በነገዋ የሴቶች ማዕከል ነገዋን ያሳመረች ወጣት

የዛሬዋ የሴቶች ባለታሪካችን ሰሚራ መሐመድ ሰይድ ትባላለች። በአፍላነት እድሜ ነበር ከቤተሰቦቿ ጋር ተጣልታ ወደ ጎዳና የወጣችው። በጎዳና ሕይወት ለተለያዩ ሱሶች ከመዳረጓ እና ከመጎሳቆሏ የተነሳ በአካባቢው ኤች አይቪ ቫይረስ እንዳለባት ይታሰብ ነበር። በዚህም ተነሳ በማህበረሰቡ ትገልል ነበር።

ከቤተሰብ ከወጣች በኋላ ከጎዳና እስከ ኡጋዴን፤ ከኡጋዴን እስከ ሳውዲ አረቢያ መሄድ ችላለች፤ ሳውዲ እያለች ባጋጠማት ችግር የተነሳ ወደ ሀገሯ ለመመለስ ተገደደች። ከተመለሰች በኋላ መግቢያ አልነበራትምና ተመልሳ ወደ ጎዳና እና ሱስ ተመለሰች። በአጠቃላይ ለ16 ዓመታት በሱስ ሕይወት ቆይታለች። በእራሷ ተስፋ በቆረጠችበት እና የሱስ ፍጆታዋም በጨመረበት ወቅት ነበር ለነገዋ የሴቶች ማገገሚያ ማዕከል የመግባት እድሉን ያገኘችው።

ሰሚራ ትውልድና እድገቷ አዲስ አበባ ከተማ ሲሆን፤ ለወላጆቿ የመጀመሪያ ልጅ ናት። ትምህርቷን በመድኃኒዓለም ትምህርት ቤት እስከ ዘጠነኛ ክፍል ተምራለች። “በትምህርቴ ደህና የነበርኩ ቢሆንም፤ መቀጠል የቻልኩት እስከ ዘጠነኛ ክፍል ነው። ከዛ በኋላ ከቤተሰብ ጋር ተጣልቼ ከቤት ወጣሁ።” ስትል ትናገራለች።

ከቤት ወጥታ ለጎዳና ሕይወት ለመዳረጓ እራሷን የምትወቅሰው ባለታሪኳ “አሁን ትምህርት ካገኘሁ በኋላ ቆም ብዬ ሳስበው፤ ከቤት ለመውጣቴ ጥፋተኛዋ እኔ ነኝ።” ስትል ትናገራለች።

በቤተሰብ ትምህርቷን ጠንክራ እንድትማር በማለት ቁጥጥር በሚያደርጉበት ወቅት፤ በእልህ ከቤተሰቧ በተቃራኒ የተለያዩ ድርጊቶችን ትፈጽም ነበር። በዚህም ላይ በጥፋት ላይ ጥፋት እየጨመረች መስመር ለቀቀች። “ለደቂቃ ያጠፋኋት ጥፋት ለዓመታት እንድንከራተት አድርጋኛለች።” ስትል የወላጆቿን ተግሳጽ ችላ ማለቷ ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈላት ትገልጻለች።

ሰሚራ ከቤት ከወጣች በኋላ አንዳንድ ሆቴሎች ላይ ተቀጥራ ለመሥራት መመኮሯ አልቀረም። ነገር ግን ሥራው ቀላል አልሆነላትም። ስለዚህ ምርጫዋ ጎዳና ሆነ። በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎችም የጎዳና ሕይዎትን ተያያዘችው። “ከቤት ትንሽ ልጅ ሆኜ ነው ወጥቼ የቀረሁት፤ ከዛን በኋላ በአራት ኪሎ፣ መሳለሚያ እና ተክለሃይማኖት ጎዳናዎች ላይ ለዓመታት ኖሪያለው።” ስትል መለስ ብላ ሕይወቷን ታስታውሳለች።

