የሕክምና አገልግሎት ግብዓት ምርት- በሀገር ውስጥ በሀገር ልጅ

መንግሥት ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የሰጠው ትልቅ ትኩረት በርካታ አምራቾች ዘርፉን እየተቀላቀሉ ይገኛሉ። በዚህም የተለያዩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት አበረታች ውጤት መመዝገብ እንደቻለም መረጃዎች ይጠቁማሉ። በተለይም ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት በመቻሉ ከውጭ የሚገባውን ምርት መጠን መቀነስ እንዲሁም ምርቱን ለማስገባት የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሬ ማስቀረት እየተቻለም ነው።

መንግሥት የዘርፉን ችግር እየገመገመ የአሰራር ማሻሻያዎች ሲያደርግ ፣ የዘርፉን የመሰረተ ልማትና የመሬት አቅርቦት ችግርም ለመፍታት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ጭምር ገንብቶ በማቅረብ ለዘርፉ የበለጠ መስፋፋት ሰርቷል። ይህን ተከትሎም በርካታ የውጭ ባለሀብቶች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ገብተዋል፤ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን የአምራች ዘርፉ ተሳትፎ ለማሳደግም ባከናወናቸው ዘርፈ ብዙ ተግባሮች የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የዘርፉ ተሳትፎ እየጨመረ መጥቷል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ተኪ ምርቶችን ለማምረቱ ስራ ትኩረት ተሰጥቷል። በተለይ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የምታወጣባቸውን መድኃኒቶች ጨምሮ ለህክምና አገልግሎት የሚውሉ ግብዓቶችን ለሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች የቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክን በመገንባት ለባለሀብቶች ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተከትሎ ኢንዱስትሪዎቹ መድኃኒትና የህክምና ቁሳቁስ ለማምረት ዘርፉን እየተቀላቀሉ ይገኛሉ።

በዘርፉ የተሰማሩ አምራች ኢንዱስትሪዎችም የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የህክምና ግብዓቶችን በማምረት ከውጭ ይገቡ የነበሩ የህክምና ቁሳቁስን በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት በዘርፉ ለራሳቸውም ለሀገርም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ናቸው። የኢትዮጵያን የሕክምና አገልግሎት ግብዓት ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥም ሰፊ ሥራ መሰራቱም ይገለጻል፡፡

ይህን ሁሉ ስራ ተከትሎ ኢትዮጵያ አሁን ላይ 36 በመቶ ያህል የመድኃኒትና የሕክምና ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መሸፈን እንደቻለች መረጃዎች ያመላክታሉ። መንግሥት ለተኪ ምርት ልማት በሰጠው ትልቅ ትኩረት በመድኃኒትና የህክምና ቁሳቁስ ምርት ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ወጪን ማዳን እንደተቻለ መረጃዎች ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያ በሕክምናው ዘርፍ ኢንቨስትመንት ያሏትን ዕድሎች መጠቀም በመቻሏ በአሁኑ ወቅት የህክምናው ዘርፍ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት ጀምራለች። በመሆኑም በርካታ አምራች ኢንዱስትሪዎች እንዲሁም አነስተኛና መካከለኛ አምራቾች በሕክምና ግብዓት ማምረት ስራ በስፋት እየገቡ ነው። የህክምና ግብዓቶችን ወደማምረት ከተቀላቀሉ አምራች ኢንዱስትሪዎች መካከል ‹‹ኤኬቢዲ ፋርማቲዩካል ማኑፋክቸሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር›› አንዱ ነው።

ድርጅቱ ከሚያመርታቸው የህክምናው ዘርፍ ምርቶች መካከል ለህክምና አገልግሎት የሚውሉ መድኃኒት፣ ቅባትና ቅባት ነክ የሆኑ ምርቶች ይጠቀሳሉ። አብዛኞቹ ምርቶች ከውጭ ሀገር ይገቡ የነበረ ሲሆን፤ አሁን ግን ጥሬ ዕቃውን ብቻ ከውጭ በማስገባት በሀገር ውስጥ ማምረት ተችሏል። ድርጅቱ አልኮልም በግብአትነት በስፋት ይጠቀማል። ድርጅቱ በህክምና አገልግሎት ትልቅ ድርሻ ያለውን አልኮል በመጠቀም ለህክምና አገልግሎት የሚውሉ መድኃኒት፣ ቅባትና ቅባት ነክ ምርቶችን እያመረተ ለገበያ ያቀርባል።

