በኢራንና በሩሲያ መካከል ያለው ግንኙነት እየተጠናከረ እንደሚገኝ አሜሪካ ገለጸች

በኢራን እና ሩሲያ መካከል ያለው ግንኙነት እየተጠናከረ እንደሚገኝ አሜሪካ ገለጸች።

የዩክሬኑ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ በወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የሀገራቱ ግንኙነት መጨመሩ ተሰምቷል በሩሲያ እና ኢራን መካከል ያለው ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እንደሚገኝ አሜሪካ አስታወቀች።

የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር መሥርያ ቤት ፔንታጎን ምክትል ቃል አቀባይ ሰብሪና ሲንግ በሳምንታዊ መግለጫቸው ላይ እንደተናገሩት የሀገራቱን ግንኙነት አሜሪካ በቅርበት እየተከታተለች ትገኛለች።

ከዋሽንግተን በተጻራሪ የቆሙት ሞስኮ እና ቴሄራን ከሶቭየት ህብረት መፍረስ ጀምሮ እያሳደጉት የሚገኘው ግንኙነት በተለያዩ ዘርፎች ላይ ተጠናክሮ ይገኛል። ሞስኮ እና ቴሄራን በመካከለኛው ምስራቅ በኢራቅ፣ ሶርያ ፣ አፍጋኒስታን የሚያንጸባርቁት ሃሳብ ተመሳሳይ ከመሆኑ ባለፈ በአንዳንድ ሀገራት ላይ ለተመሳሳይ ቡድን ወታደራዊ ድጋፍ ሲያደርጉ እንደቆዩ ይታወቃል።

ሀገራቱ በጋዛው ጦርነት ለሀማስ እንደሚወግኑም የፔንታጎን ምክትል ቃል አቀባይ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪም ሩሲያ በዩክሬን ላይ በምታደርገው ውግያ የኢራን ከፍተኛ የጦር መሣርያዎች እና ድሮኖች ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ነው ያነሱት።

ባሳለፍነው መጋቢት ሮይተርስ ባወጣው መረጃ ኢራን ለሩሲያ 400 ባላስቲክ ሚሳኤሎችን መላኳን ከውስጥ ምንጮቼ አገኘሁት ባለው መረጃ መዘገቡ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎም ሞስኮ እና ቴሄራን ጉዳዩን ቢያስተባብሉም መሰል የጦር መሳርያ ድጋፍ እና ልውውጦች በሀገራቱ መካከል እንደሚደረግ ተደጋጋሚ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ።

ሶስተኛ አመቱን ባስቆጠው የዩክሬን ጦርነት ሩሲያ የመድፍ ተተኳሾችን ፣ ድሮኖችን እና የመካከለኛ ርቀት ሚሳኤሎችን ከኢራን እንደምታስገባ ሲገለጽ በተመሳሳይ የረጅም ርቀት ሚሳኤሎችን ለኢራን በመሸጥ ላይ እንደምትገኝ ተነግሯል።

ባለፈው ዓመት ህዳር ወር ላይ ኢራን ከሩሲያ ጋር ከቀረጥ ነጻ የንግድ ስምምነት ላይ ደርሳለች፤ ከዚህ በተጨማሪም በ2010 ሀገራቱ የተፈራረሙትን የሁለትዮሽ የትብብር ስምምነት በአዲስ ስምምነት ተክተዋል።

በ2023 የታደሰው ስምምነት ኢኮኖሚ ፣ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ትብብርን የሚያካትት ሲሆን ለ20 ዓመታት የሚቆይ መሆኑም ታውቋል።

በተመሳሳይ ዓመት በሀገራቱ መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ነበር።

በዓለም አቀፍ መድረክ የሀገራቱን ወዳጅነት እና ትብብር በስጋትነት የምታየው አሜሪካ በቅርብ ዓመታት እያደገ የመጣውን ግንኙነታቸውን በቅርበት እየተከታተልኩ ነው ብላለች።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You