ዓለም የከፋ ጥፋት ውስጥ እንዳትገባ እና ከነጭራሹ እንዳትጠፋ ካሰጉ ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል ዋነኛው የአየር ንብረት ለውጥ ነው። ይህንን ጥፋት ለማስቆም ዓለም የተስማማ ቢመስልም፤ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በመግባት በኩል ሰፊ ዳተኝነት ይስተዋላል። እንደውም የሚመጣውን ቀውስ እና ጥፋት ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የነበረውን እና ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ተረድቶ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ በኩል የዓለምን አየር በስፋት ከበከሉት የበለፀጉ ሀገሮች ጀምሮ፤ ሌሎችም በአየር ንብረት ለውጥ ላይ አነስተኛ ሚና የነበራቸው ሀገራት መሬት የወረደ ውጤታማ ሥራን ሲሠሩ አይታዩም።
በሌላ በኩል ችግሩን ለይቶ አውቆ ውጤታማ ሥራ ለማከናወን በተለያዩ ሀገሮች እና ከተሞች ለ28 ጊዜ ትልልቅ ስብሰባዎች ተካሂደዋል። በስብሰባዎቹ ከ200 ያላነሱ የዓለም ሀገራት፣ የተለያዩ ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች እና ትልልቅ ባለሀብቶች ቢሳተፉም መሬት ሊነካ የሚችል ውጤት እንዳላስገኙ እየተነገረ ነው። ምንም እንኳ ችግሩ መኖሩን መተማመን ላይ ቢደረስም፤ መልሶ ወደኋላ የመንሸራተት እና በየስብሰባው በሀገራቱ ፊት የገቡትን ቃል አለመፈፀም በሰፊው ተስተውሏል። ይህን ተከትሎ ዓለም በጎርፍ እና በሙቀት እንዲሁም በረሃማነትን ጨምሮ በተለያዩ የአየር ንብረት ለውጦች እየተሰቃየች ትገኛለች።
ከተሰብሳቢዎቹ እና ቃል ከገቡ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ናት። ኢትዮጵያ የመሬትን መጎሳቆል ለመቀነስ እና የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ የሚፈጠረውን ችግር ለማቃለል ለዓለም ማህበረሰብ 22 ሚሊዮን ሄክታር መሬት እንዲያገግም እሠራለሁ ብላ ቃል ገብታለች። ይህንን ማዕከል አድርጋ መሥራት ከጀመረች ዓመታት ተቆጥረዋል። ባለፉት አምስት ዓመታት የክረምት መግባትን ተከትሎ በሚካሄድ የችግኝ ተከላ ከ32 ነጥብ አምስት ቢሊየን ያላነሰ ችግኝ መተከሉን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ዘንድሮም ይኸው ችግኝ ተከላ ተጠናክሮ እየቀጠለ ሲሆን፤ ዓመቱን ሙሉ በተለይም ከሰኔ ጀምሮ ከተተከሉት ችግኝ ባሻገር ዛሬ ማለትም ነሐሴ 17 ቀን 2016 ዓ.ም በአንድ ጀንበር 600 ሚሊየን ችግኞች የመትከል ዕቅድ ተይዟል። በእርግጥ ይህ ችግኝ በትክክል ይተከላል ወይ? ለመትከል ምን ያህል ዝግጅት ተደርጓል? ይህንን ሁሉ ችግኝ መትከል የሚኖረው ፋይዳ ምንድን ነው? ስንል በኢትዮጵያ ደን ልማት የደን ባለሞያ፤ በፎረስት ሴክተር ትራንስፎርሜሽን ክፍል የፕሮግራም አስተባባሪ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚካሔደውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ አደፍረስ ወርቁ (ዶ/ር) ን ጠይቀን እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል። መልካም ንባብ፡-
አዲስ ዘመን፡- የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ዝግጅት ምን ይመስላል?
