“ሀገራዊ መግባባት ለኢትዮጵያ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው” ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም

ኢትዮጵያ ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ጎልተው የሚታዩ የሃሳብ ልዩነቶችና አለመግባባቶች የሚስተዋሉባት ሀገር ናት። እነዚህ የሃሳብ ልዩነቶችና አለመግባባቶችን በሰለጠነ መንገድ የመፍታት ባሕል ደካማ በመሆኑ ለዘመናት ያህል ወደ ግጭትና ጦርነት ተገብቶ የበርካታ ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፤ የአካል ጉዳት ተከስቷል፤ ንብረት ወድሟል፤ ስደትና መፈናቀል በስፋት ተስተናግዷል። በአጠቃላይም የሀገሪቱ ዕድገት ወደኋላ ተጎትቷል፤ ድህነትና ጉስቁልና በርትቷል።

በአጠቃላይ የሃሳብ ልዩነትን በኃይል የመፍታት አባዜ ተጠናውቶን ቆይቷል። ዛሬም የሚታየው ሃቅ ይኸው ነው። ሆኖም የኃይል አማራጭ ዘላቂ መፍትሔ እንደማያመጣ ሩቅ ሳንሄድ ከዛሬም ከትናንትም ታሪካችን የምንረዳው ሀቅ ነው። በዚሁ መነሻ ነው እጅግ መሠረታዊና ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ላሉብን አለመግባባቶች በንግግርና በውይይት ለመፍታት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቋቁሙ በሥራ ላይ የሚገኘው።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገሪቱ ለዘመናት ያህል ሰፍነው የቆዩ ቁርሾዎችን እና አለመግባባቶችን ለመቅረፍና በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ተግባብቶ ሀገሪቱን ወደፊት የሚያሻግር ትውልድ ለመፍጠር ራዕይ ሰንቆ መንቀሳቀስ ከጀመረ ሶስት ዓመታት ሊደፍን ጥቂት ወራት ቀርተውታል። ታዲያ በነዚህ ዓመታት ውስጥ ኮሚሽኑ የሄደበት ርቀት ምን ይመስላል? የተቋቋመበትን አላማስ ምን ያህል እያሣካ ነው? በሚለው ዙሪያ ከኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበናል። መልካም ንባብ።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያን ወደ ሀገራዊ ምክክር እንድትገባ ያደረጓት አስገዳጅ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

ኮሚሽነር መላኩ፡- ኢትዮጵያ ወደ ሀገራዊ ምክክር እንድትገባ ያደረጓት ብዙ ምክንያቶች አሉ። ለረዥም ዘመናት በሃሳብ መሪዎች፣ በፖለቲካ መሪዎች እንዲሁም በህብረተሰብ ክፍሎች መካከል እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ አለመግባባቶች አሉ። የሚስተዋሉ አለመግባባቶችም ከምክክርና ከውይይት ይልቅ ጥያቄን በኃይል አማራጭ ለመፍታት በሚደረገው ሂደትም ለእርስ በእስር ጦርነት፣ ለመፈናቀል ብሎም ከፍተኛ ለሆነ ዕልቂት ተዳርገን ቆይተናል።

ከዚህ በከፋ መልኩ እነዚህ አለመግባባቶች እንዲቀጥሉ ከተፈለገ እና ችላ ከተባለ ሀገሪቱን ለከፋ አደጋ ሊያጋልጡ ስለሚችሉ ከወዲሁ ምክክር ብናደርግባቸው፤ ተመካክረን ደግሞ ወደ መግባባት ብንደርስ የተሻለ ይሆናል በሚል ነው የምክክር ኮሚሽኑ የተቋቋመው። ሀገሪቱ ወደ ምክክር እንድትገባ ያስገደዳት ምክንያቶችም አሁን በሚደረገው የምክክር ሂደት ነጥረው የሚወጡ ጉዳዮች ናቸው።

አዲስ ዘመን፡- የምክክር ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ጀምሮ አሳካሁት የሚለው ነገር ምንድን ነው?

