ለ16 ወራት የቆየውን የሱዳን ግጭት ለማስቆም ሁለቱን ተፋላሚዎች ለማቀራረብ የሚደረገው ድርድር በነገው ዕለት በጄኔቫ መካሄድ ይጀምራል::
የሱዳን ሠራዊት በድርድሩ ላይ እንደሚሳተፍ ማረጋገጫ ባይሰጥም ድርድሩ በተያዘለት ቀጠሮ እንደሚካሄድ አሜሪካ አስታውቃለች::
በአሜሪካ እና ሳዑዲ ዓረቢያ መሪነት በሲውዘርላንድ ጄኔቫ እንዲካሄድ ለቀረበው የድርድር ጥሪ የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መንግሥት ፈቃደኛ መሆኑን አስታውቆ እንደነበር ይታወሳል::
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፈው የፈረንጆቹ ወር መጨረሻ ላይ ባወጣው መግለጫ ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ጋር ለመደራደር ፈቃደኛ ነኝ ቢልም፤ ተቀናቃኝ የሆኑት ሀምዳን ዳጋሎ የሚመሩት ጦር ከተቆጣጠራቸው ስፍራዎች እንዲለቅ እና ሌሎች አካባቢዎችን ለመቆጣጠር የሚያደርገውን ውጊያ እንዲያቆም ቅድመ ሁኔታ አስቀምጧል::
በተጨማሪም በድርድሩ አጀንዳዎች ዙሪያ ከአሜሪካ ባለሥልጣናት ጋር መነጋገር እንደሚፈልግ ገልጿል::
ይህን ተከትሎ በሳዑዲ ዓረቢያ ጂዳ የሱዳን ጦር ባስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች ላይ ምክክር ሲደረግ ቢቆይም በሳምንቱ መጨረሻ እሁድ ያለ ስምምነት ተበትኗል::
በሱዳን የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ቶም ፔሪዬሎ ከሱዳን ጦር ጋር ሲደረግ የነበረው ምክክር ያለ ስምምነት መጠናቀቁን ተከትሎ የጦሩ ተወካዮች በነገው ዕለት በሚጀምረው ጉባኤ ላይ እንደሚሳተፉ ማረጋገጫ ባይሰጡም ጦርነቱን ለማስቆም የሚደረገው ዓለምአቀፋዊ ጥረት አካል የሆነው የጄኔቫው ድርድር ይካሄዳል ብለዋል::
ልዩ መልዕክተኛው አክለውም በሱዳኑ ግጭት ዙሪያ አፋጣኝ ተኩስ አቁም እና ድርድር የማይካሄድ ከሆነ የተራዘመው ጦርነት ሀገሪቱን ሊያፈርሳት ይችላል ነው ያሉት::
በንጹሐን ላይ በሚደርስ በደል እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተደጋጋሚ የሚከሰሰው የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪ ጄነራል ሃምዳን ዳጋሎ ንጹሐንን የሚጠብቅ አዲስ የፀጥታ ኃይል ማቋቋማቸውን አስታውቀዋል:: በተጨማሪም ጄኔራሉ በነገው ጉባኤ ላይ ልዑካቸው እንደሚካፈል አረጋግጠዋል::
ሮይተርስ እንደዘገበው የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በተለያዩ ስፍራዎች የሚያደርሳቸውን የተጠናከሩ ጥቃቶችን ቀጥሏል:: በቅርብ ቀናት ከዋና ከተማዋ ቅርብ ርቀት ላይ በምትገኝው ኦምዱርማን በፈጸመው ጥቃት 40 የሚጠጉ ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል::
16 ወራትን ባስቆጠረው ጦርነት 10 ሚሊዮን ሰዎች ከቀያቸው ሲፈናቀሉ በ10 ሺዎች እንዲገደሉ ምክንያት ሆኗል::
የቅርብ ጊዜ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ሱዳን ካሏት 18 ክልሎች ውስጥ ስምንቱ በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ቁጥጥር ስር ይገኛሉ::
በነገው እለት ጄኔቫ የሚካሄደው ድርድር በአሜሪካ እና ሳዑዲ መሪነት የሚደረግ ሲሆን የአፍሪካ ኅብረት፣ ግብፅ እና ዓረብ ኢምሬትስ በታዛቢነት እንደሚታደሙ ተገልጿል::
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 8 ቀን 2016 ዓ.ም