በቴልአቪቭ የደረሰው ከባድ ፍንዳታ የሽብር ጥቃት መሆኑን ፖሊስ አስታወቀ።
በእስራኤል ቴልአቪቪ እሁድ ምሽት የደረሰው ከባድ የቦምብ ፍንዳታ የሽብር ጥቃት እንደሆነ ማረጋገጡን የእስራኤል ፖሊስ እና የሀገር ውስጥ የደህንነት ኤጀንሲ በትናንትናው ዕለት አስታውቋል።
ምኩራብ አካባቢ የፈነዳውን ቦምብ የተሸከመው ግለሰብ መገደሉን እና አንድ መንገደኛ ደግሞ መቁሰሉን ፖሊስ ገልጿል። “አሁን ላይ ይህ ጥቃት የሽብር ጥቃት መሆኑ ተረጋግጧል” ብለዋል ፖሊስ እና ደህንነት ትናንት ባወጡት የጋራ መግለጫ።
ይህ ፍንዳታ የተከሰተው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን 10 ወራትን ያስቆጠረው የእስራኤል እና የሀማስ ጦርነት በተኩስ አቁም እንዲቋጭ ጥረት ለማድረግ ቴልአቪቭ ከደረሱ ከአንድ ሰዓት በኋላ ነው።
በቀጣናው ያለው አሁናዊ ውጥረት የተኩስ አቁሙን መደረስ አስፈላጊነት አንገብጋቢ አድርጎታል።
የሀማስ የፖለቲካ መሪ ሆኖ ሲያገለግል የነበረው እስማኤል ሀኒየህ በቴህራን፣ የሄዝቦላ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ ሹክር በቤሩት ከተማ ዳርቻ መገደል በመካከለኛው ምስራቅ የነበረው ውጥረት ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንዲደርስ አድርጎታል።
ኢራን እና አጋሮቿ ሀማስ እና ሄዝቦላ ለግድያዎቹ እስራኤልን ተጠያቂ አድርገዋል፤ እንደሚበቀሏትም ዝተዋል።
ኢራን የበቀል ርምጃዋን ልትተው የምትችለው፣ በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረሰ ብቻ መሆኑን ገልጻlች። የተኩስ አቁም ንግግሩ ችላ መባል የለበትም የምትለው አሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯን ብሊንከንን ወደ እስራኤል ልካለች።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ነሐሴ 14 /2016 ዓ.ም