ኮስታራው አሠልጣኝ- ዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ

ኢትዮጵያ የጀግኖች ሀገር ነች፡፡ በጦር ሜዳ ብቻ በየተሰማሩበት መስክ ሁሉ ደምቀው ኢትዮጵያን ያደመቁ፤ የሕዝብን አንገት ቀና ያደረጉ በርካታ ብርቅዮችን ከማሕፀኗ አፍርታለች፡፡ እነዚህ ጀግኖች በተነሱ ቁጥርም የኢትዮጵያ ስምም አብሮ ይነሳል፡፡

ሀገራቸውን ከውጭ ወራሪና ጠላት በመከላከል አኩሪ ታሪክ የሠሩ፣ የሕዝባቸው ደኅንነትና አንድነት እንዲጠበቅ ለማድረግ መስዋዕትነት የከፈሉና አንፀባራቂ ታሪክ የሠሩ ጥቂቶች አልበሩም፡፡ በደራሲነት፣ በሙዚቃ፣ በሥዕል፣ በስፖርት፣ በታሪክ፣ በሳይንስና በእምነት አስተምሮ፣ የኪነ ጥበብና የምርምር ሥራዎችም ኢትዮጵያን በዓለም የበለጠ እንድትታወቅ ያደረጉ ትናንትናም ዛሬም ደምቀው የሚታዩ ደማቅ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ብዙዎች ናቸው፡፡

ከእነዚህ የሀገር ባለውለታ ግለሰቦች መካከል ኢትዮጵያ በስፋት በምትታወቅበት የአትሌቲክስ ስፖርት በተለይ በረዥም እርቀት አትሌቲክስ ሥልጠና ጉልህ ተሳትፎ የነበራቸውና የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አደባባይ ማውለብለብ የቻሉ ዘመን አይሽሬ ስመ ጥር አትሌቶችን በውጤታማ አሠልጣኝነት ማፍራት የቻሉት ወልደመስቀል ኮስትሬ (ዶ/ር) በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ።

ወልደመስቀል ኮስትሬ (ዶ/ር) ጥር 21 ቀን 1939 ዓ.ም. በተጉለትና ቡልጋ አውራጃ ልዩ ስሙ ወንፈስ በተባለ ሥፍራ ነበር የተወለዱት። ዕድሜያቸው ለትምህርት በደረሰ ጊዜ የቤተ-ክህነት ትምህርት ተከታትለዋል። በመቀጠልም የትውልድ አካባቢያቸውን ለቀው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በቀድሞ ስያሜው አስፋወሰን ይባል በነበረው ት/ቤት በመግባት መደበኛ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል::

በነበራቸው የስፖርት ተሳትፎም ትምህርት ቤታቸውን እየወከሉ በ400፣ 800 እና 1500 ሜትር ይወዳደሩ ነበር:: ቀጥሎም በመምህራን ማሠልጠኛ ገብተው በስፖርት ትምህርት በመሠልጠን እንደጨረሱ በዚያው በተማሩበት ት/ቤት በመምህርነት ሠልጥነው በዚያው ሲያገለግሉ ቆዩ::

ወልደመስቀል (ዶ/ር) በ1956 ዓ.ም. የውጭ የትምህርት ዕድል አግኝተው ወደሀንጋሪ በመሄድ የተማሩ ሲሆን በዚያው ሀገር ቆይታቸው የሚማሩበትን ኮሌጅ እየወከሉ በ5,000 እና በ 10,000 ሜትሮች መወዳደራቸው ታውቋል:: በ1963 ዓ.ም. በስፖርት ሳይንስ የማስተርስ ዲግሪያቸውን ይዘው ወደ ሀገራቸው በመምጣት በኮተቤ መምህራን ኮሌጅ እያስተማሩ በተደራቢ በአትሌቲክሱ ዘርፍ የብሔራዊ ቡድኑን ከሚያሠለጥኑ አንዱ በመሆን ሠርተዋል::

በ1966 ዓ.ም. እንደገና ወደውጭ ሀገር በመሄድ ቀደም ሲል በተማሩበት ትምህርት ቤት በመግባት የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አገኙ:: በ1973 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ በቀድሞው የአካል ማሠልጠኛና ስፖርት ኮሚሽን መሥሪያ ቤት ተመድበው ሲሠሩ ቆዩ::