ኮሚሽነር መላኩ፡– ይሄ የምክክር ኮሚሽን የምክክሩን ሂደት እንዲመራና እንዲያስተባብር ኃላፊነት የተሰጠው ኮሚሽን ነው። የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቋቋመ ተቋም ከመሆኑ ጋር ተያይዢ ልምድ ሊወስድበት የሚችልበት ሌላ ተቋምም በሀገሪቱ አልነበረም። ከባዶ ተቋሙን ማቋቋም በራሱ የሚወስደው ጊዜ እና ሀብት አለ።

በዚህ ሂደትም ተቋሙ ወደፊት ሥራውን ጨርሶ ከወጣ በኋላም ሊቀጥል በሚችልበት ሁኔታ ነው እየተደራጀ ያለው። የተሰጠውን ሀገራዊ ሰላምን የማምጣትና የማጽናት ኃላፊነት ለመወጣት በሚያስችል ቁመና ላይ መገኘቱን የማረጋገጥ ሥራም ተከናውኗል።

ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ባለው ሂደትም ኮሚሽኑ የተሰጠውን ኃላፊነትና ተግባር ማወቁ የመጀመሪያውና ትልቅ ሥራ ነበር። የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነትን መነሻ በማድረግም ምን ምን ሥራዎች ማከናወን እንዳለባቸው ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቶ ወደ ሥራ ገብቷል።

እንዲሁም ኮሚሽኑ ማንኛውም ችግር ሲያጋጥም በምክክር መፍታት እንደሚቻል አምኖ ምክክር የኢትዮጵያ ሕዝብ ባሕል እንዲሆንና የምክክር ባሕል እንዲዳብር የማድረግ አላማ ይዞ እየሰራ ነው። ይህንንም መሠረት የመጣልና አላማውን ለማስተዋወቅ ብሎም አስፈላጊነቱ ላይ እውቅና እና ግንዛቤ ለመፍጠር የተለያዩ አካላት ጋር በጋራ ሰርተናል።

ኮሚሽኑ ሥራ በጀመረባቸው ባለፉት ሁለት ዓመታትም በርካታ ቦታዎች ሂደናል፤ ከበርካታ ባለድርሻ አካላትና ማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ተገናኝተናል። ይህም የወሰደው ጊዜ ቀላል አይደለም። ሀገራዊ ምክክሩ ሁሉንም አካታችና አሳታፊ በሆነ መልኩ ማካሄድ ይኖርበታል። ይህንንም ለማድረግ በ11 ኮሚሽነሮች እና ከኮሚሽነሮች ጋር ከሚሰሩ ባለሙያዎች ጋር ብቻ ይወጠዋል ተብሎ ስለማይገመት ተባባሪ አካላትን መምረጥ ነበረበት።

ይህንኑ መሠረት በማድረግ በመላው ሀገሪቱ ተሳታፊዎችን የሚለዩ ተባባሪ አካላት ተመርጠዋል። ተባባሪ አካላቱም ሀገርን ለማትረፍና ለማጽናት ብሎም የተሻለች ሀገር ለማድረግ ተልዕኮ ያለው የምክክር ሂደት መሆኑን ተገንዝበው ውግንናቸው ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ ብቻ እንደሆነ እንጂ ለፖለቲካ ፓርቲ ወይም ለአንድ ወገን እንዳልሆነ እንዲያውቁት ለማስቻልም ስልጠናና ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል።

እነዚህ ተባባሪ አካላትም ወደየወረዳቸው ሄደው ከየወረዳው የተለዩ የማህበረሰቦች ተወካዮቻቸውን እንዲያሳውቁ አድርገዋል። በአጠቃላይም ምክክሩ ላይ የሚሳተፉ ተወካዮች የመምረጥ ሂደትም በሀገሪቱ 10 ክልሎችና 2 ከተማ አስተዳደሮች ተካሂዷል።

እንዲሁም ምክክሩ የተሳካና ውጤታማ እንዲሆን ሀገር አቀፍ መሆን ስላለበት የአማራ ክልል እና ትግራይ ክልል መካተት ይኖርባቸዋል። ለዚህም በአማራ ክልል ባጋጠመው በጸጥታ ችግር ምክንያት የተፈለገውን ያክል ማከናወን ባይቻልም መሰልጠን ከሚገባቸው 2600 ተባባሪ አካላት ውስጥ 1811 ተባባሪ አካላትን አሰልጥነናል። እነዚህም በየወረዳቸው በመሄድ የልየታ ሥራ የሚሰሩ ይሆናል። በትግራይ ክልልም ይህንን ምዕራፍ ለመጀመር በሂደት ላይ ነን።

