቶ ለመሻገር በቅቷል። ነገር ግን ይህም ቢሆን በቂ ነው ለማለት አያስደፍርም በመሆኑም በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሠራበት ይሆናል።

በሌላ በኩል በዘርፉ ያሉ ማነቆዎችን ከመቅረፍ አኳያም በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል። ከነዚህም መካከል ከግብአት አቅርቦት ጋር በጥራትም በብዛትም ያለውን ክፍተት የማሻሻል ተግባር ተከናውኗል። የውጪ ምንዛሬ ቅድሚያ የሚያገኙበት እና ከዚህም ሲያልፍ በፍራንኮ ቫሉታ የሚያመጡበት ሥርዓት ተዘርግቷል። በተለያዩ ጊዜያት የታሪፍ ጫናን ለመቀነስም በሀገር ውስጥ እንደሚያመርቱ ሲረጋገጥና ለኢንዱስትሪ ግብአት ለሚቀርቡ ምርቶች ዜሮ የሚደርስ ታሪፍ የሚቀመጥበት አካሄድ አለ። በቀጣይም ውጤታማነትን ለማረጋገጥ ውጤት ተኮር የማበረታቻ ሥርዓት ትኩረት ተሰጥቶ የሚሠራበት ይሆናል። በተለይም የሀገር ውስጥ ባለሀብትን በልዩ ትኩረት የመደገፍና የማበረታታት ሥራም ተከናውኗል። በዚህ ረገድ ከዚህ ቀደም የነበረውን ክልከላ በማንሳት የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ገብተው የሚሠሩበት ሁኔታ በአዲሱ ፖሊሲ በመመቻቸቱ ገብተው ውጤት አስመዝግበዋል።

በሌላ በኩል ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች እስካሁን ከነበረው በላይ ትኩረት እየተሰጠ ይገኛል። በዘንድሮው አመት ብቻ በሀገር አቀፍ ደረጃ 3 ሺ 262 የሚደርሱ አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች ተቋቁመዋል። ከዚህ ውስጥ 2 ሺ 394 አነስተኛ፤ 868 መካከለኛ ናቸው። ዛሬም ድረስ አብዛኛው ኢንዱስትሪ መካከለኛና አነስተኛ ውስጥ ያለ ነው። አንደ ሀገር ትልልቅ የሚባሉት ኢንዱስትሪዎች ከሁለት ሺ የሚበልጡ አይደሉም። በአዲሱ አዋጅ አንድ መቶ ሚሊዮን ብር ድረስ ኢንቨስት የሚያደርጉት የሚመደቡት ከመካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ጎራ ነው። እነዚህን የመደገፍ በቂ የማምረቻና የመሸጫ ቦታ ከማዘጋጀት መሠረተ ልማት ከማሟላት አኳያ አሁንም ብዙ ሥራ ይጠይቃል።

አዲስ ዘመን፡- የጸጥታ መደፍረስ በቀዳሚነት ከሚጎዳቸው ዘርፎች መካከል የኢንዱስትሪ ዘርፉ ይጠቀሳል። በጸጥታ ችግር ሥራ አቁመው የነበሩትን ወደሥራ ለማስገባት ምን ምን ተግባራት ተከናወኑ ?

አቶ ታረቀኝ፡- የጸጥታ መደፍረስ አምራች ኢንዱስትሪውን በቀጥታ እንደሚጎዳው ይታወቃል። ነገር ግን ምንም እንኳን በትግራይ ክልል በርካታ ኢንዱስትሪዎች ሥራ አቁመው የነበር ቢሆንም የተደረጉት ጦርነቶች በአብዛኛው በገጠራማ አካባቢዎች ስለነበር የደረሰው ጉዳት እንደሚወራው አይደለም። ሙሉ ለሙሉ ውድመት የደረሰባቸው ጥቂት ናቸው። ይህም ሆኖ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመሆን የማጥናት ሥራ በማከናወን በሶስት ከፍሏቸዋል። አንደኛ መቀሌና አካባቢዋ ያሉ ኢንዱስትሪዎች የተወሰኑ ድጋፍ ተደርጎላቸው ወደሥራ መመለስ የሚችሉ፤ በሁለተኛ ደረጃ የተወሰኑ የመለዋወጫ እቃዎች መተኪያ ተደርጎላቸው ወደሥራ መግባት የሚችሉ እና በሶስተኛ ደረጃ ሙሉ ለሙሉ የወደሙ ናቸው።

