የአፍሪካ እግር ኳስ አባት

ስሙ የሚነሳው በታሪክ ለማስታወስ ብቻ አይደለም። በዜና እና በእግር ኳስ ትንተና ፕሮግራሞች ውስጥ ሁሉ ስሙ ይነሳል። ድል የራቀው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ‹‹በእሱ ጊዜ ቀረ›› ለማለት ይመስላል የስፖርት ጋዜጠኞች የዚህን ሰው ስም በተደጋጋሚ ያነሳሉ። ይድነቃቸው ተሰማ እሸቴ!

እግር ኳስን ተጫውቶታል፣ እግር ኳስን አሰልጥኖታል፣ እግር ኳስን በብቃት መርቶታል። በእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ስሙ ተደጋግሞ ይነሳል። በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን 37 ዓመታትን ወደኋላ መለስ ብለን በዚህ ሳምንት ነሐሴ 13 ቀን 1979 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለየንን የይድነቃቸው ተሰማን ዝርዝር ታሪኮች እናስታውሳለን። ለዚያ በፊት እንደተለመደው ሌሎች የዚህ ሳምንት ክስተቶችን በአጭር በአጭሩ እናስታውሳለን።

ከ82 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ነሐሴ 13 ቀን 1934 ዓ.ም ‹‹የሰማዩ ጠላቂ፣ የሰማዩ ቀዛፊ…›› እየተባሉ የሚጠሩት፤ በሶማሊያ ወረራ ጊዜ የዚያድ ባሬን የጦር አውሮፕላን አየር ላይ ዶግ አመድ ያደረጉት፤ የአየር ኃይሉ መሃንዲስ ብርጋዴር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ተወለዱ። የዚህን ጀግና ታሪክ በመስከረም ወር በዝርዝር ማስታወሳችን ይታወሳል።

ከ120 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ነሐሴ 14 ቀን 1896 ዓ.ም ከፋሺስት ጣሊያን ጋር ከፍተኛ ውጊያ አድርጎ፤ በተለይም በአንዱ የጦር ሜዳ የጠላትን አውሮፕላን በእሩምታ ተኩስ እንዲወድቅ አድርጎ ድል ያስመዘገበው፤ በአጠቃላይ በፋሽስት ጣሊያን የወረራ ሙከራ ወቅት የሀገርን ክብር ያስጠበቀው ስመ ጥሩ አርበኛ ራስ አበበ አረጋይ ተለወደ። የራስ አበበ አረጋይን ዝርዝር ታሪክ በተለያዩ አጋጣሚዎች በዝርዝር ማስታወሳችን ይታወሳል።

ከ12 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ነሐሴ 14 ቀን 2004 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። የአቶ መለስ ዜናዊን የሕይወት፣ የትግልና የአመራር ዝርዝር ታሪኮች ባለፈው ግንቦት ወር ማስታወሳችን ይታወሳል። አሁን በዝርዝር ወደምናየው የይድነቃቸው ተሰማ ታሪክ እናልፋለን።

ይድነቃቸው ተሰማ መስከረም 1 ቀን 1914 ዓ.ም ጅማ ከተማ ውስጥ ተወለደ። አባቱ የበርካታ ሙያዎች ባለቤት የነበሩት ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ሲሆኑ እናቱ ደግሞ ወይዘሮ ሙላቷ ገብረሥላሴ ይባላሉ። አዝማሪ፣ ባለቅኔ፣ ቀራፂ፣ ሰዓሊ፣ ነጋዴ፣ መካኒክ፣ ፖለቲከኛ፣ ፎቶ አንሺ … የነበሩት ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ፤ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ፣ በልጅ ኢያሱ፣ በንግሥት ዘውዲቱና በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥታት ስመ ጥር ሰው ነበሩ። በተለይ በልጅ ኢያሱ ዘመን ጉልህ ፖለቲካዊ ተሣትፎ ነበራቸው።

