የወሊድ መከላከያ ሕክምና የወሰደው አባወራ ድጋሚ አባት መሆኑን ተከትሎ ክስ መሰረተ

የአራት ልጆች አባት የሆነው ሰው እርግዝና እንዳይፈጠር የሚከላከል ሕክምና ቢያደርግም ሳይፈልግ አምስተኛ ልጅ አባት ለመሆን ተገዷል::

የሕክምና ስህተት የሰራው ተቋም ልጄ 18 ዓመት እስኪሞላው ድረስ የማሳደጊያ ይከፈለኝ ሲል ክስ መስርቷል::

ማክሲም የተሰኘው ሩሲያዊ የ45 ዓመት አባወራ ሲሆን፤ የአራት ልጆች አባትም ነው፡፡ የኢኮኖሚ እና ሌሎች አቅሙን ከግምት ውስጥ በማስገባት ከባለቤቱ ጋር ባደረገው ስምምነት መሰረት ተጨማሪ ልጆችን ላለመውለድ ይወስናሉ፡፡

ዘላቂ የወሊድ መከላከያ ለመውሰድ የተስማሙት እነዚህ ወላጆች አባትየው እርግዝና እንዲፈጠር የሚያደርገውን ወይም የዘር ፍሬ ቱቦ በማስቆረጥ ወይም በእንግሊዘኛው ቫስክቶሚ የተሰኘውን ሕክምና ያደርጋል።

በዘር ፍሬ ቱቦው ላይ ባደረገው የቀዶ ህክምና አማካኝነት ልጅ መውለድ እንደማይችል የተነገረው ይህ ሰውም ባለቤቱ አምስተኛ ልጅ እርጉዝ መሆኗን ትነግረዋለች፡፡

በውጤቱ የተጠራጠረው ይህ ሰውም ድጋሚ ባደረገው ምርመራ አምስተኛ ልጅ አባት ለመሆን የተገደደ ሲሆን፤ ህክምናውን ባደረገለት ክሊኒክ ላይ ክስ መስርቷል፡፡

ቀዶ ህክምናውን ያደረገው ክሊኒክም የተፈጠረውን ነገር ማመን ባለመቻሉ በግለሰቡ ላይ ባደረገው ድጋሚ ምርመራ አሁንም ማስረገዝ እንደሚችል ያረጋግጣል፡፡

ክስ የተመሰረተበት ክሊኒክ ከደንበኛው ለቀዶ ህክምና የተቀበለውን ክፍያ መመለስ እንደሚችል ቢናገርም ግለሰቡ ከዚህ ያለፈ ካሳ እንደሚፈልግ ተናግሯል ተብሏል፡፡

ያለ ፍላጎቱ የአምስተኛ ልጅ አባት የሆነው ግለሰብ እኔ ሕክምናውን ያደረኩት ኢኮኖሚዬን እና የማሳደግ አቅሙን አይቶ እንደነበር እንዲሁም ክሊኒኩ በሰራው ስህተት ምክንያት ለተጨማሪ ጫናዎች መዳረጉን ተናግሯል፡፡

ግለሰቡ ለደረሱበት ጫናዎች ካሳ እንደሚፈልግ ቢናገርም፤ ክሊኒኩ ግን እኔ የሰራሁት ስህተት የለም ነገር ግን ግለሰቡ በተዓምር ነው አምስተኛ ልጅ ሊወልድ የቻለው በሚል ክርክሩ እንደቀጠለ ይገኛል ሲል ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You