ተሳታፊዎች ከተለዩ በኋላ ቀጣዩ ምዕራፋ በክልል ደረጃ አጀንዳ ማሰባሰብ ነው። አጀንዳ የሚሰበሰብበት የአሰራር ሥርዓት ዘርግተን ወደ ተግባር ገብተናል። እስካሁንም በአዲስ አበባ፤ በጋምቤላ፤ በቤኒሻንጉል፤ በድሬዳዋ እና በሀረሪ ክልል አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራዎች ተከናውነዋል።

አዲስ ዘመን፡- የምክክር ኮሚሽኑ ታጣቂ ኃይሎችን ወደ ምክክር ለማስገባት ያደረገው ጥረትና የተገኘ ውጤት ምን ይመስላል?

ኮሚሽነር መላኩ፡– የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በዋነኝነት በተለያዩ አካላት መካከል ያሉ አለመግባባቶችንና የሃሳብ ልዩነቶችን በንግግርና በውይይት ለመፍታት አላማ ይዞ እየሰራ እንደሚገኝ ይታወቃል። በዋነኝነት የምክክርን አስፋላጊነትና በምክክር የማይፈታ ማንም ጥያቄ እንደሌለ ለማስገንዘብም ሰፊ ሥራ ተሰርቷል፤ እየተሰራም ነው። ሕዝብ በምክክርና በውይይት ካመነ በምክክር ሂደት ላይ ለማሳተፍ አያዳግትም።

ለዚህም የመጀመሪያው ርምጃ እና ከ50 በመቶ በላይ ሊወሰድ የሚችለው ተግባር ምክክር የችግሮቻችን መውጫ መፍትሔ ነው ብሎ ማመንና ማሳመን ብሎም ለሀገር ሰላም ግንባታ ምክክር አስፈላጊ ነው የሚል እምነት ያደረበትን ሕዝብ ማግኘት ነው።

በዚህም ምክክርና ውይይት ለችግሮቻችን መውጫ መንገድ መሆኑ የሚያምን ሕዝብ በዚህ ምክክር ሁሉም መሳተፍ አለበት ብሎ በሌሎችም ላይ ጫናም ሊፈጥር ይችላል። በምክክር አይደለም ችግራችን ሊፈታ የሚችለው፤ በነፍጥ ነው ወይም በጠመንጃ ኃይል ነው ልንፈታ የምንችለው ብለው የሚያስቡ ወገኖቻችንም ጭምር ለማሳመንና በእነሱ ላይ በጎ ተጽዕኖ ለመፍጠር የግድ ሕዝቡ ይሁንታ የሰጠው ሂደት መሆን አለበት። በሌሎችም ላይ በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል።

ምክክርን እንደዋነኛ የችግር መውጫ የተቀበለ ሕዝብ ችግሮችን በነፍጥና በጠመንጃ ኃይል ይፈታል የሚል እምነት ያላቸውን አካላት ወደ ምክክር ለመመለስና በጎ ተጽእኖ ለመፍጠር አያቅተውም። ይህንኑ መነሻ በማድረግም ኮሚሽኑ የሀገሪቱ ክፍል የሚገኙ የታጠቁ ኃይሎችንና የተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ምክክሩ እንዲመጡ በማድረግ የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች በውይይትና በምክክር መፈታት ስላለበት ተሳታፊ ለማድረግ ጥረት አድርጓል።

በዚህም እስከዛሬ የተገዳደልነውና የተጎዳዳነው ይበቃናል። ከዚህ በኋላ በሰላም ነው ችግሮችን መፍታት ያለብን። ሰላማዊ መንገድ ስልጡን መንገድ ነው። ምክክር ሰዎች የማይገደሉበት፣ የማይፈናቀሉበት፣ የማይሰደዱበት፣ ንብረት የማይወድምበት የሰላም መንገድ መሆኑን በመረዳት ከነምክንያቶቻችሁ ኑ እና ተነጋገሩ ብሎ ለማስማማትና በጎ ተጽዕኖ ለመፍጠር ጥረት ተደርጓል።

በግጭት ውስጥ ለሚገኙ አካላትም እየሄዱበት ያለው መንገድ አዋጭ እንዳልሆነ ለማስረዳት ሞክረናል። አዋጭና ኪሳራ የሌለበት መንገድ የምክክር መንገድ ነው። በምክክር ያለ ምንም ኪሳራ ችግሮቻችንን መፍታት እንችላለን። በእውነት እና በሀቅ ከተነጋግርን ወደ ሰላም መምጣት እንችላለን።