ዶ/ር አደፍርስ፡- ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሳወቁት ነሐሴ 17 ቀን 2016 ዓ.ም ኢትዮጵያ 600 ሚሊየን ችግኞችን ትተክላለች። የችግኝ ዓይነቶቹ የተለያዩ ሲሆኑ፤ የደን ችግኞች፣ የግብርና ችግኞች ፍራፍሬን ጨምሮ የውበት ችግኞች አሉ። እስከ አሁን በቁጥር የተለዩት የዛፍ ችግኞች ከ90 በላይ የዕፅዋት ዝርያዎች ናቸው።
ተከላው የሚካሔደው በተለዩ እና በታወቁ ቦታዎች ላይ ሲሆን፤ እያንዳንዷ ችግኝ የት እንዳረፈች በሚታወቅ መልኩ ይከናወናል። የተወሰነ ማጣሪያ ተደርጎባቸው ወደ 7ሺ ተከላ የሚደረግባቸው ሳይቶች ተለይተዋል። የሳይቶቹ ሄክታር የታወቀ ነው። በእነዚህ ሳይቶች ላይ የሚተከሉ 600 ሚሊየን ችግኞች አሉ።
የሚሳተፈውን ሰው በተመለከተ ከከተማ እስከ ገጠር ከልጅ እስከ አዋቂ ሕዝቡን በማንቀሳቀስ ችግኞቹን እንተክላለን። 600 ሚሊየን ለመትከል የሚያስችል ሕዝብ እቅድ ከመሬት ተሰብስቦ መጥቷል። 30 ሚሊየን ሕዝብ አካባቢ ወጥቶ መትከል መቻል እንዳለበት ታውቋል። ለምሳሌ አንድ ሳይት 4 ሄክታር ከሆነ፤ አንድ ሄክታር ላይ የሚተከለው የደን ዝርያ ሲሰላ፤ በአንድ ሄክታር ላይ በአማካኝ 2ሺህ 500 ችግኞች ይተከላሉ። በአራት ሄክታር መሬት ላይ 10ሺህ ችግኞች ይተከሉበታል ማለት ነው።
10ሺህ ችግኝን ለመትከል ደግሞ ስንት ሰው መውጣት አለበት የሚለው ሲሰላ አንድ ሰው 20 ችግኝ ቢተክል ገበሬው ከዛ በላይም ይተክላል። በነበረው ተሞክሮ 60ም ሆነ 70 ችግኞችን ሲተክል አይተናል። ነገር ግን በአማካኝ አንድ ሰው 20 ችግኝ ቢተክል ብለን አስልተን ስንት ሰው መውጣት እንዳለበት ዕቅዱ አልቋል። አሁን ወደ ተግባር መግባት ብቻ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የታቀደው 600 ሚሊየን ችግኞች መተከላቸውን ማረጋገጥ የምንችለው በምን መንገድ ነው?
ዶ/ር አደፍርስ፡- የእያንዳንዱ ሳይት ጂኦ ሪፈረንሱ መረጃ ላይ በጥንቃቄ ተሰርቷል። የሚተከለው የችግኝ መጠን ተለይቷል። የሚሳተፈው የሕዝብ ቁጥር እንዲሁ ታውቋል። ተከላ በሚካሔድበት ሳይት መረጃ የሚሰጥ ባለሞያ ተዘጋጅቷል። የቀሩት ትንንሽ የማጥራት ሥራዎች ነበሩ፤ እነርሱም ተጠናቀዋል። በኤ አይ ተቀናጅቶ በየሳይቱ ያሉ ሪፖርተሮች እያንዳንዱን መረጃ ወደ ቴሌኮም ቋት ይልካሉ። በባለሞያው አማካኝነት መረጃው ወደ ቴሌኮም የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ቋት ይላካል። አመዘጋገቡም ኮድ ላይ በተመዘገበው ልክ ብቻ መረጃ መስጠት ሲሆን፤ በዚህ መልኩ መረጃው ይሰበሰባል።
ተከላ ላይ ብቻ ሳይሆን መረጃ በማሰባሰብ ዙሪያ ከአምናው እና ከካቻምናው በተሻለ መልኩ እንፈፅማለን ብለን መሬት ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በሙሉ ርብርብ እያደረግን ነው። ስለዚህ ተከላው ይካሔዳል፤ የተተከለውን ማረጋገጥ የሚቻልበት መንገድም አለ።
አዲስ ዘመን፡- በየዓመቱ ብዛት ያላቸው ችግኞች እየተተከሉ ነው። የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት መዳረሻ የት ነው? 22 ሚሊየን ሄክታር መሬት መሸፈን ነው ወይስ ሌላ መጨረሻ አለው?
