አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ዓመታዊ ወታደራዊ ልምምዳቸውን ጀመሩ

አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ዓመታዊ የጋራ ወታደራዊ ልምምዳቸውን ጀምረዋል።

ከትናንት በስቲያ በተጀመረውና “ኡልቺ ፍሪደም ሺልድ” የሚል ስያሜ በተሰጠው ልምምድ ላይ 19 ሺህ የደቡብ ኮሪያ ወታደሮች እየተሳተፉ ሲሆን ልምምዱ እስከ ነሃሴ 23 2016 ይቆያል ተብሏል።

የዚህ ዓመታዊ የጦር ልምምድ አካል የሆነው የሀገራቱ አየር ሃይሎች ለአምስት ቀናት የሚያካሂዱት ልምምድም ይጠበቃል። በአየር ልምምዱ ከ200 በላይ የደቡብ ኮሪያ እና የአሜሪካ የውጊያ ጄቶች እንደሚሳተፉ የደቡብ ኮሪያ አየር ሃይል አስታውቋል።

ልምምዱ የሰሜን ኮሪያን አውሮፕላኖች እና ክሩዝ ሚሳኤሎች እንዴት መምታት እንደሚቻል በምስለ በረራ (ሲሙሌሽን) በመታገዝ እንደሚካሄድ ነው የተገለጸው።

በደቡብ ኮሪያ 28 ሺህ 500 ወታደሮች ያሏት አሜሪካ ምን ያህል አውሮፕላኖችን በልምምዱ እንደምታሳትፍ አልተገለጸም። ሰሜን ኮሪያ የጎረቤቷን እና የአሜሪካ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ የኒዩክሌር ጦርነት ለመጀመር የሚደረግ ዝግጅት ነው በሚል በተደጋጋሚ ተቃውማለች።

ሀገራቱ ልምምድ በጀመሩ ማግስት ሚሳኤሎችን በማስወንጨፍ ቁጣዋን ስትገልጽ መቆየቷም ይታወሳል። ከትናንት በስቲያ ለተጀመረው የሴኡልና ዋሽንግተን የጋራ ወታደራዊ ልምምድ የምትሰጠው ምላሽም እየተጠበቀ ነው።

ፒዮንግያንግ ለሚሳኤልና ኒዩክሌር ፕሮግራሟ ልዩ ትኩረት ብትሰጥም አየር ሃይሏ ዘመኑን የማይዋጅ እንደሆነ ይነገራል። አብዛኞቹ የጦር አውሮፕላኖቿም ሶቪየት ሠራሽ ሚግ ጄቶች ናቸው።

እነዚህን አውሮፕላኖች ለማዘመንና በአዲስ ለመተካት የምታደርገው ጥረት በምዕራባውያን በተጣሉባት ማዕቀቦች ምክንያት ፈተና ገጥሞታል። በመሆኑም ከሴኡል ሊቃጣ ለሚችል ጥቃት በአጭር እና ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎች ምላሽ ለመስጠት መዘጋጀትን መርጣለች ይላል የሬውተርስ ዘገባ።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 15 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You