በዚህም በቅድሚያ በተለይ ቶሎ ወደ ሥራ የሚገቡትን ለይቶ ሥራ ለማስጀመር በተከናወኑ እንቅስቃሴዎች 392 ኢንዱስትሪዎች ሥራ ጀምረዋል። ከእነዚህ ውስጥ ዛሬ ላይ ለውጪ ገበያ ምርት ለመላክ የደረሱም አሉ። አንዳንድ ባለሀብቶች የብድር ክፍያ ጊዜ እንዲራዘም ተጨማሪ ብድር እንዲያገኙና ከቀረጥና ታክስ ነጻ ያገኙዋቸው መብቶች በድጋሚ እንዲሰጧቸው ጠይቀዋል። በዚህም መሠረት መንግሥት ድጋፍ አድርጎ ባለሀብቶችም በራሳቸው ጥረት ወደማምረት እንዲገቡ ተደርጓል። በአማራ ክልልም በተመሳሳይ ቀድሞ በነበረው ግጭት ሥራ አቁመው የነበሩት ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርገዋል። የተወሰኑት የቀሩትም በኢትዮጵያ ታምርት ወደሥራ እንዲገቡ እየተደረገ ይገኛል። አሁን ላይም በየእለቱ ክትትል እየተደረገ የቆሙ ካሉ የቆሙበትን ምክንያት በመለየት እንደ መንገድ፣ ውሃ ፣ መብራት ያለ የመሠረተ ልማት ከሆነ የማሟላትና ወደ ሥራ እንዲገቡ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።

አዲስ ዘመን፡-የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪ ምርቶች የጥራት ጥያቄ ዛሬም ድረስ ይነሳባቸዋል። ይህንን ችግር ለመቅረፍ ምን እየተሠራ ይገኛል?

አቶ ታረቀኝ፡- የጥራት ጥያቄ የሚነሳው በሀገር ውስጥ ምርት ላይ ብቻ አይደለም። ከውጪም ገብተው ከፍተኛ የጥራት መጓደል ያለባቸው ምርቶች እንዳሉ የአደባባይ ሚስጥር ነው። የጥራት ቁጥጥር ሥራዎችን የሚያከናውኑ ተቋማት አሉ ። በተለይ ከምግብና ምግብ ነክ ጋር የተያያዙ ምርቶች ለይ ከፍተኛ ቁጥጥር እየተደረገ ይገኛል። ቁጥጥሩ ወደገበያ እንዲገቡ ፈቃድ የመስጠት ብቻ ሳይሆን ገበያ ውስጥም ከገቡ በኋለ የድንገቴ ቁጥጥር በማድረግም የሚከናወን ነው። እነዚህ ምርቶች በቀጥታ ከዜጎች ጤና ጋር የሚያያዙ በመሆኑ የሚደረገውም ክትትልም ሆነ ምርቶቹን የማስወገድ፤ ፈቃድ የመንጠቅና ሌሎች የሚወሰዱ ርምጃዎች ጠንካራ ናቸው።

ከሁሉም በላይ ግን በሀገር ውስጥ ምርት ላይ የእይታ ችግር አለ። ለምሳሌ እንደ ህንድ ያሉ ሀገራት ዜጎች የትም ቢሆኑ ከሀገራቸው ምርት ውጪ ሲጠቀሙ አይስተዋልም። ይህን የሚያደርጉት ግን ሁሉም ምርቶቻቸው ደረጃቸውን የጠበቁ ሆነው ወይንም የጥራት ችግር ሳይኖርባቸው ቀርቶ አይደለም። ለሀገራቸው ክብር ስለሚሰጡ ነው። በእኛ ሀገር እንደ አጠቃላይ በስፋት የሀገር ወስጥ ምርት ችግር አለበት የሚል እሳቤ ይስተዋላል። ይህ ትክክል አይደለም። በአሁኑ ወቅት በርካታ የሀገር ውስጥ ምርቶች በቱርክ፤ በታይላንድና በቻይና ስም ገበያ ውስጥ ይስተናገዳሉ። ሕዝቡ በሰላም ገዝቶ አድንቆ እየተገለገለባቸው ነው። ይህ መቀየር ያለበት አመለካከት ነው።

