በኬንያ ሚስቱን ጨምሮ 42 ሴቶችን ገድሏል በሚል በፖሊስ ቁጥጥር ስር የነበረው ተጠርጣሪ ከእስር ቤት ማምለጡ ተነገረ።
ኮሊንስ ጁማይሲ የተባለው ግለሰብ በፖሊስ ከተያዘ በኋላ ሴቶችን እየመረጠ ከ2022 ጀምሮ ሲገድል እንደነበር ቃሉን የሰጠ ቢሆንም ፍርድ ቤት በቀረበበት ጊዜ ድርጊቱን እንዳልፈጸመ ተናግሯል።
የተጠርጣሪው ጠበቃ ግለሰቡ ሴቶችን ስለመግደሉ ለፖሊስ ያመነው በደረሰበት የምርመራ ማሰቃየት ነው ሲል ገልጿል። የፖሊስ ቃል አቀባይ ርሲላ ኡንያንጎ እንደተናገሩት ግለሰቡን ጨምሮ በሕገወጥ መንገድ የገቡ 12 ኤርትራውያን ትናንት አነጋጉ ላይ ጊጊሪ ከተባለው የፖሊስ ጣቢያ እስር ቤት ማምለጣቸውን ተናግረዋል።
እስረኞቹ ማለዳ ላይ የታሳሪዎች ቆጠራ በሚከናወንበት ጊዜ እንዳመለጡ ፖሊስ ማስታወቁን ሮይተርስ ዘግቧል።
ፖሊስ አስራ ሶስቱን ከሕግ ያመለጡ ሰዎች በቁጥጥር ስር ለማዋል ሰፊ አደን እና አሰሳ እያደረገ ነው ያሉት ቃል አቀባዩ በዋና ከተማዋ ናይሮቢ የሚገኙ ነዋሪዎች ያልተለመዱ እንቅስቃሴዎችን ሲመለከቱ ለፖሊስ ጥቆማ እንዲሰጡ ጠይቀዋል።
ኮሊንስ ጆማይሲ የተባለው የ33 ዓመት ኬንያዊ ባሳለፍነው ሀምሌ ላይ የአውሮፓ ዋንጫ ፍጻሜ እየተመለከተ በሚገኝበት ወቅት በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን ግለሰቡ ለመጨረሻ ጊዜ ከገደላቸው ሴቶች መካከል ከአንዷ ጋር ባደረገው የሞባይል ገንዘብ ልውውጥ ፖሊስ ባደረገው ማጣራት ሊያዝ ችሏል።
አስክሬኖቹ ከተገኙበት አካባቢ 100 ሜትር ርቀት ላይ የሚኖር ሲሆን ፖሊስ በመኖርያ ቤቱ ውስጥ ባደረገው ፍተሻ 10 ሞባይል ስልኮችን ፣ ላፕቶፕ ፣ የሴቶች አልባሳት እና መታወቂያዎችን አግኝቷል።
በተጨማሪም የተለያየ መጠን ያላቸው የስለት መሳርያዎች እና የሟቾችን አስክሬን ከቆራረጠ በኋላ የሚጥልባቸውን በርካታ ከረጢቶች እንደተገኙ ፖሊስ አስታውቋል።
ሟቾቹ ከ18 እስ 30 እድሜ የሚጠጉ ሴቶች ሲሆኑ ሁሉም የተገደሉበት መንገድ አንድ አይነት ተብሏል።
አዲስ ዘመን ሐሙስ ነሐሴ 16 ቀን 2016 ዓ.ም