አስፈላጊ ከሆነ ሶስተኛ ወገኖችም ባሉበት መነጋገር ይቻላል ማማ ከሀገር በላይ አይደለም። ምንም ነገር ከሕዝብ በላይ አይደለም። ስለዚህ ሁሉም በተረጋጋ ሁኔታ ቁጭ ብሎ መነጋገርና መወያየት መቻል አለበት የሚል ጥሪ አድርገናል። መንግሥት የምክክር ኮሚሽኑ የሚጠይቀውን ለማድረግ ጥሪውን ተቀብሎ ፍቃደኝነቱን አሳይቷል። ሌሎችንም እየጠበቅን ነው። ወደፊትም ጥረቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

ኮሚሽኑ ምክክሩን አስመልክቶ ግንዛቤ ለመፍጠር ያደረገው ጥረትም ፍሬ እያፈራ መሆኑን ተሳታፊ በለየባቸው እና አጀንዳ በተሰበሰበባቸው አካባቢዎች ያሉ ተወካዮች ያሳዩት ፍላጎት ምስክር መሆን ይችላል። በእነዚህ አካባቢዎች ለሰላም ያለው ፍላጎት እና ጽናት እንዲሁም በምክክሩ ላይ የመሳተፍ ፍላጎትና የነቃ ተሳትፎ የሚያስደስት ነው። ሕዝቡ በዚህ ዓይነት አስከፊና አሰቃቂ ሁኔታ መቀጠል እንደሌለብን ሕዝቡ ተረድቷል። ሀገር ሰላም ውላ እንድታድር እና ዜጎች በሀገራቸው ተረጋግተው መኖር እንዳለባቸው አብዛኛው ሕዝብ ይስማማል። ስለዚህም ሀገራዊ ምክክሩ ቢያንስ የጋራ ግንዛቤ ከመፍጠር አንጻር ግቡን መትቷል ማለት ይቻላል።

አዲስ ዘመን፡- የምክክር ኮሚሽኑ አጋጠሙኝ የሚላቸው ችግሮች ምንድን ናቸው?

ኮሚሽነር መላኩ፡- በሂደቱ ላይ ያጋጠሙ ችግር የተሳሳተ ግንዛቤን የተመለከተ ነው። በአብዛኛው የማህበረሰብ ክፍል በኩል ምክክር ኮሚሽኑን መንግሥት እንዳቋቋመው እና የኮሚሽኑ አባላትም መንግሥትን ለማሸጋገር የሚሰሩ ተደርጎ መወሰዳቸው የተሳሳተ እሳቤ ነበር። ይህም ሙሉ ለሙሉ ስህተት ነው። ይህ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ነው የተቋቋመው። አዋጁን ደግሞ የሚያወጣው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተቋቋመ መሆኑ ደግሞ የነጻ እና ገለልተኛነቱ መለያው ነው። ከኮሚሽኑ በተጨማሪ ልክ እንደ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የእንባ ጠባቂ ተቋም የመሳሰሉት በሙሉ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ የተቋቋሙ ናቸው። ተጠሪነታቸውም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው። ተጠሪነታቸውም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆኑ ነፃና ገለልተኛነታቸውን ጥያቄ ውስጥ የሚያገባ አይደለም። ነፃና ገለልተኛነት የሚረጋገጠው በኮሚሽኑ አቋም፤ ድርጅቱን በሚመሩት ሰዎች አቋም ላይም ጭምር በመሆኑ ይህ ሁሉ ተረጋግጦ ነው ወደ ሥራ የተገባው። በኮሚሽኑ ሥራ ውስጥ ማንም ጣልቃ ገብቶ አያውቅም፤ እንዲገባብንም አንፈቅድም።

የውጭ ኃይላትም ሆነ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ የሀገር ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊሆኑ ይችላሉ፣ ሚዲያ ሊሆኑ ይችላሉ፣ መንግሥት ሊሆን ይችላል አንዳቸውም በዚህ ሂደት ላይ ተጽዕኖ ሊያሣድሩ አልፈቀድንም፤ አንፈቅድምም። የተቋማችንን ነፃነታችንንና ገለልተኛነታችንን የምናረጋግጠው እኛ ነን። ለዚህም ኮሚሽኑ ያለ ምንም ጣልቃ ገብነት ነፃና ገለልተኛ በሆነ መልኩ እየተገበረ ይገኛል። የትኛውም አካልም በዚህ ሂደት ላይ ተጽእኖ እንዲያሳርፉ አይፈቀድም።