ዶ/ር አደፍርስ፡- በርግጥ የዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የዓለም መንግሥታት መሪዎች እና ድርጅቶች ሲነጋገሩ በየዓመቱ የሚያስቀምጧቸው ግቦች አሉ። የአየር ንብረት ለውጥ የአንድ ሀገር ችግር አይደለም። አንዱ ሀገር በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ያለች ድሃ ሀገር ልትጎዳ ትችላለች። ነገር ግን ሌሎችም ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ መጎዳታቸው አይቀርም። ከወዲሁ መፍትሔ ካልተበጀለት ደግሞ ዛሬ ከሚመታው እና ከሚያስከትለው ጉዳት ይልቅ ነገ ሊመታ እና ሊጎዳ የሚችለው ከፍተኛ ሊሆን ይችላል።
በረሃማነት እና የዕፅዋት መመናመን በተመሳሳይ መልኩ በብዙ ሀገሮች ጉዳት ታይቷል። ጉዳቱ እንዳይደርስ ሁል ጊዜ ግብ ለማስቀመጥ ይሞከራል። ስለዚህ እ.አ.አ በ2030 እየጨመረ የመጣውን የዓለም ሙቀት ቢቻል ከ1960ዎቹ ጀምሮ ያለው የሙቀት መጠን መጨመር በ1 ነጥብ 5 ዲግሪ ላይ እንዲቆም፤ ወይም የሙቀት መጠን መጨመር ከ1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴንቲግሬድ እንዳይበልጥ ሥራ ሠርተን ማስቆም አለብን በሚለው ላይ መግባባት ተችሏል። ብክለታችንን ቀንሰን፤ የደን ሽፋናችንን ጨምረን ሌሎች ሥራዎችንም ሠርተን፤ 1 ነጥብ 5 የሚሆነውን ማሳካት ካቃተን ያለበለዚያ ተያይዘን መጥፋታችን ነው። ቢቻል እስከ 2 ዲግሪ ሴንቲግሬድ እንዲሆን ብንሠራ ጥሩ ነው።
እስከ አሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ በተካሔዱ ስብሰባዎች የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሀገራት የመሬት ማኔጅመንት ላይ ውይይት ተካሂዷል። ምን ያክሉ መሬት በደን እንዲሸፈን ሊያደርጉ ይችላሉ? የሚለው ረዥም ውይይት ሲካሄድበት እና ሲንከባለል የመጣ ግብ ነበር። ስለዚህ ኒውዮርክ ዲክላሬሽን፣ አፍሪካን ፎረስት ላንድ ስኬፕ የሚል ስምምነት ተካሔደ። ሀገራትም ይህን ያህል የአፈር እና የውሃ ጥበቃ ሥራ ሰርቼ፤ ዛፍ ተክዬ፤ ደን ጠብቄ፤ ይህን ያህል መሬት እንዲያገግም በማድረግ በረሃማነትን እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እንዲያግዝ አስተዋፅኦ አደርጋለሁ፤ ብለው ቃል ገብተዋል። ልክ እንደሌሎቹ ሁሉ ኢትዮጵያ 15 ሚሊየን ሄክታር መሬት እንዲያገግም ኒውዮርክ ዲክላሬሽን ላይ ቃል ገብታለች።
በተጨማሪ ኢትዮጵያ ደቡብ አፍሪካ ደርባን ኮፐን ላይ 7 ሚሊየን ሄክታር አለማለሁ ብላ ቃል ገብታ ነበር። ስለዚህ ኢትዮጵያ 15 ሚሊየን እና 7 ሚሊየን በአጠቃላይ 22 ሚሊየን ሄክታር መሬት እንዲያገግም እላዩ ላይ ደን ካለም ደኑ በዘላቂነት እንዲጠበቅ፤ ሥርዓተ ምህዳሩ እንዲመለስ፤ ወንዞች የሚፈሱበት ምንጮች የሚፈልቁበት እንዲሆን አደርጋለሁ ብላ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ቃል ገብታለች። ኢትዮጵያ ኒውዮርክ ዲክላሬሽን ፎረስት ላይ ብቻ ሳይሆን ኤፍ አር የአፍሪካ መሪዎች ለተሰባሰቡበት መድረክም ቃል ገብታለች።