ባለታሪኳ በጎዳና ሕይወት ለ16 ዓመታት ቆይታለች። “ጎዳና ላይ ስኖር አላፊ አግዳሚውን በመለመን ነበር የዕለት ጉርሴን የማገኘው። ገንዘብ ካላገኘሁ እና በጣም ከራበኝ ሆቴል ቤቶች በመሄድ ምግብ እለምናለሁ።” ስትል የዕለት ጉርስ ለማሟላት የነበረውን ውጣ ውረድ ትናገራለች።

ሰሚራ ወደ ጎዳና በመውጣቷ ለሱስ ሕይወት ተዳርጋለች። የሱስ ተጋላጭ በመሆኗም ከማህበረሰቡ ልትገለል ችላለች። ሱስና የማህበረሰብ ማግለል ተደምረው ሥራ እንዳታገኝ ግርዶሽ እንደሆኑባት ታስውሳለች። ሥራ ብታገኝ እንኳን የሱስ ተጽዕኖ ስላለ በተቀጠረችበት ሥራ ለመዝለቅ እንደምትቸገር ትናገራለች።

ሱስ ምን ያህል ጉዳት እንዳደረሰባት የምትገልጸው ባለታሪኳ፤ “በሱስ ውስጥ ያሉ ሰዎች የተረጋጋ ሕይወት የላቸውም። አንድ ቦታ ሆነው ሥራ መሥራት አይችሉም። በዚህ ላይ የሚቀጥረን ድርጅትም ሆኑ ሰዎች ተገቢውን ክብር ስለማይሰጡን ሥራውን የመቀጠል ሞራል አይኖረንም ” ትላለች።

“አንዳንዴ ከወረዳ እኛን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ነገሮች ቢመጡ እንኳን፤ አይ እነዚህ አጫሽ ናቸው፣ ጫት ቃሚ ናቸው፤ ጠጪ ናቸው ይሉና ይተውናል።” ስትል ትገልጻለች። ባለታሪኳ ከቤት ከወጣች በኋላ ለሁለት ዓመታት ያህል ሳውዲ አረቢያ ሄዳ ነበር፤ ሳውዲ ከነበረችባቸው ሁለት ዓመታት ውጭ ሁሉንም ዓመታት በሱስ ነበር ያሳለፈችው።

ረጅም ዓመት ሳውዲ የኖረ የአባቷ ዘመድ እንዳላት የምትገልጸው ሰሚራ፤ በእሱ አማካኝነት ነበር ወደ ሳኡዲ የሄደችው። በወቅቱ ከአዲስ አበባ ጠፍታ ኡጋዴን ነበር የምትኖረው። “ኡጋዴን በመብራት ኃይል ፕሮጀክት የሚሰሩ ሰዎች ነበሩ፤ ከእነሱ ጋር አንድ ሰው ተከትዬ ነበር የሄድኩት። አጋጣሚ ደግሞ እዛ ሥራ አገኘሁ።” ትላለች።

ወደ ሳውዲ እንድትሄድ አባቷ ነበር አድራሻዋን ፈልጎ ለሚወስዳት ዘመዷ የሰጠው። አካሄዷ በህጋዊ መንገድ ቢሆንም ሳውዲ በተፈጠረ ችግር ሁለት ዓመት ብቻ ነበር የቆየችው። ተይዛም ወደ ኢትዮጵያ እንድትመጣ ተደረገች።

“ሳውዲ ውስጥ ችግር ተፈጠረና የሚያሰራኝ ሰው ይዞ ለፖሊስ የሰጠኝ። ብዙም እስር ቤት ሳልቆይ፤ እንደ እድል ሆኖ በሶስት ቀን ውስጥ ነው ወደ ኢትዮጵያ የተመለስኩት።” የምትለው ሰሚራ ከሳውዲ ከተመለሰች በኋላም ወደ ቤተሰቦቿ አልሄደችም።