እንዲሁም ከጸጥታ አንጻር በትግራይና ክልል ፕሪቶሪያው ስምምነት ምክንያት የመሳሪያ ድምጽ የማይሰማበት ሁኔታ ነው ያለው። በቀጣይ ትግራይ ገብተን የምንሰራ ይሆናል። በአማራ ክልል በአንዳንድ ቦታዎች ያለው የጸጥታ መደፍረስ ሁኔታ የተወሰነ ተጽዕኖ አሳድሯል።

አዲስ ዘመን፡- በምክክር ሂደቱ አካታችነት ምን ይመስላል?

ኮሚሽነር መላኩ፡- እንደ ሀገር ለሚደረገው የምክክር ሂደት ውጤታማ እንዲሆን ኮሚሽኑ ከሚከተለው መርሆዎች አንደኛው አካታችነት ነው። በዚህም በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል የሚገኙ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ ተጽእኖ ፈጣሪዎች፣ መምህራን፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመሳሰሉት ከተለያዩ ቦታዎች የተመረጡ ተወካዮች በምክክር ሂደቱ ላይ እያሳተፉ ነው።

በዚህ ምክክር ላይ ሁሉምን አሳታፊ ማድረጉ ሁሉም አሉኝ የሚላቸውን ጥያቄዎች እንዲያነሱ ዕድል የሚሰጥ ነው። በተለይም ሴቶችና አካል ጉዳተኞች በተለያዩ አለመግባባቶችና ግጭቶች ምክንያት በሚደርሱ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጉዳቶች ዋነኛ ተጠቂ በመሆናቸው የግጭቶችን አስከፊነት ለመረዳት ብሎም መፍትሔ ለማበጀት ተሳትፏቸው በእጅጉ ይረዳል።

እንዲሁም ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የሚገኙ አካላት ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ተጽእኖ ፈጣሪዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉም አንድ በሚያደርጋቸው ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ጥያቄዎቻቸውን በማቅረብ፣ በመነጋገርና መፍትሔ በማበጀት የጋራ አንድነት የጋራ ሰላምና እድገት እንዲኖር ለማድረግ እየተሰራ ነው። ኮሚሽኑ ይሄንን በመወጣት ረገድም እስካሁን ባለው ሂደትም የተሳካ ሥራ ሰርቷል ማለት ይቻላል።

አዲስ ዘመን፡- አጀንዳ ማሰባሰብ ወሳኝ ሂደት ከመሆኑ አንጻር እስካሁን ያለው ውጤታማነት እንዴት ይለካል?

ኮሚሽነር መላኩ፡– የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ሀገራዊ መግባባት ሊደረግባቸው ያስፈልጋል የሚሏቸውን እጅግ መሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች በሕዝባዊ ውይይት የሚሰበስቡበት ወሳኝ ምዕራፍ ነው። ኮሚሽኑ በሚተዳደርበት አዋጅ 1265/2014 አንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ 5 ላይ ምክክሩ ተሳታፊዎች ከተለዩ በኋላ በክልሎችና በፌዴራል ደረጃ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ ይካሄዳል ይላል። በዚህም ይህንን መነሻ በማድረግ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ በክልሎች እየተካሄደ ይገኛል።

ኮሚሽኑ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፤ በጋምቤላ ክልል ፤ በድሬዳዋ ከተማ እና በሀረሪ ክልል አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራ ሰርቷል። ይህ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ኢትዮጵያውያን በመካከላቸው ያሉ የሃሳብ ልዩነቶቻችንና አለመግባባቶች መንስኤ የሆኑ ምክንያቶችና መፍትሔዎች ዙሪያ በንግግርና ውይይት መፍታት የሚቻልበትን ሁኔታ የሚያመላክት ነው።