22 ሚሊየን ሄክታርም በቂ ላይሆን ይችላል። ነገር ግን ለጊዜው የፓሪሱን ስምምነት ጨምሮ በዓለም አቀፍ መድረኮች የተቀመጠው ግብ፤ 2030ን ማዕከል ያደረገ ነው። ስለዚህ እዛ ላይ እስከ 2030 ሃያ ሁለት ሚሊየን ሄክታር መሬት እንዲያገግም እና ሽፋን እንዲኖረው እናደርጋለን ብለናል።
በሀገራችን እንደሚታወቀው ቃል ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ ይባላል። ልጅን ከዛፍ በማስበለጥ አይደለም፤ ነገር ግን ቃል ትልቅ ትርጉም ያለው በመሆኑ ቃል ቃልነውና በተገባው ቃል መሠረት በ2030 ወይም ከዛ በላይ ለሚፈጅ ዓመት የተጎዳውን መሬት አክመን ለዓለም ማሳየት አለብን።
አረንጓዴ ዐሻራን በመተግበር መሬታችንን አድነን ሀገራችንን ዛፍ ያለባት፤ ዝናብ በበቂ መጠን የምታገኝ፤ በርሃማነት የሌላባት፤ ገበሬው ዘርቶ የሚያጭድባት ሀገር እናድርጋት ብለን እየሠራን ነው። ድርቅ ቢመጣ ሕዝቡ ድርቅን የሚቋቋምበት እና የማይሰደድበት እንዲሁም ሕዝቡ በመሬቱ የሚጠቀምበትን ሁኔታ እንፈጥራለን ብለን አረንጓዴ ዐሻራን የምናሳካበት መርሃ ግብር አዘጋጅተናል። የገባነውን ቃል ለመፈፀም ደግሞ በብርቱ ጥረት እያደረግን ነው። ስለዚህ መንገዱን ያደረግነው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብርን በመሆኑ ከዚሁ ጋር ተያይዞ እናሳካዋለን የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ ሀገራዊ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ ፋይዳው ምን ይመስላል?
ዶ/ር አደፍርስ፡- የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ ዓለም አቀፋዊ ፋይዳን ለማብራራት አስቀድመን በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጡ ተግዳሮቶችን ማወቃችን ጉዳዩን ለማስረዳት ቀላል ያደርገዋል። አሁን በዓለም ላይ 200 ሀገራት እና በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሀገር አቀፍም ሆኑ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶች፣ ዓለም አቀፍ አበዳሪ ድርጅቶች፣ የዓለም የግለሰብ ሃብታሞች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ሁሉም ማለት በሚቻል መልኩ ያስቀመጧቸው ተግዳሮቶች አሉ።
ዓለም የተስማማበት እና በጋራ ካልመለስነው በስተቀር ያጠፋናል ብሎ የገለፃቸው ችግሮች አሉ። ችግሮቹ በሚቃለሉበት ሁኔታ ላይ አፈፃፀማቸውን በተመለከተ ልዩነት ሊኖራቸው ቢችልም፤ በአንድ ወይም በሁለት ዓመት ጥረት ብቻ የማይመለሱ የዓለም ችግሮች ብለው የለዩዋቸው አሉ። አንደኛው እና ዋነኛው የአየር ንብረት ለውጥ ችግር ነው። ሁለተኛው የበርሃማነት መስፋፋት ነው። ሌላኛው ዓለም አቀፍ ችግር የብዝሀ ሕይወት መመናመን ወይም የደን መጨፍጨፍ ችግር ነው። የአየር ንብረት ለውጥ ወይም በተለይ በከተሞች አካባቢ ያለ የአየር እና የውሃ ብክለት ችግር ነው።
