የሆርቲካልቸር ምርቶችን ልማት ማስፋፋትና ድንበር ማሻገር የሚያስችለው ስምምነት

ኢትዮጵያ ለሆርቲካልቸር ምርቶች ተስማሚና ምቹ ሥነ-ምህዳር፣ የአየር ንብረትና ሰፊ የሰው ኃይል እንዳላት ይታወቃል። የሆርቲካልቸር ልማት በሀገሪቱ ከተጀመረ ሁለት አስርተ ዓመታት ያስቆጠረ ሲሆን፣ ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ከሚያስገኙ የግብርና ምርቶች አንዱ ሆኗል።

ይሁን እንጂ የመንግሥትን ድጋፍ ጨምሮ በሀገሪቱ ለዘርፉ ምቹ ሁኔታ ያህል ዘርፉ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ አስተማማኝና ሁነኛ የጀርባ አጥንት እንዲሆን ለማድረግ የተሠራው ሥራ እምብዛም መሆኑን የዘርፉ ተዋናዮች ይናገራሉ። ካለው እምቅ አቅም አንፃር ተጨባጭ ውጤት ማምጣት ላይ ብዙ የሚቀሩ ሥራዎች መኖራቸውንም ያነሳሉ። በተለይም በስፋትና በጥራት በማምረት በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ መገኘት ላይ ክፍተቱ ጎልቶ እንደሚታይ ይጠቀሳሉ።

የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራቾችና ላኪዎች ማኅበር መረጃ እንደሚያሳየውም፤ በኢትዮጵያ በአበባ፣ በፍራፍሬ፣ በአትክልትና በመዓዛማ እፅዋት ልማት ዘርፍ 128 የሚደርሱ ኢንቨስትመንቶች ያሉ ሲሆን፣ 10 ሚሊዮን 897 ሺ ሄክታር መሬት በዘርፉ እየለማ ይገኛል። በዚህም 200 ሺ ለሚደርሱ ዜጎችም በዘርፉ የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል። በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከዘርፉ 658 ነጥብ 30 ሚሊዮን ዶላር ማስገባት ተችሏል። በአሁኑ ወቅት ዘርፉ ለሀገሪቱ ከፍተኛ ገቢ በማስገባት በአራተኛ ደረጃ ያለ ቢሆንም፣ ያለውን እምቅ አቅም በመጠቀም በስፋትና በጥራት ማምረት ቢቻል አሁን እየተገኘ ካለው ገቢ በላይ ማግኘት እንደሚቻል የመንግሥትም የዘርፉ ባለሙያዎችም እምነት ነው።

የግብርና ሚኒስቴር ሰሞኑን የኢትዮጵያን ሦስት የሆርቲካልቸር ምርቶች በስፋትና በጥራት በማምረት በተለያዩ የምሥራቅና ደቡብ አፍሪካ ሀገራት ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል ስምምነት ከሆርቲካልቸር አምራቾችና ላኪዎች ማኅበርና ከኮሜሳ/የምሥራቅና ደቡብ አፍሪካ የጋራ ገበያ/አባል ሀገራት ጋር ከሰሞኑ መፈራረሙ ይታወሳል። ስምምነቱ ኢትዮጵያ የምታመርታቸውን በተለይም የሽንኩርት፣ አቦካዶና ድንች ምርቶችን በኮሜሳ አባል ሀገራት ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር የግብርና ምርቶችን ንግድ ለማሳለጥ እንደሚረዳ በስምምነቱ ወቅት ተገልጿል።

የግብርና ሚኒስቴርን በመወከል ስምምነቱን የፈረሙት የግብርና ሚኒስቴር የእርሻና ሆርቲካልቸር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ፕሮፌሰር ዓሊ መሐመድ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳስታወቁት፤ ኮሜሳ በምሥራቅና ደቡብ አፍሪካ ሀገራት በንግድ የሚተባበሩበት ማኅበር እንደመሆኑ፣ የስምምነቱ መፈፀም ኢትዮጵያ የምታመርታቸው የሆርቲካልቸር ምርቶች የገበያ መዳረሻ እንዲሰፋ ያደርጋል።