በየዘርፋቸው ብሎም በክልላቸው ያጋጠሙአቸው መሠረታዊ የሚሏቸው መፍትሔ የሚፈልጉ ችግሮች እንዲሁም በሀገር ደረጃ የሚታዩ እጅግ መሠረታዊ ችግሮችን የመለየት ሥራ የተሰራበት ነው። በቀጣይም በሀገራዊ ምክክር ቀርበው ምክክር ሊደረግባቸው ይገባቸዋል የሚለውን መሠረታዊ ችግሮችና ሃሳቦች ይለያሉ። ይህም ምክክር ተደርጎባቸው መፍትሔ ተበጅቶላቸው ሀገር ሰላምና ደህንነቷ የተጠበቀ የምትሆነው ምን ምን ጉዳይ ላይ ብንመካከር ነው የሚለውን የሚለይበት ወሳኝ የምክክር ምዕራፍ ነው። በመጨረሻም በየዘርፉ የተለዩ አጀንዳዎቻቸውን በማጠናከርም የጋራ በማድረግ ለምክክር ኮሚሽኑ ያስረክባሉ።

እስካሁን ባለው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት አንጻርም ሕዝቡ ለሰላም ያለው ፍላጎትና ጽናት ውጤታማ እንደሚሆን አመላካች ነው። ሕዝቡ በሰላም መኖር ይፈልጋል። ሆኖም በሰላም እንዳይኖር ያደረጉትን ያደሩ ቁርሾዎችና አለመግባባቶች በመለየት ለውይይት እያቀረበ ይገኛል። እንደ ኮሚሽንም እነዚህን ነጥቦች በመለየት በቀጣይ ዋነኛ የመወያያ አጀንዳ ሆነው የሚወጡ ይሆናል።

በቅርቡ የተካሄደው የጋምቤላ ክልል አጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይም በክልሉ በግጭት ውስጥ የነበሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙበትና የተወያዩበት እንዲሁም 1300 በላይ ተሳታፊዎች የተሰበሰቡበት መድረክ ሲሆን ይህም የምክክር ሂደቱ አንዱ ውጤት ነው ማለት ይቻላል። ይህንንም በሌሎች አካባቢዎች ተመሳሳይ ችግሮች ባለባቸውና ትጥቅ ትግል ውስጥ የነበሩ አካላት በምክክሩ ላይ ቢሳተፉ በቀላሉ ችግሮቻቸውን ተነጋግረው መፍታት እንደሚችሉ ያመላከተ። ከሚታየው አንጻርም ምክክሩ ውጤታማ ይሆናል የሚል እምነት አለ።

ይህ በሀገሪቱ ተሳታፊዎች በተለዩባቸው 10 ክልሎች እና 2 ከተማ አስተዳደሮች የሚካሄደው አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደትም እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ የሚቀጥል ይሆናል።

አዲስ ዘመን፡- ቀጣይ የኮሚሽኑ አቅጣጫዎች ምንድን ናቸው?

ኮሚሽነር መላኩ፡- አጀንዳ ከየክልሉ እና ከከተማ አስተዳደሩ ከተሰበሰበ በኋላ ወደ ኮሚሽን ጽ/ቤት በማምራት የተሰበሰቡትን አጀንዳዎች በባለሙያዎች በየፈርጁ የመለየት ሥራ ይሰራል። ከቀረቡት አጀንዳዎች ውስጥ እጅግ መሠረታዊ የሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮችን ፤ ሀገርን እንደሀገር ለማጽናትና ለማስቀጠል ብሎም የተሻለች ሀገር ለማድረግ የሚረዱን አጀንዳዎች ምንድን ናቸው ብሎ የመለየት ሥራ ይከናወናል። ይህ ከተለየ በኋላ የመጨረሻውን አጀንዳ የሚቀርጸው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክር ቤት ነው።

በተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት መሠረት የተሳታፊዎች የሚለዩበትን ሥርዓት ሆነ አጀንዳ የሚሰበሰብበትን ሥርዓት የሚወስነው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክር ቤት ነው። አሁንም ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ይሆናሉ የሚባሉ አጀንዳዎች የመወሰን ስልጣን ያለው ምክር ቤቱ ነው። በዚህም ሀገሪቱ አሁን ካለችበት ሁኔታ ወጥታ ወደ ሰላም ልትሸጋገር የምትችለው እነዚህ አጀንዳዎች ቀርበው ምክክር ሲደረግባቸው ነው የሚለውን አጀንዳዎችን የመቅረጽ ተግባር ምክር ቤቱ ያከናውናል። ለሀገራዊ ምክክር የሚሆኑ አጀንዳዎች ከተለዩ በኋላ በሀገራዊ ጉባዔው ላይ ምክክር የሚደረግባቸውን አጀንዳዎች ለሕዝብና ለባለድርሻ አካላት ይፋ ይደረጋሉ።