የዓለም የሥነ ምህዳር አገልግሎት መናጋት ሲገጥም፤ የሰው ልጅ ከተፈጥሮ እና መሬት ከተሰኘችው ፕላኔት ጋር ያለው መስተጋብር ፈሩን እየለቀቀ ሲመጣ፤ ከትብብር ይልቅ በሰው ልጅ እና በተፈጥሮ መካከል ግጭት ይፈጠራል። ከእነዚህ ችግሮች ጋር ድህነት፣ ስደት፣ ግጭት፣ የአየር ለውጥ እና የመሬት መጎሳቆል ተያይዘው ይመጣሉ። ወረርሽኝ እና የማይታወቁ በሽታዎችም ጭምር ይከሰታሉ። ይህ እየባሰ ሲመጣ ወረርሽኞች እየተፈጠሩ ይመጣሉ። ለምሳሌ ኮቪድ በብዙ መልኩ ይተነተናል። እንደዚህ ዓይነት ትልልቅ ወረርሽኞች ይበራከታሉ።
እነዚህ ጉዳዮች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ዓለም ተስማምቷል። በርግጥ አፈፃፀሙ ላይ አንደኛው ‹‹ኢንዱስትሪ ዓለምን እየበከለ ነው ዝጋ›› ሊባል ይችላል። ሌላኛው ኢንዱስትሪህን ቀንስ ወይም ዝጋ የተባለው ደግሞ ‹‹ኢንዱስትሪዬን ብዘጋ የሥራ ዕድል ዜሮ ይሆንብኛል። ገቢዬ ይጎዳል፤ ፓርኬ ከጥቅም ውጭ ይሆናል። መንግሥቴ አደጋ ላይ ይወድቃል። እኔ ይህን ባደርግ እነእከሌ ያልፉኛል አንተ መሥራት ያለብህን ሥራ። ከዛ ይልቅ ይህንን ባደርግ ይሻለኛል ›› ብሎ ጉዳዩን ወደ ሌላ ያዞረዋል። ወይም በአፈፃፀሙ ላይ ይከራከራል። ‹‹ይሁን እንጂ ይህን አደርጋለሁ ሊል ይችላል።›› ስለዚህ በአጠቃላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተግዳሮቶች ላይ ስምምነት አለ። ችግሩን ለማቃለል የሚኬድበት መንገድ እና አፈፃፀሙ ላይ ግን ስምምነት ለመፍጠር አልተቻለም።
የበርሃማነት መስፋፋት፣ የብዝሀ ሕይወት መመናመን፣ ምርትና ምርታማነት መቀነስ፣ ድህነት፣ ስደት ግጭት የመሳሰሉት ነገሮች ዓለም አቀፋዊ ፈተናዎች ናቸው። አንዳንዶቹ የአየር ንብረት ለውጥ ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ ከማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ጋር የተሳሰሩ ናቸው። ስለዚህ እነዚህን ትልልቅ ምድራችን የገጠማትን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ፤ በዓለማችን በተለያዩ ጊዜያት በየዓመቱ ስብሰባዎች ተካሂደዋል። ለምሳሌ የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ መድረክ ለ28ኛ ጊዜ ዱባይ ላይ ተደርጓል።
የ200 ሀገራት መሪዎች እና ከተለያዩ ድርጅቶች የተሰበሰቡ የአየር ንብረት ለውጥን እንዴት እንከላከል? ልቀትን እንዴት እንቀንስ? እስከ መቼ እንቀንስ? እስከዛ ድረስ የሚጎዱ ሕዝቦች ስላሉ የማጣጣሙን ሥራ እንዴት አድርገን እንሥራ? እንዴት እንደግፍ? በማለት ተገናኝተው ተወያይተዋል። አሁን ደግሞ በአዘርባጃን ለ29ኛ ጊዜ ጉባኤው ይካሔዳል። ሌላም በርሃማነትን እና ብዝሀ ሕይወትን የተመለከቱ ጉባኤዎች አሉ።
በየዓመቱ ሀገራት መሬት ላይ ወርደው ልቀትን፣ በርሃማነትን እና የብዝሀ ሕይወት መጥፋትን የሚቀንሱ ሥራዎች እንዲተገበሩ ይነጋገራሉ። ነገር ግን ሀገሮች ተወያይተው እንዲያበቁ ብቻ ሳይሆን መሬት ላይ ወርደው እንዲሠሩ ይፈለጋል። ኢትዮጵያ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ እየተገኘች ትወያያለች። መወያየት ብቻ ሳይሆን ችግሩ መቃለል እንዳለበት በመጠቆም፤ መሠራት ባለባቸው ሥራዎች ዙሪያ ትከራከራለች። ይህንን ወደፊትም መቀጠል አለባት። ምክንያቱም ሰለባ ነች።