ከ 1977 ዓ.ም. ጀምሮ በአትሌቲክስ ፌዴሬሽን በአሠልጣኝነት ተመድበው በ800፣ በ1,500፣ በ10,000 እና እንዲሁም በማራቶን እያሠለጠኑ ብዙ አትሌቶችን ለውጤት አብቅተዋል። ወልደመስቀል ኮስትሬ (ዶ/ር) የዓለም ምርጥ የአትሌቲክስ አሠልጣኝ በመሆን በኅዳር ወር 1999 ዓ.ም. በፈረንሣይ አገር በሞናኮ ከተማ ተሸላሚ ለመሆን ችለዋል። ከሦስት አሥርታት በላይ በአትሌቲክሱ ዓለም ላቅ ያለ ተግባር ማከናወናቸው የተገነዘበው ኢንተርናሽናል አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር ‹‹ከኮከብም የሚበልጥ ኮከብ›› አለ በማለት ነው ወልደመስቀል (ዶ/ር) ዓለም አቀፍ እውቅና የሰጠው።

ወልደመስቀል (ዶ/ር) በስፖርት ዘርፍ ለሀገር ላበረከቱት የላቀ አስተዋፅዖ የ2007 ዓ.ም. ‹‹የበጎ ሰው ሽልማት›› በስፖርት ዘርፍ ተቀብለዋል።

ወልደመስቀል ኮስትሬ (ዶ/ር) በአሠልጣኝነት ዘመናቸው ካፈሯቸው ስመጥር አትሌቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙባቸዋል፦ ኃይሌ ገ/ሥላሴ፤ ሚሊዮን ወልዴ ፤ደራርቱ ቱሉ ፤ፊጣ ባይሳ፤ ጌጤ ዋሚ፤ ቀነኒሳ በቀለ፤ አሰፋ መዝገቡ፤ ስለሺ ስህን፤ ወርቅነሽ ኪዳኔ፤ ጥሩነሽ ዲባባ ፤መሠረት ደፋር እና ሌሎች በርካታ አትሌቶችን አፍርተዋል።

ወልደመስቀል (ዶ/ር) የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድንን ይዘው በተሳተፉባቸው አምስት ኦሎምፒኮች ላይ 28 ሜዳሊያዎችን ለሀገራቸው አስገኝተዋል (13 ወርቅ 5 የብር እና 10 የነሐስ ሜዳሊያን ማምጣት ችለዋል።)

በሮም ኦሊምፒክ የአበበ ቢቂላ ድል (ጳጉሜን 5 ቀን 1952 ዓ.ም.) በኋላ በወንዶች ብቻ የተገደበው የኢትዮጵያውያን የኦሊምፒክ ድል፣ በሴቶች በኩል ፍሬ ማፍራት የጀመረው ግን በ1984 ዓ.ም. ነበር፡፡ በባርሴሎና ኦሊምፒክ በዕንቁዋ ደራርቱ ቱሉ የ10,000 ሜትር ወርቃማ ድል፡፡ አበበ ቢቂላን ለድል እንዳበቁት አሠልጣኙ ሜጀሪ ኦኒ ኒስካነን ሁሉ የሴቶች ፋና ወጊ ድል የተገኘው በወልደመስቀል ኮስትሬ (ዶ/ር) አሠልጣኝነት ነበር፡፡

ከሞስኮ ኦሊምፒክ (ሐምሌ 1972 ዓ.ም.) በማጣሪያ ተፎካካሪነት ብቻ ተገድቦ የነበረው የኢትዮጵያውያት አትሌቶች የሩጫ ጉዞ በወርቅ መታጀብ የጀመረው ባርሴሎና ላይ ነበር፡፡ በአራት ዓመቱ አትላንታ ላይ ቀጠለ፡፡ በታዋቂው አሠልጣኝ ንጉሤ ሮባ ዘመን በሞስኮ ኦሊምፒክ (1972 ዓ.ም.) በ5,000 እና በ10,000 ሜትር ወርቆችን ያገኘው ምሩፅ ይፍጠር የድል ሰንደቅ ዳግም ሕይወት የዘራው ከአራት ኦሊምፒያድ 16 ዓመት ቆይታ በኋላ ነበር፡፡

በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ታሪክ በተለይ ከባርሴሎና ኦሊምፒክ ወዲህ በውጤታማነት ከተገኙባቸው የመጨረሻዎቹ አምስት ኦሊምፒያዶች የተመዘገቡት 28 ሜዳሊያዎች (13 ወርቅ፣ 5 ብርና 10 ነሐስ) ወልደመስቀል (ዶ/ር) የዋና አሠልጣኝነት ትሩፋቶች ናቸው፡፡

ወልደመስቀል (ዶ/ር) ከአሠልጣኝ ንጉሤ ሮባ ኅልፈት በኋላ የኢትዮጵያ አትሌትክስ ብሔራዊ ቡድን የዋና አሠልጣኝነት በትሩን በመቀበል ከባርሴሎና እስከ ቤጂንግ በተካሄዱት ኦሊምፒኮች፣ እንዲሁም በስምንት የዓለም ሻምፒዮናዎች በውጤታማነት የላቀ አበርክቶ ማኖር ችለዋል።

የስመ ጥር አትሌቶች ምስክርነት፦

አትሌት መሰለች መልካሙ፦ ከዶክተር ጋር ለረጅም ጊዜ ባልሠራም በቤጂንግ ኦሊምፒክ የመሠልጠን ዕድሉ ነበረኝ። ጥሩና ጠንቃቃ አሠልጣኝ መሆናቸውን እኔ ብቻ ሳልሆን ሁሉም አትሌትና የስፖርት ቤተሰብ የሚያውቀው ነው። እኔም ከዚህ የበለጠ እሳቸውን የምገልጽበት ቃላት የለኝም። በአጠቃላይ ምትክ የሌላቸው ውጤታማ አሠልጣኝ ናቸው።

ወልደመስቀል (ዶ/ር) ከሌሎች አሠልጣኞች ብዙ የሚለዩባቸው ብቃቶች አሏቸው። ሥራ ላይ ቀልድ አያውቁም። ከልባቸው ነው የሚያሠሩት። ደከመኝና ሰለቸኝ የማይሉ ታታሪ አሠልጣኝ ናቸው። በተፈጥሯቸው በጣም ለየት ያሉ ናቸው። ለሥራ ያላቸው ሥነ ምግባር በተለይ በጣም አስገራሚና ሁላችንም ልንወርሰው የሚገባ ነገር ነው።

ስለእሳቸው በጣም የሚቆጨኝ ነገር የልምምድና ሥልጠና አሠራራቸው ወደ ሌሎች ተተኪ አሠልጣኞችና ባለሙያዎች የሚተላለፍበት አጋጣሚ አለመኖሩ ነው። ከእሳቸው ብዙ መማር ይቻላልና” ትላለች።

አትሌት ስለሺ ስህን፦ “ወልደመስቀል (ዶ/ር) ከየትኛውም አሠልጣኝ የተለዩ ናቸው። በአትሌቲክስ አሠልጣኝነታቸው ውጤታማና በግል ባሕሪያቸውም ጠንካራ ሰብዕና ያላቸው ናቸው። በአትሌቲክሱ ስፖርት በቂ እውቀት አላቸው። ሥልጠናውን በደንብ ይችላሉ። በሚገባ ጠንቅቀው ያውቃሉ። ለማን ምን አይነት ሥልጠና መስጠት እንዳለባቸው ያውቃሉ። እያንዳንዱን አትሌትም ጠንካራና ደካማ ጎኑን ለይተውም ያውቃሉ። ለዚህም ነው በሥራቸው ውጤታማ መሆን የቻሉት።

እሳቸው ከሠልጣኝ አትሌቶች ጋር ያላቸው ግንኙነትም በጣም መልካምና የአባትና ልጅ አይነት ነው። አሠልጣኝ ብቻ ሳይሆን እንደአባትም እየተቆጡና እየመከሩ የሚያሠለጥኑ ናቸው። በሁሉም አትሌት ዘንድ የሚከበሩና የሚወደዱ ናቸው። በሥራቸውም በጣም የሚከበሩና ማንም አትሌት በእሳቸው በሠለጠንኩ ብሎ የሚመኛቸው ናቸው። በሕይወት ዘመናቸው ለሰጡን መልካም ነገር ሁሉ መመስገንና መከበር አለባቸው።” ይላል።