የአባል ሀገራቱ የርስ በርስ የንግድ ልውውጥ ይበልጥ እንዲጠናከር በማድረግ በኩልም ስምምነቱ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል። በተጨማሪም ሀገራቱ ምርታቸውን በጋራ በማቀናጀት ወደ ተለያዩ የዓለም ገበያዎች ለመላክና የላቀ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታንም ይፈጥራል። ከዚህም ባሻገር የግል ባለሃብቶች የግብርና ሥራቸውን ማስፋፋት የሚያስችላቸውን የፋይናንስ፣ የግብዓት፣ የቴክኖሎጂ ድጋፎችን እንዲያገኙ የሚያደርግ ሲሆን፤ በተለይም አነስተኛ አምራቾች አቅማቸው እንዲጎለብት የላቀ አስተዋፅዖ ይኖረዋል።

‹‹በዋናነትም አምራቾቹ ከመንገድ፤ ከማቀዝቀዣና ከመሰል ግብዓቶች ጋር በተያየዘ ያሉ ችግሮችን ለመፍታትም አቅም ይፈጥራል ተብሎ ይታመናል›› ያሉት ፕሮፌሰር ዓሊ፤ በስምምነቱ መሠረት ይህ በጋራ የሚሠራበት የጋራ ፕሮጀክት ከሦስት እስከ አምስት ዓመት እንደሚቆይም አስታውቀዋል። ስምምነቱ እንደየሁኔታውና እንደየአስፈላጊነቱ እየታየም በየጊዜው የሚታደስ ይሆናል ብለዋል። የአባል ሀገራቱን በጋራ ተቀናጅቶ የመሥራት ዕድልንም እንደሚያሰፋው ተናግረው፤ በተለይም የግል ባለሃብቶች ፋይናንስ እንዲያገኙና የሆርቲካልቸር ልማቱን ለማስፋፋት እንደሚያግዛቸው ያስረዳሉ።

እንደ ፕሮፌሰር ዓሊ ገለፃ፤ የሆርቲካልቸር ልማት ዘርፍ ለሀገር ኢኮኖሚ ጠቀሜታው ሰፊ ቢሆንም እስካሁን ባለው እምቅ አቅም ልክ ያለመሠራቱ ያስቆጫል። ከኮሜሳ ጋር የተመሠረተው የጋራ ትብብር ትልቁ ጠቀሜታም ምርትን ከአንድ ሃገር ወደ ሌላ ሃገር ከመውሰድ በዘለለ ጥራት ያለው ምርት በስፋት ለማምረት የሚያግዝ ነው። ይህም የሚሆነው የኢትዮጵያ ምርቶች በሁሉም የገበያ መዳረሻዎች ተወዳዳሪ ሆነው እንዲገኙ የጥራት ደረጃውና የምግብ ደኅንነታቸውን መረጋገጥ ሲቻል ነው።

‹‹ከሌሎቹ ሃገራት ጋር ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘትና በገበያው ላይ በተሻለ መልኩ ተፈላጊ ለመሆን አግባብነት ያለው የእርሻ አሠራር መከተል አለብን›› የሚሉት አማካሪው፤ በተለይም አምራቹ ኃይል ከሚጠቀመው ማዳበሪያ ጀምሮ በዘር፣ በምርት መሰብሰብና ታሽጎ ወደሚፈለግበት ስፍራ እስከሚደርስ ድረስ በከፍተኛ ጥንቃቄ መሥራት የሚጠበቅበት መሆኑን ያስረዳሉ።

መንግሥትም ሆነ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ የምርቱን ጥራት የማረጋገጥ ሥራ መሥራት እንዳለባቸውም ያስገነዝባሉ። ይህንን ማድረግ ከተቻለ የኢትዮጵያ ምርቶች አይደለም የአፍሪካ ገበያን የዓለምን ገበያም መቆጣጠር የማይችሉበት ሁኔታ እንደማይኖር አመላክተዋል።

