
አዲስ አበባ፡- ኢፕድ እና የሠላም ሚኒስቴር አብረው ለመሥራት የተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት የሠላም ግንባታና የአብሮነት እሴት ሥራዎች አጠናክሮ ለማሠራት እንደሚያስችል ተገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እና የኢፌዴሪ ሠላም ሚኒስቴር በተለያዩ ጉዳዮች አብረው ለመሥራት የሚያስችላቸውን የሁለትዮሽ ሰምምነት ፊርማ ትላንት ተፈራርመዋል፡፡
በዚሁ ወቅት ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መሳፍንት ተፈራ እንደገለጹት፤ የሀገር ግንባታ ዜጎች አዕምሮ ውስጥ የሚሠራ ነው፡፡ ሀገር የምትገነባውም በዜጎች አዕምሮና ልብ ውስጥ ነው፡፡ ይህ የሚመሠረተውም ሀሳብ ላይ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትም ሆነ የሠላም ሚኒስቴር በዋናነት የሚያገናኛቸው ጉዳይ ዜጋ ላይ መሥራታቸው ነው፡፡ ስምምነቱም አቅምን አቀናጅቶ የተሻለ የሠላም ግንባታ ሥራዎችን ለማከናወን ያስችላል፡፡
ሁለቱም ተቋማት በሀገር ግንባታ ሥራ ተመሳሳይ ኃላፊነት እንዳለባቸው የገለጹት አቶ መሳፍንት፤ የሠላም ግንባታ በኮሙኒኬሽን ላይ የተመሠረተ እንዲሆን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በታሪኩ ያካበታቸውን ልምዶች ተጠቅሞ እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡
ኢፕድ በኅትመት ሥራዎቹ ለረጅም ጊዜ ሀገር ሲገነባ እንደቆየ፤ ባሉት የኅትመት ውጤቶች በርካታ ሥራዎችን እየሠራ እንዳለ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ወደ ዲጂታል ዓለም እየገባ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ድርጅቱ “ስለ ኢትዮጵያ”ን ጨምሮ የተለያዩ ሁነቶችን በማሰናዳት ረገድም አቅሙን ማሳደግ እንደቻለም ጠቁመዋል፡፡ በእነዚህ ሥራዎች በሀገር ግንባታ ላይ የራሱን ዐሻራ ማሳረፍ መቻሉንም ነው የገለጹት፡፡
ስምምነቱ ሁለቱ ተቋማት ለየብቻቸው የሚያከናውኗቸውን ሥራዎች የጋራ የማድረግ ትልም መሆኑን ጠቅሰው፤ ነባሩን አቅም በመጠቀምና በማሳደግ ሁለቱ ተቋማት የሚያቀራርቡና የወል ትርክት ላይ በጋራ ለመሥራት ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሠላም ታሪክ በፎቶና በጽሑፍ ኢፕድ ውስጥ ይገኛል በማለት፤ ይህንን በአግባቡ በመጠቀም ዜጋው የሠላም ሀብት እንዳለው እንዲያውቅ በተለያዩ ዓውደ ርዕይዎች እንዲያዩ ይደረጋል ብለዋል፡፡ የተለያዩ ሀገራዊ አንድነትንና አብሮነትን የሚያጠናክሩ፣ የፓናል ውይይቶች እንደሚኖሩ ከዚህ ባሻገር የተለያዩ ሥልጠናዎች እንደሚሰጡም አስታውቀዋል፡፡
የሠላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የመግባቢያ ስምምነቱ በተለይ የሠላም ግንባታና የአብሮነት እሴት ሥራዎች ላይ አብሮ ለመሥራት የሚያስችል መሆኑን ጠቁመው፤ ኢፕድ ከዚህ ቀደም ሕዝቦች አንድ ላይ ተገናኝተው ስለ ሀገር እንዲነጋገሩ በማድረግ የጀመራቸው ሥራዎችና ሚኒስቴሩ በሚያደርጋቸው ሁነቶች ላይ የዜና ሽፋን በመስጠት እያደረገ ያለው ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚረዳ ነው ብለዋል፡፡