በቀጣይም ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ይጠራል። በዚህም ቁጥራቸው ከ2ሺህ 500 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል። በዚህ ጉባኤም የመፍትሔ ሃሳቦችን ያቀርባሉ። እነዚህን የመፍትሔ ሃሳቦች ኮሚሽኑ በመቀመር ወደ እቅድነትና ፕሮግራም በመቀየር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለሚመለከታቸው አካላት የኢትዮጵያ ሕዝብ ይሄ እንዲሆንለት ይፈልጋል፤ ይሄ እንዲፈጸምለት ድምጽ ሰጥቷል፤ እነዚህ ጥያቄዎች እንዲመለሱለት ይፈልጋል ተብለው በዝርዝር ይቀርባሉ። ይህንን ካቀረበ በኋላም ተግባራዊ የሚደረግበትን እቅድ ይቀይሳል። ለታቀደው እቅድ የሚፈጸምበትም ስልት ይነድፋል። እንዲሁም አፈጻጸሙን ይከታተላል። ሳይፈጸሙ የቀሩትንም ለሕዝቡ የሚያሳውቅ ይሆናል።

በአጠቃላይ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ለማስቀጠል ብሎም አንድነትና ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ሀገራዊ መግባባት የሚፈጠርበት ሂደት አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። ሀገር አቀፍ ምክክር ማካሄድ ለሀገራዊ መግባባት ወሳኝ ነው። ሀገር አቀፍ መግባባት ከመጣ ደግሞ ሀገር አቀፍ ሰላምና አንድነት እንዲሁም ሀገራዊ የሆነ አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ማምጣት ይቻላል። ነፃነቷና ደህንነቷ የተረጋገጠ ሀገር ለመገንባት፤ ለዜጎች ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ሀገር ዜጎች ምቹ ሀገር ለማድረግ፣ ሰዎች የማይሳቀቁባት፣ እንደልብ የሚንቀሳቀሱበትና የሚማሩበት ሀገር እንድትሆን ኮሚሽኑም እየሰራ ነው።

በአሁኑ ወቅት እጅግ መሠረታዊና ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ላሉብን አለመግባባቶች ምክንያት የሆኑ ነገሮችን ከምንጫቸው በሀቅና በዕውነት በመለየት፣ አጀንዳ ቀርጾ ምክክር በማድረግ መግባባት ላይ ለመድረስ፣ መግባባት ላይ የተደረሰባቸውንም ጉዳዮች ተግባራዊ ለማድረግ አዲስ ታሪክ የምንጽፍበት ሂደት ላይ እንገኛለን።

የኢትዮጵያ ሕዝብ በዚህ ታሪካዊና መሠረታዊ በሆነ ሀገራዊ የምክክር ሂደትም ሁሉም የሃሳብ ልዩነት አለኝ የሚል ሁሉ ይህንን ትልቅ እድል መጠቀም ይገባዋል። ቅር ብሏቸው ሕይወታቸውን መስዋዕት በማድረግ ጫካ የገቡ ወገኖቻችን ኢትዮጵያዊያን ናቸው። ጥያቄዎች አሏቸው። ጥያቄዎቻቸውን በአግባቡ በማቅረብ ለውይይት ሆነ ድርድር የሚያደርጉበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት። የኃይል አማራጭ የማያዋጣ እና የማይጠቅም መሆኑን ከዚህ ቀደም አይተናል። አሁንም አይጠቅምም ወደፊትም አይጠቅምም።

ከጉልበት ይልቅ የሚሻለውና የሚጠቅመው በስልጡን አመለካከት ተቀራርቦ በመነጋገርና በመወያየት ችግርን መፍታት አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው። ዜጎች ከኃይል አማራጭ ወጥተው ወደ ውይይትና ምክክር እንዲመጡ የምክክር ኮሚሽኑ ዘወትር ጥሪውን በማቅረብ ላይ ይገኛል።

ማህሌት ብዙነህ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ነሐሴ 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You