የሩስያ የፀጥታ ኃይሎች በእስር ቤት የታገቱ ሠራተኞችን አስለቀቁ

የሩስያ ብሔራዊ ዘብ ታጋቾችን ለማስለቀቅ እና እስር ቤቱን ለመቆጣጠር ባከናወነው ሥራ የታገቱ ሠራተኞችን እንደአስለቀቁ አስታውቋል፡፡ አራቱም አጋቾች በአልሞ ተኳሾች (ስናይፐርስ) መገደላቸው ነው የተነገረው፡፡

በሩሲያ ወጣ ብሎ በሚገኝ እስር ቤት በርካታ እስረኞች ባስነሱት አመፅ እና በፈፀሙት እገታ አራት የእስር ቤቱ ሠራተኞች መገደላቸውን የፌደራል ባለሥልጣናት አስታወቁ። በደቡብ ምዕራብ ቮልጎግራድ ክልል በሚገኘው አይኬ-19 ሱሮቪኪኖ በተባለው እስር ቤት ‘የእስላማዊው መንግሥት ታጣቂዎች ነን’ ያሉ ስለት የያዙ እስረኞች ሕንጻውን መቆጣጠራቸውን ከገለጹ በኋላ የፌዴራል ልዩ ኃይል በሕንጻው ላይ ኦፕሬሽን አካሂዷል።

ባለሥልጣናት እንዳሉት ልዩ ኃይሉ የሠራው ኦፕሬሽን የተወሰኑ ታጋቾችን ነፃ ያወጣ ሲሆን ጥቃት አድራሾቹም እንዲለዩ አድርጓል። ሆኖም በኋላ ላይ አራት የእስር ቤቱ ሠራተኞች መሞታቸው ተረጋግጧል። ያልተረጋገጠ እና በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተጋራ ምስልም በአመፁ ወቅት አንድ በእጁ ስለት የያዘ እስረኛ በደም ከተለወሰ የእስር ቤት ጠባቂ በላይ ቆሞ አሳይቷል።

የሩሲያ ሮስግቫርዲያ ብሔራዊ ዘብ በበኩሉ በነፍስ አድን ኦፕሬሽኑ ወቅት አልሞ ተኳሾች አራት ጥቃት አድራሾች ላይ ተኩሰዋል ብሏል። በብሔራዊ ዘቡ የቴሌግራም ገፅ ላይ በተጋራ ምሥል ላይም የታጠቁ ወታደሮች በእስር ቤቱ ውስጥ ሲደርሱ አሳይተዋል። የሩሲያ የፌዴራል ማረሚያ ቤት አገልግሎት በሰጠው መግለጫ እንዳለው ጥቃቱ የተጀመረው በሥነ ምግባር ኮሚሽን ስብሰባ ወቅት ነው።

ጥቃት አድራሾቹ የእስር ቤቱን ጠባቂዎች ገድለው በርካታ የእስር ቤቱን ሠራተኞች አቁስለዋል ተብሏል። ከዚህም በተጨማሪ ስምንት የእስር ቤቱ ሠራተኞች እና አራት ፍርደኞች ታግተው መወሰዳቸውን የማረሚያ ቤቱ አገልግሎቱ ገልጿል። ታግተው ከተወሰዱት መካከል የእስር ቤቱ ዋና ዳሬክተር እና ምክትል ዳሬክተሩ እንደሚገኙበት አንዳንድ የሩሲያ ሚዲያ ዘገባዎች አመልክተዋል።

“ወንጀለኞቹ በአራት ሠራተኞች ላይ የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት ያደረሱ ሲሆን ሦስቱ ሞተዋል። ሌሎች ጥቃቱን የተጋፈጡ አራት ሠራተኞች ደግሞ ሆስፒታል ገብተው፣ አንዱ በሆስፒታል ሕይወቱ አልፏል።” ብሏል።

የማረሚያ ቤት አገልግሎቱ ጥቃት ፈፃሚዎቹ ሙሉውን የእስር ቤቱን ሕንጻ ተቆጣጥረው ነበር መባሉን አስተባብሏል። “ጥቃት አድራሾቹ ታጋቾችን በሕንጻው በሚገኝ አንድ ክፍል ውስጥ ነው ያገቱት” ብሏል። እገታው ቀድሞ የታሰበበትና በሚገባ የታቀደ እንደነበር የሩሲያ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ታስ አንድ ሕግ አስፈፃሚ አካልን ጠቅሶ ዘግቧል።

መገኛና ብዙኃኑ ጥቃት ፈፃሚዎቹ የ28 ዓመቱ ራምዚዲን ቶሾቭ፣ የ23 ዓመቱ ኡሰታምቾን ናቭሩዚ፣ የ28 ዓመቱ ኛዚርቾን ቶሾቭ እና የ29 ዓመቱ ተሙር ኹሲኖቭ መሆናቸውን በስም ለይቷል። ሁሉም የኡዝቤኪስታን እና ታጃኪስታን ተወላጆች ናቸው ብሏል።

በጥቃት ፈፃሚዎቹ በተጋራ በሞባይል የተቀረፀ ምሥል ላይ ግለሰቦቹ የአይኤስ ታጣቂዎች መሆናቸውን ሲገልጹ ታይተዋል። በተንቀሳቃሽ ምሥሉ ላይ ግለሰቦቹ ጥቃቱን የፈፀሙት በሙስሊሞች ላይ የሚደርሰውን ግፍ ለመበቀል በማሰብ እንደሆነም ተናግረዋል። ከዚህም በተጨማሪ በተንቀሳቃሽ ምሥሉ ላይ ባለሥልጣናቱ በደም ተነክረው ወድቀው ያሳያል። በሌላ ቪዲዮ ላይ ደግሞ ጥቃት ፈፃሚዎቹ በእስር ቤቱ ግቢ ውስጥ ወዲያ ወዲህ ሲሉ ታይተዋል።

የቮልጎግራድ ግዛት ገዥ አንድሬ ቦቻሮቭ ቀደም ብለው በታጋቾች መወሰዳቸው በሠላማዊ ነዋሪዎች ላይ ምንም ስጋት እንዳልፈጠረ ተናግረዋል። ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንም በበይነ መረብ አማካኝነት በተካሄደ የፀጥታ ኃላፊዎች ስብሰባ ላይ ሲካፈሉ የታዩ ሲሆን ስለሁኔታው እንደተነገራቸው ተገልጿል። በተያዘው የበጋ ወቅት በቮልጎግራድ እገታ ሲፈፀም ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

ከዚህ ቀደም በጎረቤቷ ሮስቶቭ ክልል ከእስላማዊ መንግሥት ቡድኑ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ስድስት እስረኞች ሁለት የእስር ቤቱን ጠበቂዎች አግተው ወስደው ነበር። ከአጋቾቹ መካከል አምስቱ የተገደሉ ሲሆን አንደኛው ጥቃቱን ተከትሎ የ20 ዓመታት እስር ተፈርዶበታል። አቃቤያነ ሕጎችም ከእገታው ጋር በተያያዘ የክስ ፋይል መክፈታቸውን ተናግረዋል።

አይኬ-19 ሱሮቪኪኖ ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግለት የወንጀለኞች እስር ቤት ሲሆን 1 ሺህ 200 የሚጠጉ እስረኞች እንደሚገኙበት ይገመታል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ነሐሴ 19/2016 ዓ.ም

Recommended For You