አትሌት ወርቅነሽ ኪዳኔ፦ “በወልደመስቀል ኮስትሬ (ዶ/ር) ሁለት ኦሊምፒክና ሦስት የዓለም ሻምፒዮናዎች ላይ ተሳትፌያለሁ። በዚህ ራሴን እንደ ዕድለኛ እቆጥረዋለሁ። ቀደም ሲል እነ ደራርቱንና ጌጤ ዋሚን በሚያሠለጥኑበት ጊዜ ምናለ እኔም በእሳቸው በሠለጠንኩ ስል እመኝ ነበር። ዕድሉን አግኝቼ በመሠልጠኔ ደስተኛ ነኝ። በእሳቸው መሠልጠኔ ጠንካራ አትሌት እንደሆን አድርጎኛል።

እኔን ጨምሮ ብዙ የኢትዮጵያ አትሌቶች ላገኘነው ውጤት የእሳቸው አስተዋፅዖ በጣም የጎላ ድርሻ አለው። በጣም ውጤታማ የሥልጠና መንገድ የሚከተሉ ጠንካራ አሠልጣኝ ናቸው። እሳቸውን የሚተካ አሠልጣኝ እስከአሁን አላገኘንም። በሕይወት ዘመናቸው ካጎናጸፉን ክብርና ደስታ አንጻር የሚገባቸውን ክብርና እውቅና አግኝተዋል ብዬ አላስብም። በዚህም በጣም አዝናለሁ። እሳቸው የኢትዮጵያም ሆነ የአፍሪካ ታላቅ አሠልጣኝ ናቸው›› ትላለች።

አትሌት ገዛኸኝ አበራ፦ “በትራክ ሩጫዎች ላይ የመሠልጠን ዕድሉን ባላገኝም በቅርበት የማወቅ ዕድሉ ነበረኝ። ከብሔራዊ ቡድናችን ጋር እሳቸው ካሉ በራስ መተማመንና አሸናፊነት በሁላችንም ልብ ውስጥ ይኖራል። ለአትሌቶች ድል የእሳቸው ጠንካራ ሥራና የአሸናፊነት መንፈስ ትልቅ ሚና አለው።

ስለእሳቸው በጣም የሚቆጨኝ ነገር በሕይወት ሳሉ በስፖርቱ ያላቸው እውቀት የሚተላለፍበት መንገድ አለመፈጠሩ ነው። አንድ መጽሐፍ እንኳ አዘጋጅተው ቢሆን ጥሩ ነበር። ቢሆንም በዘመናቸው ላስገኙት ታላላቅ ድሎች ሁሌም ሊመሰገኑና ሊከበሩ ይገባል›› ይላል።

ወልደመስቀል (ዶ/ር) በአንድ ወቅት ያጋጠማቸው የከፋው የመኪና አደጋ በተደጋጋሚ በሀገር ውስጥና በውጭ አገሮች ከፍተኛ ሕክምና ሲከታተሉበት ቆይተዋል፡፡ ይህም ተጓዳኝ ሕመም በመፈጠሩ አደባባይ ከመዋል ገድቧቸው ኖሯል፡፡

ሀገራችን በእስካሁኑ የኦሊምፒክ ተሳትፎዋ ካገኘቻቸው ሜዳሊያዎች ውስጥ 28ቱ የተመዘገቡት በወልደመስቀል ኮስትሬ (ዶ/ር) የአሠልጣኝነት ዘመን መሆኑ፣ ለሀገራችን የአትሌቲክስ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ የነበራቸው አሠልጣኝ ስለመሆናቸው ትልቅ ማሳያ ነው።

በ1939 ዓ.ም ረቡዕ ጥር 21 ቀን፣ ከአባታቸው ከአቶ ኮስትሬ ሰበሬና ከእናታቸው ወ/ሮ እናት ገብርኤል ደስታ፣ የተወለዱት ወልደመስቀል (ዶ/ር) እሑድ ግንቦት 7 ቀን 2008 ዓ.ም. ነበር ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት። በ69 ዓመታቸው ያረፉት ዶ/ር ወልደመስቀል የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነበሩ።

ክብረአብ በላቸው

አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You