የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ ለቀጣዩ ምርጫ የዴሞክራቲክ ፓርቲ ፕሬዚዳንታዊ ዕጩ ሆነው በይፋ ተሰየሙ።
ኅዳር 2017 ዓ.ም. በሚካሄደው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ካማላ ሃሪስ ከቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር አሜሪካን ለቀጣይ አራት ዓመታት ለመምራት ይፎካከራሉ።
ካማላ ይህን ምርጫ የሚያሸንፉ ከሆነ የመጀመሪያዋ ሴት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በመሆን አዲስ ታሪክ ይጽፋሉ።
በቺካጎ በተደረገው የዴሞክራቲክ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የፓርቲውን ዕጩነት በተቀበሉበት ንግግራቸው “የሁሉም አሜሪካውያን ፕሬዚዳንት” ለመሆን እሠራለሁ ብለዋል።
ካማላ በንግግራቸው ለአሜሪካውያን ዕድል የሚፈጥር ምጣኔ ሀብት ለመገንባት እንዲሁም አከራካሪው የጽንስ ማቋረጥ መብት እንዲረጋገጥ እሠራለሁ ሲሉ ተናግረዋል።
“ሀገሬን በሙሉ ልቤ ነው የምወደው። በየሄድኩበት የማገኛቸው ሰዎች ወደፊት መጓዝ እንደሚፈልጉ ነው የሚነግሩኝ። አስደናቂው ጉዟችን አሁን ይጀምራል” ያሉት ካማላ፤ አሜሪካውያን ከሚለያይዋቸው ነገሮች ይልቅ አንድ የሚያደርጓቸው ብዙ መሆኑን በማስታወስ ለአንድነት ጥሪ አቅርበዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የካማላ ሃሪስን ንግግር ሲከታተሉ የነበሩት ዶናልድ ትራምፕ ትሩዝ በተሰኘው ማኅበራዊ ሚዲያቸው ትችት ሲሰነዝሩ ቆይተዋል።
ትራምፕ ምክትል ፕሬዚዳንቷ በንግግራቸው እንደ “የድንበር ጉዳይ፣ የዋጋ ግሽበት እና የወንጀል መጨመር” የተመለከቱ መሠረታዊ ጉዳዮች ከማውራት ይልቅ ስለ “አስተዳደጓ ብዙ እያወራች ነው” ሲሉ ተችተዋል።
ካማላ በንግግራቸው በልጅነታቸው አንዲት ጓደኛቸው የተፈጸመባት ፆታዊ ጥቃት እንዴት የሕግ ትምህርት እንዲከታተሉ መነሳሳት እንደሆናቸው እንዲሁም ወላጅ እናታቸው ኢፍትሐዊነትን እንዲዋጉ እንዴት እንዳስተማሯቸው በማብራራት የሕይወት ተሞክሯቸውን አጋርተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ካማላ “አስደሳች” ስለነበረው የልጅነት ጊዜያቸው ከተናገሩ በኋላ፤ እናታቸው እንዴት ያበረታቷቸው እንደነበረ፣ ታላቅ እህታቸው እንዴት ይንከባከቧቸው እንደነበረ እና ወላጅ አባታቸው ደግሞ ሕልም ለማሳካት “ሩጫ” እንዳያቆሙ ይነግራቸው እንደነበረ ተናግረዋል።
የቢቢሲው የሰሜን አሜሪካ ዘጋቢ አንተኒ ዘርከር አሜሪካውያን ካማላ ሃሪስን የሚያውቁ ቢሆንም ምክትል ፕሬዚዳንቷ ዋይት ሐውስ ቢገቡ ምን ለመሥራት እንዳቀዱ በርካቶች ላያውቁ ይችላሉ ይላል።
ሃሪስ የልጅነት ጊዜያቸውን እና የስደተኛ ልጅ መሆናቸውን የተናገሩት መራጮች ማንነታቸውን እንዲያውቁ ያደረጉት ጥረት ነው ይላል።
በተያያዘ ዜና የዴሞክራቶች ጉባኤ እየተካሄደ ከነበረበት አዳራሽ ፊት ለፊት ድጋፋቸውን ለፍልስጤማውያን ያደረጉ አሜሪካውያን የተቃውሞ ድምጻቸውን ሲያሰሙ ነበር።
“ድል ለፍልስጤማውያን” የሚል መፈክር ይዘው የወጡት ተቃዋሚዎች በከፍተኛ ቁጥር በተሰማሩ የፖሊስ አባላት ተበትነዋል።
ተቃዋሚዎቹ ተወካያቸው በዴሞክራቶች ጉባኤ ላይ ንግግር እንዲያደርጉ ያቀረቡት ጥያቄ በካማላ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን ውድቅ ተደርጓል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 18 ቀን 2016 ዓ.ም