የጋብቻ ሥነ-ሥርዓት – በጉራጌ ሶዶ ብሔረሰብ

‹‹ጋብቻ ቅዱስ ነው፤ መኝታውም ንጹሕ›› እንዲል ታላቁ መጽሐፍ፣ ጋብቻ ለሰው ልጆች የተሰጠ ቅዱስና የተባረከ ስጦታ ነው። ብዙዎችም በተቀደሰው ጋብቻ አንድ አካል አንድ አምሳል በመሆን ጋብቻን ይመሠርታል፤ ትልቁን የቤተሰብ ተቋም ይመራሉ።

ጋብቻው በልጆች ሲባረክ ደግሞ ጥንዶቹ ተጨማሪ ኃላፊነቶችን ወስደው ትዳራቸውን ወደ መምራት ይገባሉ። ‹‹አምላክ ያጣመረውን ሰው አይለየውም›› እንደሚባለውም በዘር፣ በቀለም፣ በሃይማኖትና በሌላም ልዩነት ያላቸው ሰዎች በጋብቻ ተሳስረው አንድ አካል አንድ አምሳል በመሆን ትዳር የሚባለውን ትልቁን ማኅበራዊ ተቋም በመምራት ትውልድ ያስቀጥላሉ። ለዚህም የተለያየ ባሕልና እምነት የሚስተናገድባቸው እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሃገራት ምስክር ናቸው።

ኢትዮጵያ የተለያየ እምነት ተከታዮች በአንድነት የሚኖሩባት ሀገር ናት:: አያሌ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ያሉባት እንደመሆኗም የተለያዩ የአኗኗር ዘይቤዎችን ወይም ባሕላዊ እሴቶችን በውስጧ አምቃ ይዛለች።

በኢትዮጵያ የሚከናወኑ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ እሴቶች ድንቅ፣ ውብና ዓለምን የሚያስደምሙ ናቸው። ሃይማኖታዊና ባሕላዊ ከሆኑት ከእነዚህ የኢትዮጵያ ቱባ ባሕሎች መካከልም የአመጋገብ፣ የአለባበስ፣ የለቅሶና የጋብቻ ሥነሥርዓቶች ይጠቀሳሉ።

የዕለቱ ሀገርኛ ገጻችንም ተዝቆ ከማያልቀውና የኢትዮጵያውያን ቱባ ባሕሎች መካከል አንዱ በሆነው የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ትኩረቱን አድርጓል። የሃገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የየራሳቸው የሠርግ ሥነሥርዓት እንዳላቸው ይታወቃል። ከእነዚህም መካከል የጉራጌ ብሔረሰብ የጋብቻ ሥነ-ሥርዓት አንዱ ነው።

በሥራ ወዳድነቱ በእጅጉ የሚታወቀው የጉራጌ ብሔረሰብ ለጋብቻ ትልቅ ቦታና ክብር አለው። በብሔረሰቡ ዘንድ ጋብቻ ከፍተኛ ክብርና ቦታ ያለው ማኅበራዊ ክንዋኔ ነው። ጋብቻ ሦስት ጉልቻ መሥርቶ በአንድ ጣራ ስር አብሮ መኖር መቻል ብቻ ሳይሆን፣ አብሮ ሠርቶ መለወጥ፣ ምትክ ልጆችን አፍርቶ ለወግ ማዕረግ ማብቃትም ትልቅ ቦታ የሚሰጠው እንደሆነ ይታመናል።

“ከአንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ” እንዲሉ ባልና ሚስቱ እየተረዳዱ ለተለያዩ ቤተሰባዊና ማኅበረሰባዊ ኃላፊነቶች መብቃት የሚችሉበት ተቋም ስለመሆኑም የማኅበረሰቡ አባላት በተለይም አባቶች አፅንዖት ሰጥተው ያስረዳሉ።