የኤኬቢዲ ፋርማሲቲዩካል ማኑፋክቸሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር መስራችና ባለቤት አቶ ብሩክ ዳምጠው በዘርፉ ከተሰማሩ ባለሙያዎች አንዱ ነው። አቶ ብሩክ ሲኒየር ኤክስፐርት ፋርማሲስት እና የድርጅቱ ቴክኒካል ማናጀር ነው። አቶ ብሩክ ለህክምና አገልግሎት የሚውሉ ምርቶችን ለማምረት የተነሳው ሙያውን መሰረት በማድረግ እንዲሁም በዘርፉ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላት በማሰብ መሆኑን ይናገራል።

አዲስ አበባ ከተማ ሳሪስ አካባቢ ተወልዶ ያደገው አቶ ብሩክ፤ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም በአዲስ አበባ ከተማ ተከታትሏል። የከፍተኛ ትምህርቱንም በሜድኮ ባዮ ሜዲካል ኮሌጅ ተከታትሎ በፋርማሲስትነት ሙያ የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል። ከትምህርት በኋላ በአንድ ድርጅት ውስጥ የመድኃኒት አቅርቦት ባለሙያ በመሆን ተቀጥሮ ሰርቷል። በቅጥር ቆይታው ሙያውን ማዳበር የቻለው አቶ ብሩክ፤ በዘርፉ የበለጠ እየተሳበና ፍላጎት እያሳደረ በመምጣቱ አምራች የሚሆንበት ቀዳዳ ያማትር ጀመር።

በዚህ ጊዜ ለሙያው ከፍተኛ ተነሳሽነትና ውስጣዊ ፍላጎት እያሳደረ የመጣው አቶ ብሩክ፤ መንግሥት ለአምራች ኢንዱስትሪዎች እያደረገ ያለውን ድጋፍ ተረዳ። ፍላጎቱን ዕውን ለማድረግም ተቀጥሮ ከመሥራት ይልቅ ወደ አምራች ኢንዱስትሪው መቀላቀልን መርጦ ተቀላቀለ።

መንግሥት የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ከረጅም ጊዜ ጥናት በኋላ በ200 ሺ /ሁለት መቶ ሺ/ ብር መነሻ ካፒታል የማምረት ሥራውን ይጀምራል። ወደ ምርት በገባበት ወቅትም ሥራውን በሚገባ መሥራት በመቻሉ በብዙ እንደተማረበት እና ከጊዜ ወደ ጊዜ ዕድገት በማስመዝገብ ውጤታማ መሆን ቻለ።

ይሁንና ካለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት ወዲህ ሀገሪቷን ካጋጠሟት ግጭቶች ጋር በተያያዘ ሥራው ቀዝቀዝ ብሎ መቆየቱን አስታውሶ፣ በሀገሪቱ የተረጋጋ ሁኔታ መፈጠሩን ተከትሎ ጥሩ የሚባል የሥራ እንቅስቃሴ እያረገ መሆኑን አመላክቷል።

አቶ ብሩክ መድኃኒትን ጨምሮ ለህክምና አገልግሎት የሚውሉ ምርቶችን የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች በቂ እንዳልሆኑ ጠቅሶ፣ በዘርፉ ብዙ መሥራት እንደሚያስፈልግም ጠቁሟል። ምክንያቱም በሀገሪቱ ያለው ፍላጎትና አምራች ኢንዱስትሪዎች እያመረቱ ያሉት የምርት አይነት መጠን ተመጣጣኝ አይደለም ባይ ነው።

‹‹የኤኬቢዲ ፋርቨማሲቲዩካል ማኑፋክቸሪንግ በዋናነት ከሚያመርታቸው ምርቶች መካከል የወባ ትንኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ መድኃኒቶች ይጠቀሳሉ። ይህ የሆነበት ዋናው ምክንያትም በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የወባ ትንኝ ስርጭት በመኖሩ ነው›› የሚለው አቶ ብሩክ፤ ለአፍ መጉመጥመጫ፣ ለጉንፋን፣ ለአዋቂና ለልጆች የሚሆን ለመገጣጠሚያና ለጡንቻ አካባቢ ህመም፣ ለድርቀት በተለይም ውሃ ላይ ለረጅም ጊዜ ለሚቆዩና በተፈጥሮ ድርቀት ላለባቸው ሰዎች የሚያገለግሉ ቅባቶች፣ የልጆች ቅባትና ፣ ቁስል ለማጽዳት የሚያገለግል ፈሳሽና ኮስሞቲክስ ጭምር እያመረተ መሆኑን አብራርቷል፡፡