“ከሳኡዲ እንደተመለስኩ የነበረኝን ስልክ ሸጬ ቅያሪ ልብስ ገዛሁና ፤ ሂጃቤን አውልቄ ተመልሽ የጎዳና ኑሮን ቀጠልኩ። በወቅቱ ለስደት ተመላሾች ተብሎ አንዳንድ ነገሮች እየተደረጉ ነበር እሱንም ችላ አልኩኝ። ከሰው ጋር ተቀላቅሎ መረጃ ለማግኘት እኔ ቀጥታ ወደ ሱስ ስለገባሁ አልቻልኩም።” ስትል ትናገራለች።

ሰሚራ ወደ ቤተሰቦቿ ለመመለስ ብታስብም በምትኖርባቸው አካባቢዎች የሚያጋጥሟት ሁኔታዎች ለመመለስ አልፈቀዱላትም ነበር። “ጎዳና ከወጣሁ በኋላ በየአካባቢው የምመሰርተው ሕይወት ከተለያዩ ሰዎች ጋር ትዳር እንድመሰርት አድርጎኛል። በትዳሩም ልጅ ስለወለድኩ ለመመለስ ከበደኝ። “ትላለች።

በተለያዩ ጊዚያት ትዳር ብትመሰርትም ተረጋግታ መቀመጥ እንዳልቻለች የምትገልጸው ባለታሪኳ፤ “አገባና ሳይመቸኝ ሲቀር ልጆቹን ቁጭ አደርግና ተመልሼ ወደ ጎዳና ነው የምወጣው። የሱስ ሕይወት ልጆቼን እንኳን ተረጋግቼ እንዳላሳድግ አድርጎኛል ” ስትል ትገልጻለች።

“በዚህ ሕይወት ውስጥ አራት ጊዜ በምጥ ተፈትኜ አራት ልጆችን ወልጃለሁ” የምትለው ሰሚራ ምንም እንኳን ዘጠኝ ወር በሆዷ ተሸክማ በምጥ ተጨንቃ ብትወልድም እንደ እናት የማሳደግ ወጉ አልደረሳትም። “የዛሬ አራት ዓመት መብራት ተያይዞ የምንኖርበት ሸራ ቤት ተያይዞ የአንድ ዓመት ከስምንት ወር ልጄ ሞቶብኛል።” ስትል በሀዘን ሁኔታውን ታስታውሳለች።

ሰሚራ ተክለሃይማኖት አካባቢ ሆቴል ውስጥ ተቀጥራ እየሰራች አርግዛ ሴት ልጅ ወልዳለች። ነገር ግን የልጅቷ አባት፤ አባትነቱን ስላላመናት፤ በልደታ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ አማካኝነት ተፈራርማ ለማደጎ ሰጥታታለች። “ሁለት ልጆቼ ደግሞ ኳስ ሜዳ እና እንቁላል ፋብሪካ አካባቢ በየአማቾቼ ቤት ነው የሚኖሩት።” በማለት ትናገራለች።

ሁለቱን ልጆቿን አግኝታቸው እንደማታውቅ የምትናገራው ሰሚራ” የቱንም ያህል ውስጤ ሊያገኛቸው ቢናፍቅም፤ እበትም ትል ይወልዳል እንደሚባለው፤ ምንም ላደርግላቸው ስለማልችል እና እንዳይበላሹ በማለት አልጠጋቸውም። ምንም ማድረግ እንደማልችል ውስጤ ስለሚያስብ በሱስ ውስጥ ነው እራሴን የምደብቀው።” ትላለች።

ሰሚራ ወደ ለነገዋ የሴቶች ተሃድሶና ልህቀት ማዕከል ልትገባ የቻለችው በአንዲት በምታውቃት ሴት አማካኝነት ነው። ባለታሪኳ የምትኖረው አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ሲሆን፤ እንድትመጣ የጠቆመቻት ሴት የአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ናት። ሴትየዋ ሰሚራ ለመሄድ ፍቃደኛ መሆኗን ከጠየቀቻት በኋላ፤ ወደ ማዕከሉ ለሚያመጧቸው ሰዎች በመጠቆም እንድትመጣ አደረገቻት።