የጉራጌ ዞን ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ በተለያየ ግዜ በሚያወጣቸው መረጃዎች ላይ እንደተመለከተውም ጋብቻ የማኅበረሰቡ ትልቅ እሴት ነው። በዚህ ምክንያት በጉራጌ ዞን በተለይ ደግሞ ዛሬ የዝግጅት ክፍላችን ትኩረት በሚያደርግበት የሶዶ ጉራጌ ባሕላዊ ሥርዓቱ ምን መልክ እንደሚኖረው ከዚህ እንደሚከተለው ልናቀርበው ወድደናል። መረጃውንም የባሕልና ቱሪዝም መምሪያው በተለያየ ግዜ ይፋ ካደረጋቸው ሰነዶች ላይ ተጠቅመናል።

በጉራጌ ሶዶ ብሔረሰብ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የጋብቻ ሥነ-ሥርዓት እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ቤተሰብን ከመጠየቅ ይጀምራል። አሁን አሁን ለአቅመ አዳም የደረሰ አንድ ወጣት የትዳር አጋሩን ከቤተሰብ ውጭ በራሱ መርጦ የሚያገባ ቢሆንም፤ ቀደም ባለው ጊዜ ሁለት ተጋቢዎች ከሠርጋቸው እለት አስቀድመው ለአንድም ቀን ሳይተያዩ ይጋቡ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ። ወንድየው ለአቅመ-አዳም በደረሰ ጊዜ የተለያዩ ምልክቶችን ያሳያል። ወላጅ አባትም የልጃቸውን ለአቅም-አዳም መድረስ ያስተውላሉ። በዚህ ጊዜ ታዲያ ወላጅ አባት ልጃቸው ለትዳር መድረሱንና ሚስት የምትሆነውን እንዲያፈላልጉለት ለቅርብ ዘመዶቻቸውና ጓደኞቻቸው ይነግራሉ። ፍለጋውም ከዘር ሓረጓ፣ መልኳ፣ ባልትናዋ፣ ሀብቷ እና መሰል ጉዳዮች አኳያ ታይቶ ይከናወን እንደነበር ነው መረጃዎች የሚያሳዩት።

በተለያዩ ክብረ በዓላት፣ ገበያ ስትወጣ፣ ውሃ ለመቅዳት ወንዝ ስትወርድ ወዘተ የተፈላጊዋ ልጅ ቁመና ይፈተሻል። ከምትኖርበት አካባቢም ስለቤተሰቦቿ ማንነት፣ ስለባሕሪዋ፣ ሙያዋ ተገቢው ጥናት ይካሄዳል። በዚህ አይነት መልኩ ስለልጅቷና ቤተሰቦቿ አስፈላጊ መረጃ ከተሰበሰበና የኋላ ታሪኳ ከታወቀ በኋላ የልጁ ወላጅ አባት ሁለት ሽማግሌዎችን ጨምሮ ወደ ሴቷ ልጅ ቤት ማልደው በመሄድ የጋብቻ ጥያቄያቸውን ያቀርባሉ።

ጥያቄውም “ሴት ልጃችሁን ለወንድ ልጃችን ስጡን” የሚል ነው። የልጅቷ ወላጆች የቀረበላቸውን የጋብቻ ጥያቄ በአንዴ አይቀበሉም። እሺታቸውን ላለመግለጽ የተለያዩ ምክንያቶችን ይፈጥራሉ። ለምሳሌ፡- ልጅቷ እድሜዋ ለትዳር አለመድረሱን፣ የልጆቹ ዕጣ ፈንታ ይጠየቅና ይታወቅ … ወዘተ ምክንያቶችን ይደረድራሉ።

