ትልቁ የስፖርት መድረክ ኦሊምፒክ በአራት ዓመት በመጣ ቁጥር ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ ውዝግቦች መነሳታቸው የተለመደ ጉዳይ ነው። ከአትሌቶች ምርጫ እስከ በርካታ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ንትርክ የማያጣው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ በቅርቡ በተጠናቀቀው የፓሪስ 2024 ኦሊምፒክ አስቀድሞ በተነሱ ውዝግቦች ታጅቦ ተደምድሟል።
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከሥራ አስፈፃሚ ምርጫ አንስቶ በበርካታ ጉዳዮች አካሄዱ ሕጋዊ እንዳልሆነ ሲተች ሰንብተል። ሀገር አቀፍ የስፖርት ሕግና ደንቦችን በመጣስ ብዙዎች ጥያቄ የሚያነሱበት ኮሚቴ ተገዢነቱ ከሀገር አቀፍ ሕጎች ይልቅ ለዓለም አቀፉ ደንቦች እንደሆነ በተደጋጋሚ በመግለፅም መንግሥት ጣልቃ መግባት እንደማይችል ትልቅ አጥር ሰርቶ በራሱ መንገድ ሲጓዝ እየታየ ይገኛል።
ስፖርቱን የሚመራው መንግሥታዊ አካልም እስካሁን ዝምታን መርጧል። በዓለም አቀፍ ጥላ ስር ያሉ የስፖርት ተቋማት ከሀገር አቀፍ ሕግ ጋር በምን መልኩ ይተገበራሉ? የተጣሱት ሕግና ደንቦችስ የትኞቹ ናቸው? መንግሥት ጣልቃ የማይገባውና የስፖርት ተቋማት ገለልተኝነትስ እስከምን ድረስ ነው? የሚሉ ጥያቄዎች ለብዙዎች ግልፅ አይደሉም።
አቶ ታምራት በቀለ ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ለ10 ዓመታት የጽህፈት ቤት ኃላፊ እና በዋና ጸሃፊነት አገልግለዋል። በለንደን እና ሪዮ ኦሊምፒኮች እንዲሁም በ2ኛውና 3ኛው የወጣቶች ኦሊምፒክ ላይ ሲሳተፉ፣ በሶስቱ የቡድን መሪ (ቺፍ ደሚሽን) በመሆን አገልግለዋል። ከሥራቸው ጋር በተያያዘም በዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ የሚሰጡ ሥልጠናዎችን የመከታተል እንዲሁም ጉባዔዎች ላይ የመገኘት ብዙ ዕድል ነበራቸው። የዓለም አቀፉን ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሕግና ደንብ ጠንቅቀው ከሚያውቁ ሰዎችም አንዱ ናቸው።
እንደ አቶ ታምራት ማብራሪያ፣ ብሄራዊ የኦሊምፒክ ኮሚቴዎች የሚመሠረቱት በብሄራዊ የስፖርት ማህበራት ሲሆን፤ ዕውቅና የሚሰጠውም ስፖርቱን በበላይነት በሚመራው መንግሥታዊ አካል (የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር) ነው። ይህም አካል በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ሀገር አቀፍ የስፖርት ማህበራትን ይመዘግባል፣ እውቅና እና ፈቃድ ይሰጣል። በመሆኑም ኦሊምፒክ ኮሚቴም እንደሌላው የስፖርት ማህበር (ፌዴሬሽን) ሂደቱን ተከትሎ ይቋቋማል፤ ከዚያም ከዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ቻርተር ጋር በሚጣጣም መልኩ ሥራውን ያከናውናል። ለአብነት ያህልም ኦሊምፒክን በሀገር ደረጃ ማስፋፋት፣ የኦሊምፒክ መርሆችን በደንቡ ውስጥ እንዲያካትት፣ በኮሚቴው ውስጥ አባል የሚሆኑ አካላት እነማን ናቸው የሚለውንና ወዘተ አሠራሮችን መከተል ይገባዋል። በዚህም መሠረት ብሄራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከዓለም አቀፉ ተቋም የሚቀዳቸው ሕጎች ቢኖሩም በዋናነት ግን በሀገር አቀፉ የስፖርት ሕግ የሚመራ ይሆናል።