“እኔ በአጋጣሚ ለውሎ የሚሆነኝን 50 ግራም ጫትና ሲጋራ ይዜ ወደ ሸራ ውስጥ እየገባሁ እያለ፤ እንደዚህ ዓይነት ማዕከል አለ ትሄጅያለሽ? ብላ ስትጠይቀኝ አዎ አልኳት። ከዛን ከአንድ ሰዓት በኋላ የሚወስደኝ መኪና እንደሚመጣ ነገረችኝ። መኪናው ሲመጣ ተሳፍሬ መጣሁ።” ስትል ታስረዳለች፡

ወደ ማዕከሉ ደርሳ ገና ከመኪና እንደወረደች የቆራጥነት ስሜት እንደተሰማት በመግለጽ፤ በቀድሞው ኑሮዋ ብዙ በደል እንደደረሰባት የምታስታውሰው ባለታሪኳ፤ “አንድ ሰው አደገኛ ነገር ውስጥ ለመግባቱ የሚያደርጋቸው ድርጊቶች፣ የሚውልበት ቦታ እና የሚገኛቸው ሰዎች ይወስናሉ።” በማለት ትናገራለች።

ወደ ማዕከሉ ከገባች በኋላ እየቆየች ስትመጣ ለራሷ የነበራት አስተሳሰብ ፤ አመለካከት እየተለወጠ መጣ። እራሷን መንከባከብ እና ለራሷ መጠንቀቅ ጀመረች። “አሁን ላይ እኔ ካልተናገርኩ በስተቀር ጫት እንደምቅም እና ሲጋራ እንደማጨስ ማንም አያውቅም። በቃ እዛ ነው ሱሶቼን ጥያቸው የመጣሁት ” ትላለች።

ሰሚራ ወደ ማዕከሉ ከመግባቷ በፊት በሱስ ምክንያት ኪሎዋ በጣም ዝቅተኛና በጣም ቀጫጫ እንደነበረች ታስረዳለች። “ወደ ማዕከሉ ስገባ ኪሎዬ 42 ነው። የሚሰማኝ ህመም ባይኖርም ሰውነቴ በጣም እየከዳኝ ነበር። በአጠቃላይ ለሚያየኝ ሰው እብድ ነበር የምመስለው።” ስትል ታስረዳለች።

ወደ ማዕከሉ ከገባች በኋላ በተደረገላት እንክብካቤ ኪሎዋ እየተመለሰ መጣ። “የነገዋ የሴቶች ማዕከል የመንግሥት ነው ሲባል እንደዚህ አልጠበኩም፤ ከጽዳት ጀምሮ ያለው ነገር በጣም ልዩ ነው። ሻወር ከፈለግን ቀዝቃዛ እና ሙቅ ውሃ አለ፤ ስፖርት መሥራት ከፈለግን ጂም ቤት ስላለን ሄደን እንጠቀማለን። የጥርስ ሳሙና ቡሩሽና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች በሥርዓት ነው የሚሰጡን። እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ይሟሉልኝ የነበረው አባቴ ቤት በነበርኩበት ሰዓት ነው።” ትላለች ።

ባለታሪኳ ቀደም ብላ ለነገዋ ማዕከልን ለማስገንባት በከንቲባ አዳነች አቤቤ የመሠረተ ድንጋይ ሲጣል፤ በአንዲት ሴት አማካኝነት መጥታ የነበረ ቢሆንም፤ ወደ ማዕከሉ ለመምጣት ስትነሳ ወደዚህ ማዕከል እየመጣች እንደሆነ አላወቀችም ነበር። በወቅቱ የመሠረተ ድንጋይ ሲጣል ብትመጣም ያስገቡኛል የሚል ሃሳብ እንዳልነበራት ትናገራለች።