የልጁ አባትና ሽማግሌዎችም የእነርሱም ልጅ ቢሆን በእድሜው ገና ልጅ እንደሆነና ሁለቱም እድሜያቸው ለጋብቻ እስኪደርስ በየወላጆቻቸው የቅርብ ክትትል ስር ሊቆዩ ስለሚችሉ የልጅቷ ወላጆች ፍቃደኛ እንዲሆኑላቸው ያግባቧቸዋል። የልጅቷ አባትም “እስቲ ከቤተሰቦቼ ጋር ልምከርበት” በሚል ሌላ የቀጠሮ ቀን ሰጥተው ይለያያሉ። በቀጠሯቸው መሠረትም ጥያቄያቸው ምላሽ ያገኛል። ጥያቄያቸው ምላሽ ካገኘ በኋላም የጋብቻ ሥነሥርዓቱ ቅደም ተከተሉን ጠብቆ በባሕልና ወጉ መሠረት ይከናወናል።

አሁን አሁን ተጋቢዎቹ ከወላጆቻቸው ፈቃድና ዕውቅና ውጭ እርስ በእርስ ተፈቃቅደውና ተፈላልገው የሚጋቡ ቢሆንም በአብዛኛው የጋብቻ ሥርዓቱን የሚከውኑት ግን ባሕልና ወጉን ጠብቀው ነው።

ከባሕልና ወጎቹ መካከልም ሽምግልና ቀዳሚው ነው። ለጋብቻ ትልቅ ቦታና ክብር የሚሰጠው የጉራጌ ብሔረሰብ ለሽምግልናም ትልቅ ቦታ ይሰጣል። በመሆኑም የጋብቻ ሥነሥርዓቱ የሚጀምረው ከሽምግልና ወይም ‹‹ከቸግ›› ነው። ‹‹ቸግ›› ወይም ሽምግልናውን ተከትለው የሚከናወኑ ሌሎች የጉራጌ የሠርግ ሥነሥርዓቶች ብስቆት፣ እንሶስላ፣ ሠርግ፣ መልስና ቅልቅል ናቸው።

‹‹ቸግ›› (ሽምግልና)

ቀደም ሲል የነበረውና ‹‹ልጅህን ለልጄ›› በሚል በቤተሰብ የሚፈጸም ጋብቻ አሁን አሁን ተቀይሯል። ወጣቱ ቀልቡ ያረፈባትን ሴት ለመምረጥ የተለያዩ አማራጮች አሉት። በተለይም በወርሐ መስከረም በጉራጌ ማኅበረሰብ በታላቅ ድምቀት የሚከበረው የመስቀል በዓል ትልቁና ዋናው አማራጭ ነው። ትዳር ፈላጊው ለመስቀል ጭፈራ ከሚወጡ እንስቶች መካከል ቀልቡ ያረፈባትን ሴት ይመርጣል። የመረጣትን የትዳር አጋሩ ለማድረግ የመጀመሪያው የሽምግልና ሥነ-ሥርዓት ይከናወናል።

‹‹ቸግ›› ወይም ሽምግልና የሚከናወነው ቤተሰቡ አልያም ጥንዶቹ ከተፈቃቀዱ በኋላ ነው። ሥነሥርዓቱ ሽማግሌ ከመላክ ይጀመራል። በመጀመሪያው የሽምግልና ወቅት ሽማግሌዎች ጉዳያቸውን ተናግረው ቀጠሮ ተቀብለው ይሰናበታሉ። የሴቷ ቤተሰቦች የልጃቸውን ፈቃደኝነት ካረጋገጡና እነሱም ፈቃደኛ ከሆኑ በቀጠሮ ቀን ትልቅ ድግስ ደግሰው ይጠብቃሉ። ይህም ‹‹ቸግ›› ይባላል።

የሴቷ ቤተሰቦች ባሕሉን በጠበቀ መንገድ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ በማድረግ ሽማግሌዎቹን ደግሰው በክብር ተቀብለው በጥሩ ሁኔታ ያስተናግዳሉ። በዕለቱ በጉራጌ ባሕል አለ የተባለ የባሕል ምግብ በሙሉ በዓይነት በዓይነቱ ይቀርባል። ለአብነትም ክትፎ፣ ቆጮ፣ ቅሙስ፣ አይብ፣ ጎመን፣ በቅቤ የታሸገ የገብስ ቆሎ ፣ ጭኮና ይገኙበታል። ከመጠጥም እንዲሁ ጠላ፣ ጠጅ፣ ባሕላዊ አረቄና ሌሎችም ይቀርባሉ።