አንዱ የለቀቀው ልቀት ኢትዮጵያን ተጎጂ ሊያደርጋት ይችላል። የአየር ንብረት ለውጥ ጎርፍ እንዲበላን እና መሬት እንዲንሸራተት ሊያደርገን ይችላል። በረሃማነት እንዲበላን ሊያደርግም ይችላል። ስለዚህ በተለያዩ መድረኮች ላይ በመገኘት ልቀታችሁን ቀንሱ፣ ኢኮኖሚያችሁን አረንጓዴ ኢኮኖሚ አድርጉ፤ የኢኮኖሚ አስተዳደግ መርሃ ግብራችሁን ቀይሩ እንላለን። እኛም ግን የአቅማችንን መሥራት አለብን። ነገር ግን የኢትዮጵያ ወይም የአንድ ሀገር ሥራ ብቻውን ትልቅ ለውጥ አያመጣም። ሁሉም መሥራት አለበት።
አረንጓዴ ልማት እንግዲህ በኮፕ ጉባኤ ላይ በደርባን የሲ አር ጂ ስትራቴጂያችን በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚን ስናስተዋውቅ እና ከዛ በፊት እነዚህን ሁሉ በዓለም ላይ የምናደርጋቸውን ውይይቶች ወደ መሬት አውርደን መሬት ላይ የተገበርንበት መሣሪያችን ነው። ያንን መድረክ ላይ የተከራከርነውን፣ ሌሎች እንዲያደርጉት የመከርነውን ፤ የተመኘነውን እኛ ቀድመን አድርገን እናሳይ ብለን ተነስተናል።
የትም ሀገር በየትኛውም ጥግ ከኢትዮጵያ ቀድሞ በቢሊየን የሚቆጠር ችግኝ እተክላለሁ ብሎ የተነሳ የለም። በዚህ ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ናት። ይህንንም አድርጋ አሳይታለች። ስለዚህ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ያለው ፋይዳ የመጀመሪያው በዚህ እሳቤ ላይ ሀገራት እና ተቋማት ድሃ ሃብታም ሳይሉ በየስብሰባው እየተገናኙ የሚመካከሩበትን ምክረ ሃሳብ በተግባር ማውረድ ይገባቸዋል የሚለውን በተግባር ያሳየች ሀገር ናት። አረንጓዴ ዐሻራ ያነሳው ይህንን ነው።
ብክለታችሁን ቀንሱ እያልን ነበር፤ አሁን እኛ በተግባር ብክለታችንን እየቀነስን የተበከለውን አየር ማንፃትንም በተግባር እያሳየን ነው። ምክንያቱም የተበከለውን አየር የምንተክላቸው ዛፎች እዚህ መሬት ላይ ያለው ካርበን እንዳይለቀቅ ያደርጋሉ። በተጨማሪ በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች አገራት የተለቀቀውን አየር አፅድተን መልሰን ወደ ምድር እያመጣን ነው። ስለዚህ ዓለም አቀፍ ሙቀትን ለመቀነስ ሰፊ አስተዋፅኦ እያበረከትን ነው። በርግጥ ይህ በአንድ ሀገር ብቻ የሚሠራ አይደለም። ምክንያቱም የዓለም አየር ተበክሏል። ሙቀቱ ጨምሯል። የዝናቡ ሁኔታ ተደበላልቋል። አንዳንዱን ሀገር ዝናብ እየጎዳው ነው። አንዳንዱን አካባቢ ደግሞ ድርቅ እያጠቃው ይገኛል። ይህ ኢትዮጵያ ውስጥም የታየ ጉዳይ ነው። እየሠራን ነው።
ድሃ ሀገር ብንሆንም በቢሊየን የሚቆጠር ችግኝ ተክለን እንደሚቻል አሳይተናል። ይሄ ትልቅ ፋይዳ ነው። ኢትዮጵያ የሄደችበትን መንገድ ተከትላ ኬንያም እንደ ኢትዮጵያ በስፋት ባይሆንም መትከል ጀምራለች። ሌላኛው ፋይዳ አሁን የተከልናቸው ችግኞች ከተተከሉበት ቀን ጀምሮ በካይ ጋዝን እያመቁ ነው። በሂደት አምስት እና አስር ዓመት ሲሞላቸው እና ትልልቅ ሲሆኑ መሬቱ በአረንጓዴ ሲሸፈን ብዙ ካርበን ማለትም ዓለም ላይ ሙቀት ያመጣውን ካርበን ወይም በካይ ጋዝ እናምቃለን። ይህ ትልቅ አስተዋፅኦ ነው።
