የዓለም ጤና ድርጅት የዝንጀሮ ፈንጣጣ የህብረሰብ ጤና ስጋት ሆኗል ሲል ለሁለተኛ ጊዜ አወጀ።
የዓለም ጤና ድርጅት የዝንጀሮ ፈንጣጣ በዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ መከሰቱን እና ወደ ጎረቤት ሀገራት መስፋፋቱን ተከትሎ በሁለት ዓመት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ በሽታው ዓለምአቀፋዊ የህብረተሰብ ጤና ስጋት መሆኑን አውጇል።
የአስቸኳይ ጊዜ ኮሚቴ በሽታው የህብረተሰብ ጤና ስጋት መሆኑን ወይም አለመሆኑን ለድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ለማማከር ባለፈው ረቡዕ እለት ስብሰባ አድርገው ነበር።
የህብረተሰብ ጤና ስጋት ደረጃ፣ ድርጅቱ የሚሰጠው ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ ሲሆን ይህም በበሽታው ዙሪያ ጥናት እና ርዳታ እንዲፋጠን እንዲሁም በሽታውን ለመቆጣጠር ዓለምአቀፋዊ የህብረተሰብ ጤና ርምጃዎችን ለመውሰድ ያለመ ነው።
“እነዚህን ወረረሽኞች ለማስቆም እና ሕይወት ለማዳን የተቀናጀ ዓለምአቀፋዊ ምላሽ ለመስጠት አስፈላጊ ሆኗል” ብለዋል ዶክተር ቴድሮስ።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ በንክኪ የሚተላለፍ በሽታ ነው። ብዙ ጊዜ ቀላል የሚባል ቢሆንም አልፎ አልፎ እስከሞት የሚያደርስ ነው። በሽታው የጉንፋን አይነት ምልክቶችን እና በሰውነት መግል የያዙ ትናንሽ እብጠቶችን ያስከትላል።
በኮንጎ የተሰራጨው ወረርሽኝ ልዩ መጠሪያው ወይም ዝርያ ክላድ አይቢ ተብሎ ይጠራል። ነገር ግን ክላድ አይቢ የተባለው አዲሱ ዝርያ በወሲባዊ ግንኙነት ጨምሮ በቀላሉ የሚተላለፍ ነው ተብሏል።
በሽታው ከኮንጎ ወደ ቡሩንዲ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ እና ኡጋንዳ እና ወደ ሌሎች ጎረቤት ሀገራት መሰራጨቱ የዓለምጤና ድርጅት ርምጃ እንዲወስድ አስገድዶታል።
ዶክተር ቴድሮስ የአዲሱ የበሽታው ዝርያ በፍጥነት መስፋፋት እና ከዚህ ቀደም ባልታየባቸው ጎረቤት ሀገራት መከሰት እንዲሁም በአፍሪካ ውስጥ የመስፋፋት አቅሙ እንደሚያስጨንቃቸው ገልጸዋል።
ድርጅቱ ለአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ለመስጠት 1.5 ሚሊዮን መመደቡን እና በመጪዎቹ ቀናት ተጨማሪ እንደሚለቅ ተናግረዋል ዳይሬክተሩ። የድርጀቱ የመጀመሪያ ምላሽ እቅድ 15 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው ተገልጿል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የአፍሪካ ከፍተኛ የህብረተሰብ ጤና አካል የዝንጀሮ ፈንጣጣ የአህጉሪቱ አደጋ ሲል አውጇል። በሽታው በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ ሲሆን ቢዚህ አመት ህጻናትን ጨምሮ 500 ሰዎች ሲሞቱ፣ 17ሺ የሚሆኑ ደግሞ በሽታው ሳይዛቸው አይቀርም ተብሎ ተጠርጥረዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 11 ቀን 2016 ዓ.ም