ሚኒስቴሩ በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት በብሔራዊ መግባባት፣ በአብሮነት፣ እንዲሁም የፌዴራል ሥርዓቱን ከማጠናከር አኳያ ሰፋፊ ሥራዎችን እየሠራ እንዳለ የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ እነዚህን ተግባራት ከሚዲያ ጋር አብሮ መሥራት የምርጫ ጉዳይ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡
ሀገራዊ፣ ቀጣናዊና አሕጉራዊ በሆኑ ትላልቅ መድረኮች ላይ ከዜና ሽፋን በዘለለ ሁነቶች ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲሄዱ ከኅትመት ሥራው ጎን ለጎን ተጨማሪ አቅም እየፈጠረ እየመጣ ካለው ኢፕድ ጋር አብሮ መሥራት ግድ የሚልበት ወቅት ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የሠላም ሚኒስቴር በተለይ አዎንታዊ ሠላም ግንባታና አብሮነት ላይ እና የፌዴራል ሥርዓቱ እንዲጠናከር በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች የተለያዩ የሚዲያ “ፕላትፎርሞችን” ይጠቀማል። ከተለያዩ ብዙኃን መገናኛዎች ጋር እየሠራም ይገኛል። ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር በሚኖረው ግንኙነት በተለይ በኅትመቱ ዘርፍ አንጋፋ ተቋም እንደመሆኑ መጠን ሥራዎች እስከታችኛው መዋቅር ማድረስና ዜጎች ስለ ሀገራቸው ኃላፊነት የሚሰማቸው እንዲሆኑ ከማድረግ አኳያ ሥራዎች በተለያዩ አማራጮች እንዲሄዱ ይደረጋል ሲሉ አብራርተዋል፡፡
በትውልድ ግንባታ ላይ በኢፕድ በቅርቡ የተጀመረውን የሕጻናት መጽሔትን ጨምሮ ዜጎች ከትምህርት ቤት ጀምረው እንዲታነጹ በሚያስችሉ ተግባራት ላይ በጋራ እንደሚሠራ ተናግረዋል። ከዚህም ባሻገር በወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ ለሀገር ግንባታ የሚያግዙ የጋራ ሥራዎች እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡
ኢፕድ አሕጉራዊ መድረኮችን የሚመጥን ሥራ እየሠራ መሆኑን እናምናለን ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ተቋሙ ሰፋፊ የዶክመንተሪ ልምድ ያለው በመሆኑም ሰፋፊ ሥራዎች በጋራ እንደሚሠሩ፤ በሠላምና በሀገር አንድነት ላይ ያተኮሩ ኤግዚቢሽኖች በማዘጋጀት ሀገራዊ ግንባታ ላይ ጠንካራ ሥራዎችን እንደሚያከናውኑ አስታውቀዋል፡፡
ፕሬስ በራሱ የአብሮነት ቤት እንደመሆኑ አቅሙን ልንጠቀምበት ይገባል ነው ያሉት፡፡ ኢትዮጵያን በጽሑፍ ደረጃ ከ80 ዓመታት በላይ ታሪክ የያዘ ሲሆን፤ ይህንን መጠቀም ለዘላቂ ሀገራዊ አንድነት የሚጠቅም ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ አኳያ ሠላም ሚኒስቴር ኢፕድን እንደ ቁልፍ አጋር አድርጎ እንደሚያይ ጠቅሰዋል፡፡
የሁለትዮሽ ስምምነት የፊርማ ሥነ ሥርዓቱ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መሳፍንት ተፈራ እና በኢፌዴሪ ሠላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶክተር) መካከል ተፈጽሟል፡፡
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ነሐሴ 9 /2016 ዓ.ም