በተለይም የግሉ ዘርፍ ትልቁን ሚና መጫወት እንደሚጠበቅበት የተናገሩት ፕሮፌሰር ዓሊ፤ መንግሥትም የግሉን ዘርፍ አቅም ለማጠናከር የተለያዩ የድጋፍና ክትትል ሥርዓቶችን በመዘርጋት እየሠራ መሆኑን ይጠቁማሉ። ከእነዚህም መካከል ሁሉንም የዘርፉን ተዋናዮች ተሳታፊ የሚያደርግ ጉባኤ መኖሩን ጠቅሰው፤ በዚህም በቅርበት በመሆን ችግሮች ላይ በመምከርና የመፍትሔ አቅጣጫ በማስቀመጥ የሚሠራበት አግባብ መኖሩንም ያስረዳሉ።

‹‹የዚህ ስምምነት መፈፀም የሀገር ውስጥ የግል ዘርፉ ተዋናዮች የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል›› ያሉት አማካሪው፤ ይህም ከጎረቤት ሃገራት ጋር በሚኖረው የግብርና ምርቶች የንግድ ልውውጥ ከማሳለጥ ባለፈ የኢኮኖሚ ትብብራቸው እንዲጠናከርም አወንታዊ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው ያመለክታሉ።

እሳቸው እንዳሉት፤ ስምምነቱ የአፍሪካ ነፃ ገበያን ከማሳለጥ አኳያም አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል። ከዚህ ባሻገርም ከዘር አቅርቦት ጀምሮ ባሉ የእሴት ሠንሠለቶች ሁሉ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ ሲታይም የስምምነቱ ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው።

‹‹ሆርቲካልቸር በተፈጥሮው በአንድ ሄክታር እስከ 30 ሰው ይፈልጋል፤ በተለይ ለወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል ይፈጥራል›› ሲሉም አስታውቀዋል። በአሁኑ ወቅትም የዘር ብዜት ሥራ መጀመሩን ጠቅሰው፤ በዚህም በርካታ ሰዎች እየተሳተፉ መሆናቸውን ይናገራሉ።

እንደአማካሪው ማብራሪያ፤ በስምምነቱ መሠረት በስፋት ለማምረትና ለመላክ የተመረጡት ሦስት የሰብል ዓይነቶች ናቸው፤ ይህም የተደረገው የምግብ ዋስትንና ሥርዓተ ምግብን ከማጠናከር አኳያ ያላቸው ፋይዳ ታይቶ ነው። ሰብሎቹ በአፍሪካም ሆነ በሌሎች የዓለም ሀገራት ተፈላጊና ለምግብነት የሚውሉ በመሆናቸው አሁን ከተጀመረውም በላይ በስፋት በማምረት ለሀገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለማስገባት ይሠራል።

በአሁኑ ወቅት በተለይ በአቦካዶ ላይ የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚደረግ ሲሆን፣ ሽንኩርትም በአስር ዓመቱ የልማት እቅድ ከተካተቱ ወሳኝ ሰብሎች አንዱ እንደመሆኑ በጥራትና በስፋት እንዲመረት የሚደረግ ይሆናል። በተጨማሪም ድንች በተለይ ለአግሮ ኢንዱስትሪው ሁነኛ ግብዓት በመሆኑ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲመረት ይደረጋል።

በግብርና ሚኒስቴር የሆርቲካልቸር ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ አብደላ ነጋሽ በበኩላቸው በሀገሪቱ በሆርቲካልቸር ልማት ዘርፍ ሰፋፊ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ ‹‹በተለይም አሁን ላይ ባለው የዓለም ነባራዊ ሁኔታ በሀገር ውስጥ ብቻ ተወስኖ መሥራቱ ውጤት እንደማያመጣ ታምኖበት የምርቶቹን መዳረሻ ሀገራት ለማስፋት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው›› ይላሉ። በመሆኑም ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት ሀገራት ብሎም ራቅ ላሉት የዓለም ኅብረተሰቦች በማምረት ኢትዮጵያ በሆርቲካልቸር ዘርፉ መጠቀም ያለባትን ሁሉ እንድታገኝ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ያብራራሉ።