ሰሚራ በሱስ ሕይወት ውስጥ እንደመኖሩዋ ወደ ማዕከሉ ገብታ ያለውን ሥርዓት አክብራ እራሷን ለመቀየር አልፈራችም። ምክንያቱም ቀድመው አብረዋት በሸራ ቤት ከሚኖሩ ጓደኞቿ በኤች አይቪ ቫይረስ ምክንያት የበርካቶች ሕይወት አልፏል።” ሲስተር ቤት በመባል የምትታወቅና የታመሙትን የምታነሳ ነበረች፤ አንዳንዶቹ እሷ ወስዳቸው እየታከሙ የሞቱ ሲሆን፤ ሌሎች ደግሞ ሸራ ውስጥ እየታመሙ የመጨረሻ ደረጃ ደርሰው ሕይወታቸው ያለፈ አሉ ። “ስትል ትገልጻለች።

ሰሚራ አብረዋት የነበሩ ጓደኞቿ ወደ ሲስተር ቤት ሲገቡ፤ ቫይረሱ ስላልነበረባት የመግባት እድሉን አላገኘችም ነበር። በወቅቱ ኤች አይቪ እንኳን ተመርምሮ መድኃኒት የመውሰድ ግንዛቤ የለም። በዚህ ምክንያት ብዙዎቹ አልፈዋል።” እኔ ደግሞ በሱስና በችግር ምክንያት ሰውነቴ በጣም ከመክሳቱ የተነሳ በማህበረሰቡ ዘንድ ኤች አይቪ በደሜ እንዳለብኝ ነው የሚታወቀው። ” ስትል ታስረዳለች።

ኤች አይቪ በደሟ ውስጥ እንደሌለ ብትናገርም አንድም ሰው አያምናትም።” ወንድ እንኳን እኔን ቢጠጋኝ ጠርተው ኤች አይቪ አለባት ብለው ሲናገሩ በጆሮዬ እሰማ ነበር። ” ትላለች። ሰሚራ ወደ ማዕከሉ ገና ስትገባ በተደረገላት የኤች አይቪ ምርመራ፤ በተጨማሪም ከሶስት ወር በኋላ በተደረገላት ምርመራ ከኤች አይቪ ነጻ መሆኗን አረጋግጣለች። በዚህም “ማዕከሉ ነጻነቴን አውጆልኛል” ስትል ዓይኖቿ በደስታ እምባ ተሞልቶ ትገልጻለች።

ሰሚራ በርካታ ዓመታትን በሱስ ሕይወት ስላሳለፈች፤ ወደ ማዕከሉ ከገባች በኋላ ከሱስ ለመላቀቅ በጣም ተቸግራ እንደነበር እና ትዝ እያላትም ትቸገር ነበር። የሱስ ስሜት በሚሰማት ሰዓት ባኞ ቤት ገብታ ሙቅ ውሃ ውስጥ ቁጭ እንደምትል ትገልጻለች።

“ብዙ ዓመት በሱስ ስላሳለፍኩ ተጽዕኖ ያሳድርብኛል ብዬ ፈርቼ ነበር። ያሳላፍኩት ችግር ይመስለኛል ጎበዝ እንድሆን ያደረገኝ። ሱሴ በሙቅ ውሃ ተኖ የጠፋ ነው የሚመስለኝ፤ ሌላው ደግሞ ግቢ ውስጥ ያለው ነገር ምቹ እና ጽዱ መሆኑ፤ ጊቢው ነፋሻ መሆኑ ተቋቁሜ እንዳልፍ አድርጎኛል።” ትላለች።

“አዕምሮ የለመደውን ነገር መጠየቁ አይቀርምና እንዳልሳሳት ውጭ ለመውጣት ፈቃድ ላለመጠየቅ እራሴን አሳመንኩት። ምክንያቱም ብሄድም የሚጠብቀኝ የሸራ ቤት ነው። እና ደግሞ ከሚቅሙ ከሚያጨሱ ሰዎች ስለምቀላቀል ተመልሼ ወደዛ ሕይወት መመለስ አልፈለኩም።” በማለት ትገልጻለች።

አሁን ላይ የእለት ተእለት እንቅስቃሴዋ እንደተቀየረ እና ለሃይማኖቷም ያላት መረዳት በመጨመሩ፤ በቀን ውስጥ መደረግ ያለባቸውን ሥርዓቶች ጠብቃ እንደምትከውን ታስረዳለች።”ወደ ሃይማኖቴ እንዳዘነብል አደረገኝ ለጸሎትም ተመቸኝ። በትክክል የእስልምና እምነት ተከታይ ከሆንኩ ከዚህ በፊት የማደርጋቸውን አላስፈላጊ ነገሮች ማድረግ የለብኝም።” ስትል ትናገራለች።