ከዚህ በተጨማሪም ለልጅ ኢያሱም የተለየ አክብሮት ስለነበራቸውና አብዛኛው በአዲስ አበባ ከተማ የነበረው የመሐል ሀገሩ መኳንንት ልጅ ኢያሱን ከሥልጣን ለማውረድ በተሰለፈ ጊዜ ሁሉ፤ ነጋድራስ ተሰማ ግን የልጅ ኢያሱ ታማኝ ባለሟል ሆነው እስከ መጨረሻው ድረስ በመዝለቃቸው ልጅ ኢያሱ ከሥልጣናቸው ተሽረው ዘውዲቱ ምኒልክ ንግሥት፤ ደጃዝማች ተፈሪ መኮንን ደግሞ አልጋ ወራሽ ሆነው በተሾሙበት ወቅት በቀልድ አዋቂነታቸውም ተደናቂ የነበሩት ነጋድራስ ተሰማ፣ በግዞት ወደ ጅማ ተወስደው ነበር። ይድነቃቸው የተወለደው በዚህ ወቅት ነው።

ይድነቃቸው እንደማንኛውም የዘመኑ ልጆች እድሜው ለትምህርት ሲደርስ የቄስ ትምህርት ቤት ገብቶ የመጽሐፍ ቅዱስ እና የአማርኛ ቋንቋ ትምህርትን ተምሯል። የፈረንሳይኛ ትምህርትን ደግሞ በአሊያንስ፣ በዳግማዊ ምኒልክና በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤቶች ተከታትሏል። በወቅቱም ለእግር ኳስ፣ ለብስክሌትና ለሩጫ ስፖርቶች ልዩ ፍቅር ነበረው።

ብስክሌቱንና ሩጫውን ባይገፋበትም እግር ኳሱን ግን በተጨዋችነት፣ በአሠልጣኝነትና በኋላም በአመራርነት እስከሕይወቱ ፍፃሜ ቀጥሎበት ዛሬም ድረስ ስሙን ማስጠራት የቻለበት ስፖርት ሆኖለታል። ገና በስምንት ዓመቱ የትምህርት ቤቱ የሕፃናት እግር ኳስ ቡድንን በአምበልነት እየመራ ተጫውቷል። በ1924 ዓ.ም ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴና የስዊድኑ ንጉሥ ልጅ በተገኙበት መድረክ ይድነቃቸውና የትምህርት ቤት ጓደኞቹ የስፖርት ትርዒት አቅርበው ሽልማት ተቀብለዋል።

ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ይድነቃቸው ወደ ኢጣሊያ ሚሲዮን ትምህርት ቤት በመግባት በወቅቱ ለሀገር ተወላጆች (ለኢትዮጵያውያን) ይሰጥ የነበረውን ትምህርት አጠናቋል። ይድነቃቸው በ1928 ዓ.ም ወደ ፈረንሳይ ለመሄድ ከተመረጡት ሁለት ጎበዝ ተማሪዎች መካከል አንዱ በመሆን ዝግጅቱን አጠናቅቆ የነበረ ቢሆንም ኢትዮጵያ በፋሺስት ኢጣሊያ በመወረሯ ምክንያት የፈረንሳዩ ጉዞው ሳይሳካ ቀረ።

በስምንት ዓመት ዕድሜው የስፖርት ዓለም ተሳትፎን የጀመረው ይድነቃቸው፣ በ14 ዓመቱ የአራዳ ልጆች የነበሩት አየለ አትናሽ እና ጆርጅ ዱካስ የመሠረቱትን የዛሬውን ‹‹ቅዱስ ጊዮርጊስ›› የእግር ኳስ ቡድንን ተቀላቀለ።

በወቅቱም እነይድነቃቸው ጨዋታዎችን ሲያደርጉ የግብ አግዳሚና ቋሚ እንጨቶችን ተሸክመው በየቦታው ይንከራተቱ ነበር። የግብ አግዳሚና ቋሚዎችን በቋሚነት መትከል ደግሞ የሚሞከር አልነበረም። ሌላው ሁሉ ይቅርና ‹‹ሳር ታበላሻላችሁ›› በሚል የሚደርስባቸው ተቃውሞ እንኳ ከባድ ነበር።

ይድነቃቸው ለ23 ዓመታት ያህል ለቅዱስ ጊዮርጊስ ተሰልፎ በመጫወት ለክለቡ ለረጅም ዓመታት በመጫወት እስካሁን ድረስ ባለ ክብረወሰን ነው። ከይድነቃቸው በመቀጠል ለቅዱስ ጊዮርጊስ ለብዙ ጊዜያት የተጫወተው ለ16 ዓመታት ያህል ቡድኑን ያገለገለው ዝነኛው ተጫዋች መንግሥቱ ወርቁ ነው።

በፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ይታተም የነበረውና ‹‹የሮማ ብርሃን›› የተሰኘው ጋዜጣ በወቅቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከስድስት ኪሎ ቡድን ጋር ያደረገውን ጨዋታ በዘገበበት ጽሑፉ የይድነቃቸውን ብቃት እንዲህ ሲል ገልፆት ነበር።

«… ነገር ግን ስድስት ኪሎዎች ምንም እንኳ በራቸውን አጠንክረው ይዘው ቢጫወቱም ኳሲቱ ዙራ ዙራ ከዚያው ከይድነቃቸው እግር ገባችና ይድነቃቸው እንደልማዱ ኳሲቱን ይዞ ከፊት ያገኘውን ልጅ ሁሉ እያሳለፈና እያስዘለለ ሲሮጥ ኳሲቱ በገዛ እጅዋ የምትሮጥ ትመስል ነበር እንጂ እሱ በእግሩ የሚነዳት አይመስልም ነበር …»

ይድነቃቸው በቅዱስ ጊዮርጊስ በቆየባቸው ዓመታት ከተጫዋችነት በተጨማሪ አሠልጣኝ ሆኖም አገልግሏል። በአንድ የውድድር ዘመን ለክለቡ 43 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል። ይህ ስኬትም ይድነቃቸውን እስካሁን ድረስ ባለክብረወሰን አድርጎታል። ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ተሰልፎ ተጫውቷል።

ይድነቃቸው የተጫዋችነት ዘመኑን ካጠናቀቀ በኋላ ወደ አሠልጣኝነት በመሸጋገር የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድንን መርቷል። ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ አንድ ለእናቱ የሆነውን የአፍሪካ ዋንጫዋን (1954) ስታሸንፍ የቡድኑ አሠልጣኝ ይድነቃቸው ነበር። ኢትዮጵያ ባለድል የሆነችበት የሦስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር የውድድሩ ከፍተኛ ኮከብ ግብ አስቆጣሪዎችም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አምበሉ ሉቺያኖ ቫሳሎ እና የግብፁ አብደልፋታህ በደዊ ሲሆኑ እያንዳንዳቸው ሦስት ግቦችን አስቆጥረዋል። የውድደሩ ኮከብ ተጫዋች ሆኖ የተመረጠው ደግሞ ዝነኛው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቹ መንግሥቱ ወርቁ ነበር።

ይድነቃቸው ተሰማ ከተጫዋችነትና ከአሠል ጣኝነታቸው ባሻገር ታላላቅ ተግባራትን ያከናወኑትና ታዋቂነትን ያተረፉት የስፖርት ማኅበራትን በማደራጀትና በመምራት ነው። የኢትዮጵያ ስፖርት ጽሕፈት ቤትን አቋቁመው ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን በዘመናዊ መልኩ ለማደራጀት ጥረዋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ሲመሰረትም አስተዋፅኦዋቸው እጅግ የጎላ ነበር። በወቅቱም የፌደሬሽኑ ዋና ፀሐፊ ሆነው ተመርጠው ነበር።

በ1949 ዓ.ም የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን (CAF) አህጉራዊ ውክልና ኖሮት በዓለም እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (FIFA) ውስጥ እንዲሳተፍ ታቀደ። ኮንፌደሬሽኑ በየካቲት 1949 ዓ.ም በካርቱም ከተማ ተመሠረተ። በምስረታ ስብሰባው ላይም አቶ ይድነቃቸው ኢትዮጵያን በመወከል ተገኙ። በወቅቱ የተሻለ አቅም የነበረውን ፌዴሬሽን የመሠረተችው ግብጽ የማህበሩን ጽሕፈት ቤት ወደ ካይሮ ከተማ እንዲዛወር አድርጋ ግብፃዊው ኢንጂነር አብደልአዚዝ አብደላ ሳሌም የመጀመሪያው የኮንፌደሬሽኑ ፕሬዝደንት ሆነው ተሾሙ። ከመስራቾቹ በመቀጠልም ደቡብ አፍሪካ እና ሌሎች ሀገራት ታዳጊውን ተቋም በአባልነት ተቀላቀሉ። ከድርጅቱ ምስረታ ጀርባ የይድነቃቸው ሚና የጎላ ነበር። የኮንፌደሬሽኑን መተዳደሪያ ደንብ በመቅረጽ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ነበራቸው። ይድነቃቸው ይህንኑ ኮንፌደሬሽን፣ እ.አ.አ ከ1964 እስከ1972 በምክትል ፕሬዝደንትነት፣ ከ1972 እስከ 1987 ደግሞ በፕሬዝደንትነት መርተውታል።