በአረንጓዴ ዐሻራ ብዝሀ ሕይወትን እንጠብቃለን። የኢትዮጵያን የደን ሽፋን ከፍ እናደርግበታለን። የደን ሽፋን ከፍ ሲል ብዙ ዝናብ ይዘንባል። ብዙ ዝናብ ኢትዮጵያ ውስጥ ከዘነበ የውሃ እጥረት ያለባቸው ዙሪያችን ያሉ የታችኛው ሀገሮች በድንበር ተሻጋሪ ወንዞቻችን አማካኝነት ውሃ ያገኛሉ። ስለዚህ ለጎረቤቶቻችን ውሃ የምንልክበትበት ለዓለም ደግሞ ብክለትን እና ሙቀትን የምንቀንስበት፤ የተበላሹ የሥነ ምህዳር ግልጋሎቶችን የምናሻሽልበት እንዲሁም ምርትና ምርታማነትን የምንጨምርበት ዕድል ይፈጥርልናል። ኢትዮጵያ ስታመርት የምታመርተው ለጎረቤቶቿም ጭምር ነው። ብዝሀ ሕይወት ለእኛ ብቻ አይደለም፤ ለግብፅም፤ ለኬንያም ለሁሉም ያገለግላል። ከእነዚህ ከሚተከሉት ችግኞች ውስጥ መድኃኒት ይሆናል። ለአንድ አደገኛ በሽታ መድኃኒት የሚሆን ዕፅዋት መገኘት ይችላል።
ሌላው አውሮፓዎች በተደጋጋሚ የሚያነሱት ስጋት በስደተኞች ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነው። ስደተኞችን የመጡትን ማስተዳደር አልቻልኩም፤ የሚመጡትም የጤንነት ችግር አለባቸው ብለው ስደትን የዓለም ስጋት አድርገው ያስቀምጣሉ። የእኛ ወጣቶች የሚሰደዱት ለምንድን ነው? የሚል ጥያቄ ካቀረብን ሥራ በማጣት ነው። ችግር እና ድህነት ወጣቶቻችንን እያሰደደ ነው። ምክንያቱም ትናንት ምርት ሲሰጥ የነበረ መሬት በመሸርሸሩ፤ እንኳን ላሉት ወጣቶች ለነባሮቹም ሽማግሌዎችም በቂ ምርት እየሰጠ አይደለም።
በርግጥ ወጣቶች ወደ ሌላው ዓለም እንዲሔዱ የሚስባቸው ነገር ቢኖርም፤ ከእዚህም የሚገፋቸው ድህነት አለ። ስለዚህ የአረንጓዴ ልማት ሥራ ለስደት የሚገፋቸው ነገር እንዲቀንስ ያግዛል። የችግኝ ጣቢያ ሲቋቋም ወጣቶች ሥራ ያገኛሉ። ምርትና ምርታማነትን እያሻሻልን ስንመጣ የተወሰነው ወጣት ራሱን ይቀይራል። ረሃብን ችግርን ለመቀነስ፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል፤ የበረሃማነት መስፋፋትን ለመቀነስ ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል። ፋይዳው ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊ እና አካባቢያዊ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የኢትዮጵያ ሚና ምን ይመስላል?
ዶ/ር አደፍርስ፡- በርግጥ ኢትዮጵያ ከሌሎቹ ጋር ሲነፃፀር ብዙ በካይ አይደለችም። ነገር ግን ጭራሽ አስተዋፅኦ የለንም ማለት አይቻልም። መሬታችንን እኛም ጎድተናል። በርሃማነቱን አምጥተናል። የብዝሀ ሕይወት መመናመንም ሆነ የደን መጨፍጨፍ ጀርመን በለቀቀችው ልቀት የመጣ ችግር አይደለም፤ የእኛ ሕዝብ እያደረገው ያለ ነገር ነው። ደን እንዲጠበቅ፣ በርሃማነት እንዲቀነስ፣ በጣም የተጎሳቆለ መሬት በአረንጓዴ እንዲሸፈን፤ የጠፉ የሥርዓተ ምህዳር ግልጋሎቶች እንዲመለሱ እኔም እሠራለሁ። እናንተም ሥሩ እያለች ነው።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ።
ዶ/ር አደፍረስ፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ዓርብ ነሐሴ 17 ቀን 2016 ዓ.ም