‹‹ከዚህ አንፃር ወደ ዓለም አቀፍ ትብብሮች ከመግባታችን በፊት በቀጣና ደረጃ በተለይ ከምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ጋር ተቀናጅቶ መሥራት ያስፈልጋል የሚል እምነት ይዘን ነው ከኮሜሳ አባላት ሀገራት ጋር በጋራ ለመሥራት የተስማማነው›› የሚሉት አቶ አብደላ፤ ከዚህ አንፃር ቢልኤንድ ሜሊንዳ ጌት ፋውንዴሽን የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ስለመሆኑ ይጠቅሳሉ። በተጨማሪም በእሴት ሠንሠለት ውስጥ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ያመለክታሉ።

በዚህም ከአምራቹ እስከ ኢንዱስትሪ ድረስ በአጠቃላይ በእሴት ሠንሠለቱ ያሉ ተዋናዮች የሚያሳተፉበት መሆኑን መሪ ሥራ አስፈፃሚው ተናግረው፤ ‹‹ይህም ለሆርቲካልቸር ልማቱ ውጤታማነት ሰፊ አስተዋፅዖ ይኖረዋል ብለን ነው የምናስበው›› ይላሉ። በሆርቲካልቸር ምርቶች ላይ ጥራትን መሠረት ያደረገ የአመራረት ዘዴ በመከተል፤ እንዲሁም ለሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ለውጭ ሀገርም በሚፈልገው የጥራት ደረጃ ማምረት እንደሚያስፈልግ ይገልፃሉ።

በተለይም አብዛኞቹ የሆርቲካልቸር ምርቶች ቶሎ የሚበላሹ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በስፋት ከማምረት በዘለለ በጥራትና በጥንቃቄ ጠብቆ ማድረስ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል። ለእዚህም በእሴት ሠንሠለቱ ያሉ አካላት ያልተቋረጠ ጥረት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ይህ ሲሆንም ሀገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንደምታገኝ አስታውቀዋል።

የኮሜሳ ተወካይና የአሊያንስ ፎር ኮሞዲቲ ትሬድ ኢን ኢስት ኤንድ ሳውዝ አፍሪካ (አክትሳ) ሥራ አስፈፃሚ ጆን ሙካካ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ስምምነቱ የሆርቲካልቸር ኢንዱስትሪው በተለይም በአባል ሀገራቱ እየተንቀሳቀሰ ያለውን ሃብት በሦስት እጥፍ ለማሳደግ የሚያስችል ነው። ይህም በዋናነት የግሉ ዘርፍ ተዋናዮችና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን አነስተኛ ገበሬዎች በምርታቸው የላቀ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያግዛል። በሀገራቱ መካከል በሚፈጠረው የገበያ ትስስር አማካኝነት የንግድ ልውውጥ ብቻ ሳይሆን ተሞክሮ በመቀመር ምርታማነታቸውን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ አቅም የሚሰጣቸው ይሆናል።

ስምምነቱ በተለይም በምሥራቅ አፍሪካ ያሉ አምስት ሀገራት የሆርቲካልቸር ምርቶች ንግድ ልውውጥ ይበልጥ እንዲጠናከር፣ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው እድገት እንዲመዘገብ የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት ዶክተር ጆን ያስገነዝባሉ። በዋናነትም መካከለኛ፣ አነስተኛ አምራቾች የፋይናንስ አቅርቦት እንዲመቻችላቸው፤ የአመራረት ሂደታቸውን እንዲያዘምኑ፣ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል እንዲፈጠር እንዲሁም ሥልጠና እና የቴክኖሎጂ ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግም የስምምነቱ አካል መሆኑን ያመለክታሉ።