እነዚህ ለህክምና አገልግሎት የሚውሉ ምርቶችን ለማምረት አልኮል ወሳኝ ነው የሚለው አቶ ብሩክ፤ አልኮል እጅግ በጣም ብዙ ቦታዎች ላይ እንደሚገባ አስረድቷል።

እሱ እንደሚለው፤ አልኮል በጣም ወሳኝ የሆነ መቀላቀያ ነው፤ ምርቶቹ እንዳይበላሹ ማድረግ የሚያስችል ንጥረ ነገር ነው። ስለዚህ አልኮል ከሌለ አብዛኞቹ ለህክምና አገልግሎት የሚውሉ ምርቶችን ለማምረት የሚቻል አይደለም። በሀገሪቱ የአልኮል ምርት እጥረት ተከስቶ እንደነበር አስታውሶ፣ በዚያን ወቅት እንደልብ ማምረት አልተቻለም ነበር ይላል። አሁን ላይ የአልኮል እጥረት መቀረፉን ጠቅሶ፣ ለህክምና አገልግሎት የሚውሉ ምርቶች በጥሩ ሁኔታ እየተመረቱ መሆናቸውን አስታውቋል።

እሱ እንዳለው፤ ከዚህ ቀደም በርካታ ለህክምና አገልግሎት የሚውሉ ምርቶች ከውጭ ይገቡ ነበር። አሁን ላይ አብዛኛውን ንጥረ ነገር ከውጭ በማስገባት ምርቶቹ በሀገር ውስጥ ይመረታሉ። ይህም ለዘርፉ ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ መቀነስ አስችሏል። አሁን ላይ ጥሬ ዕቃውን ብቻ ወደ ሀገር ውስጥ በማምጣት ለህክምና አገልግሎት የሚውሉ በርካታ ምርቶች አስፈላጊውን ሂደት ተከትለው በሀገር ውስጥ እየተመረቱ እንደሆነ አስረድቷል።

ያለቀለት ምርት የሚገባበት መጠንና ወጪ እንዲሁም ጥሬ ዕቃው የሚገባበት መጠንና ወጪ ከፍተኛ ልዩነት እንዳለው ነው አቶ ብሩክ የሚናገረው። ይህንንም ለአብነት ጠቅሶ ሲያብራራ፤ አንድ ኮንቲነር ያለቀለት ምርት ከማምጣት ይልቅ አንድ ኮንቴነር ወይም አንድ በርሜል ጥሬ ዕቃ ማስገባት በእጅጉ ተመራጭ ነው ይላል። ይህ ሲሆን ኢንዱስትሪው ጥሬ ዕቃውን ለረጅም ጊዜ ይጠቀምበታል፤ ብዙ ማምረትም ያስችለዋል ሲል ገልጾ፤ ይህም ለመጓጓዣና ለሌሎች በቀጥታና በተዘዋዋሪ የሚወጡ ወጪዎችን በእጥፍ መቀነስ ያስችላል ብሏል፡፡

ድርጅቱ ሥራውን ከጀመረ አምስት ዓመታትን አስቆጥሯል። ሥራው የተጀመረው ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከመከሰቱ አስቀድሞ ነበር። በወቅቱ ድርጅቱ ሳኒታይዘር በስፋት እያመረተ ለገበያ ያቀርብ ነበር። የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እየቀነሰ ሲመጣ ከኮቪድ ውጭ ያሉና ለህክምና አገልግሎት የሚውሉ ምርቶችን በስፋት ማምረት ወደ ማምረቱ ገባ። በአሁኑ ወቅትም ምርቶቹን በተለያዩ ቦታዎች ተደራሽ በማድረግ ገበያ ውስጥ መግባት ችሏል።

ድርጅቱ ምርቶቹን በአከፋፋዮች አማካኝነት ወደተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች ተደራሽ ያደረጋል። እነዚህ አከፋፋዮች መድኃኒቶችንና ለህክምና አገልግሎት የሚውሉ ምርቶችን ከአምራቹ በመረከብ አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ ለክልል ከተሞች ጭምር ያሰራጫሉ። በመሆኑም ድርጅቱ በገበያ ያለውን ፍላጎት መሰረት በማድረግ ያመርታል። ምርቶቹንም አከፋፋዮቹ በሚፈልጉት የምርት አይነትና መጠን እያቀረበ ይገኛል።