ከምግብና ከመጠጡ በኋላም በጉራጌ ማኅበረሰብ ባሕል ሽምግልና የመጡ ሰዎች የራስ ቅቤ ይቀባሉ። ከዚያም ይመራረቁና ለሠርጉ ቀጠሮ ተለዋውጠው ይለያያሉ። በመጨረሻም ሽማግሌዎቹ ከተመገቡት የምግብ አይነት በሙሉ በመሶብ ተደርጎ ከጠላና ከጠጁ ጋር ለሙሽራው ይላካል። የሙሽራው ቤተሰብም መሶቡን ተቀብሎ ይበላል፤ ይጠጣል። መሶቡም ባዶ አይመለስምና አቅማቸው እንደፈቀደ ባሕላዊ ምግብ አድርገው ይልካሉ። ይህም ጥያቄያቸውን መቀበላቸውንና ዝምድናቸውን የሚያረጋግጥ ነው።

ብስቆት

ብስቆት በሴት ሙሽራ ቤት የሚከናወን ባሕላዊ ሥነሥርዓት ሲሆን፣ ሥነሥርዓት በዋናነት ለሙሽሪት እናት የሚደረግ ነው። በባሕሉ መሠረት የሙሽሪት፣ እህቶች፣ ቤተ ዘመዶችና ጓደኞች ተሰባስበው የሙሽሪትን እናት እንኳን ደስ አለሽ ይላሉ።

እነዚህ ጓደኞችም በጋራ ገንዘብ አዋጥተው በሙሽሪት እናት ቤት ድግስ ይደግሳሉ። በዕለቱ የገብስ ቅንጬ በቅቤ ተቀላቅሎ ይበላል። ጠላ፣ ጠጅና ሌላም መጠጥ ይዘጋጃል። ከተበላ ከተጠጣ በኋላም ይጨፈራል።

የሙሽሪት እናት ጓደኞች እናትየዋን ቅቤ ይቀቧታል፤ ስጦታዎችንም ይሰጧታል። ባሕላዊ ምግብ የሆነው ጭኮን ጨምሮ ነጠላ፣ ቀሚስ፣ ሻሽ፣ ጋቢና እንደየአቅማቸውና እንደየቅርበታቸው የሚያበረከቱላት ስጦታዎች መካከል ይጠቀሳሉ። በዕለቱም የሙሽሪት እናት ብዙ ቅቤ ትቀባለች፤ ይህም ‹‹በሰቀች›› ይባላል።

ይህ ፕሮግራም የሚከናወነው ሠርጉ ቢበዛ አንድ ሳምንት አልያም ሁለት ሳምንት ሲቀረው ነው። በዕለቱ የሙሽሪት እናት፣ እህት፣ ዘመድና ጓደኞቿ ያዘጋጁት የገብስ ቅንጬ በቅቤ ተለውሶ ይበላል። ጠላ፣ ጠጅና ባሕላዊ አረቄም ይጠጣል። ቡና በቅቤም እንዲሁ ይጠጣል። ከምግብና ከመጠጡ በኋላም ጫወታ ይጀመራል፤ በዚህም የሙሽሪት እናትን ጨምሮ ሁሉም በየተራ ይጨፍራሉ።