ይድነቃቸው በደቡብ አፍሪካ ይካሄድ በነበረው የአፓርታይድ ሥርዓት ላይ በሚያሳዩት ተቃውሞም ይታወቁ ነበር። የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ሲጀመር የደቡብ አፍሪካ እግር ኳስ ማህበር ‹‹ … ‹ሁሉም ጥቁር› አልያም ‹ሁሉም ነጭ› የሆኑ ተጫዋቾች እንጂ በምንም አይነት ሁኔታ ‹ከሁለቱም የተዋሀደ› ቡድን ወደ ውድድሩ አልክም …›› ማለቱን ተከትሎ ይድነቃቸውን ጨምሮ ብዙ ኢትዮጵያውያንና ሌሎች የእኩልነት መብት ተሟጋቾች ደቡብ አፍሪካ ከአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን እንድትገለል ጫና በማሳደራቸው እ.አ.አ በ1958 ካፍ ደቡብ አፍሪካን ከአባልነት አገዳት። በወቅቱ የይድነቃቸው የሥራ ባልደረባና የካፍ ተወካይ የነበሩት አብድልሐሊም መሐመድ ደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ፖለቲካዊ ሥርዓቷን በስፖርት ውስጥ እንዲንሰራፋ በማድረጓ ካፍ ከአባልነት ሲያግዳት በይድነቃቸው የማያወላውል ጽኑ አቋም ምክንያት እንደነበር መስክረዋል።

ከቅኝ ግዛት ተላቅቀው ነፃነታቸውን የሚጎናፀፉ የአፍሪካና እስያ ሀገራት ቁጥር መጨመር ዘረኝነትን የተከተለ አሠራርን የሚተገብሩ ሀገራት ከዓለም አቀፉም ሆነ ከአህጉራዊ ማኅበራት እንዲታገዱ ጫና ማሳደሩን አጠናከረው። ይህም በወቅቱ ለዘረኛ አሠራሮች ጥብቅና ቆመው የነበሩ የፊፋ አመራሮችን ከፍተኛ ጫና ውስጥ ከተታቸው። ከአፍሪካ፣ እስያ፣ ደቡብ አሜሪካ እና ሶቭየት ኅብረት በተገኘ ሰፊ ድጋፍና በጊዜው የካፍ ምክትል ፕሬዝደንት አቶ ይድነቃቸው መሪነት የፊፋ ምክር ቤት ደቡብ አፍሪካ ላይ በድጋሚ የእገዳ ውሳኔ አሳለፈ።

በዓለም ዋንጫ ውድድር ላይ የነበረው የአፍሪካውያን ኮታ እንዲስተካከል እነአቶ ይድነቃቸው በፅናት መከራከራቸውንም ቀጠሉ። የወቅቱ የፊፋ ፕሬዝደንት የነበሩት ስታንሊ ሮውስ

‹‹ … ብዙ ሰዎች ተጨባጭ ያልሆነ ሃሳብ እንደሆነ ያምናሉ። ለምሳሌ እንደ እንግሊዝ ያለች እግር ኳስ የተጀመረባትና ምስረታውን ያደራጀች ሀገር ወይም ደግሞ ሰፊ ልምድ ያላቸው፣ በፊፋ ምስረታ ወቅት ትልቅ ድርሻ የነበራቸው እንዲሁም በዓለም እግር ኳስ ጉዳዮች ላይ በሚነሱ ችግሮች ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ጣልያንና ፈረንሳይን የመሳሰሉት ሀገሮች ከአፍሪካና እስያ ከሚመጡ ሀገሮች ጋር እኩል ድምፅ የመስጠት መብት መኖር የለበትም …›› ብለው አስተያየት ሰጡ።