ብሄራዊ ኮሚቴው በሀገር አቀፍ ደረጃ እውቅና እና ፈቃድ ካልተሰጠው መንቀሳቀስ እንደማይችል የሚያስረዱት አቶ ታምራት፤ ከኢትዮጵያ ሕግ አንጻር ከታየ መንግሥታዊ ያልሆኑ እና የውጪ ድርጅቶች ጭምር ሲቋቋሙ በሲቪል ማህበራትና ማደራጃ ምዝገባና ዕውቅና ማግኘት እንዳለባቸው ያስቀምጣሉ። የስፖርት ማህበራትም በየ 4 ዓመቱ የሚታደሱ ሲሆን፤ ሕግና ሥርዓት የማያከብሩ ደግሞ በመንግሥታዊ አካሉ እንቅስቃሴያቸውን እስከማስቆም የሚደርስ ርምጃ ሊወሰድ ይችላል። አሁን ከኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር በተያያዘ በሚታየው ሁኔታ ግን መንግሥታዊው አካል በትዕግስት እያሳለፈው ያለ ይመስላል ይላሉ።
ከዚህ ባለፈ ዓለም አቀፉ ኮሚቴ የሚከለክላቸው ውስን ጉዳዮች ብሄራዊው ኮሚቴ ላይም ይተገበራሉ፤ ለአብነትም የመንግሥት ባለሥልጣናት የኮሚቴው ሥራ አስፈጻሚ እንዳይሆኑ ይከለክላል። በኢትዮጵያ ሕግ የማህበራት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ሥራቸውን የሚያከናውኑት በአማተር በመሆኑ ባለሥልጣናት መሆናቸውን ላይከለክል ይችላል። ይሁን እንጂ ዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የመንግሥት ባለሥልጣናትን (ተሿሚዎች) እንዲሁም በሕዝብ የተመረጡ አካላት በሥራ አስፈጻሚው መካተት እንደማይችሉ በቻርተሩ (ከገጽ 63-65) ላይ በግልጽ መቀመጡንም አቶ ታምራት ያነሳሉ። ይህም ማለት የክልል ስፖርት ቢሮ ኃላፊ የሆኑ የመንግሥት ባለሥልጣናትን የሚጨምር ነው። የሥልጣን ዘመንም ቢሆን ከ4 ዓመት መብለጥ የለበትም የሚል ሲሆን፤ ምናልባት የታመነበት ከሆነ ብቻ ከዚያ በላይ ሊቆይ ይችላል። ይህ ሁኔታ በዋናነት በኢትዮጵያ የስፖርት ማህበራት መመሪያ መሠረት ሲተገበር ኮሚቴውም እንደየትኛውም ፌዴሬሽን በዚህ ጥላ ስር ማለፉ የግድ ነው።
አቶ ታምራት እንደሚያስረዱት፣ የኦሊምፒክ ቻርተሩ እንዲተገበሩ ከሚያመላክታቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የምርጫ ጊዜ ከኦሊምፒክ መካሄድ በኋላ እንደሚደረግ ነው። የሀገር ውስጥ ደንቡም በተመሳሳይ ኦሊምፒክ ከተካሄደ እስከ 2 ወር ይደረጋል በሚል ያስቀምጠዋል። ምክንያቱም ለ4 ዓመታት የተከናወኑ ጉዳዮች ኦሊምፒክን ጨምሮ በወቅቱ የሚገመገም በመሆኑ ነው። ከዚያ ቀደሞ የሚደረግ ምርጫ ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የተደረገውም ሕገ ወጥ ምርጫ ነው። በመሆኑም ከቻርተሩ ጋር የሚጣረስ ነገር በመንግሥት (ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር) በኩል አይተግበር እንጂ ይህን በመሰለው ሕገወጥ አካሄድ ግን ርምጃ መውሰድ ይቻላል። ይህም በየትኛውም አካሄድ ሀገርን ሊያስቀጣ ወይም ሊያሳግድ የሚያስችል ሁኔታም በዓለም አቀፉ ኮሚቴ በኩል እንደማይኖር ያረጋግጣሉ።
አሁን በሥራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ይህም ብቻ ሳይሆን ቻርተሩን የጣሱ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑንም አቶ ታምራት ይጠቁማሉ። ‹‹ተቋማት የሚመሩት በሕግና ደንብ ሆኖ ሳለ ይህንን መጣስ ትልቁ ጥፋት ነው፤ ለሌሎች ፌዴሬሽኖችም መልካም አርዓያ ሊሆን አይችልም። ስፖርቱን ለማሳደግ ሥርዓት ማበጀት አስፈላጊ ነው፤ ለሞራል መገዛትም እንደዚያው። ›› የሚሉት አቶ ታምራት፣ ስፖርቱ እየጎዱ የሚገኙ አካሄዶች በቀጣይ እንዳይባባሱ መንግሥት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ያወጣውን ደንብ የማስከበር ኃላፊነት እንዳለበት ያስረዳሉ። በመሆኑም እየተስተዋሉ የሚገኙ ችግሮችን በመመርመር መንግሥት ርምጃ መውሰድ እንደሚገባው አቶ ታምራት ምክረ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 9 /2016 ዓ.ም