እንሶስላ

በጉራጌ ሶዶ ብሔረሰብ ከሰርጉ ዕለት በበለጠ የሚወደድና የሚናፈቀው የእንሶስላ ባሕላዊ ሥርዓት ነው። የእንሶስላ ባሕላዊ ሥነሥርዓት የሚከወነው ከሠርጉ ቀን ሁለት ቀን ቀደም ብሎ ነው። እንሶስላን ሴቷም ወንዱም በየቤታቸው ያከብሩታል። በዕለቱ ጠላና ዳቦም ይዘጋጃል። ጠላ እየተጠጣ ዳቦ እየተበላ መጫወት፣ መዝፈንና መጨፈር ዋናው የሥርዓቱ መገለጫ ነው:: ብዙ ጊዜ ሠርግ እሁድ ቀን የሚደረግ በመሆኑ የእንሶስላ ፕሮግራም ዓርብ ዕለት ማታ ይከናወናል። ወንዱም ሴቷም በየቤታቸው ከሚዜዎቻቸው ጋር በመሆን ቤተሰብ ዘመድ አዝማድ በተሰበሰበበት የሚከናወን ትልቅ ሥነሥርዓት ነው።

ሥርዓቱ በሚከናወንበት ወቅት ቤተሰብ ዘመድ አዝማድና ጎረቤት በሙሉ ይሰባሰባል። ሙሽሪት ከሚዜዎቿ ጋር በነጠላ ተሸፋፍና በተሰባሰበው ቤተዘመድ መሐል ከቃጫ በተሠራ ጅባ ላይ ትቀመጣለች። በዚህ ጊዜ ከወላጅ አባት ጀምሮ እናት፣ አጎት፣ አክስት እያለ በየተራ ባሕላዊ የሆነውን ዘፈን ይዘፍናሉ። በዘፈኑም በሞት የተለዩ ዘመዶች ቤተሰቦች ይጠራሉ፤ በዚህ ጊዜ የተወሰነ ለቅሶ ይኖራል። ምክንያቱም በሞት የተለዩ ዘመዶቿ በሕይወት በኖሩና ይህን ዓለም ቢያዩ የሚል መልዕክት ያለው በመሆኑ ነው። በሞት የተለዩ ወላጆች ከሆኑ ለቅሶው ጠንከር ይላል። በተለይም ሙሽሪት ከሚዜዎቿ ጋር በነጠላ ተሸፋፍና ባለችበት ታለቅሳለች፤ ቤተሰቡም ሁሉ ያለቅሳል።

በዘፈኑ ግጥም እህት ወንድም እንዲሁም በሕይወት የሌሉ ዘመዶች ሁሉ ይጠራሉ፤ ይወደሳሉ። ባሕላዊ ዘፈኑ በወላጅ አባት ተጀምሮ ቤተዘመዶቹ ጋ በየተራ ከተዳረሰ በኋላ ወደ ጭፈራ ይጓዛሉ።

ጭፈራው ከመጀመሩ አስቀድሞ የተዘጋጀውን ጠላ በተሰበሰበው ቤተዘመድ ፊት እየመጣ ወደ እንሥራ ይጨመራል። በዚህ ጊዜ ሁሉ ሙሽሪት ከሚዜዎቿ ጋር በነጠላ እንደ ተሸፋፈነች ነው።

ጠላው ወደ እንስራ ሲገለበጥ ቤተዘመዱ ባሕላዊ ዘፈኑን ይጀምራል። በዚህ ጊዜ የሚዘፈነው ባሕላዊ ዘፈንም፤ ‹‹ሞላ አልሞላ፤ ሞላ አልሞላ›› የሚል ሲሆን፣ እንስራው በጠላ እስኪሞላ ‹‹ሞላ አልሞላ፤ ስከሪ አልሞላ፤ ስከሪ አልሞላ›› የሚል ይሆናል። ይህ ዘፈን የሚዘፈነው ጠላው ወደ እንስራ እየተገለበጠ እስኪሞላ ድረስ ሲሆን፤ ትርጉሙም ‹‹ጠላው ሞልቷል አልሞላም›› ማለት ነው።

