የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን ከአጸደቀ እነሆ 70 ዓመቱን አከበረ፡፡ እነዚህ ድንጋጌዎች ሁሉም አባል አገራት ያጸደቋቸው እኤአ በ1948 ቢሆንም አተገባበራቸው ግን እንደየአገራቱ መንግስት ቁርጠኝነት የሚለያይ ነው፡፡ ኢትዮጵያም የተመድ መስራችና አባል እንደመሆኗም እነዚህን ድንጋጌዎቹን ተቀብላለች፡፡ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎቹን በመቀበል የህገ መንግስቷ አካል ብታደርግም በሰብዓዊ መብት አያያዝ ረገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ መልካም ስም አልነበራትም፡፡
ዜጎች በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት እንደወጡ የሚቀሩበት፣ ያለ ፍርድ ስውር እስር ቤት የሚታሰሩበት፣ የሚገረፉበትና የሚሰቃዩበት ሀገር ተብላ ስሟ በአሉታዊ መልኩ ይጠቀሳል፡፡ ለአብነትም በቅርቡ መንግስት ጥፍር መንቀል፣ በወንድ ብልት ላይ ውሃ የሞላው ላስቲክ ማንጠልጠል፣ የወንድን የዘር ፍሬ ማምከን፣ በሌሊት ጫካ ወስዶ እርቃን ማሳደርና አፍንጫ ውስጥ የእስክሪፕቶ ቀፎ መክተትና መሰል ኢሰብዓዊ ድርጊቶች በዜጎች ላይ መፈጸማቸውን ይፋ አድርጓል፡፡ እነዚህ ድርጊቶችም በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ ምን ያህል የከፋ እንደሆነ ማሳያ ነው፡፡ እነዚህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በሃይማኖትም ሆነ ከህገ መንግስት አንጻር መወገዝ ያለባቸው ናቸው፡፡
የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በተለያየ መልኩ መፈጸማቸውን ተጎጂዎች ለፍርድ ቤት ሳይቀር አቤት ቢሉም ሰሜ አላገኙም፡፡ ይህም የፍትህ ሥርዓቱ የተንጋደደ መሆኑን አጎልቶ የሚያሳይ ነው፡፡ ምክንያቱም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በመንግስት በኩል ተገቢ የሆነ ምርመራ ተካሂዶ የድርጊቱ ፈጻሚዎች ናቸው ተብለው የሚጠረጠሩት ለሕግ አልቀረቡም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን እነዚህ ተጠርጣሪዎችን በህግ ተጠያቂ የማድረግ ተግባር እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የመንጋ ፍትህ የወለዳቸው እዚህም እዚያ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተስተውለዋል፡፡ እነዚህ አካላት በህግ ተጠያቂ ማድረግም ተገቢ ይሆናል፡፡
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለሰብአዊ መብት መከበር ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው፡፡ ለአብነት ያህልም መንግስት በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን ፈትቷል፤ በፍትህ ሥርዓቱ ላይ ከፍተኛ ሊባል የሚችል ለውጥ እያደረገ ነው፡፡ የፀረ ሽብርና የመገናኛ ብዙሃን አዋጆችን ጨምሮ የተለያዩ ሕጎች እንዲሻሻሉ ስራዎች ተጀምረዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ እርምጃዎች መንግስት ለዜጎች ሰብአዊ መብት መከበር ያለውን ቁርጠኝነት ያረጋግጣሉ፡፡
ሆኖም አሁንም ቢሆን ኢ- ህገመንግስታዊ ተግባራትና የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በዘላቂነት ለማስቀረት በመንግስት በኩል ብዙ ስራዎች መሰራት አለባቸው፡፡ የፍትህ ሥርዓቱን ችሎታ ባላቸውና ህግን መሰረት አድርገው በሚሰሩ ባለሙያዎች መመደቡ፣ አፋኝ ህጎችን እንዲሻሻሉ ማድረግ፤ በአጠቃላይ መንግስት ዜጎችን ለማገልገል እንጂ ለማፈን እንዳልተፈጠረ ማሳየት የሚያስችል ለውጥ ያለማቋረጥ ማካሄድ አለበት፡፡
እርግጥ ነው መንግስት ብዙዎች የተሰቃዩበትና የተፈረጁበትን የጸረ ሽብር ህግ ጨምሮ ሌሎች ህጎችን ለማሻሻል ተግባራዊ እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ ይህን አበረታች ጅማሮውን ዳር ለማድረስ አሁንም ብዙ መስራት ይጠበቅበታል፡፡
በዜጎች ላይ ኢ ሰብዓዊ ድርጊት ፈጽመዋል የተባሉ አሁንም በህግ ቁጥጥር ስር ያልዋሉ ተጠርጣሪዎችንም እያደነ በህግ ተጠያቂ የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡
የመከላከያ ሰራዊቱንና የደህንነት አካሉን ገለልተኛ ሆኖ ሁሉንም ህዝብ በሚያገለግል መልኩ እንደገና ማዋቀሩ አስፈላጊ ነው፡፡ የብሄር ብሄረሰቦች ስብጥሩም መስተካከል ይኖርበታል፡፡ በተለይ የደህንነት አካሉ ከማሰርና ከመመርመር ድርብ ስራው መውጣት አለበት፡፡ ስለዚህ መንግስት በእነዚህ ተቋማት የጀመረውን የለውጥ ስራ አጠናክሮና መቀጠል ይኖርበታል፡፡ እንዲሁም እንባ ጠባቂ ተቋምና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የዜጎች ሰብዓዊ መብት መከበር በሚፈለገው መልኩ እንዲሰሩ አቅማቸውን ማጠናከር አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግስት የጀመረውን ስራዎች በቁርጠኝነት ዳር ሊያደርሳቸው ይገባል፡፡
እንዲሁም በዘላቂነት ደግሞ መንግስት ከህጻናት መዋያ ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ በስነ ምግባር የበለጸገና የሰዎችን መብት የሚያከብር ዜጋ በማነጽ ረገድ ትልቅ የቤት ስራ ይጠብቀዋል፡፡ ህጻናት ከአስተዳደግ ጀምሮ በትምህርት ቤትም ጭምር ሥነ ምግባር ያላቸው፣ የሰዎችን ሰብዓዊ መብት የሚያከብሩ፣ ለህግ የሚገዙና ለእውነት እንጂ ለገንዘብ ህሊናቸውን የማይሸጡ ዜጎች አድርጎ የማፍራት ስራ ቤተሰብ፣ ህብረተሰቡ፣ የሃይማኖት አባቶችና መንግስትም ሃላፊነት ነው፡፡ ስለዚህ ዜጎች የመልካም እሴት እንዲገነቡ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም ሰብዓዊ መብትን ለማክበር ሁሉም ባለድርሻ አካል በቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባል፡፡
This blog covers important and relevant topics that many are afraid to address Thank you for being a voice for the voiceless