የመላው ሕዝባችን የትናንት ሆነ የዛሬ የልብ መሻት ሰላም እና ልማት ነው። ይህ እንደ ሀገር ከመጣንበት ብዙ ዋጋ ካስከፈለን እና እያስከፈለን ካለው የግጭት ፣ የኋላቀርነት እና የድህነት ታሪክ ለዘለቄታው ለመውጣት ከመፈለግ የሚመነጭ ፤ተጨባጭ እስካልሆነ ድረስ የመጪዎቹ ትውልዶችም መሻት ሆኖ የሚቀጥል ነው።
እኛ ኢትዮጵያውያን የረጅም ዘመን የሀገረ- መንግሥት ግንባታ ታሪክ ካላቸው ጥቂት የዓለም ሀገራት በዋነኛነት የምንጠቀስ ፤ በነዚህ ረጅም ዓመታትም የታላላቅ ስልጣኔዎች ፣የብዙ ታሪክ እና ባህል ባለቤት በመሆን፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እና ሞገስ ማግኘት የቻልን፤ የሰው ልጅ መገኛ በመሆንም ተጠቃሽ ነን።
ይህም ሆኖ ግን እንደሀገር በየዘመኑ እያጋጠመን ካለው የሰላም እጦት ፣ ከዚህ ከሚመነጭ ድህነት እና ኋላቀርነት የተነሳ፤ በአብዛኛው መታወቂያችን ጦርነት ፣ ጦርነት የሚፈጥረው ሁለንተናዊ ጉስቁልና እና ተመጽዋችነት ከሆነ ውሎ አድሯል። በዚህም የታሪካችንን ያህል ቀና ብለን እንዳንሄድ ሆነናል።
በአንድ በኩል ከቀደሙ የግጭት ታሪኮቻችን/ ስህተቶቻችን በአግባቡ መማር አለመቻላችን፣ ከዚያም ባለፈ ችግሮቻችንን ዘመን በሚዋጅ የአስተሳሰብ መሠረት ላይ ቆመን ለመፍታት የሚያስችል ዝግጁነት አለመፍጠራችን ፣ እንደ ሕዝብ የምንመኘውን ሰላም እና ልማት እውን ማድረግ ሳይቻለን ቀርቷል።
እንደ ጥላ እየተከተለን ያለውን ይህንን ችግር አሸንፎ ለመውጣት በተለያዩ ዘመናት የነበሩ ትውልዶች ከፍ ባለ የለውጥ መነቃቃት ተነሳስተው፤ የተስፋ መዝሙር እየዘመሩ ብዙ መስዋዕትነት ከፍለዋል ፤ለዚህ የለውጥ /የመለወጥ ድምጽ ጎልቶ የተሰማባቸውን ታሪኮቻችንን ማየት በራሱ ከበቂ በላይ ነው።
የነዚህ ትውልዶች የለውጥ መነቃቃት በተለያዩ የቡድን እሳቤዎች እና እሳቤዎቹ በሚፈጥሯቸው ተቃርኖዎች ተጠልፈው፤ ሀገር እንደ ሀገር ተስፈኛ ትውልዶችን ከማጣቷ ባለፈ፤ ትውልዶቹ የተመኙትን በብዙ መነቃቃት ዋጋ የከፈሉበት ሀገራዊ ሰላም እና ልማት /ብልጽግና እውን መሆን ሳይችል ቀርቷል።
በተስፈኛ ትውልዶች መቃብር ላይ የሚመሰረቱ የፖለቲካ ሥርዓቶችም፤ ሀገርን ወዳልተገባ ተቃርኖ እና የግጭት አዙሪት ውስጥ ከመክተት ባለፈ ሀገርን ከትናንት ጥፋቶች በመታደግ ፣ ወደ አዲስ የለውጥ / የመለወጥ የታሪክ ምዕራፍ ማሸጋገር ፣ በዚህም ለሀገር እና ለሕዝብ መሻት ተጨባጭ ምላሽ መሆን አልቻሉም።
ለዚህ ደግሞ ላለፉት ስድስት አስርት ዓመታት ያለውን የሀገራችንን የለውጥ ታሪክ መመልከት ፤በዚህ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ በቡድኖች መካከል የተፈጠረ ተቃርኖ ፣ ሀገር እና ሕዝብን የቱን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለ ፣ ችግሩ አድጎ ትናንት የሀገር ህልውና ስጋት ሆኖ እንደነበርም መመልከቱ ተገቢ ነው።