እንስራው የዶሮ ዓይን በመሰለው ጠላ ሲሞላ ጠላው መጠጣት ይጀምራል፤ ድፎ ዳቦውም ተቆርሶ ይበላል። ጭፈራውም ድብልቅልቅ ይላል። እናት፣ አባት፣ አክስት፣ አጎት አጠቃላይ ቤተሰቡና ቤተዘመዱ በሙሉ እየተነሳ ይጨፍራል። የሙሽሪት ሚዜዎችም በየተራ ይነሳሉ፤ በስተመጨረሻም ሙሽሪትም ተነስታ ትጨፍራለች። ይህ ሥነ-ሥርዓት በሙሽራውም ቤት በተመሳሳይ ሁኔታ ይከናወናል።

ሠርግ

ሠርግ ከላይ ከተጠቀሱት ሂደቶች በኋላ የሚከናወን ሲሆን፤ እንደማንኛውም ሠርግ ቅዳሜ አልያም እሁድ ቀን ይከናወናል። በዚህም እለት ድግስ ተደግሶ ከዘመድ አዝማድ ጋር የደስታ ተካፋይ ይሆናሉ።

ሙሽሪት ከቤት ስትወጣ በባሕሉ መሠረት ተመርቃና የቤተሰቦቿንና የዘመድ አዝማዱን ጉልበት ስማ ትወጣለች። በሠርጉ ዕለት በምርቃት ወቅት የሚቀርበው የጉራጌ ባሕላዊ ምግብ የሆነው ጭኮ ነው፤ አረቄም አይቀርም።

ሠርጉ በገጠር የሚከናወን ከሆነ ሙሽራው ሙሽሪትን ይዞ ወደ ቤተሰቦቹ ቤት ይገባል። በአብዛኛው በገጠር ያለው ባሕል ሙሽሪት ከሙሽራው ቤተሰብ ጋር አብራ ትኖራለች። ይህ የሚሆነውም ቤተሰቡን እንድትለምድ፣ ሥራም ከአማቷ ትልመድ በሚል ነው። አሁን አሁን ግን ሙሽራውና ሙሽሪት የራሳቸውን ጎጆ ቀልሰው ይኖራሉ።

መልስ

ከሠርግ ቀጥሎ የሚመጣው መልስ ነው፤ በጉራጌ ሶዶ ባሕል ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መልስ በሙሽሪት ቤተሰብ ይከናወናል። በባሕሉ መሠረት በወርሐ ሚያዝያ አልያም ጥር የተጋቡ ሙሽሮች መልስ የሚጠሩት በመስቀል ነው። መስቀል ትልቅ በዓል እንደመሆኑ መልሱም ከዚሁ ታላቅ ከሆነው የመስቀል በዓል ጋር ተያይዞ ይከናወናል።

መልስ የተጠሩት ሙሽሮችም ውለው አድረው ሰነባብተው ነው የሚመለሱት። የመስቀል በዓል በጉራጌ ብሔረሰብ ከአንድ ሳምንት በላይ የሚከበር እንደመሆኑ መልስ የተጠሩ ሙሽሮች ቢያንስ ለአንድ ሳምንት ቆይተው ‹‹አዳብና›› በመባል የሚታወቀውን የመስቀል በዓል በመታደም ይስተናገዳሉ።

ቅልቅል

ከመልስ ቀጥሎ የሚመጣው ቅልቅል ሲሆን፤ እንደማንኛውም ሠርግ የወንዱ ቤተሰብ በሚያዘጋጀው ዝግጅት ላይ የሙሽሪት ቤተሰቦች ተሰባስበው የሚቀላቀሉበት ፕሮግራም ይሆናል። በዚህ ጊዜ የሁለቱ ተጋቢዎች ቤተሰቦች እርስ በእርስ በደንብ የሚተዋወቁበትና የሚግባቡበትን አጋጣሚ በማስፋት ቤተሰብነታቸውን የሚያጠናክሩበት ነው።

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ዓርብ ነሐሴ 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You