በውስጧ ሰላም እንደሚሰማት የምትናገረው ባለታሪኳ፤ የሚሰማትን ሰላም ለማስጠበቅ ጠዋት 11 ሰዓት ከእንቅልፏ ተነስታ ዱአ አድርጋ፤ ስፖርት ሰርታ ሻወር ውስዳ ቁርስ ከበላች በኋላ ወደ ትምህርት እንደምትገባ ታስረዳለች።

“ወደ ማዕከሉ ከመግባቴ በፊት ሂጃብ እንኳን አልጠመጥምም ነበር፤ ጸጉሬን ፈትቼ ሱሪ ለብሼ ነው የምራመደው። የምትለው ሰሚራ” ያገኘችው የሕይወት ክህሎት ስልጠና ለራሷ ምን እንደሚያስፈልግ፤ ፈጣሪ ምን እንደሚወድ እና ከማህበረሰቡ ጋር በምን መልኩ መኖር እንዳለባት ስላስተማራት፤ እራሷን ለመቀየር እና ከሱስ ለመውጣት ወስና በመነሳቷ፤ ወደ ቀድመው ሕይወቷ እንዳትመለስ በፍጹም ከጊቢው እንዳልወጣች” ትናገራለች።

“እንደዚህ እለወጣለሁ ብዩ አስቤ አላውቅም ፤ አሁን የሆንኳትን እኔን ማመን ይከብደኛል። ይህን አቅም ከየት ነው ያመጣሁት? በማለት እራሴን እጠይቃለሁ። ምናልባት ያሳለፍኩት ሕይወት መሰለኝ እንድጠነክር ያደረገኝ። እኔ ነኝ እንዴ ?እስከምል ድረስ ነው ማዕከሉ የለወጠኝ።” ትላለች።

ሰሚራ በማዕከሉ ያገኘችውን ስልጠና ላንድ ስኬች የሚባል ዘርፍ ነው። በተለይ ለአረንጓዴ ልማትና ለአካባቢ ጥበቃ ተመራጭ ሙያ ነው። ትምህርቱን የመረጠችው ስለትምህርቶቹ በተሰጠው ገለጻ አማካኝነት፤ የአረንጓዴ ልማት አሁን ከተሰጠው ትኩረት ጋር ተያይዞ በቀጥታ ሥራ የምታገኝበት በመሆኑ እንደመረጠች ትናገራለች።

ማጨስ ፣መቃም እና መጠጣት ከማህበረሰቡ ጋር እንዳንቀላቀል፤ ክብር እንድናጣ ፣ ለራሳችን ያለን አመለካከት እንዲወርድ እና ሥራ እንዳናገኝ ግርዶሽ የሚሆንብን ስለሆነ፣ ማንም ሰው ከአላማው ባይወጣ መልካም ነው። ወደ ማዕከሉ በቀጣይ የሚገቡትም ቢሆን፤ ወደ ማዕከሉ ገብተው እራሳቸውን ለመቀየር እንዳይፈሩ እና እድሉን አግኝተው ከገቡ በኋላም ወደ ኋላ መመለስ እንደሌለባቸው ትመክራለች።

በቀጣይ በወሰደችው ስልጠና እራሷን ለማሳደግ እና ሥራዋን ጠንክራ ለመሥራት መዘጋጀቷን የምትገልጸው ባለታሪኳ፤ ለፈጣሪዋ እና ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ በማዕከሉ ከጥበቃ አንስቶ እስከ አስተዳደር ድረስ ላሉት፤ በተጨማሪም ጎዳና ላይ በምትኖርበት ወቅት ሸራ ገዝተው ለሰጧት የሰፈር ሰዎች ምስጋናዋን አቅርባለች።

አመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 14 /2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You