ይህንን ችግር ለዘለቄታው ለመፍታት ከሁሉም በላይ ከትናንት ስህተቶቻችን መማር ፣ ችግሮችን በቀደመው የኃይል አሰላለፍ ትምክህት ፣ የአሸናፊ ተሸናፊ ትርክት ለመፍታት ከመሞከር ታቅቦ፣ በውይይት እና በድርድር ፣ ህግ እና ህጋዊነትን መሰረት ባደረገ መንገድ ለመፍታት የሚያስችል የፖለቲካ ባህል ማጎልበት ወሳኝ ነው።
የለውጥ ኃይሉ ወደ ስልጣን ከመጣ ማግስት ጀምሮ እንደ ሀገር ይህንን አዲስ የፖለቲካ ባህል ተግባራዊ ለማድረግ የሄደበት መንገድ በብዙ ፈተናዎች የታጀበ ፣የለውጡ የጉዞ ፍጥነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ የፈጠረ ቢሆንም፤ ከትናንት ተምሮ ለሕዝባችን የሰላም እና የልማት መሻት እውን መሆን የሚኖረው ስትራቴጂክ አስተዋጽኦ አልፋ እና ኦሜጋ ነው።
አንዳንድ ኃይሎች ቀደም ሲል ከፌዴራል መንግሥት ጋር የገቡበትን ችግር በሰለጠነ መንገድ ፣ በሰላማዊ ውይይት እና ድርድር ለመፍታት አለመቻላቸው በአጠቃላይ ሀገርን ፣ ከሁሉም በላይ ሕዝብን ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለው ፣ ችግሩ በድርድር በሰላም ስምምነት መቋጨቱ የቱን ያህል እፎይታ ይዞ እንደመጣ የአደባባይ ምስጢር ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ የዘመናት መሻቱ ሰላም እና ልማት ነው። እስከ ዛሬ የከፈላቸው መስዋእትነቶችም ይህንን እውነታ ተጨባጭ ለማድረግ የተከፈሉ ናቸው። የትኛውም ለሕዝብ ፍላጎት እታገላለሁ የሚል ኃይል ለዚህ የሕዝቡ ፍላጎት ተገዥ መሆን ይጠበቅበታል።
ሰላም እና ልማት የሚመነጨው ለሕግ እና ለሕግ የበላይነት የተገዛ ማኅበረሰብ ማፍራት ሲቻል ነው። ችግሮችን በውይይት እና በድርድር በሰላማዊ መንገድ መፍታት የሚያስችል የፖለቲካ ሥርዓት መፍጠር ሲቻል ነው። ይህም የትናንት ስህተቶቻችንን በዘላቂነት ማረም የሚያስችል ብቸኛው መንገድ ነው ።
ከዚህ አኳያ ማንኛውም የሕዝብ ፍላጎት ፍላጎቴ ነው የሚል አካል ሕግ እና ሕጋዊ ሥርዓትን ማክበር ፣ልዩነቶችን በውይይት እና በድርድር መፍታት ፣ ከሁሉም በላይ ሕጋዊ ሰውነት ያላቸውን ተቋማት ውሳኔ ማክበር ፣ ለውሳኔያቸው ተፈጻሚነት ራሱን ማዘጋጀት ይኖርበታል። ከዚህ ውጪ በሕዝብ ስም የሚደረግ የትኛውም እንቅስቃሴ ከሕዝብ ፍላጎት ጋር ተቃርኖ መቆምን በተጨባጭ አመላካች ነው!
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 8 ቀን 2016 ዓ.ም