እንደአጠቃላይ የመንግሥት የግዥ ተቋማት የሀገር ውስጥ ምርትን እንዲጠቀሙ የተላለፈ መመሪያ ስላለ ያንንም በአግባቡ በመተግበር የሀገር ውስጥ ምርት ተጠቃሚነትን ለማስፋፋት እየተሠራ ይገኛል። በግለሰብ ደረጃ ያለውን አመለካከት ለመቀየር ግን አሁንም ብዙ ሥራ የሚጠበቅብን ይሆናል።

አዲስ ዘመን፡- በሥራ እድል ፈጠራ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ባለፉት ዓመታት ምን ውጤት አስመዝግቧል ?

አቶ ታረቀኝ፡- የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ እንደሚያመላክተውና በኢትዮጵያም አዋጭ የሚሆነው ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ማስፋፋት ነው። በዚህ ረገድ በየአመቱ በዘርፉ አበረታች ውጤት እየተመዘገበ መጥቷል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ዘርፉ ከተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመርቀው ለወጡና ለሌሎችም በስፋት የሥራ እድል መፍጠር የሚጠበቅበት ይሆናል። በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ 147 ሺ 310 በአነስተኛና መካከለኛ ፤ 124 ሺ 694 በጥቅሉ ለ272 ሺ ዜጎች በኢንዱስትሪዎች የሥራ እድል መፍጠር ተችሏል። ይሄ እያደረገ ሄዶ በየአመቱ 800ሺ የሥራ እድል እንዲፈጥር ይጠበቃል። በአስር አመቱ የልማት እቅድ ማጠናቀቂያ አጠቃላይ አምስት ሚሊዮን አዲስ የሥራ እድል በአምራች ኢንዱስትሪውን ለመፍጠር እቅድ ተቀምጦ እየተሠራ ይገኛል። ለዚህም ከአስራ አንድ ሺ በላይ አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ የሚሠራ ይሆናል።

በዚህ ሂደት የሰለጠነ የሰው ሃይል ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ከማቅረብ አኳያ ብዙ መሥራት የሚጠበቅ ይሆናል። በአሁኑ ወቅት ከቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ተቋማትና ከዩኒቨርሲቲዎች የሚወጡ ምሩቃን በቀጥታ ሥራውን ሲቀላቀሉ የሚያዳግቷቸው ነገሮች ይኖራሉ። በመሆኑም የተለያዩ የተግባር ሥልጠናዎች መስጠት አስፈልጓል። ለዚህም ዘንድሮ ብቻ ከምረቃ በኋላ 28ሺ በተግባር የሠለጠኑ ተማሪዎችን ለኢንዱስትሪው ማቅረብ ተችሏል።

አዲስ ዘመን፡- ዘርፉ በሚቀጥሉት ዓመታት በቀዳሚነት ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራቸው ሥራዎች ምን ምን ይሆናሉ ?

አቶ ታረቀኝ፡- እንዳጠቃላይ ሊገለጽ የሚችለው ሃሳብ ኢንዱስትሪው በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ያለውን ድርሻ በአስተማማኝነት ማሳደግ ነው። ለዚህም ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን አጠናክሮ መቀጠል፤ ተኪ ምርት ላይ ትኩረት የሚደረግ ይሆናል፡፡ የወጪ ንግድን በማሳደግ በቀጣዩ በጀት አመት 518 ሚሊዮን ዶላር ማድረስ የሚል ዕቅድ ተይዟል። ተጨማሪ ኢንቨስትመንት የመሳብ እና ያሉትን በማጠናከር የሥራ እድል ፈጠራውን በሚጠበቀው ደረጃ የማሳደግና የአገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን ትኩረት የሚሰጣቸው ይሆናል።

አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ግዜ እናመሰግናለን

አቶ ታረቀኝ፡- አመሰግናለሁ

ራስወርቅ ሙሉጌታ

አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You