የሆርቲካልቸር አምራቾችና ላኪዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ቴዎድሮስ ዘውዴ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ለሆርቲካልቸር ምቹ ከሆኑ ጥቂት የዓለም ሀገራት መካከል ትመደባለች። ከዚህ አንፃር ባለፉት ዓመታት ዘርፉ መጠነኛ የሚባል እድገት ከማስመዝገብ ባለፈ በውጭ ምንዛሪ ግኝት፣ በሥራ ፈጠራና በሌሎችም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች አነስተኛ አስተዋፅዖ እያደረገ ነው። ይህ የሆነውም በዋናነት በመሬት፣ በፋይናንስና የሎጀስቲክስ አቅርቦት ጋር ተያይዞ ባሉ ችግሮች ምክንያት ነው። በተለይም ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሃገራት ጭምር ማቅረብ የሚያስችል አቅም ቢኖራትም፣ ይህንን አቅም መጠቀም ላይ ውስንነት ይስተዋላል ።

ስምምነቱ በተለይም በኮሜሳ ውስጥ ያሉ 21 ሀገራትን ያቀፈ እንደመሆኑ በተለይም እንደ ኬንያ ያሉና በዘርፉ የተሻለ ምርጥ ተሞክሮ ካላቸው ሀገራት ልምድ በመቀመር ወደ ሀገር ውስጥ ማምጣት ያስችላል። በቀጣናው ላይ ፖሊሲዎች ወደአንድ መጥተው እውቀትና ተሞክሮ የሚዳቀልበትና የተሻለ አፈፃፀም የሚመዘገብበት ሁኔታ እንዲፈጠር ይረዳል ተብሎ ይታመናል።

አቶ ፋሲካ ሥዩም ፍሪ-ኤል ኢትዮጵያ የተሰኘ የሆርቲካልቸር አምራች ኩባንያ ቢዝነስ ኦፕሬሽን ማናጀር ናቸው። እርሳቸው እንደገለፁት፤ ስምምነቱ የኢትዮጵያን የሆርቲካልቸር ዘርፍ ወደፊት የሚያራምድ ከመሆኑም ባሻገር አምራቹ በስፋት እንዲያመርትና ለሀገር ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እንዲያስገኝ ያደርጋል። በዚህ ረገድ መንግሥት ከኮሜሳ ጋር ካደረገው ስምምነት በተጨማሪ ባለፉት ዓመታት ዘርፉን ለማሳደግና የሚገኘውን ገቢ ከፍ ለማድረግ እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ ነው።

በሀገሪቱ በሆርቲካልቸር ዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት በኩል መሻሻሎች እየታዩ መምጣታቸውን አቶ ፋሲካ ይናገራሉ። ‹‹በተለይም ከግብዓትና ሎጀስቲክስ አቅርቦት አኳያ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት ረገድ መሻሻሎች እየታዩ ናቸው። ከሠላምና ደኅንነት ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮች አሁንም የአምራች ኃይሉ ስጋት ናቸው›› ይላሉ። በተለይም የእርሳቸው ድርጅት እርሻ ደቡብ ኦሞ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ ብዙ ክልሎችንና ኪሎ ሜትሮችን አቋርጦ መጓዝን እንደሚጠይቅና የሠላም ጉዳይ አንገብጋቢ ጉዳዩ መሆኑን ጠቅሰዋል።

‹‹በግጭት ምክንያት መንገዶች ሲዘጉ ብዙ ምርት የሚበላሹበት ሁኔታ ያጋጥመናል፤ ይህ ሁኔታ በአጭር ጊዜ ውስጥ እልባት ካልተሰጠውና አስተማማኝ ሠላም ማስፈን ካልተቻለ የሀገሪቱን ምርት ለውጭ ገበያው በስፋት ተደራሽ ለማድረግ ለተያዘው ሀገራዊ ጥረት እንቅፋት እንዳይሆን ስጋት አለኝ›› ይላሉ። በየመንገዱ ባሉ ኬላዎች ላይ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች አሁን እየተቃለሉ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ። እንደተሽከርካሪ ያሉ ቁሳቁስን ከቀረጥ ነፃ ማስገባት ላይ በአንዳንድ ተቋማት የሚጋጥመው ቢሮክራሲ የበዛበት አሠራር መሻሻል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ማሕሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You