ምርቶቹ ለህክምና አገልግሎት የሚውሉና እንደ ህክምና የሚታዩ በመሆናቸው በከፍተኛ ጥንቃቄ የሚመረቱ ናቸው። የተወሰኑ ለኮስሞቲክስ የሚውሉ ቅባቶችና ቅባት ነክ ምርቶችም እንዲሁ ይመረታሉ። እነዚህ ምርቶችም በተለይም የቅባት ምርቶቹ በተለያዩ ፋርማሲዎች የሚገኙ ሲሆን፤ በዋናው የገበያ ማዕከል መርካቶ ውስጥ በሚገኙ ተረካቢዎችና በወኪል አከፋፋዮች አማካኝነት ማህበረሰቡ ጋር እንደሚቀርቡ ተናግሯል፡፡

ድርጅቱ አሁን ባለው የማምረት አቅም በዓመት ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ጠርሙስ የሚደርስ ምርት ማምረት የሚችል ቢሆንም፤ ከዚህ የበለጠ የገበያ ፍላጎት ቢመጣ ለማምረት የሚያስችል በቂ አቅም እንዳለው አቶ ብሩክ አስታውቀዋል። ገበያው በሚፈልገው መጠን ለማምረትም በቂ የማምረቻ ማሽን፣ የሰው ኃይልና ጥሬ ዕቃ እንዳለም ገልጿል።

በአሁኑ ወቅት 20 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለ ሲሆን፤ ካፒታሉም ወደ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ደርሷል። በቀጣይ ሥራውንና የመሥሪያ ቦታውን በማስፋት ተጨማሪ የሥራ ዕድል የመፍጠር እና ካፒታሉን የማሳደግ ዕቅድ እንዳለው አስረድቷል፡፡

ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንጻር ድርጅቱ የአቅሙን እያረገ መሆኑን አቶ ብሩክ ይገልፃል። ድርጅቱ ሥራ በጀመረ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ኮቪድ 19 ወረርሽን መከሰቱን አስታውሶ፣ በወቅቱ በጣም ተፈላጊ የነበረውን ሳኒታይዘር በስፋት እያመረተ ለገበያ ያቀርብም እንደነበርም ተናግሯል። ድጋፍ ለሚሹ የማህበረሰብ ክፍሎች በአይነትም በገንዘብም ድጋፍ ማድረጉንም ጠቅሷል። በተጨማሪም መንግሥታዊ ለሆኑ ጥሪዎች ምላሽ በመስጠት የድርሻውን እንደሚወጣም ነው ያስታወቀው፡፡

‹‹በአሁኑ ወቅት አብዛኛው ሕዝብ ዘመናዊ ህክምናን እየመረጠ አይደለም›› የሚለው አቶ ብሩክ፤ ወደፊት ስልጣኔ እየጨመረ ሲመጣ ማህበረሰቡ ወደ ዘመናዊ ህክምና መምጣቱ እንደማይቀር ይገልጻል። ለዚህም ዝግጁ ሆኖ ለመገኘት በህክምናው ዘርፍ ብዙ መስራት እንደሚጠበቅ አስታውቋል። መንግሥት ለአምራች ኢንዱስትሪዎች እየሰጠ ያለውን ድጋፍ አሟጦ በመጠቀም አምራቾች መድኃኒቶችን ጨምሮ ለህክምና አገልግሎት የሚውሉ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ፍላጎቱን መሙላትና ማህበረሰቡ ጋ ለመድረስ መስራት እንደሚገባቸው አመልክቷል።

ኤኬቢዲ ፋርማሲቲዩካል ማኑፋክቸሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት በቀጣይ የምርት አይነቶቹን በአይነትና በመጠን ከፍ የማድረግ ዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ነው። በተለይም የምርት መጠኑን ከጥራት ጋር ከፍ አድርጎ ለማቅረብ ዝግጁ መሆኑን አቶ ብሩክ ተናግሯል። ተጨማሪ ምርቶችን እንዲሁም ተጨማሪ የሥራ ዕድል በመፍጠር በተሻለ ጥራት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት አልሞ እየሰራ መሆኑን ጠቅሶ፤ ይህን ዕቅድ ለማሳካትም ማህበረሰቡ የሀገር ውስጥ ምርትን ገዝቶ በመጠቀም የድርሻውን መወጣት እንዳለበትም አስገንዝቧል።

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You