አቶ ይድነቀቻውም በዚህ የሮውስ የማን አለብኝነት አመለካከት ተገርመው ‹‹… ምንም እንኳ ለፊፋ መመሥረት የተወሰኑ አህጉራት በተቋሙ የእድገት ሒደት ውስጥ በሃሳብ፣ በቁሳቁስና በገንዘብ ረገድ ያበረከቱትን የተሻለ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ብንረዳም እኛ የምንጠብቀው ግን ተቋሙ ዓለምአቀፋዊ ድርጅት የመሆኑን ያህል በዴሞክራሲያዊ አሠራር የሁሉንም አባል ሀገራት መብቶች በተመሳሳይ ሁኔታ የሚያስከብር እንዲሆን ነው። ስለዚህም አሠራሩ በሕጋዊ ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ የዓለም እግር ኳስን ጥቅምና አንድነትን በዘላቂ ሒደትን የሚከተል እንዲሁም በፊፋ ወስጥ ያሉት አባላት በሚያድግ ሚዛናዊ ውክልና እንዲሳተፉ መደረግ አለበት …›› ሲሉ ሞገቱ።

አቶ ይድነቃቸው ‹‹አንድ ሀገር አንድ ድምጽ›› የሚለውን የምክር ቤቱን መመሪያ በስኬታማነት ከመታገላቸውም በላይ በሮውስ አመራር የዓለም ዋንጫ አውሮፓን ማዕከል ባደረገው ንፍቀ ክበብ ብቻ ተወስኖ እንዳይዘልቅና ለሌሎች አህጉራትም እንዲዳረስ ረጃጅምና ተከታታይ የደብዳቤ ግንኙነቶችን ከሮውስ ጋር በማድረግ አፍሪካ የቀጥታ ተሳትፎ ኮታ ኖሯት እግር ኳሷ እንዲበረታታና እንዲያድግ ያላሰለሰ ጥረት አድርገዋል። በዚህም ስኬታማ ነበሩ።

የአፍሪካን እግር ኳስ ጥቅምና ፍላጎት በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስጠበቅ ረገድ የአቶ ይድነቃቸው ሚና እየጎለበተ ሄዶ ኃላፊነታቸውም ጨመረ። እ.አ.አ በ1966 ዓ.ም የፊፋ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል፣ በ1967 የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ እንዲሁም በ1972 ዓ.ም ደግሞ የካፍ ፕሬዝደንት ሆነው ተሾሙ። በአንደበተ ርቱዕነታቸው የሚታወቁት አቶ ይድነቃቸው ከጥሩ አማርኛ ተናጋሪነታቸው በተጨማሪ እንግሊዝኛን፣ ፈረንሳይኛን እና ጣልያንኛን በጥሩ ሁኔታ መናገር መቻላቸው በዓለም አቀፍ ስፖርት አስተዳደር መድረኮች ውስጥ ያለውን ውስብስቡን ፖለቲካ በአፍሪካ የእንግሊዝኛና ፈረንሳይኛ ቋንቋዎች ተናጋሪ ማዕዘናት በተሟላ ክህሎት ለማሰስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቶላቸዋል።

እ.አ.አ በ1974 ብራዚላዊው ዥያን ማሪ ፎስቲን ጎድፍሮይድ ጆኣዎ ዴ ሃቨላንጅ (‹‹ጆ ሃቨላንጅ››) የፊፋ ፕሬዝደንት ሆነው ተመረጡ። ወቅቱ አቶ ይድነቃቸው የካፍ ፕሬዝደንት ሆነው ማገልገል የጀመሩበት ጊዜ ነበር። አፍሪካም በ1960ዎቹ ስትታገልላቸው ለነበሩት ዓላማዎቿ ግልጽ ድጋፍ የሚያደርግ የእግር ኳስ መሪን እ.አ.አ በ1970ዎቹ አጋማሽ አገኘች።

ካፍ ቀደም ሲል ከፊፋ ጋር ባለመስማማቱ ይፈጠሩ የነበሩ ከውድድሮች ራስን የማግለል እና ከባለስልጣናቱ ጋር የሚደረጉ እልህ አስጨራሽ ትግሎች ቀርተው የአፍሪካን ግቦች ማሳካት ተጀመረ። እ.አ.አ በ1974 በፍራንክፈርት በተካሄደው የፊፋ ስብሰባ ላይ የጎሳ፣ የዘር እና የሃይማኖት መድልዎን በሀገሩ ውስጥ የሚያሰፍን ማንኛውም የፊፋ አባል ሀገር ከዚህ ድርጊቱ የማይታቀብ ከሆነ ፈጣን የእገዳ ውሳኔ እንዲተላለፍበት ካፍ ሃሳብ አቀረበ። ደቡብ አፍሪካም ከፊፋ አባልነቷ ተባረረች። በዓለም ዋንጫ የሚሳተፉ የአፍሪካ ተወካዮች ቁጥርም አደገ።

