ጀርመን ለዩክሬን የምትሰጠውን ድጋፍ እንደምታቆም ገለጸች

ጀርመን ለዩክሬን የምትሰጠውን ድጋፍ እንደምታቆም ገለጸች፡፡

ሶስተኛ ዓመቱ ላይ የሚገኘው የሩሲያ- ዩክሬን ጦርነት እንደቀጠለ ሲሆን፤ ጀርመንን ጨምሮ ምዕራባዊያን ሀገራት ለዩክሬን ገንዘብን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ ናቸው፡፡

ዩክሬን ከሩሲያ የሚሰነዘርባትን ጥቃት ለመመከት ድጋፍ ከሚያደርጉላት ሀገራት መካከል ጀርመን ዋነኛዋ ስትሆን ከ2025 ጀምሮ ድጋፏን እንደምታቆም አስታውቃለች፡፡

ጀርመን ለዩክሬን የምትሰጠውን ድጋፍ የምታቆመው ሀገሪቱ ያለባት የብድር ጫና እየጨመረ በመምጣቱ ምክንያት እንደሆነ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

አሜሪካ ለዩክሬን ከፍተኛ ገንዘብ እና የጦር መሳሪያዎችን ለዩክሬን ድጋፍ ከሚያደርጉ ሀገራት መካከል ቀዳሚዋ ስትሆን ጀርመን በሁለተኝነት ላይ ተቀምጣለች።

ጀርመን በተያዘው የፈረንጆቹ 2024 ዓመት ውስጥ ብቻ ለዩክሬን ስምንት ቢሊዮን ዩሮ ድጋፍ ማድረጓ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡

ጀርመንን ጨምሮ በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት 300 ቢሊዮን ዩሮ የሩሲያ መንግሥት ሀብት እንዳይንቀሳቀስ የታገደ ሲሆን፤ ይህ ገንዘብ ለዩክሬን መልሶ ልማት እንዲውል ጥረቶች በመደረግ ላይ ናቸው፡፡

በጀርመን ከታገደ የሩሲያ መንግሥት ሀብት ላይ በወለድ መልክ የሚገኘው 4 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዩሮ ለዩክሬን ድጋፍ እንደሚሰጥ የመራሄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ መንግሥት አስታውቋል፡፡

በምርጫ ቅስቀሳ ላይ ያሉት ዶናልድ ትራምፕ ምርጫውን ካሸነፉ ለዩክሬን የሚደረገውን ድጋፍ እንደሚያቆሙ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡

ትራምፕ አክለውም ፕሬዚዳንት ባይደን የአሜሪካዊያንን ገንዘብ ለዩክሬን በመስጠት ሀብት አባክኗል ሲሉ የወቀሱ ሲሆን፤ ስልጣን በያዙ ማግስት ጦርነቱን እንደሚያስቆሙ ቃል ገብተዋል፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You