አቶ ይድነቃቸው በካፍና በፊፋ ውስጥ ከነበራቸው የሥራ ኃላፊነት በተጨማሪ የአፍሪካ ስፖርት ኮንፌደሬሽኖች ኅብረት ፕሬዝደንት፣ የአፍሪካ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች የክብር ፕሬዝደንት እንዲሁም የአፍሪካ ስፖርት ጠቅላይ ምክር ቤት እና የዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አባል ሆነውም አገልግለዋል።

ከሦስት አሥርት ዓመታት በፊት ጋዜጠኞች ለወቅቱ የፊፋ ፕሬዝደንት ጆ ሀቨላንጅ ‹‹ከእርስዎ በኋላ የፊፋ ፕሬዝደንት ማን ይሆናል? እርስዎን የሚተካው ማነው?›› ብለው ሲጠይቋቸው ባጭር ቋንቋ ‹‹ሚስተር ተሰማ ነዋ!›› በማለት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ለቦታው እንደሚመጥኑ ተናግረው ነበር።

ሃቨላንጅ ያለምክንያት አልነበረም እኚህን ታላቅ ኢትዮጵያዊና አፍሪካዊ የስፖርትና የኦሊምፒክ ግንባር ቀደም መሪን ለትልቁ የኃላፊነት ቦታ ያጯቸው። አቶ ይድነቃቸው የኢትዮጵያን ዘመናዊ ስፖርት ያደራጁ፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴን ትክክለኛ መስመር ያስያዙ፣ ለአፍሪካ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማኅበር ብቻ ሳይሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃም ለብሔራዊ ኢሊምፒክ ኮሚቴዎች ማኅበር ህልውና የተጉ፣ ልዩ ልዩ ሕጎችንና መተዳደሪያ ደንቦችን በአማርኛ ያዘጋጁና ለአፍሪካም የተረፉ ታላቅ ሰው ናቸው። አቶ ይድነቃቸው ተሰማ፣ ዘርንና ሃይማኖትን መሠረት ያደረገን የስፖርት ክለቦች አደረጃጀትን በጥብቅ ያወግዙና ይቃወሙ ነበር። ከዚህ ባሻገር በስፖርታዊ ክንውኖች ወቅት የሲጋራና የአልኮል ምርቶች በስታዲየሞች አካባቢዎች እንዳይተዋወቁ በፅናት ይከራከሩም ነበር።

ታዲያ ሃቨላንጅ ያኔ አቶ ይድነቃቸውን ለፊፋ ፕሬዝደንትነት ሲያስቧቸው ለጥቆማቸው አክብሮታቸውን የገለፁት ታላቁ ኢትዮጵያዊ፣ በጤና እክል ምክንያት እጩነቱን ለመቀበል እንደሚቸገሩ ተናግረዋል። የበርካታ ሪከርዶች ባለቤት የሆኑት አቶ ይድነቃቸው፤ ከውጭ ሀገራት መንግሥታት ሳይቀር ብዙ ዋንጫዎችን፣ ሜዳሊያዎችንና ሌሎች ሽልማቶችን አግኝተዋል።

በእርግጥ አቶ ይድነቃቸው የአፍሪካ እግር ኳስ የወደፊት አቅጣጫን በሚመለከት ከፍተኛ የሆነ ሃሳብ ነበራቸው። እ.አ.አ በ1974 ዓ.ም በተካሄደው የካፍ ስብሰባ ላይ ‹‹ … በዚህ ጠቅላላ ጉባዔ አፍሪካ አንድ እና የማትከፋፈል መሆኗን በማረጋገጥ፣ የአፍሪካን አንድነት ለማስጠበቅ በጋራ እንድንሠራ፣ በእግር ኳሳችን እና በአጠቃላይ የኑሮ ገጽታችን ላይ የተንሰራፋውን ባዕድ አምልኮ፣ ጎሰኝነትና ሌሎች የምንገለልባቸውን ነገሮች በሙሉ እንድናወግዝ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ …›› በማለት ተናግረው ነበር።

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 19/2016 ዓ.ም

Recommended For You